Wednesday, March 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በ28 ቢሊዮን ብር ካፒታል በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ልሰማራ ነው ያለው ኩባንያ የመጀመርያውን ግንባታ ሊያስጀምር ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በ28 ቢሊዮን ብር የመነሻ ካፒታል አራት ግዙፍ ድርጅቶን በማቋቋም ወደ ሥራ እገባለሁ ያለው ገዳ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ፣ የመጀመርያ የሆነውን ድርጅት ግንባታ በሚቀጥለው ሳምንት ሊያስጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡

የገዳ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ አካል ይሆናሉ ተብለው ከተገለጹት ጂ ፕላስ ፋስት ፉድ፣ ጂ ጄላ የጨርቃ ጨርቅና የሌዘር ምርት፣ ጂ ፋርምና ጂ ኢምፓየር ቴክኖሎጂ ድርጅቶች ውስጥ፣ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እንደሚያመርት የሚጠበቀው ድርጅት የመሠረት ድንጋይ በሱሉልታ ከተማ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚቀመጥ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ቢንያም ኃይሉ ተናግረዋል፡፡

‹‹ከመጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የመሠረት ድንጋይ እንጥላለን፡፡ የቴክስታይሉን የምንጀምር ሲሆን በሌላ በኩል እስከ 2016 ዓ.ም. አጋማሽ ድረስ ፈጣን ምግቦችን ይዘን ወደ ገበያ እንገባለን፤›› ሲል አቶ ቢንያም አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ ሳምንት ሱሉልታ ከተማ ላይ ለሚገነባው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ግንባታ የሚሆን 4,500 ካሬ ሜትር መሬት መገኘቱን የተናገሩት አቶ ቢንያም፣ ገዳ ስታር ምን ያህል ካፒታል ግሩፕ ይዞ ወደ ሥራ የሚገባው? የኢንቨስትመንት መሬቱንስ ለማግኘት ምን ያህል ገንዘብ አወጣ በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ፣ ጥያቄው የመሠረተ ድንጋይ በሚጣልበት መርሐ ግብር ላይ የሚገለጽ እንደሆነ ነው፡፡ 

የገዳ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ አባል የሆኑት አራት ድርጅቶች የፈጣን ምግቦች፣ ዘመናዊ ግብርና፣ ጨርቃ ጨርቅ ቆዳና የቆዳ ውጤችን እንደሚያመርቱ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በተለይም ርካሽ የሆኑ ምርቶችን እንደሚያቀርብ የሚጠበቀው ድርጅት ግብዓቶችን ከሌላው አባል ድርጅት ከሆነው ጂ ፋርም እንዲጠቀም እንደሚደረግ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ሰኞ መጋቢት 4 ቀን 2015 ዓ.ም. በተዘጋጀ የድርጅቱ የምሥረታ መርሐ ግብር ላይ ተገልጿል፡፡

አንድ አክሲዮን በ250 ሺሕ ብር እንደሚሸጥ ያስታወቀው ገዳ ስታር ግሩፕ፣ የሚሸጠውም የአራቱን ድርጅቱን አክሲዮን እንደሆነና አንድ ባለ አክሲዮን የሚገዛው ዝቅተኛው የገንዘብ መጠን አንድ ሚሊዮን ብር ነው ብሏል፡፡

በ28 ቢሊዮን ብር ተመሥርቶ በዓመቱ ከ64.7 ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ የሚያስገኝ ተቋም እመሠርታለሁ ያለው ገዳ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ፣ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባም ከ45 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን በመርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የቢዝነስ ግሩፑ ፈጣን ምግቦችን በሃምሳ ብር አቀርባለሁ ማለቱን፣ እንዲሁም በየዓመቱ ከድርጅቶቹ ይገኛል የተባለው ከፍተኛ ትርፍ እንዴት ሊጣጣም ይችላል? አልተጋነነም ወይ? የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል፡፡

ድርጅቱ ዕውን ለሚያደርጋቸው ፕሮጀክቶች በራሱ ከሚሰበስበው ድርሻ በተጨማሪ ከባንኮች ጋር የተጀመሩ ንግግሮች እንዳሉ፣ ለማሽነሪዎች ግዥ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የውጭ አገሮች የፈንድ አማራጮች እንደሚጠቀም፣ በሌላ በኩል ወደ አገልግሎት ሲገባ የሚጠቀማቸው ግብዓቶች እርስ በርስ ትስስር የሚፈጠርባቸው በመሆናቸው ለምርቶቹ የሚጠይቀው ዋጋ ዝቅተኛ እንደሚሆን የቢዝነስ ግሩፑ የሥራ ኃላፊዎች አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች