Wednesday, March 29, 2023

የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲን በአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ውስጥ የማካተት ፍላጎትና ተቃርኖ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ አሁን ለደረሰችበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የውጭ ግንኙነት የብሔራዊ ደኅንነትና መሰል ዓውዶችና እየተስተዋለ ላለው አለመረጋጋት መነሻዎች የተለያዩ አመክንዮዎች በየአቅጣጫው ሲሰነዘሩ ይደመጣል፡፡

የታሪክ መዛግብት ኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው፣ አሁን ራሳቸውን ችለው ሉዓላዊ የሆኑና በኢኮኖሚያቸው አድገውና ተመንድገው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች ተምሳሌት ከሆኑት አገሮች የቀደመና ዳጎስ ያለ ታሪክ ያላት፣ ዳር ድንበሯ አይነኬ፣ ለረዥም ጊዜ የመንግሥት አስተዳደርና ሥርዓት ይዛ የቆየች ስለመሆኗ ይናገራሉ፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው በርካታ የታሪክ ውጣ ውረዶች በተፈጠረ ወጥ ያልሆነ አረዳድ የተነሳ በርካታ ንትርኮች በስፋት ይደመጣሉ፡፡ ይህ ንትርክ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ብሎም የማኅበራዊ መስተጋብር ላይ የሰርክ ኩነት እየሆነ ከመምጣት ባለፈ፣ የታሪክ ትርጓሜ አሰጣጥ በእጅጉ እየተራራቀና ጽንፍ እየያዘ መጥቶ የአገሪቱ ብሔራዊ ሥነ ልቦና ውስጥ ሥር እየሰደደ ስለመምጣቱ ይወሳል፡፡

ይህ ለዘመናት የዘለቀው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አነሰም በዛም ሁሉንም የሚያስደስትና የሚያስፈነጥዝ፣ ወይም ሌለውን በአጠቃላይ የሚያሳዝን አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ይሁን እንጂ ተበደልን የሚለው ወገን በደሉን በይቅርታ ለማለፍና ወደፊት አንድ ዕርምጃ ከመሄድ ይልቅ፣ የነበሩ ታሪኮች ላይ ቆሞ የሚተክዝ መሆኑ ሲታወቅ፣ በዚያው ልክ ደግሞ በተበዳይ ወገን የሚነሱ ቁርሾዎች ላይ ተማምኖ ለመሄድ የሚግደረደሩና አሻፈረኝ ባዮችም አልጠፉም የሚል ክርክር አለ፡፡

ታዲያ በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ እያለፈች ያለችውን ኢትዮጵያን ለሁሉም የምትሆን አድርገን እንዴት በአዲስ እንገንባት በሚል በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከዚህ በፊት ለተፈጠሩ ልዩነቶች፣ ወሳኝ ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት ምክክር እንዲደረግ የሚያመቻች 11 አባላት ያሉት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን  ከአንድ ዓመት በፊት መቋቋሙ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ተፈጽመዋል የተባሉ ጉልህ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የተፈጠሩ ቁርሾዎች አሳታፊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ፣ ሲንከባለሉ የመጡ በደሎችና ቁርሾዎች እንዲጠገኑና ዘላቂ ሰላም በመፍጠር ወደ ተሻለ የዴሞክራሲ ሥርዓት ለመሸጋገር የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ብሔራዊ የሽግግር ፍትሕ የፖሊሲ አማራጮችን የያዘ ሰነድ ተዘጋጅቶ የግብዓት መሰብሰቢያ የውይይት መድረኮች ተጀምረዋል፡፡

ይሁን እንጂ ተስፋ በተጣለባቸው ሁለቱም መንገዶች ማለትም ወደ ሥራ በገባው አገራዊ የምክክር ኮሚሽንም ሆነ በዝግጅት ላይ ባለው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አተገባበር ላይ የሚነሱ፣ በተለይም ከአሁናዊ አገራዊ ሁኔታ የመነጩ ሥጋቶች፣ ተቃርኖዎች፣ የገለልተኝነት ጥያቄ፣ አጀንዳውን ጠንሳሽ በሆነው መንግሥት ላይ እምነት ማጣት፣ የተፈጻሚነት ወሰን ላይ ባለ ጥርጣሬ፣ እንዲሁም በኮሚሽኑና በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መካከል የኃላፊነት መጣረስና መሰል በርካታ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ይደመጣሉ፡፡

በአገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ላይ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እምነት የለንም በሚል ድምዳሜ የጋራ መግለጫ አውጥተውም ነበር፡፡ ኮሚሽኑ ሥራ በጀመረ ማግሥት ይፋ በተደረገው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ላይም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢትዮጵያ ወቅታዊ የሰላም ሁኔታ ለጉዳዩ አስቻይ ባለመሆኑ፣ መንግሥት የአገርን ሰላም ያስቀድም የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡ በሌላ በኩል የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ጋር የኃላፊነት መደበላለቅና መሀል መስመር ላይ የሚያገናኙ ጉዳዮች መኖራቸው አይቀሬ በመሆኑ፣ አካሄዱ ከወዲሁ ሊታሰብበት እንደሚገባ ሥጋቱን አሰምቷል፡፡

ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጭ ሐሳቦችን በያዘው የግብዓት ማሰባሰቢያ ሰነድ ላይ በሁሉም ባለድርሻ አካላት መካከል፣ ተመሳሳይ የዓላማ አንድነትና አረዳድ ለመፍጠር ባለመ የምክክር የማስጀመሪያ መድረክ፣ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ተከናውኗል፡፡

በመድረኩ አስተያየታቸውን የሰጡት አገራዊ የምክክር ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ የኢትዮጵያ አገራዊ የምክከር ኮሚሽን ኃላፊነት ተቀብሎ እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ኮሚሽኑ ወደ ሥራ ሲገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ኮሚሽኑ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን መባሉ ቀርቶ ‹‹የአገራዊ ምክክርና ዕርቅ ኮሚሽን›› ቢባል፣ ሁለቱንም ሥራ አጠናክሮ መሄድ ይችል እንደነበርና በየቀኑ ኮሚሽኖችን ከማቋቋም አዋጁን እንደገና ዓይቶ በመከለስ አብሮ ማስኬድ ይሻላል የሚል ሐሳብ ቀርቦላቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ የተባለ ነገር ባይኖርም አገራዊ የምክከር ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ችግር ይፈታሉ ተብለው ተቋቁመው የታለመላቸውን ዓላማ ሳይፈቱ ከፈረሱት የዕርቀ ሰላም ኮሚሽንና የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽኖች ብዙ ተሞክሮ መውሰዱን ገልጸው፣ አሁንም ይህ የሽግግር ፍትሕ ሕይወት ካለውና እየተራመደ ካለው የምክክር ኮሚሽን ልምድ ሊወሰድ እንደሚችል ዋና ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡

‹‹ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ ኮሚሽኑ ኅብረተሰቡ ውስጥ ዘልቆ ወደ ሥራ ገብቻለሁ እያለ፣ የሽግግር ፍትሕም እዚያው ላይ መግባቱ በኮሚሽኑ ላይ ምን ዓይነት ተግዳሮት ይፈጥር ይሆን የሚል ጥያቄ ፈጥሮብኛል፤›› ሲሉ መሰፍን (ፕሮፌሰር) አክለው ተናግረዋል፡፡

ከላይ የተነሱት አስተያየቶችን ጨምሮ በበርካቶች ከሚነሳው ሥጋት ውስጥ አገሪቱ ውስጥ የቆዩ ታሪካዊ ቁርሾዎችንም ሆነ የፖለቲካ አለመግባባቶችን ለመፍታት፣ ትርጉም ያለው ሁሉን አቀፍና አሳታፊ የሆነ የምክክር፣ የውይይትና የንግግር መድረክ ከማዘጋጀት ውጪ በየጊዜው እየተነሱ ኮሚሽን ማቋቋም ጉንጭ ማልፋት መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡

አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር)፣ ኮሚሽን በማቋቋምና በማብዛት የኢትዮጵያ ችግር ሊፈታ እንደማይችል፣ በመሆኑም በቀጣይ በአገራዊ ምክክሩ መነሻ ከኅብረተሰቡ ጋር በሚደረጉ ውይይቶች በሚገኙ ውጤቶች ላይ ተመሥርቶ ወደ ሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ መገባት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲውን ለማስፈጸም አዲስ ኮሚሽን ከማቋቋም፣ በሥራ ላይ ያለውን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ እንደ አዲስ በማሻሻል የሽግግር ፍትሕና የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተብሎ መጠቃለል ቢኖርበት ሲሉ ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ የሽግግር ፍትሕ ከየትኛው ዓመት ይጀመር የሚለው ጉዳይ በጣም ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ ካልተከናወነ፣ ማኅበረሰቦችን ላልተፈለገ ግጭት ሊዳርግ እንደሚችል በመግለጽ፣ ድሮ የነበረውን አካል ለመጠየቅ ጠያቂም ተጠያቂም ስለማይኖር ሒደቱ መልስ ሊሰጥ በሚችል መንገድ መከናወን አለበት ብለዋል፡፡

ለዚህም ያመች ዘንድ በአመዛኙ ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀበት ጊዜ ጀምሮ ተፈጸሙ የተባሉትን በደሎች በማጥራት መጠየቅ ያለባቸው ተጠይቀው፣ ካሳ ለሚከፈላቸው ካሳ ተከፍሎዋቸው፣ ምሕረትም ለሚያስፈልጋቸው ምሕረት ተደርጎላቸው የመጨረሻ ፍፃሜ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

‹‹በመርህ ደረጃ ሁለቱንም የምንደግፈው ቢሆንም፣ ነገር ግን መሠረታዊ የሆነው ችግር እነዚህ ተቋማት አደረጃጀታቸው ምን መምሰል አለበት? የትኛው መቅደም አለበት የሚለው ጥያቄ ነው፤›› ያሉት ደግሞ፣ ኢትዮጵያዊ ተነሳሽነት ለሰብዓዊ መብቶች የተሰኘ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሐንስ ሰሎሞን ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ አብዛኛው ችግር ሊፈታ የሚችለው በሕግ ሳይሆን በፖለቲካ ውይይት መሆኑን፣ መጀመሪያ መቅደም ያለበት አገር አቀፍ የሆነ ሁሉን ያሳተፈ የፖለቲካ ጉባዔ በማድረግ ፖለቲካ መፍትሔ ማምጣት እንጂ ኮሚሽን በማቋቋም በራሱ መፍትሔ ሊያመጣ እንደማይችል አስረድተዋል፡፡

 በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የሕግ ባለሙያው አቶ አሮን ደጎል፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ራሱን የቻለ ትኩረትና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ሥራ ነው ብለዋል፡፡ በአገራዊ ምክክሩ ውስጥ ይካተት ሲባል ለዚህ ኮሚሽን የተሰጠው ኃላፊነት መድረክ ማመቻቸትና ሁነቶችን መፍጠር እንጂ፣ እንደ ሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ማስታረቅ ወይም ክስ የመመሥረት ተግባራት አይደለም ሲሉ አክለዋል፡፡

በመሆኑም የሽግግር ፍትሕ በዋነኛነት ከሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከሕግ የበላይነት አለመስፈን፣ እንዲሁም ከወንጀል ድርጊት ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን የሚመለከት በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚፈልግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በተቃራኒው ግን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች ከሚነሱበት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ጋር አብሮ ይሂድ ከተባለ የሽግግር ፍትሕ ዓላማውን ላይመታ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

   በመሆኑም አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን እንደገና አሻሽሎ ይህን ማስገባቱ ያልተጠበቀ ውጤቶች ሊመጡ ስለሚችሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ነገር ግን የሽግግር ፍትሕ ቀድሞ ቢተገበር፣ የሆነ አካል ላይ የደረሰ ጉዳት ወይም ጥቃት ካለና መጠየቅ ካለበት መጀመሪያ ማን አጠፋ? ማን ላይ ጉዳት ደረሰ? እነማን ናቸው መቀጣትና መጠየቅ ያለባቸው? ለሚሉት ጉዳዮች መልስ ማግኘት ቢቻልና በቅጣት ወይም በይቅርታ የሚታየው ታልፎ፣ መከሰስ ያለባቸው ሁሉ ተከሰው መልስ ካገኙ በኋላ ወደ ምክክር መሄድ ቢቻል የተሻለ አማራጭ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ያጠፋ መቀጣት አለበት፣ ይቅርታ የሚደረግለት አካል ይቅርታ ሊደረግለት ይገባል፣ የተበደለ መካስ አለበት፣ ከዚያ እነዚህ የሕግ ጉዳዮች ሲጠናቀቁ ወደ ምክክር መገባት ይኖርበታል፡፡ በመሆኑም አገራዊ ምክክሩና የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት ሒደቱ አንድ ላይ መጀመሩ አይታየኝም፣ የሕግ ጉዳይ መፍትሔ ሳያገኝ ነገሮች በምክክር ተውጠው ፍትሕ ላይሰፍን ይችላል፡፡ ስለዚህ የፍትሕ መስፈንና ሰላም የማምጣት ጉዳይ ተለያይተው መምጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ፍትሕ ሳይረጋገጥ ሰላምን ማምጣት አስቸጋሪ ነው፤›› ሲሉ አቶ አሮን ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ ምክክርና የሽግግር ፍትሕ አተገባበር ዓለም አቀፍ ልምድ ሁለቱም አንድ ላይ ሆነው እንደሚተገበሩ የገለጹት፣ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አዘጋጅ ባለሙያዎች ቡድን አባል የሆኑት አቶ ምሥጋናው ሙሉጌታ ናቸው፡፡ በዚህም አንዳንድ አገሮች አገራዊ ምክክር ካደረጉ በኋላ ከምክክሩ የሚወጡ ምክረ ሐሳቦች ላይ በመመርኮዝ የሽግግር ፍትሕ ሒደቶች ውስጥ እንደሚገቡ፣ አንዳንድ አገሮች ደግሞ አገራዊ ምክክር ሳያደርጉ የሽግግር ፍትሕ ትግበራ ውስጥ ይገባሉ ብለዋል፡፡

ይሁን አንጂ በቀረበው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማራጭ ውስጥ የተዘረዘሩት እውነታን ማፈላለግና ማካካሻ የሚባሉት ጉዳዮች፣ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን በማሻሻልና ወደ በኮሚሽኑ እንዲተገበሩ በማድረግ የሁለቱ ሒደቶች ተመጋጋቢ ሆነው እንዲሄዱ ማድረግ ይቻላል እንጂ፣ አንዱ ሌላውን የመተካት ሥራ አያከናውንም ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ጠቅለል ያለና ሁሉም ዓይነት ግጭቶች ቢካተቱ፣ የሽግግር ፍትሕ እንዴት ሊተገበር ይችላል ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -