የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሽግግር ኢኮኖሚ ተብለው የሚገለጹ 138 አገሮችን ልማትና ዕድገት የሚመዝን የልማት መለኪያ (Development Index) ሊያዘጋጅ ነው፡፡
በሦስት ዓመታት ውስጥ ሙሉ ዝግጅቱ የሚጠናቀቀውና በአጠቃላይ 2.2 ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቀው ይህ ፕሮጀክት፣ ከመቶ በላይ የልማት መለኪያዎችን በመጠቀም በዓለም ያሉ አገሮች አድገዋል? ወይስ አላደጉም? የሚለውን አንድና ወጥ የሆነ መመዘኛ የሚያወጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የሪሰርችና ፕሮግራም ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር)፣ የፕሮጀክቱ ዋና ሐሳብ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ልማት የሚለካበት ክፍተት ወይም ውስንነት አለበት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ይህን ያህል አድጋለች፣ አላደገችም? ዕድገቱ ይታያል፣ አይታይም? የሚለው ከዝቅተኛው ማኅበረሰብ አንስቶ እስከ ሳይንቲስት ነው የሚባለው ኅብረተሰብ ድረስ ከፍተኛ ልዩነት መኖሩንና ይህ ልዩነት የተፈጠረው ለምንድነው ተብሎ ሲገመገም በዋናነት የልማት መለኪያው እጥረት ስላለው እንደሆነ የኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ፈርጀ ብዙ የልማት መለኪያ ፕሮጀክትን ወደ ሥራ ለማስገባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በኢንተርለግዠሪ ሆቴል ባደረገው የውይይት መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ፕሬዚዳንት አምዲሳ ተሾመ (ዶ/ር) እንዳስረዱት፣ ላለፉት 30 ዓመታት በርካታ የምርምርና ጥናት ሥራዎችን ያደረገው አሶሴሽኑ በዚህ ወቅት የጠነሰሰው ፕሮጀክት ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ያለው ነው፡፡
‹‹ዕድገትን መለካት ቀላል አይደለም፡፡ ዕድገት ሲባል ምንድነው? ዕድገት መኖሩን በቀጥታ የሚያቀርቡት ጉዳዮች ምንድናቸው? የሚለውን ለይቶ በአንድ መመዘኛ (Index) ማቅረብ ቀላል ነገር አይደለም፤›› ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡
በዚህ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ልማትንና ዕድገትን ለመለካት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው መመዘኛ ጥቅል አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) እንደሆነ፣ ይህ መመዘኛ ደግሞ ለረዥም ዓመታት አገሪቱ እንደተገለገለችበትና ነገር ግን መመዘኛው የራሱ የሆኑ ድክመቶች እንዳሉበት አምዲሳ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
መለኪያው የማያካትታቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዳሉ ፕሬዚዳንቱ አክለው፣ ከዚህ በመነሳት ፈርጀ ብዙ የሆነ አመላካች (Multidimensional Indicator) ለአገርና ለዓለም አቀፍ ኅብረተሰብ ለማቅረብ በሚል ጥናቱ እንደተጠነሰሰ፣ አሶሴሽኑ እስካሁን ካደረጋቸው ጥናቶች አስተዋጽኦው ከፍተኛ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ፕሮጀክቱ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ አንደኛው የፈርጀ ብዙ ልማት መመዘኛ (Multidimensional Development Index – MDI) የሚባለው ሲሆን፣ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የልማት መመዘኛ (Ethiopian Multidimensional Index – EDI) የሚባለው ነው፡፡
የፈርጀ ብዙ ልማት መመዘኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራና በዓለም ላይ የሚገኙ 138 የሽግግር (ትራንዚሽናል) ኢኮኖሚ አገሮች በሚዘጋጀው መለኪያ ደረጃ የሚሰጥ ነው፡፡ በየሁለት ዓመቱ ደረጃቸውን መወሰን የሚያስችልም ነው ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የልማት መመዘኛው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ፈርጀ ብዙ ዕድገት ምን ይመስላል የሚለውን ከ11 ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች አንፃር ምን ይመስላል የሚለውን የሚለካ፣ ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ልማቷ ምን ያህል ነው የሚለውንም በመለኪያዎቹ ደረጃ የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡
‹‹አደግን ይባላል፣ እኛ ጋ ግን ጠብ ያለ ነገር የለም የሚል ሐሳብ አለ፡፡ እነዚህን ሁሉ ለመመለስ የሚያስችሉ ፈርጀ ብዙ መለኪያዎችን ያካተተ ሳይንሳዊ መመዘኛ ማዘጋጀት፣ ምናልባት ወገንተኝነትን ሊቀንስ ይችላል፤›› ሲሉ ደግዬ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ አጋሮች ጋር በመነጋገር ፕሮጀክቱ ከዚህ በኋላ ወደ ሥራ እንደሚገባ የገለጹት ደግዬ (ዶ/ር)፣ በዚህ ዓመት የዶክመንት ሥራውን በማጠናቀር ገንዘብ መዳቢ አጋሮች የሚያወጡትን መርሐ ግብር መሠረት በማድረግ አንደሚሠራ፣ ፕሮጀክቱ በጠቅላላው ሦስት ዓመት የሚወስድና 2.2 ሚሊዮን ዶላር የሚፈልግ መሆኑን አክለዋል፡፡