የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የሊጉን ቀሪ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ለማከናወን ለባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ ጥያቄውን መጋቢት 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ያቀረበ ሲሆን፣ በእድሳት ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ስታዲየም የሊጉን መርሐ ግብር ማለትም፣ ከ27ኛ ሳምንት ጀምሮ እስከ 30ኛ ሳምንታት ያሉትን ጨዋታዎች እንዲያስተናግድ ጥያቄ ማቅረቡን፣ የአክሲዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ከተሞች መከናወን ከጀመረ ከሁለት ዓመታት በላይ የዘለቀው የሊጉ መርሐ ግብር፣ የዘንድሮ የመጠናቀቂያ ውድድር በአዲስ አበባ ለማድረግ እየጣረ እንደሚገኝ የገለጸው ማኅበሩ፣ ከሚኒስቴሩ ቀና ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በአንፃሩ የስታዲየሙ እድሳት ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ፣ በቀሪው ጊዜ ተጠናቅቆ ለውድድሩ ዝግጁ መሆን እንደሚገባው አቶ ክፍሌ ጠቁመዋል፡፡
‹‹ግንባታው አብዛኛው ሒደት ተጋምሷል፡፡ የሊጉን ቀሪ ጨዋታዎች ለማከናወን በቀሩት ወራት በአግባቡ ማጠናቀቅ ከተቻለ፣ ውድድሩን ማስተናገድ የሚቻልበት ደረጃ ይደርሳል የሚል እምነት አለኝ፤›› በማለት አቶ ክፍሌ ስለሁኔታው ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳን የሊግ ካምፓኒ በቅርቡ በድሬዳዋ ሲካሄድ የነበረው ውድድር በጣለው ያልተጠበቀ ዝናብ መቋረጡን ተከትሎ፣ ቀጣይ መርሐ ግብሮችን የሚያስተናግዱ ስታዲየሞች ይፋ ቢያደርግም፣ የመጠናቀቂያ ሳምንቱን ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ማድረግ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው ይነገራል፡፡
በአዲስ አበባ የሊጉን ውድድር ማድረግ ለአብዛኛዎቹ ተሳታፊ ክለቦች አዋጭ መሆኑና እንዲሁም በመዲናዋ በርካታ ተመልካቾች መኖሩ ይጠቀሳል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ከዚህ ቀደም የቴሌቪዥን መብት ባለቤቱ ዲኤስቲቪ ለሊግ ካምፓኒው የተመልካች ቁጥር እንዲጨምር ማሳሰቢያውን ከቅሬታ ጋር ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
ከዚህም ባሻገር በክልል ከተሞች በመዘዋወር የሚደረገው ውድድር ክለቦችን ለከፍተኛ ወጪ መዳረጉ ሲነሳ ከርሟል፡፡
በአንፃሩ የአዲስ አበባ ስታዲየም ግንባታ ሁለት ዓመታት መሻገሩንና ተደጋጋሚ የበጀት እጥረት እየገጠመው መጠናቀቅ አለመቻሉ ምክንያት ሆኗል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እድሳቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ሲገልጽ ቢከርምም፣ ላለመጠናቀቁ የተለያዩ ምክንያቶች ሲያነሳ ቆይቷል፡፡
ይህም ዋነኛው የበጀት እጥረት ቢሆንም፣ በቅርቡ ደግሞ በስታዲየሙ የዲዛይን ሒደት ወቅት በመጀመርያ ምዕራፍ ውስጥ ያልተካተቱ ግንባታዎች በድጋሚ መካተታቸው ዳግም እንዲከለስ አስገድዶታል፡፡ በዚህም መሠረት ሚኒስቴሩ በድጋሚ ጨረታ ለማውጣት ተገዷል፡፡
በመጀመርያው ምዕራፍ ያልተካተቱ የግንባታ ሒደቶች ደግሞ በተከለሰው ዲዛይን ውስጥ ተካትተው ግንባታው እየተካሄደ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ስታዲየም ግንባታ ተጠናቆ ክፍት መሆን የነበረበት በነሐሴ 2014 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም፣ በተያዘለት ጊዜ ማለቅ አለመቻሉን ሚኒስቴሩ መግለጹ ይታወሳል። በመጀመርያ ምዕራፍ ዲዛይን ሲሠራ ያልታዩ ጉዳዮች በመኖራቸው፣ እንዲሁም ለሳር ተከላው የተለያዩ አማራጮች በመቅረባቸው እንደነበረም ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከሳር ተከላው ጋር በተያያዘ፣ በአገር ውስጥ በሚገኝ ሳር ከተተከለ አኅጉራዊው ኮንፌዴሬሽን ካፍ ላይቀበል ይችላል የሚል ሐሳብ በማቅረቡ ጥናት እስኪደረግ ከሦስት ወራት በላይ ወስዷል፡፡
በዚህም መሠረት ከሳር ተከላው ጋር በተያያዘ በተለያዩ አገሮች ያሉ ተቋራጮች የሚያቀርቡት ዋጋ በጣም የተጋነነ በመሆኑ፣ በመጨረሻም ቀድሞ ከገባው ተቋራጭ ጋር በመመካከር ‹ኩኩዩ› የተባለ የሳር ዘር መተከል መቻሉ ተብራርቷል።
በአንፃሩ የአንደኛ ምዕራፍ ግንባታ ስለተጠናቀቀ ብቻ ለውድድር ዝግጁ ባለመሆኑ፣ በዲዛይኑ ሳይካተቱ የቀሩ ግንባታዎች በሁለተኛ ዙር ለማጠናቀቅ መገደዱ ተነግሯል።
በዚህም ሁለተኛውን ዙር ለማጠናቀቅ በጀት ባለመኖሩ ምክንያት በድጋሚ ሚኒስቴሩ ከመንግሥት ተጨማሪ 150 ሚሊዮን ብር በማስፈቀድና አዲስ ጨረታ በማውጣት ሁለተኛውን ምዕራፍ መጀመሩ ተጠቁሟል። የአዲስ አበባ ስታዲየም ግንባታ የመጫወቻ ሳር፣ መልበሻ ክፍል፣ መፀዳጃ፣ ቪአይፒ እንዲሁም የተለያዩ ክፍሎች ዕድሳት መጠናቀቃቸው የተገለጸ ሲሆን፣ የተመልካች ወንበር ገጠማና የትራክ ዕድሳት እንዳልተጠናቀቁ ታውቋል።
በሌላ በኩል የሊጉን 17ኛ ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ሐዋሳና ኢትዮጵያ ቡናን ጨዋታ ቢያስተናግድም፣ በድሬዳዋ በጣለው ያልተጠበቀ ዝናብ ምክንያት ቀጣዩን የሳምንቱ ጨዋታ ማድረግ እንዳልተቻለ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አስታውቃል፡፡
በዚህም ምክንያት የ2015 ዓ.ም. የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ17ኛ ሳምንት ሊካሄዱ የነበሩ ቀሪ ጨዋታዎች ለሌላ ተስተካካይ መርሐ ግብር መዘዋወራቸውን አክሲዮን ማኅበሩ ገልጾ ነበር።
በድሬዳዋ ስታዲየም መጋቢት 3 ቀን መከናወን የነበረባቸው የመቻልና አዳማ ከተማ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጨዋታዎች በቀጣይ በተስተካካይ መርሐ ግብር እንደሚከናወኑ ተገልጿል፡፡
ቀጣይ መርሐ ግብሮችን ለማስተናገድ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የአዳማ ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስታዲየሞች ውድድሩን ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ የአክሲዮን ማኅበሩ የግምገማ ቡድን ግምገማውን ካጠናቀቀ በኋላ፣ ከ17ኛ እስከ 27ኛ ሳምንት ያሉትን መርሐ ግብሮች አዳማና ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚያስተናግዱ ሐሙስ መጋቢት 7 ቀን ይፋ አድርጓል።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለአይቮሪኮስቱ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት መጀመሩን ተከትሎ ሊጉ የሚቋረጥ ሲሆን፣ ብሔራዊ ቡድኑ ዝግጅቱን ከሚጀምርበት አሥር ቀናት አስቀድሞ እንዲሁም የማጣሪያ ጨዋታውን ካደረገ በኋላ አምስት ቀናት፣ በአጠቃላይ ለ15 ቀናት እንደሚቋረጥ ተገልጿል፡፡
በዚህም መሠረት ብሔራዊ ቡድኑ የምድብ ጨዋታውን ከጊኒ አቻው ጋር በሞሮኮ ራባት መጋቢት 15 እና 18 ቀን ካከናወነ በኋላ፣ ከመጋቢት 25 ቀን ጀምሮ የ17ኛ ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎችና የ18ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚቀጥሉ ታውቋል።.