- በአዲስ አበባ ከሦስት እጥፍ በላይ የውኃ ታሪፍ መጨመሩ ተጠቆመ
- በቀን ተጨማሪ 200 ሺሕ ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ካልተገኘ በቀጣይ ዓመታት ከተማዋ ከባድ የውኃ እጥረት ያጋጥማታል
በአዲስ አበባ ከተማ እያጋጠመ ያለውን የውኃ ችግር ለመቅረፍ አዳዲስ የውኃ ጉድጓዶችን ለመቅረፍ ቢፈለግም መሬት ማግኘት እንዳልተቻለ ተገለጸ፡፡ የከርሰ ምድር ውኃ መያዛቸው በጥናት ተረጋጋጦ ለፕሮጀክት የተቀመጡ ቦታዎች ለከተማዋ መስፋፋት ለሌሎች ዓላማዎች መዋላቸው ከተማዋ ተጨማሪ የውኃ ጉድጓድ እንዳይኖራት አድርጓል ተብሏል፡፡
በተለይ ትልቅ የውኃ አቅም እንዳለው ተለይቶ የነበረው የጀሞና የፉሪ አካባቢዎች በከተማ ግንባታና በቆሻሻ መድፊያነት በመያዛቸው፣ ትልቅ እንቅፋት መሆኑን እንደማሳያ ተገልጿል፡፡
‹‹የውኃ ጉድጓድ መቆፈሪያ ጠፍቷል፡፡ የለም፡፡ ተለይተው የነበሩት ቦታዎች የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ ባለመኖሩ ለሌላ ተግባር ተወስደዋል፤›› ያሉት የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ሥራ አስኪያጅ ዘሪሁን አባተ (ኢንጂነር) ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔና የስድስት ወር አፈጻጸም ሪፖርት ትናንት ማክሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ባቀረበበት ወቅት ከተማዋን እየተፈታተኑ ካሉ ችግሮች ማለትም ከትምህርት እስከ ፀጥታ የተነሳ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የውኃ ዘርፉም አንዱ ነበር፡፡
መዲናዋ በቀን 1.2 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ የሚያስፈልጋት ሲሆን አሁን ያለው የማቅረብ አቅም ግን 725 ሺሕ ኪዩቢክ ሜትር ብቻ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ተጨማሪ 200 ሺሕ ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በቀን ማቅረብ ካልተቻለ፣ ከተማዋ ከባድ የውኃ እጥረት እንደሚያጋጥማት ተጠቅሷል፡፡
‹‹ለአንድ ቀን አየር መንገድ ወይም ቤተ መንግሥት ውኃ ቢቋረጥ ለከተማዋም ለአገሪቱም ገጽታ ጥሩ አይደለም፤›› ያሉት ዘሪሁን (ኢንጂነር)፣ ችግሩ በጣም አሳሳቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ለከተማዋ ውኃ የሚቀርብባቸው 230 ጉድጓዶች ብቻ ያሉ ሲሆን፣ በቂ አለመሆኑን ባለሥልጣኑ ገልጿል፡፡ ከተጨማሪ የገርቢ ውኃ ፕሮጀክት እንዲጀመር ፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ ለወልመራ አካባቢ ውኃ ለማቅረብ ያስችላል ተብሏል፡፡ ሌላኛው እየየጀመረ ያለው የጩቃላ ጉድጓድ ውኃ ሲሆን እስከ 2018 ከተጠናቀቀ እስከ 100 ሺሕ ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ለከተማዋ ለማቅረብ ያስችላል፡፡ ‹‹ይኼ ፕሮጀክት ካልደረሰ ከተማዋ ችግር ውስጥ ትገባለች፡፡ አዲስ አበባ ውኃ ላይ የተቀመጠች ከተማ ብትሆንም፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት እስከ 200 ሺሕ ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ወደ ሲስተም ካላስገባን ከተማዋ ትልቅ ችግር ውስጥ ትገባለች፤›› ሲሉ ዘሪሁን (ኢንጂነር) አክለዋል፡፡
በተያያዘ ዜና ቀኑና ወራቱ ለተጠቃሚው የአዲስ አበባ ሕዝብ ባይገለጽም፣ የውኃ ታሪፍ በሦስት እጥፍ መጨመሩ ተጠቁሟል፡፡ ሪፖርተር ከባለሥልጣኑ መረጃውን ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ‹‹አሁን ላይ ለመግለጽ ፈቃደኞች አይደለንም›› በማለት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የባለሥልጣኑ አንድ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡