በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ተፈጸሙ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ቁርሾዎችን አግባብነት ባለው መንገድ ለመፍታት ያግዛል ለተባለለት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ፣ የግብዓት መሰብሰቢያ ሰነድ ላይ ሐሳባቸውን እንዲሰጡ የተጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግሥት ከሽግግር ፍትሕ በፊት የአገርን ሰላም ያስቀድም ሲሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡
በቀደሙት ጊዜያት ተከናውነዋል የተባሉ ኢፍትሐዊ የሆኑና በቁርሾ የተሞሉ ታሪኮችን የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት በመዘርጋት የተሻለ አገራዊ አንድነት ለማምጣት ያግዛል የተባለለትን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ለማዘጋጀት፣ አማራጭ አቅጣጫዎችን የያዘ የግብዓት ማሰባሰቢያ ሰነድ ከቀናት በፊት ይፋ ተደርጓል፡፡
በዚህ ሰነድ ላይ እንዲሳተፉ ከተጠሩ ከ50 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች በመድረኩ በሰጡት አስተያየት፣ የኢትዮጵያ አሁናዊ የሰላም ሁኔታ ለጉዳዩ አስቻይ ባለመሆኑ መንግሥት የአገርን ሰላም ያስቀድም ሲሉ ድምፃቸውን አስምተዋል፡፡
በውይይቱ ሐሳባቸውን ለሪፖርተር ያጋሩት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ ምክትል መሪ ዮሐንስ መኰንን (አርክቴክት)፣ እንደ አገር ሐሳቡ መልካም ቢሆንም የተቀባይነቱ ሁኔታ ግን ያሳስባል ብለዋል፡፡
‹‹እንደ አገር ወቅቱን ስንመለከት ቀውስ ውስጥ ነን፣ እጅግ አሳዛኝ ቀውስ ምንአልባትም እንደ አገር ቆመን እንቀጥላለን? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ሁኔታ ውስጥ ሆነን፣ የሽግግር ፍትሕ ብሎ ማንሳት ለአንዳንዶቹ እንደ ፌዝ ይቆጠራል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት ከዚህ የሚቀድም አንገብጋቢ አጀንዳ አለ፣ ብረት ምጣድ ላይ የተቀመጠ ሰው የልብስ ዓይነቱን ብትመርጥለት ወይም የሚመገበውን ብትጠይቀው፣ መጀመሪያ የሚልህ ከእሳቱ ላይ አንሳኝ ነው፡፡ ስለዚህ ዝንጀሮ መጀመሪ የመቀመጫዬን አለች እንደሚባለው ሕዝቡ መቆሚያ መቀመጫ ባጣበት፣ ለሕይወቱ ዋስትና በሌለበት ይህ መታሰቡ አይዋጥልንም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
‹‹በሠለጠነው ዓለም መንግሥት የሚባለው ጽንሰ ሐሳብና በሰው ልጆች ታሪክ መንግሥትን ያዋቀሩት አካላት፣ መጀመሪያ ገበያ ፈጠሩ ሀብት አፈሩ፡፡ ይህን ደግሞ በጉልበት የሚቀማቸው ሰው እንዳይኖር እናዋጣና አንድ የሚጠብቀን ይኑር በማለት የሕይወት ዋስትና፣ የአካልና የንብረት፣ ዋስትና ሰላምና ደኅንነት እንዲያስጠብቅ መንግሥት የሚባል ተቋም መሠረቱ፡፡ የሚፈጽመው ተግባር በጣም ውስን ኃላፊነቶችን ነበር፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ አሁን ያለው መንግሥት ይህን ውስን ኃላፊነት እንኳ ማሟላት አልቻለም፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት እየሄደበት ያለው፣ የሰው ልጆች መንግሥት የፈጠሩበትን ጽንሰ ሐሳብ አለማሟላት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አለመታደል ሆኖ አንዳንዴ ለሰላም ዕጦቱ ዋነኛ ተዋናይ ራሱ ነው በማለት ወቅሰዋል፡፡
በመሆኑም የአካል፣ የሕይወትና፣ የንብረት ዋስትና በሌለበት ሁኔታ ላይ ያለፈውን ቁስል ለመሻር እንነጋገር ማለት አንዳንድ ጊዜ ቅንጦት ሊመስል እንደሚችል አክለው አስረድተዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ አቶ አዲሱ ሐረገወይን በበኩላቸው፣ ‹‹ጥቃትና ዓለም አቀፍ በደሎች እየተፈጸሙባት ባለች አገር ውስጥ እንዲያው ሰላማዊ አገር እንዳለና ብሩህ ተስፋ እንዳለው ሕዝብ፣ ስለሽግግር ፍትሕ የምናወራበት ጊዜ ላይ አይደለንም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹አሁን በምንነጋገርበት በዚህ ጊዜ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ቤታቸው እየፈረሰ እየተፈናቀሉ ነው፣ እየተገደሉ ነው፣ አንደ አገር የጦር ወንጀል እየተፈጸመ ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይ ሕዝቡ ፋታ እንዳገኘ ተቆጥሮ ስለሽግግር ፍትሕ ሥርዓት የምናወራበት ጊዜ ነው ብሎ ፍትሕ ሚኒስቴር ይህን ጉዳይ ሲያመጣ፣ እየተፈጸመ ያለውን ግድያና መፈናቀል መቆም የለበትም ወይ በማለት ጠይቀዋል፡፡
‹‹ይህ እንዲያው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ለማታለልና ለማባበል፣ እንዲሁም ለተራ ፕሮፓጋንዳ እንጂ ትክክለኛ የሆነ የሽግግር ፍትሕ ለማምጣት የሚደረግ ሒደት ነው ብዬ አላምንም፣ እንደ ፓርቲም አናምንም፤›› ብለዋል፡፡
የሽግግር ወቅት የሚመጣበትና እኛ ስለመሻገራችን እርግጠኛ የምንሆንበትን ወቅት መለየት አለብን ሲሉ አስተያየት የሰጡት ደግሞ፣ የጌዲኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌሕዴድ) አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ አላሳ መንገሻ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ እሳት የማጥፋት ዓይነት ተግባር እንጂ በመሠረታዊነት የተጠና ሥራ የመሥራት ልምድ እንደሌለ የገለጹት ደግሞ የእናት ፓርቲ ፕሬዚዳንት ሠይፈ ሥላሴ አያሌው (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ከቀደሙት ጊዜያት በከፋ ችግር ውስጥ ላይ ነው ያለችው፣ ይህ በሆነበት ሁኔታ የሽግግር ፍትሕ ብሎ እዚህ ላይ መናገሩ አዋጭ አይደለም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ተወካይ አቶ ማሙሸት አማረ የቀረበው የሽግግር ፍትሕ ከዓውዱ የወጣ መሆኑን በመግለጽ፣ የሽግግር ፍትሕ ሊመጣ የሚገባው መጀመሪያ ሞት፣ መፈናቀል፣ ጦርነትና ስደት ሲቆም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
‹‹መንግሥት የዜጎችን ሕይወት አደጋ ውስጥ መጣሉን በመግለጽ፣ ይህን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ሰነድ ሲቀርብ ጉዳዩ ቀልድ ይሆንብኛል፤›› የሚሉት አቶ ማሙሸት፣ ከጅምሩ የሽግግር ፍትሕ መምጣት የነበረበት ከአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንጂ ከፍትሕ ሚኒስቴር መሆኑ ጉዳዩ እንደሞተ ይገባኛል፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተወካይ ዝናቡ አበራ (ፕሮፌሰር)፣ ‹‹ከትናንት ወዲያ በዓድዋ ድል፣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ በሻሸመኔ፣ በወልቂጤ በሕዝብ ላይ የተደረገው ግፍ ሳይረሳ ሕዝቡን ምን አድርግ ነው የምትሉት?›› በማለት ጠይቀዋል፡፡
‹‹መንግሥት በሕግ አምላክ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ እጁን ይሰብስብ ከዚያ ወደ ሽግግር ፍትሕ መሄድ እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ጊዜውም አይደለም ሕዝቡም እየተገደለና መፈናቀሉ፣ መጎስቆሉ ሳይቆምና የሥነ ልቦና ቀውስ ባለበት ዝግጅት ሳይኖር ወደ ሽግግር ፍትሕ መሄድ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡
ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ አካል ከመድረኩ ከፍትሕ ሚኒስቴርም ሆነ ከሌሎች የመንግሥት ኃላፊዎች አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አርቃቂ ቡድን አባላት እንደተናገሩት፣ አሁን እየተባለ ያለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን እንተግብር ሳይሆን፣ ፖሊሲ የማርቀቅ ሒደት ላይ ስለተሆነ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ሥጋት መነሳት የነበረበት ወደ ትግባራ ቢገባ እንደነበረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡