Wednesday, March 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ስታትስቲክስ አገልግሎት የሰብል እህሎች የዋጋ ንረት በየካቲት ወርም መቀጠሉን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሰብል እህሎች ላይ የሚመመዘገበው የዋጋ ንረት በተከታታይ ወራት እንደቀጠለና በየካቲት ወርም አብዛኛዎቹ እህሎች ጭማሪ ማሳየታቸውን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ይፋ አደረገ፡፡

አገልግሎቱ ይፋ ባደረገው የወርኃ የካቲት 2015 ዓ.ም. የአገር አቀፍና የክልሎች የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ላይ እንደተገለጸው፣ የአገሪቱ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር በመጠኑ ቢቀንስም፣ በተጠቀሰው ወር አብዛኛዎቹ እህሎች ጥራጥሬ፣ ሥጋ፣ ወተት፣ ዓይብና ዕንቁላል መጠነኛ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡

የየካቲት ወር 2015 ዓ.ም. የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር 29.6 ከመቶ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ በተገባደደው ወር እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስና ማሽላ በመሳሰሉት እህሎች ዋጋ ላይ ጭማሪ እንደነበር የስታትስቲክስ አገልግሎት ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ሪፖርተር ከሰሞኑ ባደረገው የገበያ ቅኝት ከሰብል እህሎች፣ በተለይም ጤፍ ከወር በፊት በአማካይ ከ58.00 እስከ 60.00 ብር ከነበረበት ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ በኪሎ ከ85.00 ብር እስከ 90.00 ብር እየተሸጠ መሆኑን የታዘበ ሲሆን፣ በተጨማሪም ከፍተኛ እጥረት እንዳለ ሸማቾች ጭምር አረጋግጠዋል፡፡

ምንም እንኳን በኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚሸጡ የጤፍ ምርቶች ተመን ከ5,500 ብር እንዳይበልጥ ስምምነት ላይ መደረሱን የኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን ቢገልጽም፣ ምርቱን ከገበያ ላይ ማጣቸው ሥጋት እንዳሳደረባቸው ሸማቾች በፊናቸው የገለጹ ሲሆን፣ በተያዘው ወር የተስተዋለው ጤፍን ጨምሮ በሌሎች የሰብል እህሎች ላይ የተስተዋለው ዋጋ አገራዊ የምግብ ዋጋ ንረትን እንዲቀጥል እንደሚያደርገው የአገሪቱን ኢኮኖሚ በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡

በየካቲት ወር ከምግብ ምርቶች በተጨማሪ ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች ማለትም ልብስና ጫማ፣ የቤት ጥገና ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ ጫትና የአሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ጭማሪ እንዳሳዩ የተገለጸ ሲሆን፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር የዋጋ ግሽበቱ ጭማሪዎች የተስተዋሉበት ነው ተብሏል፡፡

ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋነኛ ምክንያቶች ውስጥ፣ በተለይም በልብስና ጫማ፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጂ፣ የቤት መሥሪያ ዕቃዎች፣ ነዳጅ፣ ሕክምና ላይ የተስተዋለው የዋጋ ጭማሪ እንደሚገኝበት የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት አስታውቋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ በሚሰጡት ምክረ ሐሳብ በአገሪቱ አኃዙን የሰፋውን ዋጋ ግሽበትንና መዘዞቹን ለማስወገድ በአምራቹና በሸማቹ መካከል የአቅርቦት ሰንሰለቶችን ማጥበብ ዋነኛው ዘዴ ሲሆን፣ ይህም በሁለቱ አካላት መካከል እዚህ ግባ የሚባል እሴት ሳይጨምሩ፣ ነገር ግን በርከት ያለ ትርፍ በማጋበስ የምርት ዋጋ እንዲንር ምክንያት የሚሆኑትን ደላሎች ከሒደቱ ለማውጣት የሚረዳ መሆኑን በማስረዳት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች