Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ግራ አጋቢው የኤሌክትሪክ መኪና ጉዳይ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ በወርኃ ጥቅምት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 39 ለሚሆኑ ምርቶች ሌተር ኦፍ ክሬዲት እንዳይከፈት ሲያግድ፣ ከታገዱት ምርቶች መካከል ተሽከርካሪዎች ይገኙበታል። በወቅቱ ውሳኔው ለመንግሥት የውጭ ምንዛሪን ከማዳን አኳያ ሚናው ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም፣ በመኪና ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ያስደነገጠ ነበር። የመኪናን ንግድ የሚዘውሩት ደላላዎች ዋጋ ይጨምራል የሚል ፍራቻቸውን ሲገልጹ ነበር። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎችም የተጣለው ዕግድ አቅርቦት እንዲቀንስ ማድረጉ አይቀርም በማለት የመኪና ዋጋ መጨመሩ አይቀርም በማለት ሐሳባቸውን በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ሲገልጹ ነበር። መሬት ላይ ያጋጠመው እውነታ ቀድመው ከተሰጡ ትንታኔዎችና ሙያዊ ግምታዎች ፈጽሞ ተቃራኒ ነበር።

በገበያ ላይ ተፈላጊ ከሆኑት እንደ ቶዮታ ቪትዝና ያሪስ ያሉ ተሽከርካሪዎች እስከ ከተመረቱ አንድ ዓመት ያልሞላቸው እንደ ሱዙኪ ዲዛየር 2022 ያሉ ተሽከርካሪዎች ዋጋቸው ባልተጠበቀ መልኩ ሊቀንስ ችሏል። ታዲያ ለዋጋው መቀነስ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው የተጣለው ዕግድ ኤሌክትሪክ መኪናን አለማካተቱ ነበር። አንዳንዶችም የነዳጅ ተሽከርካሪዎች የሚያስመጡ ነጋዴዎች የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ከሚያስመጡ ነጋዴዎች ጋር የፈጠሩት ፉክክርን ተከትሎ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ የተከፈቱ ዘመቻዎች እንደ ምክንያት ሲያነሱ ነበር።

መንግሥት በበኩሉ የኤሌከትሪክ መኪናን ለማበረታታት መሰል ተሽከርካሪዎችን የሚያስመጡ ነጋዴዎች ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ሱር ታክስና ኤክሳይዝ ታክስ እንዳይከፍሉ በመመርያ ውሳኔ አስተላልፏል። በአገር ውስጥ መገጣጠም ለሚፈልጉ ተገጣጣሚ አካላትን ሲያስገቡ የሚከፍሉት ግብር አምስት በመቶ ከስተም ታክስ ብቻ ሲሆን፣ አስመጪዎች በበኩላቸው የሚጠበቅባቸው 15 በመቶ እንዲሆን ተደርጓል። እነዚህ ዕርምጃዎች ዋነኛ ዓላማቸው የኤሌከትሪክ መኪና በስፋት እንዲገባ ማበረታታትና በየዓመቱ ለነዳጅ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሪ መቀነስ ነው። ምንም እንኳን የኤሌክትሪክ ኃይል በአገር ውስጥ በስፋት እንደመመረቱ መጠን ውሳኔው ከውጭ ሲታይ ተፈጻሚነቱ ቀላል ሊመስል ይችላል። በተለይም ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች በቀላሉ ቤት ውሰጥ ቻርጅ መደረግ መቻላቸው ከነዳጅ ዋጋ መጨመር ጋር ተዳምሮ ተቀባይነት የማግኘት ዕድላቸው ሰፊ ሊያስመስለው ይችላል። ነገር ግን በመሬት ላይ ያለው እውነታ ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው።

የገዢዎች ፍላጎት ማነስ

ለኤሌከትሪክ ተሽከርካሪዎች ያለው ፍላጎት አነስተኛ መሆኑን ለመረዳት ተሽከርካሪዎቹን የሚያስመጡ ድርጅቶችን መሸጫ ቦታ ማየት በቂ ነው። ቀላል የማይባሉ አስመጪዎች መንግሥት የሰጠውን ማበረታቻዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ ቢያስገቡም ገዢ ለማግኘት መቸገራቸውን ይገልጻሉ። በሃያ ሁለት አካባቢ የሚገኘው የናሆም መኪና መሸጫ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ናሆም ክንደያ መሰል ችግር ከገጠማቸው ነጋዴዎች መካከል ናቸው። ምንም እንኳን የተደረጉ ማሻሻያዎችን ተከትሎ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ከቻይና ቢያስመጡም ምንም አለመሸጣቸውን ያነሳሉ።

በሸማቾች በኩል ያለው ፍላጎት አነስተኛ መሆኑን ማሳያ በተለያዩ ዲጂታል መገበያያዎች ለገበያ የሚቀርቡ ተሽከርካሪዎች ዓይነት በነዳጅ የሚነዱ መሆናቸው ሲሆን የኤሌክትሪክ መኪና በተመሳሳይ መልኩ ለገበያ ቢቀርብም ያላቸው ተፈላጊነት አነስተኛ መሆኑ ይነሳል።

የመለዋወጫ ችግር

አቶ ዳዊት መኮንን ለመኪና ግዢ በቅርቡ ወደ ገበያ ከወጡ ሸማቾች መካከል ናቸው። የኤሌክትሪክ መኪና ለመግዛት ይፈልጋሉ ተብሎ በሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ መልሳቸው አልፈልግም የሚል ነበር። ለዚህም እንደ ምክንያት በዋነኝነት የሚያነሱት የመለዋወጫ አለመኖርን ሲሆን፣ ኤሌክትሪክ መኪና መግዛት አደጋ ወይም ብልሽት ካጋጠመ የሚያመጣው ኪሣራ ቀላል አለመሆኑን ነው። ‹‹መኪናው ሙሉ የኢንሹራንስ ሽፋን አለው ብለን ብናስብ እንኳን የተበላሸው ዕቃ ከውጭ እስኪመጣ ጊዜ ይፈልጋል›› የሚሉት አቶ ዳዊት ‹‹ይህም ዕቃውን ከውጭ ለማምጣት የሚወስደው የውጭ ምንዛሪ የማስፈቀድ ሒደት ጋር ተዳምሮ የኤሌክትሪክ መኪና መግዛት አዋጭ አይደለም፤›› ይላሉ።

አነስተኛ የፋይናንስ አቅርቦት

ምንም እንኳን በሁሉም ዘርፎች በኢትዮጵያ ያለው የፋይናንስ አቅርቦት ካለው ፍላጎት አንፃር በጣም አነስተኛ ቢሆንም፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ላይ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እጅጉን የባሰ ነው። አቶ ናሆም በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት አስተያየት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ምንም ዓይነት ፋይናንስ በባንኮችና ማይክሮ ፋይናንሶች አለመቅረቡ በደንበኞች በኩል ያለውን ፍላጎት ይበልጡኑ አሳንሶታል። በባንኮች በኩል የሚነሳው ምርቶቹን አናውቃቸውም፣ ኪሣራ ላይ ይጥለናል የሚሉት ምክንያቶች ፈጽሞ ትርጉም የማይሰጡ ናቸው የሚሉት አቶ ናሆም፣ መንግሥት የሰጠውን የፖሊሲ አቅጣጫ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብድር መሰጠት ይኖርበታል ብለዋል።

በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና በቁጠባና ብድር ማኅበራት በኩል ያለው ምልከታ ከዚህ የተለየ ነው።

የአዋጭ ቁጠባና ብድር የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት ትዕግስት ጎርሜሳ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ገዢዎች የኢንሹራንስ ሽፋን እስካመጡ ድረስ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ብድር መስጠት እንደሚቻል የተናገሩ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ ድርጅታቸው ለመሰል ተሽከርካሪዎች ብድር እንዳልሰጠ ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የዋሳ ማይክሮፋይናንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አምሳሉ ዓለማየሁ ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የተለየ የብድር አፈቃቀድ ሥርዓት አለመኖሩን የተናገሩ ሲሆን፣ የተመረቱበት ዓመት ከ2006 ወዲህ እስከሆነ ድረስ ብድር መስጠት እንደሚቻል ተናግረዋል።

የፋይናንስ ባለሙያው ጥሩነህ አሰፋ በበኩላቸው ለኤሌክትሪክ ተሽከርከሪዎች ብድር መስጠት ለፋይናንስ ተቋማት ቀላል እንደማይሆን ያነሳሉ።

ምርቶቹ ለገበያው አዲስ እንደመሆናቸው መጠን ኪሣራና ወጪያቸውን መለየት ቀላል አይደለም፡፡ ይህም ለባንኮች የሚያስከፍሉትን ወለድ፣ ለኢንሹራንሶች ደግሞ የዓረቦን መጠኑን ተገማች እንዳይሆን ያደርገዋል ብለዋል። የመለዋወጫ ጉዳይም በቀላሉ ችላ የሚባል ነገር አይደለም የሚሉት አቶ ጥሩነህ የፋይናንስ ተቋማት ላይ የሚያመጣው ኪሣራ ቀላል እንደማይሆን ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች