Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየኤክሳይስ ረቂቅ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት ጉዳት በሚያመጡ ምርቶች ላይ የተጣለው ምጣኔ እንዲታይ...

የኤክሳይስ ረቂቅ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት ጉዳት በሚያመጡ ምርቶች ላይ የተጣለው ምጣኔ እንዲታይ ተጠየቀ

ቀን:

በሚስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራው የተሻሻለው ረቂቅ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት፣ በጤና ላይ ጉዳት በሚያመጡ ምርቶች ላይ የተጣለው ምጣኔ ዳግም እንዲያጤንና የሚመለከታቸው የሲቪክ ማኅበረሰብ አካላት እንዲወያዩበት ተጠየቀ፡፡

በተለይ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መንስዔ የሆኑ ስኳር፣ ጨውና ዘይት የበዛባቸው የታሸጉ ምግቦች፣ አልኮል መጠጦችና ትምባሆን በተመለከተ፣ በረቂቅ ኤክሳይስ ታክሱ የተቀመጠው ምጣኔ አነስተኛና የኢትዮጵያን በሽታን ቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ የጤና ፖሊሲ ያላገናዘበ በመሆኑ፣ ፓርላማው በእነዚህ ላይ የተጣለውን ምጣኔ በጥልቀት ሳይመረምር እንዳያፀድቀው፣ ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር መጋቢት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ተገልጿል፡፡

የጤና ጉዳት በሚያስከትሉት ትምባሆ፣ አልኮል መጠጦች እንዲሁም ምግቦች አጠቃቀምን የተመለከቱ ጤናማ የፖሊሲ ማዕቀፎች እንዲኖሩ፣ ጤና ሚኒስቴር ከሚተገብረው በሽታን ቀድሞ የመከላከል ፖሊሲ ጋር የተጣጣሙ ፖሊሲዎች እንዲወጡ፣ ኅብረተሰቡ፣ ፖሊሲ አውጪዎችና ሕግ አስከባሪዎች ግንዛቤ እንዲያኙ በመሥራት ላይ የሚገኙት ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማኅበር አቶ የማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ እንዲሁም መቋሚያ ኮሚዩኒቲ ዴቨሎፕመንት በጋራ በሰጡት ምክረ ሐሳብም፣ በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶች ላይ ፓርላው ከሲቪል ሶሳይቲዎችና ከጤና ባለሙያዎች ጋር ውይይት እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡

- Advertisement -

የተሻሻለው ረቂቅ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለፓርላው ቢመራም፣ ፓርላው በአሠራር ሥርዓቱም ሆነ በሥነ ምግባር ደንቡ መሠረት አዋጁን ከማፅደቁ በፊት ከሚመለከታቸውና ጥያቄ አለን ከሚሉ አካላት ጋር ለመወያየት ዕድል እንዳለው የኢትዮጵያ የምግብና የመድኃኒት ባለሥልጣን የሕግ አማካሪ አቶ ደሞዝ አማን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የባለሥልጣኑ የሕግ አማካሪ አቶ ደሞዝ እንዳሉት፣ የፓርላማ አባላት ማተኮር ያለባቸው ከኤክሳይስ ታክስ አዋጅ አንፃር የተቀመጠው ምጣኔ ዓላማውን ያሳካል ወይም አያሳካም? የሚለውን ነው፡፡

 ለ17 ዓመታት ሲተገበር የነበረውና ከሦስት ዓመታት በፊት የተሻሻለው ኤክሳይዝስ ታክስ፣ በጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ምርቶች ላይ የታክስ ምጣኔ በመጨመሩ የተወሰነ ለውጥ ማሳየቱን፣ ይህ ለውጥ በቂ ባልሆነበት ደረጃ በአሁኑ ረቂቅ አዋጅ በሕግ የተከለከሉ ምርቶች ጭምር ታክስ ተጥሎባቸው መምጣታቸውንም ፓርላማው ሊያየው ይገባል ብለዋል፡፡

ለአብነትም ትምባሆ ላይ ከዚህ ቀደም የተከለከሉ ኤሌክትሮኒክ ኒኮቲን ሲጋራና ከሲጋራ ወጣ ያሉ ምርቶችን ሁሉ ሊፈቅድ የሚችል ሐሳብ ይዞ መምጣቱ ትክክል አለመሆኑን በመግለጽ፣ ይህ ከምግብና ከመድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ጋር ስለሚጋጭ፣ በተሻሻለው ረቂቅ ኤክሳይዝ ታክስ የተካተቱ ምርቶች ሙሉ ለሙሉ መውጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

እንደ አቶ ደሞዝ፣ ትራንስፋት ማለትም በዘይት ውስጥና በከፊል ሃይድሮጅኔትድ ዘይት (በሚረጉ)፣ የተለያዩ በሽታዎች የሚያመጡ ስኳር፣ ዘይትና ጨው የበዛባቸው የታሸጉ ምግቦች፣ ተላላፊ ላልሆኑ ለልብ ሕመም፣ ለስኳርና ከፍተኛ ለሆነ የደም ግፊት መንስዔ ስለሆኑ በበፊቱ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ተካተው የነበሩ ቢሆንም፣ አሁን በቀረበው ረቂቅ እንዲወጡ መደረጉ ጉዳቱ እንጂ ጥቅሙ አያመዝንም፡፡

‹ይህ ለምን ሆነ?› የሚል ጥያቄ ተነስቶ እንደነበር የተሰጠው ማብራሪያም ‹ለማስፈም ስለማይቻል ነው› የሚል እንደነበርና ነገር ግን ለማስፈጸም የማይቻልበት ምክንያት ግልጽ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቀደመው 1186 ኤክሳይስ ታክስ አዋጅ እነዚህን ምርቶች በተመለከተ ማስፈጸሚያ ሥልት እንደያዘ፣ ከእነዚህም ምርቱ ማሸጊያ ላይ ገላጭ ጽሑፍ እንዲኖር፣ ይህንንም መሠረት አድርጎ የምርቱን ይዘት ማወቅ እንደሚቻል ያስቀመጠ ነበር ብለዋል፡፡

ከተዘጋጀ 100 ግራም ምግብ ውስጥ 40 ግራም ወይም የበለጠ ሳቹሬትድ ስብ የያዘ ወይም የሳቹሬትድ ቅባት መጠኑን ከተለጠፈበት መግለጫ ላይ ለማወቅ የማይቻል ከሆነ 30 በመቶ ታክስ ያስቀምጥ እንደነበር ሆኖም ይህ መውጣቱን ያክላሉ፡፡ የይዘት መግለጫው ላይ አጠራጣሪ መጠን ከተካተተም በቤተ ሙከራ ማረጋገጥ የሚቻልበት አማራጭ እያለ ከተሻሻለው ረቂቅ እንዲወጣ መደረጉ አግባብ ባለመሆኑ ፓርላማው ይህንን በደንብ ማየት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

በተሻሻላው ረቂቅ የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ አሁን የተቀመጠው ምጣኔ በቂ አይደለም ያሉት አቶ ደሞዝ፣ ለአብነት በ2012 አንድ ፓኮ ሲጋራ ላይ 8.00 ብር እና 30 በመቶ ኤክሳይዝ ታክስ እንዲከፈል እንደሚል፣ በ2012 ላይ 8.00 ብር የነበረው የመግዛት አቅም አሁን ላይ መውረዱን፣ አዋጁ ላይ የዋጋ ግሽበት ሲኖርና የሰዎች ገቢ ሲያድግ ገንዘብ ሚኒስቴር ይህንን ታሳቢ እያደረገ እስከ 10 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ እንዲጨምር ሥልጣን ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ በተሻሻለው ላይ የቀደመው ምጣኔ መቀመጡ በፓርላማው መታየት አለበት ብለዋል፡፡

  ዓላማችን ለጤና ጎጂ የሆኑ ምግብና ትምባሆ ተጠቃሚዎችን ቁጥር መቀነስ፣ የኅብረተሰቡን ጤና መጠበቅና የመንግሥትን ግብር ማሳደግ በመሆኑም፣ ጤናን በሚጎዱ ምርቶች ላይ አስፈላጊ የታክስ ምጣኔ እንዲጨመር፣ ያላግባብ የገቡ ምርቶች እንዲወጡ፣ ያላግባብ እንዲወጡ የተደረጉ ምርቶች ተመልሰው እንዲገቡ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ፓርላማው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሊመክርበት እንደሚገባ አቶ ደሞዝ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...