Wednesday, March 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየስደተኞች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በበቂ ደረጃ እየተተገበረ እንዳልሆነ ተገለጸ

የስደተኞች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በበቂ ደረጃ እየተተገበረ እንዳልሆነ ተገለጸ

ቀን:

በኢትዮጵያ የስደተኞች የፋይናንስ አካታችነት በጥሩ ሁኔታ እየተተገበረ እንደሚገኝ፣ ነገር ግን በኢኮኖሚው ላይ ያላቸው ተጠቃሚነት እንደተጠበቀው በበቂ ደረጃ እየተተገበረ እንዳልሆነ ተገለጸ።

ኢትዮጵያ ከአራት ዓመታት በፊት ባፀደቀችው የስደተኞች ጉዳይ አዋጅ መሠረት፣ ስደተኞች በኢትዮጵያ እንዲሠሩና የኢኮኖሚም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይፈቅድላቸዋል። የሕግ ማዕቀፉም ጥሩ ጅማሮ እንደሆነና አተገባበሩ ግን አጥጋቢ እንዳልሆነ፣ በትናንትናው ዕለት የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የማኅበራዊ ሳይንስ የምርምር ተቋም ከባለድሻ አካላት ጋር ባደረገው ስብሰባ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች ገለጹ።

የተቋሙ የስደተኞች ጉዳይ ላይ የምርምር ባለሙያ የሆኑት ፍቃዱ አዱኛ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዋጁ በ2011 ሲፀድቅ ጥሩ ተብሎ የተመሠገነና ብዙ ነገሮችን ይዞ እንደነበር ተናግረዋል። አንደኛው የፋይናንስ አካታችነት የነበረና ሌሎች ጥሩ ጥሩ ድንጋጌዎች እንደነበሩት ተናግረዋል። ከአዋጁ በፊት ስደተኞች የባንክ አገልግሎት እንደማያገኙ፣ ነገር ግን ከፀደቀ በኋላ ስደተኞች የባንክ ሒሳብ ከፍተው እንዲጠቀሙ በመፈቀዱ፣ በአሁን ጊዜ ሁሉም ስደተኞች ሊባል በሚችል ደረጃ የባንክ አካውንት እንዳላቸው ተናግረዋል።

‹‹ትንሽ የተንቀራፈፈው የኢኮኖሚ አካታችነቱ ነው። መቀጠርና የራስን ሥራ መፍጠር መሳተፍ የሚለው ጉዳይ ላይ ሒደቱ ትንሽ ቀርፈፍ ያለ ነው፤›› ብለው የተናገሩት ፍቃዱ (ዶ/ር)፣ ‹‹የፋይናንስ አካታችነቱ ግን በጣም ጥሩ ደረጃ ላይ ነው፤›› ብለዋል።

በቀብሪ በያህ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ያሉት ግማሹና ዶሎ ካምፕ ያሉት ሙሉው ዕርዳታ በራሽን ከሚሰጣቸው በስተቀር፣ አዲስ አበባም ሆነ ሌላ ቦታ ያሉ ስደተኞች ከድጋፍ አድራጊዎች ገንዘብ ሲሰጣቸውም በባንክ እንደሚቀበሉ ባለሙያው ገልጸዋል።

ስደተኞች የንግድ ፍቃድ ለማግኘት ኢትዮጵያዊ መሆን እንደሚጠበቅባቸው፣ ይህም አንደኛው ሒደቱን የጎተተው ነገር መሆኑን፣ ነገር ግን እንደ መፍትሔ የተወሰኑ አካባቢዎች ላይ በለጋሽ ድርጅቶች አማካይነት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በሽርክና እየከፈቱ የሥራ ፈቃድ በማግኘት እየሠሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

‹‹ተፈናቅለው የሚመጣው ብቻ ሳይሆን በአካባቢ የሚኖሩትንም በአገልግሎት መጨናነቅ ይጎዳሉ። ይህን ለመቅረፍ ስደተኛውንና የአካባቢውን ማኅበረሰው ሽርክና አስፈጥረው አብረው እያሠሯቸው ነው፤›› ብለዋል። ባለሙያው አክለውም ሲገልጹ፣ አንዳንዴ የስደተኞች ካምፕ አካባቢ ስደተኞች ሱቅ ሲከፍቱ እንዲጠቀሙ በሚል ኃላፊዎች አውቀው እንደማይጠይቋቸውም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ስደተኞች በብዙ የፋይናንስ አገልግሎትና የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ነው። በተለይ በካምፖች ውስጥ በራሳቸውም ገቢ ማስገኛ ሆነ ከአጋር ጋር በሚደረጉ ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ እንደሚገኙ አክለው ተናግረዋል።

‹‹አዋጁ መብት ነው የሚሰጠው፣ ያንን መብት ተጠቅመው ወደ ፕሮጀክት እንዲቀየርና ተጨባጭ የሆነ የኢኮኖሚ ዕድሎች እንዲያገኙ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ድጋፍ ያስፈልጋል። መንግሥት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ሥራ ባጡበት ሁኔታ ለስደተኞች ራሱ ሥራ ይፈጥራል ተብሎ አይታሰብም፤›› በማለት ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በመንግሥት የሕግ ድጋፍ እንደተደረገና ድጋፉ አሁንም እንዳለ የተናገሩት አቶ ተስፋሁን፣ እሱንም ተጠቅመው ስደተኞች እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ‹‹ከዚህ በላይ እንዲሰፋ ዓለም አቀፍ የማኅበረሰብ ድጋፍ መደረግ አለበት። ያኔ የነበረው ዓይነት ቃል መግባት አልተተገበረም ብለን እናምናለን፤›› ብለዋል።

የተመድ የስደተኞች ዋና ኮሚሽነር በኢትዮጵያ ዋና ተወካይ ማማዱ ባልዴ ባለፈው ሳምንት ከሪፖርተር ጋር አድረገውት በነበረው ቆይታ ተናግረው እንደነበረው፣የስደተኞች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በበቂ ሁኔታ እንዳይካሄድ ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት አሳልፋው የነበረውን ጦርነት እንደ ምክንያት አቅርበዋል።

ከሥራ ፈቃድና መሥፈርት ጋር በተያያዘ የተወሰኑ እክሎች እንደነበሩ፣ በእነዚህም ላይ ከሚከተሉት አካላት ጋር ውይይት እያደረጉ እንደነበር የገለጹት ዋና ተወካዩ፣ ተጀምረው የነበሩትም ሒደቶች በጦርነቱ ምክንያት እክል እንደገጠማቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ወደ 900 ሺሕ የሚጠጉ የተለያዩ አገሮች ስደተኞችና ጥገኝነት ጠያቂዎች የሚገኙ ሲሆን፣ 46 በመቶ የሚሆኑት ከደቡብ ሱዳን የመጡ ናቸው። የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ደግሞ ከ2.7 ሚሊዮን እንደሚበልጡ ከተመድ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...

አይ የእኛ ነገር!

የዛሬው ጉዞ ከጀሞ ወደ ፒያሳ ነው፡፡ መንገዱ ለሥራ በሚጣደፉ፣...

የዓለም ኢኮኖሚ መናጋት ለወቅታዊው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 16...