Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየኢትዮጵያ እውነታ የመላ ኅብረተሰብ የእምነት አባቶችን የሚሻ ነው!

የኢትዮጵያ እውነታ የመላ ኅብረተሰብ የእምነት አባቶችን የሚሻ ነው!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኩራት…›› ምንትስ የሚል ኅብረ ዝማሬን ልብ ብዬ ያጤንኩት በቅርቡ ነው፡፡ ያኔ የተሰማኝ ኩራት ሳይሆን ራሳችንን ከማሞካሸት በፊት ገመናችንን በማራገፍ ላይ ባተኮርን የሚል መርኮምኮም ነበር፡፡ እዚያ ስሜት ውስጥ ለመግባት የበቃሁትም ያን ሰሞን የሌላ ቤተ እምነት መጻሕፍት እየተቸ ስለሰበከ ሰው ሰምቼ ተከፍቼ ስለነበር ነው፡፡ የሰውየውን ስብከት ለሙሉ ደቂቃ እንኳ ለመስማት ትዕግሥቱ አልነረበኝም፡፡ የተናደደኩት ‹የእኔ ቤተ እምነት መጽሐፍት ምን ሲባል ተነካ›› ከሚል ማዕዘን ተነስቼ አልነበረም፣ ወይም ‹ማንም ሰው የፈለገውን የማመን መብት አለውና እንዱ የሌላውን እምነት ማክበር እንጂ ነቃፊ መሆን የለበትም› ከሚል አቋም አኳያ ቆሜ አልነበረም፡፡ የሃይማኖቶች መከባበር ፅኑ አቋሜ ቢሆንም፣ የፅድቅና ኩነኔ ዕይታዬም ሆነ የጥሩ አማካይነት መለኪያዬ በራሴ ቤተ እምነት ውስጥ የታጠረ አይደለም፡፡ የ7ኛና የ8ኛ ክፍል ተማሪ ከነርኩበት ጊዜ አንስቶ ከቤተሰቤ ከወረስኩት እምነት ውጪ ብዙ ቤተ እምነቶች ዘንድ ሄጃለሁ፣ ካቶሊክ፣ አድቬንቲስት፣ መካነ ኢየሱስ፣ ጆሆባ ምስክርነት፣ ጴንጤ ቆስጤ አልቀሩኝም፡፡ የረዥም ዕድሜ ተቋም በነበራቸው ቤተ እምነቶች ውስጥ ያገኘሁት እምነታዊ እንቅስቃሴ ረጋ ያለና የሰከነ ነበር፡፡ በመጨረሻዎቹ ሁለቱ ዘንድ የነበረው እንቅስቃሴ በጊዜው ሠፈር ለሠፈር የሚካሄድ ነበር፡፡ ወጣትነትና ስሜታዊነት ይንቀለቀልባቸውም ነበር፡፡ በቀዘቀዘውም በሞቀውም ስሜት ውስጥ አልፌያለሁ፡፡ ከዚያ በኋላም የቡድሂስትና የባሃኢ እምነቶችን በንባብ እስከመመርመር ተሻግሬ ነበር፡፡

በዚህ ጉዞዬ ውስጥ የተወሰኑ ነገሮችን አንጥሬ ይዣለሁ፡፡ በየትኞቹም እምነቶች ውስጥ ካስማ የሆኑት ነገሮች ፈጣሪን የማመን፣ የእምነት ትዕዛዛቱንና ግዴታዎችን አክብሮ መኖርን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ በእኔ አረዳድ የትኛውም አማኝ የሚሠፈረው በእምነት ፅናቱና ተግባራቱ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ሥነ መለኮት ውስጥ ገብቶ መመራመር፣ ቅዱሳንና መላዕክት ሊያድርጉት ስለሚችሉትና ስለማይችሉት መመርመር ትርፍ ነገር ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን የእምነት መለያ አድርጎ መከራከርና ዓይንህ ላፈር መባባል የፅድቅ መሥፈሪያ የሚሆን አይመስለኝምና ምርምርም ሆነ ክርክር ውስጥ አልገባም፡፡ ለተከራካሪዎቹም ጆሮ የለኝም፡፡ ወደ ፈጣሪ ለመቅረብ አማላጅ አያስፈልገኝም፤ አማላጅም ፈልጌ አላውቅም፡፡ እነ እከሌ የማማለድ ሥልጣን አላቸው/የላቸውም የሚል ክርክር አስፈልጎኝም አያውቅም፡፡

ብዙ እምነቶችን ማሰሴ፣ ፈጣሪን በራሴ እምነት ውስጥ አጥሬ እንዳላይም አስችሎኛል፡፡ ‹‹በአንተ እምነት ውስጥ ያለው ፈጣሪ፣ በእኔ እምነት ውስጥ ካለው ጋር አንድ አይደለም፤›› የሚሉ አማኒያን ቢኖሩም፣ በእኔ በኩል የትኞቹም ሰዎች (አማኒ የሆኑም ያልሆኑም) የአንድ ፈጣሪ ፍጡሮች ናቸው፡፡ በዚህም ላይ ተከራክሬ አላውቅም፡፡ ግን፣ ሰው እምነቱን በተለያዩ ምክንያቶች ሲለዋውጥ ኖሯል፡፡ ከእምነት ለውጥ ጋር ስለፈጣሪ ያለን ዕሳቤ ይለወጥ እንደሆን እንጂ፣ ፈጣሪ አይለወጥም ብዬ አምናለሁ፡፡ ፈጣሪ አንድ ቢሆንም ሃይማኖቶች ብዙ ናቸውና፣ የፅድቅ ሃይማኖት (ትክክለኛው) የቱ ነው የሚል ጥያቄ የሰዎች አይቀሬ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህም ጉዞዬ መልስ ሰጥቶኛል፡፡ በሁሉም ኃጢያትን የሚሸሹ እምነቶች ውስጥ ፅድቅ አለ፡፡ ማዘር ቴሪዛ ከእኔ እምነት ውጪ ነበር እምነታቸው፡፡ የእሳቸውን ፃድቅነት ግን ለአንድ ቅፅበት ለመጠራጠር የሚያበቃ አቅም የለኝም፡፡ ‹‹አማኝ ከእኔ በላይ ላሳር›› ከሚሉ ሰዎች ውስጥም ሆነ የቅዱስነትን፣ የሐዋሪያነትን/የነብይነትን ማዕረግ ካንጠላጠሉ ህያው ሰዎች ውስጥ እንኳ አጠገባቸው የሚቆም የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ምንም ዓይነት ቅፅል ሳያንጠለጥሉ በእምዬ ቴሬዛ ጎዳና ውስጥ በአሁኗ ሰዓት ለሰዎች እየኖሩ ያሉ ጠንካራ የእምነት ሰዎች በክርስትናም በእስልምናም ውስጥ አውቃለሁ፡፡ በጎ ሥራቸው የእምነት ልዩነትን የማያደርግ፣ ሩኅሩኅነታቸውና የዕርዳታ ተግባራቸው ሥጋዬን ቆርጬ ልስጥ እስከማለት የሚሄድ፣ ዕርዳታን እምነት ለማስለወጥ ጉቦ የማያደርጉና መመፃደቅ በቤታቸው የሌለ፣ የተቸገሩ ሰዎችን ማየት ብስክስካቸውን የሚያወጣቸው የሰው ሰዎችን በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ውስጥ አውቃለሁ፡፡ እነዚህም በፅድቅ መንገድ መሆናቸውን አልጠራጠራም፡፡ የእነዚህ ሰዎች በጎ ምሳሌነት ተከባሪነት ወይም አባትነትና እናትነት ከቤተ እምነታቸው ቅጥር ግቢ አልፎ የሚሄድ ነው፡፡

ከእምነቴ ግቢ ውጪ ፃድቆችንና የፅድቅ መንገደኞችን ለማሰብ እንደቻልኩ ሁሉ፣ ሌላ እምነት የማይተናኮሉ ጥሩ አማኞችንም ሆነ መጥፎ አማኞችንም ማስተዋል ችያለሁ፡፡ አስተውሎቴ ከተራ አማኝ አንስቶ የእምነት መሪ ነን እስከሚሉ ድረስ የረዘመ ነው፡፡ ‹‹እኔ ድኛለሁ/የጌታ ሰው ሆኛለሁ/ የአፍ አማኝ አይደለሁም፤›› የሚል ፍርድን ለራስ ሰጥቶ፣ ሌላውን እንደጠፋ በግ የማየትን አመለካከት የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ከነበርኩበት ጊዜ ጀምሮ አውቀዋለሁ፡፡

በክርስትና እምነት ውስጥ ያሉ አሥርቱ ትዕዛዛትን በደንብ አክብሮ ከሰዓት ወደ ሰዓት፣ ከዕለት ወደ ዕለት መኖር ምን ያህል ከባድ እንደሆነም በተግባር አይቸዋለሁ፡፡ ሌሎችም ምን ያህል እንደሚሳካላቸው ታዝቤያለሁ፡፡ ሰው ፍፁም መሆን እንደማይችል፣ ስህተትና ጥፋት ትነስም ትብዛ እየሠራ እንደገና ንስሐ ከመግባት እንደማያመልጥ ተረድቻለሁ፡፡ ለዚህ ነው ራስን በድፍረት ‹‹ከኃጢያት መንገድ የተመለሰና የዳነ/በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ እውነተኛ አማኝ›› አድርጎ ሌላውን ግን ‹‹መናፍቅ፣ የጠፋ/የአፍ አማኝ ብሎ መፈረጅ ትልቅ ግብዝነት የሚሆነው፡፡ የዚህ ዓይነት ግብዝ አቋም ይዘው ሌላውን ሊሰብኩ የሞከሩ ሰዎች ሲከሽፋባቸው ብቻ ሳይሆን ባካሄዳቸው ሲተናኮሉና ስድብና አምባጓሮ ሲያነሳሱ ብዙ ጊዜ አይቻለሁ፡፡ ‹‹መዳን ዛሬ ነው›› እያሉ መንገድ ላይ ሲሰብኩም ሆነ በየቤቱ እያንኳኩ የመጽሐፍ ቅዱስን ቃል እናስተምራችሁ ሲሉ፣ ለምፅአት ቀን የሚቆጠር ነጥብ ከማስመዝገብ ባለፈ ሰዎችን ለክፉ ቃላትና ለፀብ ሳያጋልጡ እንደምን መቅረብ እንዳላባቸው አይጨነቁም፡፡ አነጋገራቸው በራሱ ነገር ፈላጊ ነው፤ ‹‹አለመዳኔን/መጽሐፍ ቅዱስ አለመማሬን ማን ነገረህ?!›› የሚል ነገር ያስነሳል፡፡ በዚህም መጥፎ ንግግርንና ግጭትን ይጠራል፡፡ አውቶቡስ ውስጥ ልስበክ እስከማለት በደረሰ ጥፋት መጥፎ ንግግሮችና መጎሻሸም የተከሰቱበት ጊዜ ነበር፡፡

በአዲስ መጥ ሰባኪያን ተንኳሽነትና ምዕመኖቻችንን አስከዱብን በሚል ንጭንጭ ምክንያት በፕሮቴስታንት መስመር ውስጥ ያሉ ቤተ እምነቶችን ‹‹ከእርዳታ እህል ጋር የገቡ›› እና ‹‹የኢምፔሪያሊዝም ወኪሎች›› የሚል ስም እስከ መስጠት፣ አማኒያኑንም ‹‹በዕርዳታ እህል የተለወጡ›› እስከ ማለት መባለግ ነበር፡፡ በነባር ሃይማኖቶች ውስጥ ካሉ ሰዎች ዘንድ ከምዕመናን እስከ እምነት መሪ ድረስ በዚህ ብልግና መጉደፍ አስተውያለሁ በኑሮ ልምዴ፡፡ ወደ እነዚህ እምነቶች መግባትም የመሠረት/የዘር ማንዘር እምነትን መካድ ወይም ቤተሰብን መካሄድ ተብሎ እየተተረጎመ፣ ወደ እነዚህ እምነት የገባን ሰው ከቤተ ዘመድ ማቆራረጥ ሁሉ ይደረግ ነበር፡፡ እንዲህ ያለ ማጨካከንም ሆነ ለእምነት ክፉ ስም መስጠት የፈጣሪና የፅድቅ መንገድ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ሌላውን እምነት የስህተት መንገድ አድርገው ፈርደው የሚገበዙና በሌላው እምነት ውስጥ ገብተው እያቦኩ ሰዎች ከመልካም መንገድ ወጥተው፣ ወደ ስድብና መተናኮል ውስጥ እንዲገቡ የሚያድርጉ ሰባኪያንም በፈጣሪ ዘንድ ይጠየቁ እንደሆን እንጂ አበጃችሁ ይባላሉ ብዬ አላምንም፡፡ በእስልምናም ሆነ በክርስትና ውስጥ ከዋናዎቹ የእምነት ካስማዎች ውጪ የሆኑ ጭርፍራፊ ነገሮችን መለያና መከፋፈያ አድርገው በማክረር ከእነሱ ያልተደበለቁትን እንደ ሐሰተኛ አማኝ አድርገው ሲዘልፉ/ሲያራክሱ የሚውሉ ሰዎች አጥባቂ ይምሰሉ እንጂ፣ በኃጢያት ውስጥ ከመንደባለል ውጪ አይመስሉኝም፡፡ እንደዚህ ያሉ ሰዎች እምነት አጥባቂ ሳይሆኑ ከፋፋዮች ናቸው፡፡ በሌላው እምነት ውስጥ ገብተው ሲያቦኩም ነገር አላኳሾች/ፀብ ፈላጊዎች እንጂ እምነት አክራሪዎች አይሆኑም፡፡ ከቅርብ ጊዜ በፊት ዮናታን በሚባል ሰው የሆነውም ይኼው ነው፡፡ ያውም ኢትዮጵያን በሃይማኖት ለማበጣበጥ የሃይማኖት መሪ መስለው በክርስትና ላይም ሆነ በእስልምና ላይ የሚሳለቁ ሰዎችን ደጋግመን ባያንበት ጊዜ!! ይህን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ አስገብተው እንዲህ ያለው ብልግና በሃይማኖት ጉባዔ አሠራርም ሆነ በሕግ በኩል መጠበቂያ እንዲበጅለት በዕርጋታ የጣሩ የእምነት ሰዎችን አክብረናቸዋል፡፡ በእነሱ ቤተ እምነት ውስጥ የማገጡ ሰባኪያን ያልታዩ ይመስል፣ ወይም የእነሱ የአፀፋ ምግጠት ከማር የተሠራ ይመስል እጥፍ እየባለጉ ነገር ባጋጋሉት ደግሞ አፍረናል፡፡

በኢትዮጵያ መተሳሰብንና መከባበርን ተገቢ የሚያደርጉ የሃይማኖቶች ታሪካዊና አሁናዊ ተራክቦዎች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ እያንዳንዱ ቤተ እምነት ያለው ታሪክ ከሌላው ጋር ያልተደራረሰ አይደለም፡፡ ከፕሮቴስታንት ክርስትና ጀርባ አገር በቀል እምነቶች፣ ኦርቶዶክስ ክርስትናና እስልምና አሉ፡፡ ከእስልምና ታሪክ ጀርባ አገር በቀል እምነቶችና ኦርቶዶክስ ክርስትና አሉ፡፡ ከክርስትና ጀርባም አገር በቀል እምነቶችና እስልምና አሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች በተናጠልም በቡድንም ከአንድ እምነት ወደ ሌላ እምነት የዞሩበት ሁነት በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ውስጥ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ዛሬ ባለን የቅርብ ቤተ ዝምድና ውስጥ ሙስሊም፣ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን፣ ፕሮቴስታንት ወይም ዋቄፈታ የሆኑ ሰዎች ማግኘት የሚያስገርም አይደለም፡፡ በአንድ ቤተሰብ ውስጥም በወላጆችና በልጆች ዘንድ ወይም በልጆች መሀል የእምነት ልዩነት መከሰት በኢትዮጵያ እንግዳ አይደለም፡፡ ‹‹ልጃችሁ የሚሽን ሃይማኖት ውስጥ ገብቷል›› የሚል ወሬ ደርሷቸው የገረፉኝ ወላጆቼ ከጊዜ በኋላ የሙሉ ወንጌል ቤተ እምነት ተከታዮች ሆነዋል፡፡ በእኛ ሰፊ ቤተሰብ ውስጥ የብሔረሰብ ቅይጥነት እንዳለ ሁሉ፣ የእምነት ብፌም አለ፡፡ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታይነት፣ ፕሮቴስታንትነት እንደ ልብ ነው፡፡ የሙስሊምና የክርስቲያን ጋብቻም አለ፡፡ ከአንድ ቤት ልጆች ውስጥ አንደኛው ወደ እስልምና ሲያመራ፣ ሌሎች ክርስትና ላይ የረጉበት ሁኔታም አለ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ዘራፍ ልበል ወይም ልፀየፍ/ልኮንን ያለ የለም፡፡ ይህ ሁሉ ውጥንቅጥ አንድ ላይ ገበታ ሲቀረብ ፀሎት የግል ስለሆነ ችግር የለም፡፡

በመሀላችን የአንዱ እምነት በሌላው አይነቀፍም፡፡ ይከበራል፡፡ በእስልምና ሃይማኖትም ላይ ሆነ በክርስትና ውስጥ ባሉ የእምነት ዘርፎች ላይ የሚሰነዘር ዘለፉ፣ ለእኛ ሰፊ ቤተሰብ በራስ ላይ እንደተሰነዘረ ጥቃት ይቆረቁራል/ያስከፋል፡፡ የትኛውንም ሃይማኖት መሳለቂያ ማድረግ ነውራችን ነው፡፡ በቤተ እምነት መሪዎች ደረጃ በሌላ እምነት ላይ የሚሰነዘር ነቀፋም ሆነ ‹‹አግልሉ/ቡና አትጣጡ›› የሚል ትዕዛዝ እንደኛ የተወራረሰ ቤተ ዘመድን መልካም ግንኙነት ነው የሚበጠብጠው፡፡ እናም በዚህ ረገድ የሃይማኖት መሪዎች በእምነት ተከባብረው ከሚኖሩ ዜጎች ማነስ የለባቸውም፡፡ የኢትዮጵያን የተወራረሰ ማኅበራዊ እውነታ አጢነው የሃይማኖት መከባበርንና ተሳስቦ መኖርን የሚሰብኩ፣ ቅንነትንና በጎነትን ለሁሉ ሰው የሚያሳዩ መሆን ይጠበቅቸዋል፡፡

ይህንን ልምድ ይዤ ሳሰላስል ሌላ አስደንጋጭ ቀውስ ተከሰተ፡፡ የተወሰኑ መሪዎች ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አፈንግጠውና ተሿሹመው ‹‹የኦሮሚያና የደቡብ…›› የሚል ስም የያዘ ሲኖዶስ የማቋቋማቸው ወሬ ጆሮዬን አጣበበው፡፡ ይህ ሁሉ የእነእከሌ ሴራ ነው እያሉ አፍ እንዳመጣ የተናገሩ ባይታጡም፣ የሁሉም ቤተ እምነቶች ሰዎችና መሪዎች ቀውሱ በራሳቸው ውስጥ የደረሰ ያህል ተሰምቷቸው ነበር፡፡ ጉዳቱ ለሁሉም የሚተርፍ መሆኑ አሳስቧቸውም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ተሰብስቦ በይቅርታ የመመለስን ዕድል ክፍት ያደረገ የውግዘትና የክህነት ገፋፋ ውሳኔ በሰጠም ጊዜ ሆነ፣ አፈንጋጮቹ በመንግሥታዊ አካል እየታገዙ ቤተ ክርስቲያናትን ከሕግ ውጪ የመቆጣጠር እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ሌሎቹ የአገሪቱ ቤተ እምነቶች ምንተዳዬ አላሉም፡፡ መንግሥታዊ ጣልቃ ገብነትና ሕገወጥ አካሄድ ቆሞ ችግሮች በሰላምና በቤተ ክርስቲያኗ አሠራር እንዲፈቱ የጠየቁ ድምፆች ጎልተው ወጥተው ነበር፡፡ እነዚህ ድምፆች ለአገር ሰላም ከመሥጋት የተነሳሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ለቤተ እምነት መብትና ነፃነት መቆም ከራስ ቤተ                                                                                                                      እምነት አልፎ ለሌላውም የመቆምን ኃላፊነት የሚፈልግ መሆኑንም ያጤኑ ነበሩ፡፡

በመንግሥት አካላት ታቅፎ ኦሮሚያ ውስጥ የተደረገው ሕገወጥ ሥራ በጣም የሚያሳፍር ነው፡፡ እንደ እኔ ዕይታ፣ ለዴሞክራሲ የሚጥር ለውጥ መጥቷል በሚባልበት ጊዜ በኦሮሚያ ውስጥ መንግሥታዊ እጅን ሃይማኖት ውስጥ ሰዶ የጉልበት ሥራ አጃቢ መሆን፣ አጅቦም ሕገወጥነትን በተቃወሙ ሰዎች ላይ ጥቃት ማድረስ፣ በሚጣርለት ዴሞክራሲ ላይ ምላስ ከማውጣት የሚቆጠር ነው፡፡ መብትና ሕግ አክብሮ የማስከበር ተግባር፣ ሲሻኝ የማደርገው ሲሻኝ የምገፈትረው ነው ብሎ በአዋጅ ከመንገርም የሚያንስ አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ከዚህ የበለጠ በአሁኑ ሰዓት መናገር አያስፈልገኝም፡፡

እኔ ልዩ ልዩ እምነቶች ጋር ደርሼ ወደ ኦርቶዶክስ ክርስትና ስመለስ ፈላስፋው ዘርዓያቆብን፣ እነደቀ እስጢፋኖስንና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የታዩትን ክርክሮችና የዕድገቴን ትዝታዎች ሁሉ ቅርሴ ብዬ ግን፣ ለአንዱም ክርክር ስህተትና ልክ የሚል ፍርድ ሳልሰጥ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን አልሳለምም፡፡ የሰባካ ጉባዔ አባል አይደለሁም፡፡ በተለያዩ ምክንያቶችም ቤተ ክርስቲያን አዘውትሮ የመሄድ ልምድ የለኝም፡፡ የስብከት ትምህርት ፍለጋ ቤተ ክርስቲያን ባልሄድም የሚነበብ መጽሐፍ ይዤም ሆነ ባዶ እጄን ቤተ ክርስቲያን ገብቼ ታዛ ውስጥ ባርምሞ መቀመጥ ፍስሐና ሰላም ይሰጠኛል፡፡ ‹‹ኦርቶዶክስ ነው እምነቴ›› ስል የማይዋጥላቸው ቢኖሩም፣ በበኩሌ ኦርቶዶክስ ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡ ነኝ ብሎ ማመንን፣ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያበረከተቻቸውን የዕውቀት ሀብቶችና ታላላቅ ሰዎች ሀብቴ ማለትን ማንም አይከለክለኝም፡፡ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ቅዳሴ ማኅሌትንም ሆነ ወረብ/ሽብሻቦውን እየተከታተልኩ ለነፍሴ ሐሴት መስጠትን የሚከለክለኝ የለም፡፡

የነፍስ አባት ስለሌለኝ ከእግዜር ርቄያለሁ ብዬ አልፈራም፡፡ ‹‹ሃይማኖት አጥባቂ ነን›› የሚሉ የልዩ ልዩ እምነት ሰዎችን ተግባራዊ ሕይወት ከእኔ አኗኗር ጋር ሳነፃፅር፣ እንዲያውም ለእነ እከሌ አምላክ የገነት በርን ከከፈተ ያለ ጥርጥር እኔን አይዘለኝም ለማለት እደፋፈራለሁ፡፡ በእኔ ላይ የማየው የሥጋ ለባሽ ድክመት የብዙ ሰዎች ነው፡፡ እንዲያውም ራስን በቅድስና/በፅድቅ ውስጥ አድርጎ መመደብ፣ ‹‹ስብሰባዬና ውሳኔዬ/ንግግሬ በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ነው›› ብሎ ማለትም ሆነ ነብይነትን እንደ ማዕረግ ማንጠልጠል፣ አጠፋሁ ድካም አሳየሁ ብሎ ለንስሐ ከመቅረብ የሚጋርድ ይመስለኛል፡፡ በፅድቅ ውስጥ ነኝ ብለው የሚያስቡ ሰዎች፣ ጋራ የሚያካክል ጥፋት ሲሠሩም አስተውያለሁ፡፡ እምነትን በስብከት የሚያስተምሩ ሰዎች ጭምር በትምህርታቸው ብዙ በጎችን የማሰባሰብ ሥራ ከመሥራት ይልቅ ማቃቃርና ማራራቅን ሲያስተምሩ አይቻለሁ፡፡

በእምነት ላላ ያልኩ (Moderate) ብሆንም ግን እምነት ከሚያጠብቁት ርቄ አልኖርም፡፡ በቤተ ዘመዳችን ውስጥ እምነትን ላላ አድርገው የያዙና የሚያጠብቁ ከእስልምናም ከኦርቶዶክስም ከፕሮቴስታንትም አሉ፡፡ ከሁሉም ጋር ተስማምተንና ሳንራራቅ እንኖራለን፡፡ እንደ አንድ አገር ወዳድ ደግሞ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉም ሃይማኖቶች ንፋስ የማያስገባ ኅብረትና ትስስር ኖሯቸው፣ በሃይማኖት ሰላምና ተሳስቦ በመኖር ረገድ የዓለም ምሳሌ እንዲሆኑ በጣም የምሻ ሰው ነኝ፡፡ ይህም መቃዠት አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከአፍቃሪ አፍሪካዊነት ጋር፣ እንዲሁም ከራስታዎች ጋር በተያያዘ ታሪክ ዕውቅናዋ ከኢትዮጵያ የዘለለ ነው፡፡ መዝለል ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ መታወቂያ ምልክትነት ከፊል ድርሻ አላት፡፡ በእስላምናም ታሪክ ውስጥ ከነብዩ መሐመድ ግለ ታሪክ አንስቶ የመጀመሪያውን የፀሎት ሰዓት ለፋፊ (ሙአዚን) በማበርከት ረገድና ለቀዳሚዎቹ ሰላሚዎች (እስልምናን የተቀበሉ) የስደት መጠጊያ በመሆን ኢትዮጵያ በዓለም እስልምና ውስጥ ልዩ ሥፍራ ያላት አገር ነች፡፡ ባሻ መተናኮል እንዳይደርስባትም የሚከለክል ነብያዊ ቃል ተቀምጦላታል፡፡ ከዚህ አኳያ እስልምናም ለኢትዮጵያ ውድና ልዩ መታወቂያዋ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረውና ዛሬ ላይ ያደረሰን የክርስትናና የእስልምና መስፋፋት ታሪክ የብዙ ዓይነት ተራክቦዎች ውጤት ነው፡፡ በሃይማኖት ትምህርት አማካይነት፣ ከተራ ሰው እስከ ገዥዎች ድረስ ይካሄድ በነበረ ጋብቻዊ መዘማመድ፣ ንግድና አብሮ መኖር በሚፈጥረው መወራረስ፣ በጦርነትና በኃይል መንገድ ከአንድ እምነት ወደ ሌላው መገላበጥ ሁሉ ተካሂዷል፡፡ ከዚህ አኳያ የእስልምናም የክርስትናም ታሪክ መላ ኅብረተሰባችንን የሚመለከት የጋራ ታሪክ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ታሪክ ውስጥ አጠር ያለ ዕድሜ ያለው የፕሮቴስታንት ታሪክም ጥንታዊ ሃይማኖቶችና ‹‹ባህላዊ›› የሚባሉት እምነቶች ጀርባዎቹ ናቸው፡፡ ጀርባነታቸው ዛሬም ርቆ አልቀረም፡፡

በጎንዮሽ የሚኖረው መወራረስም እንደዚያው ነው፡፡ በሥጋና በባዕድ ዝምድናችን ውስጥም ሆነ በጓደኛማች ግንኙነታችን ውስጥ፣ ዛሬም ድረስ የሁሉም ዋና ዋና እምነት ሰዎች አሉ ብለን ብንል፣ አጠቃላዩን የኅብረተሰባችንን ሁኔታ የሚገልጽ ነው፡፡ ከእኔ የተለየ እምነት ያለውን አባቴን፣ አያቴን፣ ዘመዴን፣ ጓደኛዬን፣ ወዘተ የምወድና የማከብር ከሆነ እምነቱን ልንቅና ልፀየፍ አልችልም፡፡ በግለሰብ ተዛምዶ ባየነው መከባበር በቤተ እምነቶችና በሃይማኖት መሪዎች ደረጃም እንዲኖር የሚጠበቅ ነው፡፡ ቤተ እምነቶችና የሃይማኖት መሪዎች ምዕመናኖቻቸው የተለያየ እምነት ተከታይ አዝማዶች እንዳሏቸው ማሰብና ለእነዚያ ቤተ ዘመዶቻቸው እምነት አክብሮት መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከእነሱ ውጪ ያሉ እምነቶችን እያንቋሸሹ (በዚህም ተከታዮቻቸውን ቅር እያሰኙ፣ አለዚያም ከአዝማዶቻቸው የሚያሸካክር ነገር አዕምሯቸው ውስጥ እየሻጡ) አክብሮት ሰጠን ሊሉ አይችሉም፡፡ በሃይማኖት ደረጃ ያውም በአንድ እስልምናና በአንድ ክርስትና ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው በውስን ልዩነቶች እየተዘረጣጠጡ ምዕመናንን ያከበረ የመላ ኅብረተሰባችን የእምነት መሪዎች ሊሆኑ አይችሉም፡፡

የሃይማኖት መሪዎች ሁሉንም እምነቶች ያከበሩ የመላ ኅብረተሰባችን መሪዎች እንዲሆኑ የሚያስገድዳቸው ሌላም እውነታ አለ፡፡ ዛሬ እየተካሄደ ባለው፣ የተሻለ ሕይወትና ነፃነት የዳበረባት አገር የመገንባት ተጋድሎ ውስጥ፣ የሁሉም እምነት ሰዎችና ባለሀብቶች አስገራሚና በተስፋ የተሞላ እንቅስቃሴ እያደረጉ ነው፡፡ የሁሉም ዓይነት አማኒያን የኅብረተሰብ እንቅስቃሴዎች (ከሲቪል እስከ ወታደራዊ መስክ ባሉ) ውስጥ በንቃት እየተሰማሩ ነው፡፡ የበጎ አድራጎት ሥራዎች፣ ማዕድ የማጋራት መርሐ ግብሮችና መዋጮች ሁሉ በእምነቴ ሰዎች አካባቢ ልታጠር ባይነት የሌለበት ሁሉን ወገኔ አለኝታዬ ያለ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ወርቃማ የትግግዝ ዘመን የሃይማኖቶች መሪዎቻችንን ዓይን ከፍቶ ሁሉን እምነቶች ያከበሩና ያከባበሩ መሪዎች እንዲሆኑ የሚጎተጉት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የሃይማኖት መሪዎች ለሁሉም እምነቶች አክብሮት የሚሰጡ (በሌላው እምነት ውስጥ ገብተው የማይፈተፍቱ) መሪዎች መሆን ካልቻሉ፣ የመላ ኅብረተሰቡ መሪዎች ለመሆን አልበቁም ማለት ነው፡፡ አስተምህሮታቸው የፖለቲካ ወገንተኛነት ውስጥ ከወደቀና የእውነት አጣማሚዎች ከሆኑ በእርግጠኝነት የዓይነተኛ ቤተ እምነቶቻቸውን ምዕመናንም ሊያከብሩ አይቻላቸውም፣ ምዕመኖቻቸው ለእነሱ የሚሰጧቸው ከበሬታም አስተማማኝ አይሆንም፣ የሚከፉባቸው ይኖራሉና፡፡ ይኼ ሆነ ማለት በእምነት ያልታጠረ አስደናቂ ትግግዝ እያደረጉ ካሉ ምዕመናን በታች መሪዎች ዋሉ (ተመሪ መሆን እንኳ ቸገራቸው) ማለት ነው፡፡

በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በቅርቡ ተከስቶ የነበረው አፈንጋጭነት መሠረቱ በእምነት አዕማድ ላይ የተፈጠረ ልዩነት እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ‹‹እምነት የሃይማኖት መሪዎችና የምዕመናኑ ጉዳይ›› መሆኑም አያከራክርም፡፡ ‹‹መንግሥት በሃይማኖት ውስጥ እጅህን መስደድ አቁም!!›› መባሉም በጥብቅ መያዝ ያለበት አቋም ነው፡፡ ነገር ግን ፖለቲካና ጥቅም ሃይማኖቶች ውስጥ የመግባቱን ፈተና በቃላት ብቻ መግታት አይቻልም፡፡ ከሃይማኖት መሪዎች ውስጥ ፖለቲከኞች ይመጣሉ፡፡ ምዕመናንም ፖለቲከኞች ይሆናሉ፡፡ የሃይማኖት ተቋም ለፖለቲካ ፍትጊያ የሚሆኑ ስስ ብልቶች ካሉት እነዚን ስስ ብልቶች በሚያነፈንፉ ፖለቲከኞች መታመሱ አይቀርም፡፡ ዛሬ ቢረግቡ ወይም ቢያጎነብሱ ነገ ተነገ ወዲያ ጊዜ እየጠበቁ ብቅ ብቅ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ፖለቲከኞችን የሚስቡ ነገሮችን እያረሙ ካልሄዱ፣ የምዕመናንና የመሪዎቻቸው ሃይማኖታዊ መስተጋብር ፖለቲካን እቤት ጥሎ የመምጣት መርህን አጥብቆ የያዘ ካልሆነ፣ ራሱ ቤተ እምነቱ ሳያውቀው ወደ ፖለቲካኛነት (የፖለቲከኞች መሣሪያ ወደ መሆን) ሊንሸራተት ይችላል፡፡ ያ ሲሆን ደግሞ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነትና ጫና በራሱ ላይ ይጠራል፡፡ በሌላ አነጋገር ማንኛውም ቤተ እምነት በፖለቲካ ከመታመስ የመጠበቁ ብዙው ጉዳይ (ለዴሞክራሲ የመጣጣር ሁኔታ ባለበት አገር) በራሱ በቤተ እምነቱ እጅ ውስጥ ያለ ነው፡፡ የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት ላይ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ ተከስቶ የነበረው ክፍፍልና መፈናገጥ በንግግር መፈታቱን ባበሰረው ዜና ላይ የሰማናቸው የቤተ ክርስቲያኗ ውሳኔዎች ብዙ ነገሮች እንደሚሻሻሉ ተስፋ የሚሰጡ ናቸው፡፡

የአሁኑ የደፋ ቀና ልምድ፣ ለጉንተላና ለፖለቲካ ልፊያ የሚያጋልጡ ነገሮችን ሥራዬ ብሎ ለማቃለል የመሥራትን አስፈላጊነት አስተምሯል፡፡ ሁሉም ቤተ እምነቶች ከሌላ እምነት ጋር ሳንናቆር፣ ፖለቲካም ውስጣችንን ሳያምሰንና ከመንግሥት ጋር ሳንላተም፣ የመላ ኅብረተሰባችንን ሰላም በታደገ አኳኗን በዚህ ፈጣን ዓለምና ዘመን ውስጥ እንደምን መጓዝ እንችላለን የሚለውን ጥያቄ ከእነ ምላሹ የጋራቸው ለማድረግ ቤተ እምነቶቻችን እንደሚሠሩ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና እስልምና ተቀዳሚ ባለታሪኮች እንደ መሆናቸው፣ ይህንን ተግባር በማሳካት ረገድና ንፋስ የማይገባው የሃይማኖቶች ኅብረት በኢትዮጵያ ውስጥ በመገንባት ተግባር ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከሁለቱ ዋናና ተቀዳሚ ቤተ እምነቶች ውስጥ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያለባት ኃላፊነት ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ኃላፊነቷን እጅግ ከፍተኛ ያደረገውም ከተቀዳሚ ጥንታዊነቷና ከሌሎች ነገሮች በላይ፣ ለሌሎች ቤተ እምነቶችና ለአገር የሚተርፍ ፈተና ያለባት መሆኑ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ በሌላ ርዕስ ሥር ሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...