Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሴት አትሌቶችን ወደ አትሌቲክስ አመራርነት የማምጣት ትልም

ሴት አትሌቶችን ወደ አትሌቲክስ አመራርነት የማምጣት ትልም

ቀን:

እ.ኤ.አ. በ1992 የባርሴሎና ኦሊምፒክ ጨዋታ በሴቶች 10,000 ሜትር ውድድር ላይ የወርቅ ሜዳሊያን ማሳካት የቻለችው ደራርቱ ቱሉ፣ የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት ኦሊምፒያን መሆኗ ዕሙን ነው፡፡ በአትሌቲክሱ የእሷን ፈለግ ተከትለው የስኬት ማማ ላይ መውጣት ለቻሉ በርካታ ሴቶች ምሳሌ መሆን መቻሏ ሌላኛው ታሪክ የማይረሳው ተግባር ያደርገዋል፡፡

የእሷን መንገድ በመከተል ፋጡማ ሮባ፣ ጌጤ ዋሚ፣ እልፍነሽ ዓለሙ፣ መሠረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ አልማዝ አያና እንዲሁም የዘመኑ ድንቅ አትሌቶች ለተሰንበት ግደይ፣ ጉዳፍ ፀጋይ በቅብብሎሽ የአገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ  በዓለም አደባባይ እንዲውለበለብ አስችለዋል፡፡

አትሌቶቹ በውድድር ማሳካት ከቻሉት ድል በላይ፣ በንግዱም ዓለም በመግባት ስኬታማ መሆን እንደሚቻል አስመስክረዋል፡፡ በአትሌቲክሱና በንግዱ የታየው ስኬት ደግሞ አትሌቶቹ ወደ አመራርነት በመግባት፣ ለአዲሱ የስፖርት ትውልድ ያላቸውን ልምድና ዕውቀት ለማካፈል፣ ሲተጉ መመልከት እየተለመደ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በደራርቱ ፕሬዚዳንትነት ከመመራቱም በላይ ዘንድሮ በተደረገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከተመረጡት 11 ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባሎች መካከል ስድስት ሴቶች ናቸው።

በክልላቸው ተወክለው በሥራ አስፈጻሚ ውስጥ መካተት ከቻሉት እንስቶች መካከል፣ ኢትዮጵያን ወክላ በተለያዩ ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድሮች ላይ መካፈል የቻለችው መሰለች መልካሙ ትጠቀሳለች፡፡

ከዚህም ባሻገር በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ውስጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ተመድበው የሚገኙ ሠራተኞች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው ይጠቀሳል።

በሌላ በኩል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የዓለም ሻምፒዮናንና የኦሊምፒክ ጨዋታን፣ እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የበለጠ ስኬታማ እየሆኑ መምጣት ችለዋል። በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መካፈል ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ 23 የወርቅ ሜዳሊያ መሰብሰብ የቻለች ሲሆን፣ ዘጠኝ ወርቅ በሴቶች አትሌቶች የተሳኩ ናቸው። በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና ተሳትፎዋ በአጠቃላይ 34 የወርቅ ሜዳልያ መሰብሰብ የቻለች ሲሆን፣ 18 ሜዳልያ በሴት አትሌቶች የተሳካ ነው።

ሴቶች በርካታ ፈታኝ ችግሮች ቢኖሩባቸውም፣ ችግሮቹን ተቋቁመው ድል ማድረግ መቻላቸው የሚደነቅ መሆኑን በርካቶች ይስማማሉ።

በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የስፖርትና መዝናኛ ክፍል ኃላፊ አቶ ቦጋለ አበበ አስተያየት ከሆነ፣ ሴት አትሌቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ አልፈው ስኬታማ መሆን መቻላቸው ትልቅ ድል እንደሆነ ጠቅሶ፣ ምቹ ሁኔታዎች ቢመቻችላቸው የበለጠ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ማሳያ እንደሆነ ያስረዳል።

‹‹የሴት ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን የስኬት ጉዞ ለመመልከት በዓለም ሻምፒዮናና ኦሊምፒክ ላይ ያሳኩት ድል መመልከት በቂ ነው፤› በማለት ይገልጻል።

እንደ ባለሙያው ማብራሪያ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሴት ፕሬዚዳንት ከመመራቱም በላይ ተሳትፏቸው የበለጠ እንዲጠነክር ዕድል መስጠት እንደሚገባ ይጠቁማል።

የዓለም አትሌቲክስ የዓለም የሴቶች ቀንን አስመልክቶ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት በምክር ቤቱ 40 በመቶ ሴት ተወካዮች እንዲኖሩ፣ እንዲሁም ቢያንስ አንድ ሴት ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲኖር ለማድረግ ማቀዱን ገልጿል፡፡ ዕቅዱ እ.ኤ.አ. በ2023 መጨረሻ እንደሚተገበር ያብራራ ሲሆን፣ በ214 አባል አገሮች ፖሊሲውን ተግባራዊ እንደሚያደርግም ጠቁሟል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ በስፖርቱ የፆታ ፍትሐዊነት ለማሻሻልና በአትሌቲክሱ  ያለውን የሥርዓተ ፆታ ልዩነት ለማጥበብ እያሠራ በሚገኘው ‹‹አትሌቲክስን እናሳድገው›› በሚለው ዘመቻው ላይ እያስተዋወቀው እንደሚገኝ ያብራራል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 ሴቶች በአትሌቲክስ ውስጥ እኩል ውክልና እንዲኖራቸው የማሻሻያ ሐሳብ መቅረቡን የሚያነሱት የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሳባስቲያን ኮ፣ በስፖርቱ ላይ እውነተኛ ፍትሐዊነትን ለማስፈን ሴት አትሌቶችን በአስተዳደሩም፣ በአሠልጣኝነቱም እንዲሁም በሁሉም የአትሌቲክስ ዕርከኖች ውስጥ በሙያቸው እንዲቀጥሉ የሚያስችላቸውን ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

‹‹በምክር ቤታችን የሴቶች ውክልና ኮታ በማዘጋጀት በተሻለ ሁኔታ ለሴቶች የሚስማሙ የመማርና ራሳቸውን የሚያሳድጉበት ፍትሐዊ ዕድል ለመስጠት ቁርጠኛ ነን፤›› ሲሉ ሳባስቲያን ኮ ተናግረዋል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ በፖሊሲው ውስጥ አካቶ የሴቶች በአትሌክስ አመራርነት የሥራ ድርሻ በታቀደው መሠረት ግቡን ስኬታማ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚገባቸው ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2013 ነሐሴ ላይ በሚደረገው የዓለም አትሌቲክስ የምክር ቤት ምርጫ የሴቶችን አባላት ቁጥር ከስምንት ወደ አሥር ለማሳደግ መታቀዱን የዓለም አትሌቲክስ ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከ2023 እስከ 2027 የሥራ ዘመን የሴቶችን የምክር ቤት አባልነትና በአስተዳደር የመወዳደር ፍላጎትና ተጨማሪ ዕድል ለመፍጠር 50 በመቶ ለማድረስ መታቀዱም ተገልጿል፡፡

እንደ ዓለም አትሌቲክስ ማብራሪያ መሠረት፣ በ2025 የቶኪዮ ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ የሚካፈሉ አባል አገሮች በርካታ ሴት አሠልጣኞችን እንዲልኩና ዝቅተኛ የሴቶች ውክልና ያላቸው አባል ፌዴሬሽኖችን የሚያበረታታ ዘዴዎችን መቀየሱ ተቀምጧል፡፡ በዚህም መሠረት በመጪው የዓለም ሻምፒዮና ላይ ለመሳተፍ ከሚመጡት ፌዴሬሽኖች ቢያንስ 20 በመቶ ሴት አሠልጣኞችን በቡድናቸው ውስጥ ማካተት እንደሚገባቸው አስቀምጧል፡፡

ይህንን ለማሳካት እንዲረዳ የሥርዓተ ፆታ አመራር ግብረ ኃይል ከኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) የሴት አሠልጣኝ አመራር ፕሮግራም ጋር በጋራ በመሥራት ብቁ የሆኑ ሴት አሠልጣኞችን ለፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታ የብሔራዊ ቡድናቸው አካል ሆነው እንዲመረጡ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ ለዝግጅት ይረዳ ዘንድም ከአትሌቲክስ ስምንት ሴቶች መመረጣቸው ጠቅሷል፡፡

የዓለም አትሌቲክስ ሴቶች በአትሌቲክስ ውስጥ ውክልና እና የሥራ ድርሻ እንዲኖራቸው በመረዳት በተለያዩ የውድድር መድረኮች፣ የማኅበራዊ ሚዲያ እንዲሁም በተለያዩ ሚዲያዎች ተሳታፊነታቸው እንዲጨምር ዘመቻዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሷል፡፡

ከዚህም ባሻገር የተለያዩ ሥልጠናዎችን ከማሰናዳት በዘለለ፣ በሴት አትሌቶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ትንኮሳ የሚያወግዝ ዘመቻን ሲያቀርብ ነበር፡፡ የዓለም አትሌቲክስ በተለያዩ ጊዚያት ባደረገው ጥናት መሠረት በማኅበራዊ ሚዲያ በሴት አትሌቶች ላይ የተለያዩ የቃል ፆታዊ ትንኮሳዎች እንደሚደርስባቸው ማረጋገጡን ገልጿል፡፡ ጥናቱ በበይነ መረብ አማካይነት በወንዶች ላይ ከሚደርሰው በበለጠ በሴቶች እንደሚደርስ ጠቅሶ፣ በቡዳፔስት የ2023 ዓለም ሻምፒዮና ተመሳሳይ ትንኮሳ ከደረሰ ትንኮሳ የሚያደርሰውን አካል ተከታትሎ ለሕግ ለማቅረብ እንደሚሠራም ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል በዓለም አትሌቲክስ ከአንድ ዓመት በላይ በጦርነት ውስጥ የነበሩት የዩክሬን ሴት አትሌቶችን ለመደገፍ መሰናዳቱን አስታውቋል፡፡ የዓለም አትሌቲክስ ዓምና በሶሊዳሪቲ ፈንድ በማቋቋም ከ100 በላይ የዩክሬን አትሌቶች፣ አሠልጣኞች  የቴክኒክ ኮሚቴ አባሎች በዓለም አቀፍ ውድድሮች በተከታታይ መካፈል እንዲችሉ ድጋፍ ሲደረግ እንደነበር ጠቅሶ፣ 70 በመቶ የሚሆኑ ሴት አትሌቶች ተጠቃሚ መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...