የጮቄ ተራራ ኢኮ ቱሪዝም ልማት የዓለም ድንቅ ቱሪዝም መንደርነት ሽልማትን ከዓለም ቱሪዝም ድርጅት ተቀብሏል፡፡ ሽልማቱን የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ከጮቄ ሙሉ ኢኮ ሎጅ ተወካዮች ጋር በሳዑዲ ዓረቢያ አሉልኣ ከተማ ሰሞኑን ተቀብለዋል።
በምሥራቅ ጎጃም የሚገኘውን የጮቄ ተራራና አካባቢውን የዓለም የቱሪዝም ድርጅት፣ ከዓለም ‹‹ምርጥ የቱሪዝም መንደሮች›› አንዱ አድርጎ የመረጠው ታኅሣሥ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በስፔን ማድሪድ ባወጣው መግለጫ ነበር፡፡ የጮቄ ተራራ ኢኮ ቪሌጅን ጨምሮ ከአምስቱ አኅጉሮች ከ18 አገሮች በድምሩ 32 መንደሮች የ2022 ‹‹ምርጥ የቱሪዝም መንደር››ነት እውቅና ተሰጥቷቸዋል። ለ2022 ውድድር ከ57 አባል አገሮች በአጠቃላይ 136 መንደሮች (እያንዳንዱ አባል አገር ቢበዛ ሦስት መንደሮችን ማቅረብ ይችላል) ቀርበዋል። ኢትዮጵያ ያቀረበችው አንድ መንደር ያም የጮቄ ተራራ ብቻ ነው፡፡
ከአፍሪካ ከኢትዮጵያ ሌላ ፣ ሞሮኮ ሁለት መንደሮችን አስመርጣለች፡፡ ዓለም አቀፉ የቱሪዝም ድርጅት በሌላ ምድብ መንደሮችን ለማሳደግ ከተለያዩ አገሮች ከተመረጡት 20 መንደሮች ውስጥ የኢትዮጵያ አዳባ፣ የኬንያ፣ የሞሪሸስና የኬፕ ቨርዴ ይገኙበታል፡፡
ምርጥ የቱሪዝም መንደሮችን የመምረጥ ተነሳሽነት፣ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት የተለመው የገጠር መንደሮችን ከነመልክዓ ምድራቸው፣ እንዲሁም የኅብረተሰቡን ተፈጥሯዊና ባህላዊ ብዝኃነታቸው ማኅበራዊ እሴቶቻቸውን የአካባቢያቸውን የምግብ ባህል ጨምሮ ከመጠበቅና ከማክበር አንፃር የቱሪዝምን ሚናን ለማጉላት ነው፡፡
ምርጥ የቱሪዝም መንደሮች ተነሳሽነት (Best Tourism Villages initiative) ቱሪዝምን እንደ አንድ መዘውር ለዕድገትና ብልፅግና በመጠቀም ለተጉ ጠንካራ መንደሮች ዕውቅና የሚሰጥበት ነው፡፡