Wednesday, March 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሶማሌላንድ ስደተኞች የተጠለሉባቸው የሶማሌ ክልል ሦስት ወረዳዎች ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው ተነገረ

የሶማሌላንድ ስደተኞች የተጠለሉባቸው የሶማሌ ክልል ሦስት ወረዳዎች ለከፍተኛ ችግር መጋለጣቸው ተነገረ

ቀን:

ከሶማሌላንድ ግዛት ተፈናቅለው ወደ ኢትዮጵያ የሚፈልሱ ስደተኞች ቁጥር እያደገ በመምጣቱ፣ በሶማሌ ክልል ዶሎ ዞን ውስጥ ያሉ ሦስት ወረዳዎች ለአስከፊ ችግር እየተጋለጡ መሆናቸው ተገለጸ።

ዶሎ ዞን ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለድርቅ አደጋ ተጋልጦ የነበረና ማኅበረሰቡም ለራሱ በቂ አቅም ሳይኖረው በርካታ ቁጥር ያላቸው ስደተኞችን ተቀብሎ እያስተናገደ መሆኑን በመግለጽ፣ በቂ ዕርዳታ ቀርቦ ችግሩ በጊዜ የማይቀረፍ ከሆነ፣ የከፋ ችግር ሊያጋጥም እንደሚችል የዞኑ ኃላፊዎች ተናገሩ።

በሶማሌላንድ በርካታ ሕይወቶችን እየቀጠፈ ያለውን ግጭት በመሸሽ በዶሎ ዞን ቦህ፣ ገልሃሙርና ዳኖድ ወረዳዎች እየተጠለሉ የሚገኙት ስደተኞች ቁጥራቸው ከሦስት ሳምንታት በፊት 83 ሺሕ ደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ግን ከ100 ሺሕ ሊበልጥ እንደሚችሉ ይገመታል ተብሏል።

ከአንድ ወር በፊት ድንበር ተሻግረው መምጣት የጀመሩት ነዋሪዎች መጠለያ ካምፕ ባለመኖሩ፣ በአካባቢው ባሉ 13 መንደሮች ከማኅበረሰቡ ጋር በመቀላቀልና በተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ሥፍራዎች በመጠለል ላይ እንደሚገኙ ያስታወቁት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙባረክ አህመድ፣ የመጠለያ ካምፖች በአፋጣኝ ተሠርተው ስደተኞቹ አስፈላጊ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንዲሰፍሩ ጠይቀዋል።

‹‹የአካባቢው ማኅበረሰብ በድርቅ ተጎድተው የነበረ በመሆኑ ያለው ውኃና ሌላ ሀብት ድሮም አይበቃም ነበር። ዕርዳታ በፍጥነት ካልቀረበ አሁን የመጡት ስደተኞች ከሦስቱ ወረዳ ሕዝብ በላይ ሆነዋል፡፡ ማኅበረሰቡ እየተቸገረ አገዘ እንጂ ኃላፊነቱ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መሆን ነበረበት፤›› ሲሉ አቶ ሙባረክ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

ላለፈው ወር እሳቸውን ጨምሮ በርካቶች ከወረዳ ጽሕፈት ቤት ወደ ሥፍራው በማቅናት ካምፖች እስኪሠሩ እያስተባበሩና እያገዙ እንደሚገኙ የሚናገሩት አስተዳዳሪው፣ ከተመድ የስደተኞች ዋና ኮሚሽነርና ከዓለም የምግብ ፕሮግራም የተወሰኑ ምግብ ነክ ዕርዳታ እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል። በተቻለ አቅም እንደሚታገዙ ቃል እየተገባላቸው እንደሆነና የመጀመርያ ዙር ምዝገባም እንደተጀመረ፣ ‹‹እስካሁን ግን በቂ የሆነ የሚደርስ ነገር የለም›› ሲሉ አክለዋል።

ከዓለም አቀፍ አጋዥ ድርጅቶች ጋር በመሆን ስደተኞችን እየመዘገበና እያስተባበረ የሚገኘው የኢትዮጵያ ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፣ የስደተኞች ሁኔታ በተመለከተ ለሪፖርተር ሲገልጹ፣ አብዛኞቹ ስደተኞች እየኖሩ ያሉት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር እንደሆነ አረጋግጠዋል።

ለስደተኞቹ ካምፖችን ለመሥራት ዓለም አቀፍ መሥፈርቶች ወጥተው ሁለት ቦታዎች መመረጣቸውን አቶ ተስፋሁን ጠቁመው፣ ይዘንና ‘ሚርቃን’ በሚባለው ሥፍራ ቅድሚያ ተሰጥቶ ማስፈር እንደሚጀመርም ገልጸዋል። ‹‹እዚያው ማኅበረሰቡ በሚኖርባቸው አካባቢዎች፣ ነገር ግን ክፍት ቦታዎች ላይ ነው የምናስቀምጣቸው። አቀማመጣቸውም ካምፕና የአካባቢው ማኅበረሰብ የሚኖርበት በሚል ሩቅ ለሩቅ አይደለም የሚሆነው፤›› ብለዋል።

እየተካሄደ ባለው የመጀመርያ ደረጃ ምዝገባ 56 ሺሕ ስደተኞች የተመዘገቡ መሆናቸውን የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የስደተኞች ቁጥርን በተመለከተ ከአካባቢው ኃላፊዎች ከደረሳቸው ከ100 ሺሕ ይበልጣሉ ከሚለው መረጃ በስተቀር እርግጠኛ እንደማይሆኑ አስረድተዋል። ጤና ጣቢያና ትምህርት ቤት ዓይነት መገልገያ ሥፍራዎች አቅማቸው እንዲጎለብት ሥራዎች እንደሚከናወኑ፣ እንዲሁም ከስደተኞች ጋር በተያያዘ ከሚደረጉ ሌሎች ፕሮጀክቶች የአካባቢው ማኅበረሰብም ተጠቃሚ እንደሚሆን አክለዋል።

እስካሁን የተገመተው የስደተኞች ቁጥር ከ100 ሺሕ በላይ እንደሚሆን፣ ነገር ግን ወደ ዋናዋ ሶማሊያ ተፈናቅለው የነበሩትም በአሁኑ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በከፍተኛ ቁጥር እየተሰደዱ እንደሚገኙ አቶ ሙባረክ ገልጸዋል።

‹‹ከሁለት ሳምንታት በፊት ወደ ሶማሊያ ተፈናቅለው የነበሩት 85 ሺሕ እንደሆኑ ነበር የሚገመተው፡፡ ከእነሱ አብዛኞቹ ወደዚህ እየመጡ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜም ቁጥራቸው ከ100 እስከ 150 ሺሕ ይደርሳል በእርግጠኝነት፤›› ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይ በውኃ በኩል ማኅበረሰቡ አስከፊ ችግር ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት አቶ ሙባረክ፣ ከሕዝቡ ቁጥር በላይ ለሆነው ስደተኛ ቀርቶ ለራሱ ለማኅበረሰቡም እንደሌለው ነው የገለጹት። ‹‹በሚያዝያ ወር ነው አላህ ዝናብ ካመጣልን የምንጠብቀው እንጂ፣ ማኅበረሰቡ በድርቅ ተመቷል፤›› በማለት ማኅበረሰቡ ስለገጠመው ድርቅ ጠቁመዋል።

በንጽህና ጉድለት ምክንያት በአካባቢው የተለያዩ በሽታዎች እየተከሰቱ እንደሆነ በተለያዩ አካባቢዎች ቢነገርም፣ አቶ ተስፋሁንና አቶ ሙባረክ የተረጋገጠ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል። እንደ አቶ ሙባረክ ገለጻ፣ የተመድ የስደተኞች ዋና ኮሚሽነር ሐኪሞች በሥፍራው ምርመራ እያደረጉ እንደሆነና በእርግጠኝነት የሚታወቀውም በምርመራ ውጤት እንደሆነ አክለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...