Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ብሔራዊ የሥነ ምግብ መረጃ ኢኒሼቲቭና ፕሮጀክቱ

በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የሥነ ምግብ መረጃ ላይ ትኩረት ያደረገ ፕሮጀክት በመካሄድ ላይ ነው፡፡ አረጋሽ ሳሙኤል (ዶ/ር) የኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ናቸው፡፡ በፕሮጀክቱ እንቅስቃሴ ዙሪያ አስተባባሪዋን ታደሰ ገብረማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ የሥነ ምግብ መረጃ ማዕከል ወይም መድረክ በሥነ ምግብ ዙሪያ ምን እየሠራ ነው?

ዶ/ር አረጋሽ፡- ብሔራዊ የሥነ ምግብ መረጃ ማዕከል ወይም መድረክ ዓለም አቀፍ ኢንሽዬቲቭ ሆኖ በተለያዩ ስምንት አገሮች የሚተገበር ፕሮጀክት ነው፡፡ አገሮችም ከአፍሪካ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ኒዠር፣ አይቮሪኮስትና ቡርኪናፋሶ፤ ከደቡብ አሜሪካ ጓቲማላ፤ ከእስያ ላኦስ-ዲፔዲያ ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱ አራት ዓላማዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ አንደኛው በማስረጃ የተደገፈ የሥነ ምግብ መረጃዎችን በተለያዩ ሴክተሮች ለሚገኙ ውሳኔ ሰጪ አካላት ማቅረብ፣ ሁለተኛው ከተለያዩ አካላት ተሠርተው የተቀመጡ መረጃዎችን ሥርዓት ባለው መልክ መሰብሰብ፣ ሦስተኛው የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሰጠት ሲሆን፣ አራተኛው ደግሞ ምርምር ተሠርቶ የተገኙት ውጤቶች በመደርደርያ ማስቀመጥ ቀርቶ ውሳኔ ሰጪዎች እንዲያውቁትና እንዲሠራጭ ማድረግ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በሁለቱ ክፍሎች የተደራጀ ሲሆን የመጀመርያው ክፍል ፕሮጀክት ቆይታ ዕድሜ የአራት ዓመት ወይም ከ2018 እስከ 2021 የሚዘልቁ ነው፡፡ ሁለተኛው ክፍል ደግሞ የሦስት ዓመት ሆኖ ከ2022 እስከ 2024 ይዘልቃል፡፡ ለመጀመርደው ዙር ፕሮጀክት ማከናወኛ የሚያስፈልገውን በጀት የመደበው የአውሮፓ ኅብረት ሲሆን ኅብረቱ ባጀቱን ያገኘው ከዩናይትድ ኪንግደም ፎር ኢንተርሽናል ዴቨሎፕመንትና ከቢል ኤንድ ሚሊንዳ  ጌትስ ፋውንዴሽን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የመጀመርያው ክፍል ፕሮጀክት ምን ውጤት አስገኘ? ለዚያስ የተያዘው በጀቱ ምን ያህል ነው? ፕሮጀክቱን ማን ነው የሚያስተዳድረው?

ዶ/ር አረጋሽ፡- በኢትዮጵያ ውስጥ በሁለት ክፍሎች ተደራጅቶ እየተተገበረ ያለውን ፕሮጀክት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሲሆን፣ የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርገውም ቢሮውን በኢንተርናሽናል ላይቭ ስቶክ ኢንስቲትዩት ቅጥር ግቢ ውስጥ ያደረገው ኢንተርናሽናል ፉድ ፖሊሲ ሪሰርች ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ለሥራውም ማከናወኛ 1.5 ሚሊዮን ዩሮ በጀት ተይዞለታል፡፡ ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የመጀመርያው ዙር ፕሮጀክት የተመደበለት በጀት ሁለት ሚሊዮን ዩሮ ነው፡፡ በዚህም በጀት በመጠቀም ከሥነ ምግብ ጋር የተያያዙና ጠቃሚ የሆኑ ልዩ ልዩ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከተከናወኑትም ሥራዎች መካከል ዋነኛ የሆነው ለረዥም ጊዜ የሚቆይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መሰጠቱ ነው፡፡ ስለሆነም ስድስት የኢንስቲትዩቱ ተመራማሪዎች ወደ አውሮፓና አሜሪካ ሄደው የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም ሌላ በበጀት እጥረት ሳቢያ የፒኤችዲ ሥልጠና አቋርጠው የነበሩ ሌሎች ሁለት ባለሙያዎችም ያቋረጡትን ሥልጠና መጀመር የሚያስችላቸው የ34,000 ዩሮ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ በአጫጭር ሥልጠና ፕሮግራም ደግሞ 453 ሰዎች የተሳተፉበት 21 ሥልጠናዎች ተከናውነዋል፡፡ ለጋዜጠኞች፣ ለሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች፣ ከተለያዩ ሴክተሮች ለመጡ ተመራማሪዎች ሥነ ምግብን በተመለከተና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ትምህርት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተለይ ለጋዜጠኞች የተሰጠው ሥልጠና ሥነ ምግብን በተመለከተ እንዴት ነው የሚዘግቡት? በድንገት የሚከሰቱ ችግሮችን ለኅብረተሰቡ በምን መልኩ ነው የሚያሳውቁት? ኒውትሪሽን ላይ ለምንድነው ትኩረት የተደረገው? በሚሉና በሌሎችም ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ መረጃዎች እንዴት እንደሚተነተኑና እንደሚያዙም የሚጠቁሙ ነጥቦች በሥልጠናው የተካተቱ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የመጀመርያው ዙር ፕሮጀክት ተፈጽሟል ለማለት ይቻላል?

ዶ/ር አረጋሽ፡- አንድ ለመግለጽ የምፈልገው ነገር ቢኖር ከኢትዮጵያ በስተቀር በፕሮጀክቱ የታቀፉት አገሮች የመጀመርያውን ዙር ሥራ አጠናቀው፣ ሁለተኛውን ዙር በማገባደድ ላይ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ የመጀመርያውን ዙር ሥራ በጥሩ ሁኔታ እያሳካች ብትገኝም ለዚህ የተመደበላትን በጀት ግን በተለያዩ ምክንያት በወቅቱ አልጨረሰችም፡፡ በጀቱን በተያዘላት የጊዜ ገደብ እንዳታጠናቅቅ ያደረጋትና እንደ ዓብይ ተግዳሮት ሆኖ የሚታይ ከቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ የልዩ ልዩ ዕቃዎች ግዥ በየምክንያቱ በመጓተቱ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ተመድቦላት ሳትጨርስ የቀረውን ወይም የተረፈውን በጀት ከመመለስ ይልቅ የመጀመርያውን ዙር ፕሮጀክት ቆይታ ዕድሜ በተጨማሪ ለሁለት ዓመት እንዲራዘምላት የሚጠቁም የመፍትሔ ሐሳብ አቀረበች፡፡ በእነዚህም ዓመታት ውስጥ አዲስ ወይም ተጨማሪ በጀት ሳትጠየቅ በተረፈው በጀቷ ብቻ ሥራዎችን ዳር እንደምታደርስ አስታውቃለች፡፡ ይህም ማለት ተጨማሪ በጀት አትጠይቅም ማለት ነው፡፡ ጥያቄዋም ተቀባይነት አግኝቶ የመጀመርያው ዙር ፕሮጀክት ከ2022 እስከ 2023 ድረስ እንዲቀጥልላት ተደርጓል፡፡ ሥራውንም ያለ በጀት ጥያቄ ዳር እንድታደርስ ስምምነት ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ የሥነ ምግብ መረጃ ማዕከል ወይም መድረክ ሁለተኛው ዙር የፕሮጀክት ትግበራ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ዶ/ር አረጋሽ፡- የፕሮጀክቱ ሁለተኛው ዙር ሥራ ጅማሮ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው፡፡ በዚህም ሥራ በመጀመርያው ዙር ያልተጠናቀቁ ወይም ሳይከናወኑ የቀሩ ሥራዎች ከሁለተኛው ዙር ሥራ ጋር አብረው እየተከናወኑ ለመሆናቸው መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ይህም ሆኖ ግን ሁለተኛው ዙር ፕሮጀክት አራት ዋና ዋና ጉዳዮችን አካቷል፡፡ እነርሱም የቴክኒክና የፖሊሲ ድጋፍ መስጠት፣ ቀጣይነት ዓለም አቀፍ ተሳትፎ ናቸው፡፡ በፖሊሲ ኢንሐንስመንት ተመራማሪዎችና ውሳኔ ሰጪ አካላት በአጠቃላዩ ፕሮጀክት ዙሪያ መጠየቅ የሚችሉበትን ሁኔታ ማብቃት ላይ ያተኮረ ሥራ የሚከናወን ሲሆን፣ በቴክኒካል ድጋፍ ደግሞ የአቅም ግንባታው ሥልጠና ይቀጥላል፡፡ ቀጣይነቱ ደግሞ ፕሮጀክቱ ቀጣይነት እንዲኖረው የማድረግ ሥራን ይመለከታል፡፡

ሪፖርተር፡- የሁለተኛው ዙር ፕሮጀክት ሥራ ከመጀመርያው ዙር በምን ይለያል? በሁለቱም ዙር የፕሮጀክት አፈጻጸም ዙሪያ ከስምንቱ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ በምን ደረጃ ላይ ትገኛለች?

ዶ/ር አረጋሽ፡- ከተጠቀሱት አገሮች መካከል የኢትዮጵያ በጀት አፈጻጸም ደካማ ቢሆንም በፕሮጀክት አፈጻጸም ስትታይ ግን ከኒዠር ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ትገኛለች፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለተኛ ለመውጣቷ እንዴት ይረጋገጣል? ኒዠርስ እንዴት ቀዳሚ ልትሆን ቻለች?

ዶ/ር አረጋሽ፡- ሁለተኛ መውጣቷ የተረጋገው የስምንቱም አገሮች ፕሮጀክት አፈጻጸም ከተገመገመ በኋላ በተገኘው ውጤት መሠረት ነው፡፡ ግምገማውንም ያካሄደው ገለልተኛ የሆነ አንድ የውጭ አገር ገምጋሚ ተቋም ነው፡፡ ኒዠር ግንባር ቀደም ልትሆን የቻለችውም የፕሮጀክቱን ትግበራ ከኢትዮጵያ ቀድማ በመጀመሯ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሮጀክቱ የያዘውን ሥራ ካጠናቀቀ በኋላ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የዚህ ኢንሺየቲቭ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?

ዶ/ር አረጋሽ፡- ፕሮጀክቱ ፌዝ አውት የሚያደርገው በ2024 ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እንደ ቡድን (ቲም) ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ተፈልጎ ነበር፡፡ ይህ ግን አልተቻለም፡፡ ምክንያቱም የአንድ መንግሥት መሥሪያ ቤትን መዋቅር እንደተፈለገው መቀየር ስለማይቻል ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በቅርቡ አዲስ ባቋቋመው ብሔራዊ ዳታ ማኔጅመንት ሴንተር ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ ታቅዷል፡፡ ይህም የሚያሳየው ነገር ቢኖር በመንግሥት ተቋም መዋቅር ውስጥ መግባቱን ነው፡፡ ይህም የኢንሽየቲቩን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን

ቢሻን ጋሪ ፒውሪፊኬሽን ኢንዱስትሪ ወደ ውኃ የማከም ቴክኖሎጂ ሥራ የገባው በየጊዜው በኢትዮጵያ የተከሰቱ ውኃ ወለድ በሽታዎች መደጋገምን ዓይቶና ጥናት አድርጎ ነው፡፡ በ2000 ዓ.ም. ቢሻን...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...

ሕይወትን ለመቀየር ያለሙ የቁጠባና ብድር ማኅበራት

ወ/ሮ ቅድስት ሽመልስ በግሎባል ስተዲስ ኤንድ ኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ በፕሮጀክት ማኔጅመንት እንዲሁም በኢንተርናሽናል ሪሌሽንስ ሠርተዋል፡፡ በኮርፖሬት ፋይናንስ ካናዳ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ...