በኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ የተማከለና የተቀናጀ መረጃ አቅርቦት አለመኖር፣ በዘርፉ አዳዲስ ግኝቶች እንዳይበራከቱ እንቅፋት መሆኑ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ኦርቢት የልህቀት ማዕከል ከዓለም የንግድ ማዕከል (International Trade Center)፣ እንዲሁም ከኔዘርላንድ ትረስት ፈንድ ጋር በመተባበር ‹‹የግብርና ቴክኖሎጂ ለምግብ ዋስትናና ሥራ ፈጠራ›› በሚል ርዕስ መጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. በሂልተን ሆቴል ባዘጋጁት የባለድርሻ አካላት ሲምፖዚየም ላይ ነው፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ እንደተገለጸው የግብርና ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂና ዲጂታይዜሽንን የተላበሰ እንዲሆን ዘመናዊ የተቀናጀ መረጃ ሊኖር ይገባል፡፡
አንድ አገር ያሏት አንጡራ ሀብቶች እንዲለሙ መሠረተ ልማቶች እንደሚያስፈልግ ሁሉ፣ የግብርና መረጃዎችም በአግባቡ ተሰናድተው እንዲቀርቡና አገልግሎት ላይ እንዲውሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች አገሮች ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ ተገኝተው ሥራቸውን ያስተዋወቁ ወጣት የሥራ ፈጣሪዎች ግብርናን በፈጠራና በአዳዲስ ግኝት ለማጀብ ፈተና ከሚሆንባቸው ጉዳዮች ውስጥ፣ የተቀናጀ ማዕከላዊ የግብርና መረጃ አለመኖሩ ዋነኛው መሆኑን በመግለጽ በአገሪቱ ብሔራዊ የግብርና መረጃ የሚገኝበት የዳታ ቤዝ አለመኖሩን በማስረጃ አቅርበዋል፡፡
የሴንተር ፎር አግሪካልቸራል ኤንድ ሩራል ኮርፖሬሽን (The Technical Centre for Agricultural and Rural Cooperation – CTA) ፕሮግራም አስተባባሪ ቤንጃሚን ኳሲ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የትኛውንም ቴክኖሎጂና አገልግሎት በግብርናው ዘርፍ ላይ ለመተግበር ወሳኙ ጉዳይ የተቀናጀና የተሟላ መረጃ ማዘጋጀት ነው፡፡
አንድ አገር የውጭ ኢንቬስተርን ስትጋብዝ ከምንም ነገር በላይ በመጀመርያ ልታቀርበው የሚገባው ጉዳይ ፍላጎቱ በቀረበበት ዘርፍ ላይ ያለውን አጠቃላይ መረጃ መሆኑን፣ ኢትዮጵያም በዚህ ጉዳይ ክፍተት ካለባቸው አገሮች አንዷ እንደሆነች ቤንጃሚን (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
በሚቀጥሉት አምስትና አሥር ዓመታት የዓለም አገሮች ሉዓላዊነት የሚወሰነው በገነቡት የመረጃ አቅም በመሆኑ፣ ለዚያ የሚሆን ዝግጅት የማያደርጉ ከሆነ የአገሮቹ ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚወድቅ እንደሆነ አስጠንቅቀዋል፡፡
የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴን (ዶ/ር) በመወከል ንግግር ያደረጉት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር)፣ በባህላዊ መንገድ የሚዘወተረው ግብርና በተለይም ለወጣቱ ትውልድ የማይመከርና አገሪቱም በተለይም በግብርና የተሰማራውን ወጣት የኅብረተሰብ ክፍልን ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጋር ማስተሳሰር እንደሚጠበቅባት ተናግረዋል፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ በነበረው ውይይት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በተለይም በኢትዮጵያ በዲጂታላይዜሽንና በሜካናይዜሽን የሚያከናውናቸው ሥራዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ የቴክኖሎጂ ሽግግሩ አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን በመግለጽ እንደ መንግሥታዊ ተቋም ተግባራቱን በሚከውንበት ጊዜ የተገኙ ውጤቶችንና ተግዳሮቶችን እንዲያጋራ ተደርጓል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ሐሰን ሁሴን (ዶ/ር)፣ ግብርና የአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እንደሆነና የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድም ብዙኃኑን የሰው ኃይል የተሸከመ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
የግብርናው ዘርፍ የተለያዩ አዳዲስ ግኝቶችና የሥራ ፈጠራዎችን የሚሻ እንደሆነ የገለጹት ሐሰን (ዶ/ር)፣ ይህም ዘርፉ ለአገሪቱ ፍሬያማ ልማት እንዲያስገኝ ስለሚጠበቅበት ነው ብለዋል፡፡