ብልፅግና በነፃነት ስም በሚፈጸም ወንጀል ምክንያት በትግሉ ያገኘውን ነፃነት እያጣ መሆኑን አስታውቆ፣ ነፃነት ከኃላፊነት ጋር ሚዛናዊነቱን ጠብቆ እንዲሄድ የመንግሥት ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሚዲያዎች፣ የፍትሕ ተቋማት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ ምሁራንና የአገር ሽማግሌዎች የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ አስፈጻሚ ጥሪ አቀረበ፡፡
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከመጋቢት 7 እና 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ፣ ኢትዮጵያ ካለፈው መንገድ የመጣችበትን፣ ወደ ብልፅግና ለመሻገር በድልድዩ ላይ የቆየችበትን፣ በድልድዩ ላይ በቆየችባቸው ወቅቶች ያገጠሟትን ፈተናዎችና ተግዳሮቶች በዝርዝር መርምሮ፣ እያጋጠሙት ያሉ ፈተናዎች በዋናነት ከአምስት ነገሮች የመጡ መሆናቸውንና ለእነዚህም ተገቢ ነው ያለውን የትግል ስልት ቀይሷል፡፡ ታሪክ የሚመነጭ፣ ነፃነትን ለማስተዳደር አለመቻል፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችንን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች እየገነገኑ መምጣታቸው፣ የኑሮ ውድነትና ሌብነት መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ኢትዮጵያውያን አያሌ አኩሪ ታሪኮችና በታሪክ ውስጥ ያገኘናቸው ዕድሎች ቢኖሩም፣ በተቃራኒው ደግሞ በታሪካችን ውስጥ ያልፈታናቸው፣ ተጨማሪ ችግር አድርገን የጨመርናቸውና ያልተግባባንባቸው ዕዳዎችም መኖራቸውን ጠቁሟል፡፡ ”እነዚህ ዕዳዎች የመነታረኪያ፣ የመጋጫና የመከፋፈያ ምክንያቶች ሊሆኑብን አይገባም፡፡ ዕዳዎቹን ወረስናቸው እንጂ አልፈጠርናቸውም፡፡ መጡብን እንጂ አልሄድንባቸውም” ብሏል፡፡
የተሻለው የመጀመሪያ መፍትሔ ለዕድሉም ለዕዳውም ተገቢውን ዕውቅና መስጠት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዕድሉን ለመጠቀም፣ ዕዳውን ደግሞ ለማራገፍ ጠንክሮ መሥራት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሠለጠነና የሰከነ አካኼድ አዋጪ መሆኑን የዓለም ታሪክ አሳይቶናል፡፡ በመሆኑም ያለፉ ዕዳዎቻቸውን በሠለጠነና በሰከነ መንገድ በምክክርና በውይይት፣ በይቅርታና በዕርቅ ለመፍታት የሞከሩ አገሮች ግን ወደ ተሻለ መግባባትና ወደላቀ አንድነት ለመምጣት ችለዋል፡፡ እኛም የሚያዋጣን ይኼ ነው፡፡ የጀመርነው አገራዊ ምክክር እንዲሳካ እናድርግ ብሏል፡፡
ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግለጫው እንዳብራራው፣ እንደ ውሻ አጥንት ከጠላት በሚወረወርልን አጀንዳ እየተራኮትን፣ ለልማት የምናውለውን ጉልበትና ጊዜ ለሤራ ትንተና እያባከንን፣ አንድ ጋት ወደ ብልፅግና ፈቀቅ ልንል አንችልም፡፡ አገር መውደድ ሌላውን ወገን በመውደድ እንጂ በመጥላት አይገለጽም፡፡ ለሌላው ወገን መስዋዕትነት በመክፈል እንጂ በግጭትና በትንኮሳ አይለካም፡፡ የሕዝብን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ከሚንዱ፣ ጥላቻንና ግጭትን ከሚያባብሱ ንግግሮችና ድርጊቶች በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥትና የፓርቲ ኃላፊዎች ሊቆጠቡ እንደሚገባና የፓርቲና የመንግሥት አመራሮች ችግሮች በውይይትና በሕግ አግባብ ብቻ እንዲፈቱ ማድረግ እንዳለባቸው አብራርቷል፡፡
የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩና መሠረት እንዲይዙ መሥራት አለባቸው፡፡ ሰላም እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲጠናከር፣ ሕግና ሥርዓት እንዲከበር፣ መታገል በዋናነት ከአመራር የሚጠበቅ ሚና መሆኑን ለአፍታም ሊዘነጋ እንደማይገባና የሃይማኖት አባቶች፣ ሚዲያዎች፣ አክቲቪስቶችና ምሁራን ያለፉ ቁስሎችን ከሚቀሰቅሱ፣ ጥላቻን ከሚያነግሡ፣ ሕዝብ በጥርጣሬ እንዲተያይ ከሚያደርጉ፣ የሀገርን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ከሚጥሉ ድርጊቶችና ንግግሮች እንዲጠበቁ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡
በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ባጋጠሙ ችግሮች የተነሳ በተፈጠረው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት የኑሮ ውድነቱ እየጨመረ መምጣቱን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መገምገሙን ጠቁሞ፣ ከኑሮ ውድነቱ ጋርም የሥራ አጥ መጠኑ መጨመሩን፣ ችግሩን በጊዜያዊነትና በዘላቂነት ለመፍታት ዕርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑንና ፈተናውን በብቃት ለመሻገር መንግሥት መራር ውሳኔ ሊወስንባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውንም አረጋግጧል፡፡ ችግሩ በዘላቂነት እስከሚፈታ ድረስ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን የሚያቃልሉ ጊዜያዊ ዕርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበትና በችግሩ ላይ ቤንዚን የሚጨምሩ አካሄዶችን ማረም ተገቢ መሆኑን፣ ምርትን በተገቢ መጠን ለማምረትና ወደ ገበያ ለማድረስ የሚታዩ የአመራርና የአሠራር ችግሮች እንዳለባቸው አቅጣጫ አስቀምተጣል፡፡ በየአካባቢው የሚዘረጉ ኬላዎች ከሕግ አግባብ ውጭ የሚያካሂዱት ዕገዳና ዘረፋ በአመራር ቁርጠኝነትና ሕግን በማስከበር ሊፈታ ይገባዋል ብሏል፡፡
ብልፅግና ትልቅ ፈተና የሆነበት ሌብነት ሲሆን፣ አራት ኃይሎች የጋራ ግንባር ፈጥረው እየፈጸሙት መሆኑንና እነሱም በመንግሥት ውስጥ የሚገኙ ሌቦች፣ በባለሀብቱ አካባቢ ያሉ ሌቦች፣ በብሔር ዙሪያ ያሉ ሌቦችና በሚዲያው አካባቢ ያሉ ሌቦች እንደሆኑና ለአንድ ዓላማ አራት ሆነው እየሠሩ አገር እያጠፉ መሆናቸውን ኮሚቴው አብራርቷል፡፡ መንግሥት ሁሉንም ዓይነት ሌቦች ለማጥፋት የጀመረውን ዘመቻ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ለዚህም የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እጃቸውን አስቀድመው ንጹሕ በማድረግ ትግሉን እንዲመሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡