ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍ.ኤስ.ኤስ.)
የፖሊሲ ፍሬ ሐሳቦች
የሴት ሠራተኞች የሥራ ሁኔታ እና ለውጦች በኢትዮጲያ ፦ በተመረጡ ካፌ ዎችና እና ሬስቶራንቶች የተገኙ ተሞክሮዎች
ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍ.ኤስ.ኤስ.) ካለፉት ሁለት ዓስርት ዓመታት ጀምሮ በዜጎች ማህበራዊ ህይወትና ምጣኔ ሃብታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ በተለያዩ የአገራችን ማህበራዊ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ የሕዝብ መድረኮችን በማዘጋጀትና ውጤታማ የፖሊሲ ትግበራና አዳዲስ አማራጭ አቅጣጫዎችን ለሚመለከታቸው አካላት በማሳየት ጥሩ አስተዋጽዖ እያደረገ የሚገኝ መንግስታዊ ያልሆነ ሀገር በቀል ድርጅት ነው፡፡
በኤፍኤስኤስ እየተከናወኑ የሚገኙ የጥናት ውጤቶችን የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም ለህብረተሰቡ በሰፊው እንዲደርስ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ የህትመት ውጤቶች ጋዜጦች ሲሆኑ በዚህ አምድም በልማት ጉዳዮች ዙሪያ በሚካሄዱ የምርምር ስራዎች ላይ የተመሰረቱ የጥናት ውጤቶች አንዱ የሆነውንና በርካታ አንጋፋ ተመራማሪዎች የተሳተፉበትንና ለፖሊሲ አውጭዎች በርካታ ምክረ ሀሳቦችን ያካተተውን ‹‹የሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ እና የታዩ ለውጦች በኢትዮጲያ፤ ጨርቃ-ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች፣ የአበባእርሻዎች እና በካፌ እና ሬስቶራንቶች፣ በሚል ርእስ የተካሄደባቸውን ጥናቶች በዚህ ዓምድ በተከታታይ ማቅረብ መጀመሩን ተከትሎ በዚህ ሳምንት የሴት ሠራተኞች የሥራ ሁኔታ እና ለውጦች በኢትዮጲያ “በተመረጡ ካፌ ዎችና እና ሬስቶራንቶች የተገኙ ተሞክሮዎች” በሚል ርእስ የተካሄደው ጥናት ቀርቧል፡፡
- መግቢያ
እንግዳን የመቀበልና የማስተናገድ አገልግሎት በተለምዶ የመስተንግዶ ኢንዱስትሪ (Hospitality industry )ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ሆቴሎችን፤ ካፍቴረያዎችን፤ ሬስቶራንቶችንና ሌሎች የምግብና መጠጥ አግልግሎት ሰጪ ተቌማትን አቅፎ የሚይዝ የ አገልግሎት ኢዱስትሪ ክፍል ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ይህ ኢንዱስትሪ በሃገሪቱ የኢኮኖሜ ዕድገት ውስጥ የስራ ዕድልን በመፍጠር፤ የውች ምንዛሪን በማስገኘትና በድህንነት ቅነሳ አንቅስቃሴዎችን በማገዝ መከተማም ሆነ በገጠሪቱ የሃገሪቱ ክፍል ጉልህ እተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሜ ቀጥሎ ሁለተኛው ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚገኝበት ነው፡፡
በዚህ የአገልግሎት ሰጪ ውስጥ ወጣቶች በአነስተኛ የትምህርት ደረጃና እውቀት የሚገኙ በተለይም ሴቶች ተሳትፈው የሚገኙ ሲሆን ከሌሎች ኢንዱሰትሪዎች ጋር ሲነጻጸር የስራ ቦታዎች ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ሆኖ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ የሴቶች የሥራ ስምሪት መጠን እና የሰው ሃይል ተሳትፎ ከወንዶች ያነሰ ሲሆን በሴቶች ላይ ያለው የሥራ አጥነት መጠን በከተሞች በጣም ከፍ ያለ ነው። በመሆኑም መንግስት የተለያዮ እቅዶችን በመንደፍ፣ ፖሊሲዎችን በማሻሻል ስራ የሚፈጥሩ አካለትን በማበረታታት፣ ሁሉን አቀፍ የሆኑ ድጋፍ ሰጪ ውይይቶች እና የተለያዩ አዎንታዊ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ጥረት ቢያደርግም የሥራ አጥነት ሁኔታ በተለይም የሴቶች ሥራአጥነት ይበልጡን እየተባባሰ ሄዷል፡፡ በዚህም የተነሳ የሴቶችን እና የወጣቶችን የሥራ እድል ማስፋፋት የመንግስት ዋነኛ እቅድ ሆኖ ቀጥሏል። በዚህም መሠረት በቱሪዝሙ መስክ የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻል እና ብቁ የስራ ሀይልን አቅም መገንባት እና ማፍራት የ10 ዓመቱ የልማት አቅድ (2021-2030) ዋነኛ ትኩረት ነው።
በተጨማሪም በቅርቡ የተሻሻለው የኢትዮጵያ የሠራተኛ ሕግ (አዋጅ ቁጥር 1156/2019) የሴቶችን የሥራ ሁኔታ በሚመለከት (አንቀጽ 87) ሴቶችን በጾታ ላይ የተመሠረተ አድልዎ እንዳይደርስባቸው መከላከልን የሚያስችሉ ህጎችን ደንግጓል፡፡ በተመሳሳይም፣ የአስር ዓመቱ የእድገት እቅድ (2021-2030) የሴቶችን አጠቃላይ አቅም ግንባታን ለማጎልበት እና በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ እና ባህላዊ ጉዳዮች ላይ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ ለማመቻቸት ያለሙ አቅጣጫዎችን በማሰቀመጥ የሴቶችን ደህንነትና መብት ማስጠበቅ፣ በኢኮኖሚ ልማት ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንዲሁም ከአካላዊ፣ ከጾታዊ እና ከስነልቦናዊ ጥቃቶች ነፃ የሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠርእንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡
የሆቴል እና ቱሪዝም ዘርፍ ለ2. 2 ሚሊየን ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር በሃገራችን ካለው አጠቃላይ የሥራ እድል 8.3 በመቶው የሚሆነውን የማህበረሰብ አካል የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ያደረገ ቢሆንም በዘርፉ የተቀጠሩ የሴት ሰራተኞች መብትና ጥቅም እስካሁን በተገቢው መልኩ አልተከበረም። ወሲባዊ እና ስነልቦናዊ ጥቃቶችን ጨምሮ ምቹ ላልሆነ የሥራ ሁኔታ መጋለጥ ፤ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት፣ በቂ ያልሆነ ክፍያ እና ጥቅማጥቅሞች፣ ዝቅተኛ የአገልግሎት የጥራት ደረጃ እና ዝቅተኛ የደንበኛ እርካታ በዘርፉ ክሚስተዋሉት ችግሮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
የዚህ ጥናት ዋነኛ ዓላማ በአዲስ አበባ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች ውስጥ ያሉ የሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ በመመልከት የማህበራዊ እና ስነ-ሕዝብ ባህሪያትን፥ የመደራደር አቅምን፥ ገቢን፥ ጥቅማጥቅሞችን እና የሴት ሰራተኞችን የሥራ ሁኔታ በመገምገም በዘርፉ የሚገኙ ተግዳሮቶችን በመለየት መፍትሔ የሚሆኑ ምክረ ኃሻቦችን ማቅረብ ነው
ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (ኤፍ.ኤስ.ኤስ) በቅርቡ ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ የማህበራዊ ሳይንስ ምሁራን አማካኝነት በኢትዮጲያ በካፌ እና ሬስቶራንቶች፣ ጨርቃ-ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪዎች፣ እና የአበባ እርሻዎች የተሰማሩ ሴት ሰራተኞች ተከትሎ አጠቃላይ የዳሰሳ ጥናት አካሂዶል፡፡ የጥናቱ ውጤቶች እንደሚያሳዩት ዘርፉ ባስገኘላቸው የስራ እድሎች ደመወዝተኛ በመሆንና ገቢ በማግኘት ኑሮአቸውን እየመሩ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በተለይም ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር በሚበዛባቸው እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ሀገራት የአበባ እርሻዎችም ሆኑ፤ የመስተንግዶ ኢንዱትሪ እንዲሁም የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች እየፈጠሩ የሚገኘው የስራ እድል አበረታች ናቸው፡፡
ይህ ጽሁፍ ከእነዚህ ዘርፎች አንዱ በሆነው የመስተንግዶ አገልግሎት ኢንዱስትሪ የሴት ሰራተኞች የስራ ሁኔታ ፤ የታዩ ለውጦችና ተሞክሮዎችን በመዳሰስ በሃገራችን ኢትዮጰያ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታበመዳሰስ ለፖሊሲ ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ ምክረ ሃሰቦችን አቅreቧል፡፡
- ጥናቱ ምንን ያመለክታል ?
2.1 የስራ አድል ማመቻቸትን በተመለከተ
በጥናቱ እነደተመለከተው በአዲስ አበባ በሚገኙ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች ውስጥ ያሉ የሴት ሰራተኞች በአብዛኛው ወጣትሲሆኑ ከአማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልል ገጠራማ አካባቢዎች የመጡ ፤ ያላገቡ ሲሆኑ በእነሱ ጥገኛ የሆኑ የቤተሰብ አባላት ያሏቸው ናቸው። አብዛኞቹ አስተናጋጆች ገና በወጣትነት እድሜ ክልል ያሉ ሲሆኑ ወደ አዲስ አበባ የተሰደዱት በዋናነት የሥራ ዕድል እና የተሻለ ትምህርት እድል ፍለጋ ወይንም በከተማው ውስጥ ከሚኖሩ ዘመዶቻቸው ጋር ለመኖር የመጡ ናቸው። በዘርፉ ከተሰማሩት ውስጥ ወደ አንድ- አራተኛ (¼ኛ) የሚጠጉት የሁለተኛ ደረጃ ወይም ከዚያ ከፍ ያለ የትምህርት ደረጃ ያላቸው ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ከሆቴል አገልግሎት ጋር የተያያዘ የሙያ ስልጠና የወሰዱ ናቸው። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች ውስጥ ከሚሰሩት ውሰጥ ውስጥ ሩብ ያህሉ በዘርፉ ከአንድ ዓመት በላይ በስራው ላይ ያልቆዩ ተቀጣሪዎች ናቸው።
የቅጥር አሠራር መስፈርትን በተመለከተ የሥራ ልምድ እና ክህሎት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጡ መስፈርቶች ሲሆኑ በአንደኛ ደረጃ ወጣትነት፣ አጠቃላይ አካላዊ ውበት እና የተቋሙን የአለባበስ ህግጋት ለመከተል ፈቃደኛ መሆን የካፌዎችና ሬስቶራንቶች አስተዳዳሪዎች እና ባለቤቶች የሴት ሰራተኞች በሚቀጠሩበት ወቅት ቅድሚያ የሚሰጧቸው መስፈርቶች ሆነው ተገኝቷል።
እነደጥናቱ ዘገባ ከሆነ የሥራቸው ባህሪ ለአካላዊ እና አእምሮአዊ ጫና የሚዳርግ ቢሆንም የሴት አስተናጋጆች ደመወዝ በሁሉም መለኪያ ዝቅተኛ ነው። ይህም በመሆኑ ሴት አስተናጋጆች አብዛኛውን ገቢያቸውን የሚያገኙት ከመደበኛ ደመወዝ ሳይሆን ደንበኞች በሚተዉላቸው የአግልግሎት ጉርሻ (tip) ነው ። የሴት አስተናጋጆች አማካይ ገቢ 3254 ብር ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 951 ብር (28 ከመቶ) ብቻ ከደመወዝ፥ 1956 ብር ( 60 ከመቶ) ከጉርሻ (tip) ይገኛል። የጥናቱ ግኝት ከደንበኞች የተሻለ ጉርሻ የሚያገኙት ከፍ ያለ ትምህርት ደረጃ ያላቸው፥ በወጣትነት እድሜ ክልል ላይ ያሉ፥ እና በቀን ውስጥ ለተወሰኑ ሰዓታት ብቻ የሚሰሩ አስተናጋጆች እንደሆኑ አመላክቷል።
ለአብዛኛዎቹ ዝቅተኛ ክፍያ በሚከፈልባቸው ስራዎች ውስጥ ላሉ ሠራተኞች ገንዘብ-ነክ ያልሆኑ ማበረታቻዎች እና ጥቅማ-ጥቅሞች ከመደበኛ ደመወዝ ባልተናነሰ ሁኔታ የሠራተኞችን ተነሳሽነት ቢያሳድግም የጥናቱ ውጤት እንዳመለከተው አብዛኛዎቹ የሴት ሰራተኞች እንደ ማበረታቻ የሚያገኙት ዋነኛው ጥቅም ምግብ ሲሆን እንደ መኖሪያ ቤት፣ መጓጓዣ፣ የህክምና ወጪ ፣ ትምህርት እና ስልጠና የመሳሰሉ ጥቅሞችን የሚያገኙት ሰራተኞች በቁጥር አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
የኑሮ ወጪን በተመለከተ ምግብ፥ የቤት ኪራይ እና ቤተሰብን መደገፍ በሴት አሰተናጋጅ ሰራተኞች የኑሮ ሕይወት ላይ ትልቁ ወጪ ሲሆን ትራንስፖርት፥ የአየር ሰዓት፥ የጤና እንክብካቤ እና ትምህርት ሌሎች የተጠቀሱ ወጪዎች ናቸው፡፡ምንም እንኳን የኢትዮጵያ የአሠሪና ሠራተኛ ህግ ቀጣሪዎች ከሠራተኛው ጋር የኮንትራት ውል እንዲፈርሙ ና በተፈለገ ጊዜ ሁሉ የስራ ልምድ ደብዳቤ እንዲሰጣቸው ግዴታ ቢጥልም በካፌ እና ሬስቶራንት ውስጥ ከሚገኙት ሰራተኞች በጥናቱ እንደታየው ከሁለት ሶስተኛው በላይ የሚሆኑት የሚቀጠሩት በመንደር በሚገኙ ደላሎች ሲሆን በአሰሪው በኩል የሚሰጣቸው የቅጥር ደብዳቤም ሆነ ውል ወይም ፊርማ የለም ። በተጨማሪም ተቋማቱን ለቀው ሲወጡም ቢሆን አብዛኛዎቹ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች ለሰራተኞቻቸው የስራ ልምድ ማስረጃም አይሰጡም።
ይሀም ሆኖ አብዛኛዎቹ ሴት አስተናጋጆች በሚሰሩበት ድርጅት ውስጥ በቋሚነት መቀጠርን ካለመፈለጋቸውም በላይ የበለጠ ትርፋማና አማራጮችን በመፈለግ ሲሉ ውል አለመዋዋልን ይመርጣሉ፡፡ በአንድ ተቋም ውስጥ የሚኖራቸው የተራዘመ ቆይታ በአጠቃላይ ከደንበኞት በሚያገኙት ጥቅማ-ጥቅም (ቲፕ) መጠን ላይ የሚወሰን ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ በአብላጫው ገቢያቸው በዚህ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ መሆኑን ጥናቱ ያመላክታል፡፡ ፡፡
በካፌና ሬስቶራንቶች ውስጥ የተቋቋሙ የሠራተኛ ማኅበራትን የማይገኙ ሲሆን የስራ ኃላፊዎች ሠራተኞች በማህበር እንዳይደራጁ የማይፈቀድላቸው ሲሆን በአግልግሎቱ የሚገኙ ሴት አስተናጋጆች እንደ እቁብና እድር በመሳሰሉ መደበኛ ባልሆኑ አደረጃጀት በመጠቀም እንደ የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ ሠርግ፣ ወዘተ ባሉ አጋጣሚዎች እርስ በእርስ ለመደጋገፍ የግል ችግሮቻቸውን እየፈቱ ይገኛሉ፡፡
- የስራ ዋሰትና
ይህ በእጃቸው የሥራ ኮንትራት ውል አለመኖሩ ጥናቱ ማመላከቱም የሰራተኞቹን የስራ ዋስትናና የህግ ከለላ እንደሌላቸው አመላካች ከመሆኑም በላይ በራስ የመተማመንና ተስፋን የመሰነቅ፤ የአጭርና የረጅም ጊዜ የስራ የትምህርትና የቤተሰብ ዕቅድን የመተለምን ስነ ልቦና እንዳያዳብሩ አስስችሏቸዋል፡፡
የሠራተኛ ጉዳይ ይመለከታቸዋል የሚባሉ የመንግስት መስሪያ ቤቶች በካፌ እና ሬስቶራንቶች ላይ በቂ ቁጥጥር እና ክትትል ካለማድረገቸውም በላይ ከሬስቶራንቱ ወይም ካፌው ስራ አስኪያጅ ወይም ከሌሎች ሠራተኞች ጋር የሚፈጠሩ አለመግባባት፣ የእድሜ መግፋት እና የክብደት መጨመር ወደ መባረር እና የስራ ውልን እስከ ማቛረጥ የሚያደርሱ በመሆናቸው ይህም በተለይም የስት ሰራተኞችን አሰተማማኝ የስራ ዋሰትና እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡
- ተግዳሮቶች
ሴት አስተናጋጆችን ከሚገጥሟቸው መሰናክሎችና ተግዳሮቶች መካከል፣ የስራው አጠቃላይ ባህሪ፣ ከባልደረቦቻቸው ጋር በሚፈጠር ግጭት ምክንያትያላቸው ግንኙነት መሻከር፣ ማህበረሰባዊ ብሂሎች እና ሃላፊነቶች፣ መድልዎ፣ የሠራተኝነት መብትን መነፈግ፤ አነስተኛ ደመወዝ፣ የጥቅማ ጥቅሞች እና የሥራ እድገት እድል አለመኖር ፣ እና የተለያዩ አይነት ፆታዊ ትንኮሳዎች ይሀንንም ለመከላከል ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ የፖሊሲ ውሱንነት አለመኖር ናቸው፡፡
ካፌዎችን እና ሬስቶራንቶችን በማስተዳደር ላይ የተሰማሩት አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ወንዶች ሲሆኑ ይህም በሴት አስተናጋጆቹ ላይ ብዙውን ጊዜ የሚደርሰው የወሲባዊ ትንኮሳ እና አካላዊ ጥቃት እና ሴት አስተናጋጆችን በሴትነታቸው የሚገጥሙዋቸው አስቸጋሪ ፈተናዎች እና የህይወት መሰናክሎች ጫናውን ያበረታዋል፡፡
በተጨማሪም በዘርፉ ለተሰማሩ የሴት ሰራተኞች ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችሉ ሕጋዊ እና የፖሊሲ ምላሾች የክፍያና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች ውሱንነ፤ የክህሎት አቅም ውስንነትና ዝቅተኛ ውክልና በውሳኔ ሰጭነትና አመራርነት ፡ በተለየ ለሴቶች ተስማሚ የሆነ የስራ አከባቤ አለመኖር (Lack of women-friendly facilities) እና አሰተማማኝና ፍትሃዊ የሰራተኛ ቅጥርና የሰራተኛ ምርጫና ተከታታይ የትምህርት የተግባር ስልጠና በዘርፉ አለመኖር ዋንኛዎቹ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡
- ም ይደረግ ?
ከላይ የተጠቀሱትን የጥናቱ ውጤቶች ተከትሎ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ምክረ-ሃሳቦች አቅርቧል፡፡
4,1 የሠራተኛ ማሕበራትን መመስረት፦
የሠራተኛ ማሕበራት ሠራተኞች ምቹ የሥራ ሁኔታ እንዲኖራቸውና በጥቅማ ጥቅሞች ዙሪያ የመደራደር አቅም እንዲኖራቸው እንደሚያግዝ ይታመናል። ነገር ግን በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ካፌ እና ሬስቶራንቶች ውስጥ አስተናጋጆችን ያቀፈ የሠራተኞች ማሕበር የለም ። የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማሕበራት ኮንፌዴሬሽንና የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በጋራ በመሆን ለሠራተኛ ማሕበራት ምስረታ አጋዥ የሚሆን የፖሊሲ ማዕቀፍና መመሪያ ማዘጋጀት አለባቸው።
- ተከታተይነት ያለው ቁጥጥርና ክትትል፦
በአዲስ አበባ በሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ካፌ እና ሬስቶራንቶች ውስጥ ያለው የሠራተኛና አሠሪ ግንኙነት ዙሪያ የሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር በጣም አነስተኛ በመሆኑ ምክንያት የሠራተኛ ማሕበራት ኮንፌዴሬሽን እና የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በአነስተኛ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች ውስጥ የሚደረግን ክትትልና ቁጥጥር ማጠናከር አለባቸው።
4.3 በዘርፉ ያለውን የአቅም ግንባታ ማጠናከር ፦
ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ አነስተኛ ሆቴሎች፣ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች ያለው ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ እና የአገልግሎት ጥራት ማነስ በዘርፉ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእና እያሳደረ ሲሆን ቸግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የደረሰ ነው። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት – በዋናነት ባህልና ቱሪዝም፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ንግድ ቢሮ፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና የስልጠና እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአስተናጋጆችን አቅም በስልጠና እና በክትትል ማሻሻል አለባቸው።
4.5 ደመወዝ፦
የካፌዎች እና ሬስቶራንቶች የሴት አስተናጋጆች ደመወዝ በሁሉም መመዘኛዎች ዝቅተኛ የሚባል ሲሆን የሥራው ባህሪ አካላዊ እና ስነ-ልቦናዊ ጫና ያለው ነው። የአስተናጋጆቹ አብዛኛው ገቢያቸው ከደንበኞች በሚተውላቸው ጉርሻ (ቲፕ) ላይ የተመሠረተ ነው። በመሆኑም በ2019ኙ የሠራተኛ አዋጅ በተደነገገው መሠረት የደመወዝ መጠንን የሚወስንን አካል ማቋቋም፣ ለሠራተኞች እና ለቤተሰቦቻቸው የተሻለ ህይወትን ለመፍጠር፣ እና ሠራተኞች (ሴት አስተናጋጆች) ህይወታቸውን እንዲያሻሽሉ ለማነሳሳት የሚረዳ ወሳኝ እርምጃ ማከናወን ይኖርበታል።
4.6 የሥራ ቦታ ደህንነት ጥበቃን ማጠናከር
የሥራ ቦታ ደህንነት ደንቦችን በተመለከተ በጥናቱ እንደተስተዋለው በዚህ ረገድ የተወሰኑ ጥረቶች ይኑሩ እንጂ፣ ይበልጥ ትኩረት በሚሹ ቦታዎች ላይ የክትትል እና የቁጥጥር መመሪያዎች፣ ተቋማዊ የደንብ ማስከበሪያ ስርዓቶች እንዲሁም በየጊዜው የሚደረጉ የጤና ምርመራዎች የሠራተኞችን ደህንነት ለማረጋገጥ አስፈላጊነታቸው የጐላ በመሆኑ የሥራ ቦታ ደህንነት ደንቦች በሥራ አስፈጻሚዎችም ሆነ በሠራተኞች በራሳቸው ያለ ልዩነት በጥብቅ መከበር አለባቸው፡፡ በዚህ ረገድ በአገልግሎቱ ውስጥ የሚገኙት የሠራተኞች ማህበራት በማደራጅትና በማገዝ ፣ ደህንነታቸው የተጠበቁና ምቹ የሥራ ቦታዎች መኖራቸውን ለማረጋገጥ እና የሴት ሰራተኞችን መብቶች ለማስጠበቅ ከአሰሪዎች ጋር በጣምራ መስራት ይኖረባቸዋል፡፡