ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ለመሄድ ታክሲ ተሳፍረናል። በውጥረት የታፈነው ጎዳና ወጪ ወራጁን አየር የነሳው ይመስላል። ጩኸት ኑሮው የሆነው ወያላ ዕድሜው በለቅሶ ተጀምሮ በጩኸት በሚገባደድ ሕዝብ መሀል ያለ ዕረፍት ይጮኻል። እንደ ንጋት ጎርናና ድምፁ ሁሉ ጎርበጥባጣ ኑሮው የሚቀጥል ይመስል እሪ ሲል አይታክትም። ጥሪ በማይፈልገው የትግል ጎዳና ላይ የወያላው ልፋት መና የቀረ ይመስላል። የወያላው ጩኸት ቀርቶ ከወዲያ ወዲህ እየተሯሯጠ ላቡን ጠብ አድርጎ ለፍቶ ከሚኖርበት መንደር፣ ወረዳ፣ ዞንና ክልል በግፍ የሚባው ወገን የሚያባራ አይመስልም። የእኛ ሰው ይህንን ሁሉ መገፋት እያሰበ ስለአዋዋሉ፣ ስለኑሮው፣ ስለቤተሰቡ፣ ስለሥራውና በአጠቃላይ ስለአገሩ ዕጣ ፈንታ በሥጋት ተውጦ እያውጠነጠ ባላሰበው በሚገኝበት በዚህ ጊዜ፣ የሕልማችንና የሩጫችን ውጤት በአብዛኛው አንገት ያስደፋል። ከደሳሳ ጎጆ መፈናቀል ሲታከልበት ደግሞ ከሚችሉት በላይ ነው፡፡ ምርር ይላል!
ሲዘሉ መሰበር የመንገዱ ህልውና መሠረት ቢሆንም ቅሉ፣ በዚህ በአገራችን የአረማመድ ዘዬ ሳንዘል በተቀመጥንበት የተሰበርን ጥቂት አይደለንም። የዚህ ጎዳና ትርክት ብዙ ነው። ከመብዛቱ የተነሳም እርስ በርስም ሆነ ከሩቅ ካሉት ጋር ጭምር ያወዛግባል። ነፃ ሐሳብ፣ ነፃ መንፈስና አልጋ በአልጋ የሆነ ጎዳና ለኢትዮጵያ ልጆች አይገባም የተባለ ይመስል ሁሌም ጭንቀትና ውጥረት ነው። በአንድ በኩል ግጭቱ፣ ተንኮሉ፣ ክፋቱና ስግብግብነቱ ከመጠን በላይ እየሆነ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ትንሽ ሥልጣን ያለችውም ሆነ በትልቁ ሥልጣን ላይ ያለው ትናንትን ረስቶ ዛሬን ያስረግመናል። በፈተለው ልክ ሁሉም የድርሻውን ሕይወት እየሸመነና እየለበሰ፣ ለታሪክ ደግሞ ለታዛቢ በሩን መክፈት ሲገባው ራሱ ከሳሽ፣ ራሱ ዳኛ ሆኖ ፍትሕን የጨረባ ተስካር ያደርገዋል። ይህ ዘመን ሁሉን ያስተዛዝባል። የፍትሕ ያለህ ባዩ ወዮታ ግን አድሮ እየተባባሰ የፈጣሪን ቁጣ እየተጣራ ይመስላል። መልካሙና በጎው ነገር እየናፈቀ ዕድሜ ይነጉዳል፡፡ ይገርማል!
ጉዟችን ተጀምሯል። ‹‹ጠላም ይጠጣና ይፈሳል አተላው፣ ጠጅም ይጠጣና ይፈሳል አንቡላው፣ ሥጋም ይበላና ይጣላል አጥንቱ፣ ዕዳም ይከፈላል እየሰነበቱ ዓይኑን ያፈጥና ይቀራል ትዝብቱ…›› ይላል በክራር የሚቀኘው ዘፋኝ፡፡ ዕድሜና ዘመን አሳላፊው መንገደኛ ታክሲያችን ጣራ ሥር ተሰባስቦ አንገቱን እየወዘወዘ ያፏጫል። እኩል ሲያፏጭ የቆየው መልሶ፣ ‹‹ማን እያለቀሰ ማን ያፏጫል?›› ብሎ ሲያፈጥበት፣ ‹‹እገጭ እገው ይላል ቆርቆሮ ሲመታ፣ ዘንድሮ ልወዝወዝ በካቻምናው ፋንታ…›› ብሎ ዘፋኙ ያቋርጣቸዋል። ‹‹ይወዘውዘኛል ይወዝውዝ አባቱ አለ የአገሬ ሰው። እንዲህ ከተፈጠርኩ ጀምሮ በመወዝወዝ ዕድሜዬን ገፍቼ አላውቅም…›› ብለው ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ አዛውንት ተናገሩ። ባለክራሩ ዘፋኝ ቀጥሏል፣ ‹‹ዝንጀሮ በገል አድጦት አይወድቅም፣ እንዲህ ያለ ዘመን አጋጥሞኝ አያውቅም…›› ሲል ከአዛውንቱ ጋር ብቻ ሳይሆን ሐዘን ውስጥ ከወደቁ ጋር አንድ ላይ ያለ ይመስላል። ከመምሰልም በላይ ሆኗል!
ከአዛውንቱ ጋር አዲስ ጨዋታ ተጀምሮ፣ ‹‹እሱንስ ማን አየብዎ? ጨለማ በመልበስ ከጀመሩት ጎራ ቢሆኑስ ኑሮ?›› ሲላቸው ከጎናቸው የተሰየመ ወጣት ከጀርባቸው የተሰየመች ወይዘሮ ደግሞ፣ ‹‹እሱንማ መብራት ኃይል ቀድሞ ጀመረው። እንዲሁ ብልጭ ድርግም ሲያደርግብን ዋለ…›› ብላ አሽሟጠጠች። ‹‹ብልጭ ድርግሙንማ ለመድነው እኮ። እኛን መልመድ ያቃተን ከኃይል ብዛት የተነሳ እየተቆራረጠ ያስቸገረንን አለመግባባት ነው…›› አላት አጠገቧ የተሰየመ ጎልማሳ። ‹‹ኦ ለካ እሱም አለ? ነገር እየበዛ ሚሞሪዬ ሞላ እኮ እናንተ?›› ብላ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ዘመናይ ፈገግ አለች። ‹‹ለምን ‘ዴሊት’ አታደርጊም የተወሰነውን?›› መጨረሻ ወንበር ከተሰየሙት ወጣቶች አንድ ፀጉረ ጨብራራ ሲያናግራት፣ ‹‹እስኪ መጀመሪያ የውስጣችንን ቆሻሻ በቅጡ ማስወገድ እንቻል። መጀመሪያ ሰው በሰው ዴሊት መደረጉ ይቁም፣ ከዚያ ሚሞሪ እናፀዳለን…›› ብላ ጮኸችበት። በትንሽ ትልቁ የሚጯጯኸው ሰው ግን አልበዛባችሁም? ‹‹ምን ይደረግ ደህና ጊዜ መጣ ሲባል ተረኛ አልቃሽ በመብዛቱ እኮ ነው…›› የሚለን ልጅ እግር ቢጤ ነው፡፡ ጉድ እኮ ነው!
ወያላችን ሒሳብ መቀበል ጀምሯል። መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ወጣት የሱቅ ነጋዴዎች ሳይታሰብ ጭቅጭቅ ጀመሩ። አንደኛው፣ ‹‹እንዴት ያለ ደረሰኝ የገዛሁት ዕቃ አለ ትለኛለህ? ሒሳብ እንደምናወራርድ አርባ ጊዜ ማስረዳት አለብኝ? መቼ ነው ግን አንተ የምትሠለጥነው?›› ይላል። ያኛው ደግሞ፣ ‹‹ይኼ ከመሠልጠን ጋር ምን ይገናኛል?›› ይለዋል። ወያላው ከመቅፅበት ከተፍ ብሎ፣ ‹‹ሒሳብ!›› ሲለው አንደኛው ወያላውን ትኩር ብሎ ዓይቶት፣ ‹‹ለስንቱ እንክፈል ዘንድሮ? ከታች እስከ ላይ መቀበል ብቻ? እዚህ ወዳጄ እንደ ቤት እመቤት ያለ ደረሰኝ ይሸምታል…›› ሲል አጉረመረመ። ‹‹አትበሳጭ ወንድሜ ብታወራርደውም ያው ማዋጣትህ አይቀር…›› ይላል ከጎኑ የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ኧረ ተወኝ፣ ሞባይል ሲጎረጉር ሲውል አንደኛ ነው። ሥልጣኔ እሱ ቤት ፌስቡክና ዩቲዩብ ላይ ማፍጠጥ ነው። ሥራ ላይ ደግሞ ያለምጣል…›› ሲል ስለባልደረባው ተረከለት። ያኛው ቀልጠፍ ብሎ፣ ‹‹ዕድሜ ለአንተና ለቢጤዎችህ እሱም ተዘግቶ የሥራና የመረጃ ጉሮሮአችን ተዘግቷል…›› ሲለው ሌሎችም በቁጭት ጭንቅላታቸውን እየነቀነቁ ድጋፋቸውን ለገሱት፡፡ ድንቄም ድጋፍና ተቃውሞ አትሉም ታዲያ!
‹‹መቼ እሱ ብቻ ሆነ ብለህ ነው? በሥልጣኔና በዘመናዊነት ስም መስሎኝ ሁላችንም አሳራችንን የምናየው። ደርሰው ሠለጠንን ባዮች አይደሉም እንዴ የፈጠራ ታሪክ በመንዛት በመገንባት ፈንታ ሲያፈርሱ፣ አንድ በማድረግ ስም ሲሰነጣጥቁ የምንታዘባቸው…›› ካለው በኋላ የአፍታ ዝምታ ነገሠ። ወያላው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይመስላል ተንጠራርቶ፣ ‹‹‘ሒሳብ!›› አለው። ‘ከዚህ በኋላ ብታስጮኸኝ አንተ ታውቃለህ’ ይመስላል ነጋዴው ሒሳቡን ከፍሎ ሲያበቃ በሐሳብ እንደተዋጠ ተክዞ ቀረ። ይኼን የሚታዘቡ ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ ሁለት ጎልማሶች፣ ‹‹ነጋዴ ሁሉ ሌባ፣ ነጋዴ ሁሉ አጭበርባሪና አቁስል ተደርጎ በሚታሰብበት አገር ይኼን ሰው እንዲህ ሆኖ ማየት አይገርምም?›› ይባባላሉ። ቆም ብለው ሲያጤኑት ሁሉም በራሱ ጭንቀት ተውጦ የሰው የሚያዳምጥበት ጊዜ አጥሮታል። ይኼኔ ችግርና ችግርተኛ በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ እየተላከኩ በመፍትሔ ዕጦት ዘመን የሚቆጥረው ወገን እያደር በእጥፍ ይጨምራል። ማጣፊያው ሲያጥር ደግሞ መጥኔ ያሰኛል!
ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ምን ዓይነት ዘመን ነው ዘመነ ድሪቶ፣ አባቱን ያዘዋል ልጁ ተቀምጦ…›› ብለው አዛውንቱ ሲያንጎራጉሩ፣ ‹‹ምን ይደረግ? ይኼ አሁን ያሉት በደስታ ተቀብለን በመከራ የምንሸኛቸው ጊዜያት ድምር ውጤት ነው…›› አላቸው ከጎናቸው የተሰየመ ወጣት። ‹‹እንዲህ አይደለም ወይ ሰው ያለ ቦታው፣ ብሳና ይሆናል ሸንኮራ አገዳው’ የተባለው ታዲያ እኮ ለእኔ ነው ይህን ያህል ዘመን ኖረህ ብሎ ይኼን የሚያሳየኝ…›› ይሉታል። ‹‹ተመሥገን ነው፣ ደግ ደጉን ካዩ እኮ ብዙ ለውጥ አለ። ግን አንዳች ከሚያህል ነጭ ይልቅ ትንኝ የምታህል ጥቁር ነጥብ ትጎላለች…›› ብሎ ሳይጨርስ ከወደ ጋቢና፣ ‹‹ተው… ተው… እንደዚህማ ነገር አታቃል…›› ብሎ አንዱ አቋረጠው፡፡ አዛውንቱ ይኼኔ ፈገግ ብለው፣ ‹‹አይ ወጣት መሆን እንዴት ደስ የሚል ነገር ነው። አደራ ልጆቼ ይኼ ያገባኛል ባይነታችሁ፣ ይኼ ለአገር ለወገን የማሰብ ስሜታችሁ መቼም ቢሆን አይቀዝቅዝ… ብቻ…›› አሉ፡፡ ሐሳብ ጠፍቶ ሳይሆን ሥጋት ሲሰነቀር በሉት!
‹‹…ብቻ ምን?›› አለች ከጎኔ። ‹‹ብቻ ከክፉ መካሪ፣ አገር ከሚያተራምሱና ወገን ከሚበድሉ ጋር አታብሩ። ይኼ በነፍስም በሥጋም እየተጋለጡ ‘እኔ… እኔ…’ ማለት አያዋጣም። መጀመሪያ ለአገር ነው ማሰብ። አገር ማለት እያንዳንዳችን ነን። ሀብትና ሥልጣን ፍለጋ ሲበዛ ነው ከነፍስ ጋር ፀብ የሚጀመረው፡፡ በከንቱ ነገሮች አትሸወዱ። የሚያስከብረው በሥነ ምግባር የተገነባ ሰብዕና ነው፡፡ በልዩነት እመኑ፣ ልዩነትን ማክበር ራስን ማክበር ነው፣ አገር ማክበር ነው፣ መሠልጠን ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ፈጣሪን አትርሱ፣ በገዛ ወገናችሁ ላይ ሰይፍ አትምዘዙ፣ ድሆችን አትበድሉ፣ ጊዜ ሰጠን ብላችሁ አትመፃደቁ፣ ሥልጣን ስትይዙም ሆነ ሀብት ስታፈሩ ለደሃ እዘኑ፣ ከምንም ነገር በላይ እንደ ጀግኖቹ ቅድመ አያቶቻችሁ አገራችሁን አስቡ…›› ሲሉ ታክሲያችን ጥጓን ይዛ ቆመች። ‹‹አዛውንቱ በተለይ ሥልጣን ስትይዙ ለደሃ እዘኑ ያሉት ልብ ይነካል፣ ያለ ድካም የተገኘ ሀብትና ያልተገራ ሥልጣን የደሃ ጠላት ናቸው ማለታቸው እኮ ነው…›› የሚለው ያ ታዳጊ ነበር፡፡ እንዲህ ተባብለን በሰላም ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!