Monday, March 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ መንግሥቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ እንደሆነ ነው የሚታወቀው፡፡ የዜጎችን ከቦታ ወደ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት ሰበብ እየደረደሩ ለማደናቀፍ መሞከር ከሕጉ ጋር ይፃረራል፡፡ ማንም ሰው ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኝነቱ እስካልተረጋገጠ ድረስ ወንጀለኛ ካለመባሉም በላይ፣ ንፁህ እንደሆነ የመገመት መብት እንዳለው በሕግ ጭምር የተረጋገጠ ነው፡፡ ከአንዳንድ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ የሚደረገው ፍልሰት መንግሥትን በኃይል በመጣል ሥልጣን ለመቆጣጠር ያለመ እንደሆነ በይፋ ሲነገር፣ የዜጎች መብትና ነፃነት ጉዳይ ካልታሰበበት አጠያያቂ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሐሳብ ከሕግም፣ ከፖለቲካም ሆነ ከሞራል አኳያ ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ የሰዎችን ሕጋዊ እንቅስቃሴ ለመገደብ ሊውል ጭምር ይችላልና፡፡ በዚህ ዘመን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን እንዳያካሂዱ በሕግ አስፈጻሚ አካላት ሲታወኩ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ደግሞ በአዋኪዎች ላይ ፍትሕ ሚኒስቴር ክስ እንዲመሠርት ሲጠይቅ መስማት ያስደነግጣል፡፡ የግለሰቦችንም ሆነ የፓርቲዎችን ሕጋዊ መብትና ነፃነት መጋፋት በሕግ ማስጠየቅ አለበት፡፡

ለአንድ አገር ሰላምና ለሕዝብ ደኅንነት ዋነኛው መሠረት የሕግ የበላይነት መከበር ነው፡፡ አገር በሕግና በሥርዓት ስትመራ የዜጎች መብትና ነፃነት እንደሚከበረው ሁሉ፣ ዜጎችም ነፃነታቸውንና መብታቸውን ሲያጣጥሙ ሕጋዊ ግዴታቸውን በመወጣት ጭምር ይሆናል፡፡ መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን ሲወጣም የዜጎችን መብትና ነፃነት እንዳይጋፋ መጠንቀቅ አለበት፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲኖር ብልሹ አሠራሮችም ካለመኖራቸውም በላይ፣ እንዳሻን እንሁን የሚሉ ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች አይኖሩም፡፡ በተደጋጋሚ በምሳሌነት የሚጠቀሱት የ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ የሥነ መንግሥትና የምጣኔ ሀብት ሊቁ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ ‹‹…በሥርዓት ከማይተዳደር ትልቅ አገር ይልቅ በሥርዓት የምትተዳደር ትንሽ ከተማ ትልቅ ሙያ አላት…›› እንዳሉት፣ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር አገርን በሕግና በሥርዓት መምራት ነው፡፡ ይህ ዕሳቤ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ከመንግሥት የሚጠበቅ ትንሹ ኃላፊነት ነው፡፡ መንግሥት የሕዝብ አመኔታ የሚያገኘው ሥራውን በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ ለማከናወን የሚያስችል ቁመና ሲኖረው ነው፡፡ እዚህ ቁመና ላይ ለመገኘት ደግሞ ከላይ እስከ ታች ያለው መዋቅሩ ለሕግ መገዛት አለበት፡፡ በዚህ መሠረት ሲንቀሳቀስ የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት አይቸገርም፡፡

መንግሥት ለሁሉም ዜጎቹ ባለበት ኃላፊነት መሠረት ለሚነሱ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡ ዜጎች ሥቃይ ደረሰብን፣ ያላግባብ ታሰርን፣ ንብረታችንን ተቀማን፣ በግፍ ተፈናቀልን፣ ከቦታ ወደ ቦታ እንዳንንቀሳቀስ ታገድንና የመሳሰሉ የመብት ጥያቄዎች ሲያቀርቡ የመደመጥ መብት አላቸው፡፡ የሕግ የበላይነት አለ በሚባልበት አገር ውስጥ ሕገወጦች መፈንጨት የለባቸውም፡፡ ሕግ የሚከበረው የእያንዳንዱ ዜጋ ነፃነትና መብት ሲከበር ነው፡፡ ይህ መብት በሕግ የተረጋገጠ ስለሆነ መከበር አለበት፡፡  ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ ክብሩና መልካም ስሙ ተጠብቆ በአገሩ በነፃነት እንዲኖር የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል እስከሆኑ ድረስ በመካከላቸው ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ በመሆኑም በብሔር፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አቋም፣ በማኅበራዊ አመጣጥ፣ በሀብት፣ ወይም በሌላ ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት እንዳላቸው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ተደንግጓል፡፡ እነዚህን መብቶች የማስከበር ኃላፊነት ደግሞ መንግሥት ላይ ተጭኗል፡፡

ተፈለገም አልተፈለገም ሕገ መንግሥቱ በሥራ ላይ እስካለ ድረስ፣ በውስጡ በያዛቸው የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብት አንቀጾች ክርክር ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 10 መሠረት ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፈፉ በመሆናቸው የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበራሉ ይላል፡፡ ዜጎች በሕግ የበላይነት ጥላ ሥር በሰላም ሥራቸውን እንዲያከናውኑ፣ በአገራቸው ሁለንተናዊ ጉዳዮች ባለቤት እንዲሆኑ፣ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲከናወንና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ ማንኛውም የመንግሥት ባለሥልጣንና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንዲሆን፣ የአገሪቱ ሀብት ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲከፋፈልና የመሳሰሉት ጠቃሚ ጉዳዮች ተደንግገዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ እ.ኤ.አ በ1948 የፀደቀውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ሁለንተናዊ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን በውስጡ ይዟል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመያዝና የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግና አቤቱታ የማቅረብ፣ የመደራጀት፣ የመዘዋወር፣ የዜግነትና የመሳሰሉት መብቶችና ነፃነቶች በግልጽ ሠፍረውበታል፡፡ ማንኛውም የመንግሥት ሹም በመብት ጥሰቶች ላይ ተሰማርቶ ሲገኝ በሕግ መጠየቅ አለበት፡፡

ሕዝብ የመብት ጥያቄዎቹን በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርብ በሕግ የተረጋገጡ መብቶች መከበር አለባቸው፡፡ በተለይ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ይዞታው አሁን ካለበት አገሪቱን ከማይመጥናት አዘቅት ውስጥ ይውጣ፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በተግባር ይከበር፡፡ ዜጎችን በሐሳባቸው ምክንያት ማሸማቀቅ ይቁም፡፡ እነዚህ መብቶች ካልተከበሩ በስተቀር አላስፈላጊ ንትርክና ትንቅንቅ ሕይወት ይገበርበታል፡፡ ሰሞኑን በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ አጓጉል ድርጊቶች ለማንም አይጠቅሙም፡፡ በዚህ ሁኔታ እንኳን ስለልማት ለመነጋገር የቅራኔው ደረጃ ይጨምራል፡፡ ሕጋዊ መብቶች ተከብረው በሠለጠነ መንገድ መነጋገር ይበጃል፡፡ ይህም የሕዝብን ተሳትፎና ባለቤትነት ያረጋግጣል፡፡ በአገር ጉዳይ አንዱ ባለቤት ሌላው ባዕድ አይሁን፡፡ ኢትዮጵያ በስፋት ወደ ልማት መግባት የምትችለው የሕዝብ ተሳትፎ ሲጎለብት ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ሲከበሩ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት ሲኖር ነው፡፡ ሕገወጥነት አደብ ሲገዛ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎች እኩል አገር የምትሆነው አድሎአዊና አጥፊ አስተሳሰብ ሲወገድ ነው፡፡ በዜጎች መካከል መሻከር የሚፈጥሩ ብልሹ አሠራሮች አገር ከማጥፋት ውጪ ፋይዳ የላቸውም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ሊከናወኑ የሚገባቸው በርካታ ተግባራት፣ ለአላስፈላጊ ንትርኮችና ትንቅንቆች እየተዳረጉ ሕዝብ እየተጎዳ ነው፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያና በተለያዩ አካባቢዎች የተከናወኑ ጦርነቶችና ግጭቶች ጠባሳቸው ሳይሽር፣ ለሌላ ዙር ዕልቂትና ውድመት የሚዳርጉ ቅራኔዎች ከየአቅጣጫው እየተስፋፉ በሕዝቡ ላይ ትልቅ ሥጋት እየፈጠሩ ነው፡፡ መሰንበቻውን በኢትዮጵያ ቆይታ ያደረጉት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት ወደ ነበረበት የሚመለሰው የሰላም ስምምነቱ በተግባር ሲረጋገጥ መሆኑን ገልጸው፣ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተካሄደ አለመሆኑም ሲረጋገጥ ነው ብለዋል፡፡ ይህ እንግዲህ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ያሉትን ግጭቶች ማስቆምና ተጨማሪ ጥፋትና ውድመት እንዳይደርስ መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ማለት ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት ተከብሮ ዜጎች በሰላም ወጥተው መግባት መቻል አለባቸው፡፡ የፈለጉት ሥፍራ ተንቀሳቅሰው እንዲሠሩ ዋስትና ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ

በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል ከ1.4 ቢሊዮን...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

የዜጎች ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ ጥበቃ ያስፈልገዋል!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢገታም፣ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የዜጎች ሰቆቃዎች በስፋት ይሰማሉ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር...