Wednesday, March 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከያቤሎ ከተማና ከዙሪያዋ እስከ ሞያሌ የተዘረጋው የነዳጅ ጥቁር ገበያ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ከዓለም ገበያ በውጭ ምንዛሪ ገዝቶ ለአገር ውስጥ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የሚያቀርበው ነዳጅ፣ የጥቁር ገበያ ሲሳይ ሆኗል። 

ይህ ሕገወጥ ተግባር ከአዲስ አበባ ከተማ አንስቶ እስከ ጠረፍ ባሉ ከተሞች የተለመደ ተግባር ከሆነ ሰነባብቷል። ሪፖርተር ሰሞኑን በያቤሎ ከተማ በተገኘበት ወቅትም የተመለከተው ይህንኑ እውነታ ነው። 

በያቤሎ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች ቀኑን አገልግሎት ከሰጡ በኋላ ምሽቱን ለነገ መንቀሳቀሻ የሚሆናቸውን ነዳጅ ለመቅዳት በየማደያው ተሠልፈው ይስተዋላሉ።

በያቤሎ ከተማ በጎበኘነው አንድ ነዳጅ ማደያ ጣቢያ ከተሠለፉ በርካታ የባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪ (ባጃጅ) ሹፌሮች መካከል አንዱ ነዳጅ ለመቅዳት በማደያው ተገኝቶ ወረፋ የያዘው ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ እንደሆነ በሥፍራው ለተገኘው የሪፖርተር ዘጋቢ ገልጿል።

ከምሽቱ አንድ ሰዓት ቤንዚል ለማግኘት የተሠለፈው ይኼ ወጣት እስከ ረፋዱ ሦስት ሰዓት ወረፋው እንዳልደረሰው በምሬት ያስረዳል፡፡

በከተማው አሥር የነዳጅ ማደያዎች ቢኖሩም፣ ሕገወጦች ተመሳጥረው ለከተማዋ የቀረበውን ነዳጅ በድብቅ ወደ በሞያሌ መስመር እንደ ሚያስወጡ የሚናገሩት አሽከርካሪዎች፣ በዚህም እነሱ መቸገራቸውን ያስረዳሉ።

በተዘዋወርንባቸው ማደያዎች አንድ ሊትር ቤንዚል በ65 ብር እንደሚሸጥ የተመለከትን ሲሆን፣ ለከተማዋ የሚቀርበውን ነዳጅ ከማደያዎች ተመሳጥረው የሚያስወጡት ሕገወጥ ነጋዴዎች ደግሞ አንዱን ሊትር ቤንዚን ሞያሌ ላይ በ150 ብር እንደሚሸጡት ያነጋገርናቸው ገልጸዋል። 

ማደያዎቹ ጭምር የቀረበላቸውን ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ እንደሚሸጡ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች፣ በከተማ በሚገኙ ሱቆችም ቤንዚን በሊትር እስከ 140 ብር ድረስ እንደሚሸጥ ጠቁመዋል፡፡

በያቤሎ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡት ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች ብቻ ሲሆኑ እነሱም በነዳጅ ዕጦት ለቀናት ስለሚቆሙ ማኅበረሰቡ ለትራንስፖርት ችግር መዳረጉን አስተውለናል። 

ችግሩን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የቦረና ዞን ንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሐሰን ጉዮ፣ ከሕገወጥ የነዳጅ ንግዱ በተጨማሪ ወደ ዞኑ የሚላከው የነዳጅ መጠን አነስተኛ መሆን ችግሩን እንዳባባሰው ይገልጻሉ።

ለያቤሎ ከተማ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለዞኑ የሚላከው የነዳጅ መጠን ዝቅተኛ ነው የሚሉት አቶ ሐሰን፣ በዞኑ የሚገኝ አንድ ማደያ በሦስት ወር አራት ቦቴ ነዳጅ ብቻ እንደሚቀርብለት ገልጸዋል።

በቦረና ዞን አሥራ ሦስት ወረዳዎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች እንደሚገኙ ገልጸው፣ የያቤሎ ከተማ ማደያዎች የሚጠቀሙት ደግሞ ዘጠኝ ወረዳዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡  የባለ ሦስት እግር አሽከርካሪዎች በሁለት ማደያዎች ብቻ ቤንዚን እንደሚያገኙ፣ በቅርቡም አንዱ ማደያ ብልሽት ስላጋጠመው ለጊዜው አገልግሎት እየሰጠ እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ለዞኑ የሚቀርበው የነዳጅ መጠን ዝቅተኛ ሆኖ ሳለ፣ የሚቀርበውን ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ ከአገር ስለሚወጣ በነዳጅ እጥረት ችግር ውስጥ መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡

በከተማው የቤንዚል እጥረት መከሰቱን የሚናገሩ አቶ ሐሰን፣ ችግሩን ያባባሰው ደግሞ በኮታው መሠረት እየገባ ባለመሆኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በኮታው መሠረት በጊዜ ነዳጅ እንዲቀርብላቸው የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ጥያቄ ማቅረባቸውንም ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ሐሰን ገለጻ፣ በየማዳያዎቹ ነዳጅ ለመቅዳት የሚሠለፉት የባለ ሦስት እግር (ባጃጅ) አሽከርካሪዎችም ቢሆኑ የሕገወጥ ንግዱ አካል ናቸው።

ነዳጅ ለመቅዳት በረጅም ሠልፍ ወረፋ ሲጠብቁ የሚታዩት አብዛኞቹ የባጃጅ አሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት ሊሰጡ ፈልገው ሳይሆን የቀዱትን ነዳጅ ዋጋ ጨምረው በጥቁር ገበያ ሊሸጡት እንደሆነም አቶ ሐሰን ገልጸዋል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ ነዳጅ በኩፖን እንዲሸጥ የአሠራር ሥርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ የታቀደው አሠራር በቅርቡ መተግበር ሲጀምርም ችግሩ ይፈታል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል። የነዳጅ ማደያዎቹም በሕገወጥ መንገድ ሲሸጡ ከተያዙ በኋላ ይታሸጉና ያላቸው የነዳጅ መጠን ተለክቶ በድጋሚ እንዲከፈቱ ይደረጋሉ ብለዋል፡፡ 

ከዞኑ በሕገወጥ መንገድ ከአገር የሚመጣውን ነዳጅ ቁጥጥር ማድረግና ማደያዎችን መዝጋት ከተጀመረ በኋላ የነዳጁ ጥቁር ገበያ ለዘብ ማለቱን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡ በዞኑ ከሌላ ወረዳዎች የሚመጣ ሕገወጥ ነዳጅ ዝውውር እንደሚታይ የሚያስረዱት ኃላፊው፣ ከዞኑ በተጨማሪ ከሌሎች አካባቢዎችም ነዳጅ ጭነው ወደ ሞያሌ የሚተሙ መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ከቡሌ ሆራ፣ ከአርባ ምንጭና ለዞኑ አዋሳኝ ከሆኑ አካባቢዎችም ሕገወጥ ነዳጅ ወደ ሞያሌ ለማስወጣት የሚደረግ ትርምስ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ለዞኑ የሚላከው የነዳጅ ኮታ በሕገወጦች ወደ ውጪ እንዳይወጣ በቴክኖሎጂ የተደገፍ የአሠራር እየተዘረጋ በመሆኑ፣ ችግሩ በዘላቂነት ይፈታል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ሐሰን ገልጸዋል፡፡ በቅርብ ጊዜም አሥር ሺሕ ሊትር ነዳጅ በሕገወጥ መንገድ ከዞኑ ሊወጣ ሲል በተደረገው ክትትል መያዙን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዳይሬክተር ጄኔራል ወ/ሮ ሰሐረላ አብዲላሂ እንደተናገሩት፣ የነዳጅ ጥቁር ገበያ ወደ ሞያሌ አካባቢ በስፋት ይስተዋላል፡፡ ባለ ሥልጣኑ የነዳጅ ጥቁር ገበያ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን፣ መጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ሁለት የነዳጅ ቦቴዎች መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ሳህረላ ገለጻ፣ የነዳጅ ቦቴዎች ከማድረሻቸው ውጪ እየተጓዙ እንደነበሩ፣ በዚህም አስፈላጊው ክትትል ተደርጎባቸው መያዛቸውን ጠቁመዋል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በሞያሌ በኩል ሕገወጥ የነዳጅ ግብይት መጨመሩን የሚናገሩት ዳይሬክተሯ፣ በከተማዋ የሚገኘው ማደያ ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ችግሩ መባባሱን እንደ ምክንያትነት አንስተዋል፡፡

ባለ ሥልጣኑ ሕገወጦችን ለመቆጣጠር የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱን፣ ነዳጅ አመላላሽ ቦቴዎች ላይ ጂፒስ በመግጠም በእንቅስቃሴያቸው ላይ ቁጥጥር ማድረግ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ገና ከጅምሩ የተወሰኑ ሾፌሮች ጂፒኤሱን ነቅለው የመጥፋት አዝማሚያ መታየቱንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከውጭ ለምታስገባው ነዳጅ በዓመት ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ ጠቁመው፣ በሕገወጦች ምክንያት የአገር ሀብት ለጎረቤት አገሮች ሲሳይ እየሆነ የመጣበትን ሁኔታ መለወጥና ችግሮችን መቅረፍ የግድ እንዲሚል ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች