Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጂዲፒ የሚለካውን የኢኮኖሚ ዕድገት ሁሉን አቀፍ በሆነ መመዘኛ የመተካት ውጥን

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቀን አንድ ዶላርና ከዚያ በታች ገቢ የሚያገኝ ማኅበረሰብ ከድህነት ወለል በታች ነው በሚለው መመዘኛ መሠረት 40 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ከአሥርና 15 ዓመት በፊት ከድህነት ወለል በታች ምድብ ውስጥ ነበር። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ይህ ቁጥር በዚሁ መመዘኛ መሠረት በግማሽ እንደቀነሰ ወይም 20 በመቶ እንደሆነ ይነገራል። ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢን መሠረት ባደረገ መለኪያ ሲመዘን ድህነት ባለፉት አሥርና 15 ዓመታት ውስጥ በግማሽ ቀንሷል እንደ ማለት ነው።

ነገር ግን አንድ ሰው በሕይወት ሲኖር ሊሟሉለት የሚገቡ የሚባሉ የተለያዩ አመለካከቶችን ማለትም እንደ ትምህርት፣ ጤና፣ ንፅህናው የተጠበቀ የመኖሪያ ሥፍራና በሌሎች መሰል መመዘኛዎች ሲለካ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል ከድህነት በታች መሆኑ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን አሰናጅነት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ተጠቅሷል።

በመድረኩ በአወያይነት የተገኙት በዓለም አቀፍ የልማት ማዕከል (International Growth Center IGC) ኢኮኖሚስትና በኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ቴዎድሮስ መኰንን (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ከሚታማባቸው ጉዳዮች አንዱ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዘኛ መሥፈርቶቹ ቁጥር ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆናቸው ነው። ቴዎድሮስ እንደሚሉት፣ ለምሳሌ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲመዘን የሰው ልጅ ደኅንነት (Welfare) እንደ መስፈርት ከግንዛቤ ሲገባ አይታይም፡፡ 

የተለያዩ የሰውን ደኅንነት ሊገልጹ የሚችሉ መመዘኛዎችን እንዴት አድርገን በአንድ ላይ ሰብስበን ማምጣት እንችላለን? ያንን አንድ መገለጫ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተከታትለን እንዴት መለካት እንችላለን? የሚለው መንገድ ከሚታይባቸው አንዱ የዕድገት የልማት መለኪያ (Multidimensional Development Index- MDI) ነው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ልማት የሚለካበት ብዙ ነገሮች አሉ፣ ነገር ግን ሁሉም ለየብቻቸው የሚከወኑ ናቸው፡፡ ልማት ፈርጀ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ እያንዳንዱ ልማት የሚለካበት መመዘኛ ከሞላ ጎደል ቢኖርም፣ በቂና የተሟላ ግን አይደለም፡፡

በአንድ አገር በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ምርትና አገልግሎት ቀርቦ ምን ውጤት ተገኘ የሚለውን ለመመዘን ጥቅም ላይ ከሚውሉ መመዘኛዎች ጥቅል አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) ይጠቀሳል፣ በኢትዮጵያም ጂዲፒ ዋናው መመዘኛ ነው፡፡ ነገር ግን መመዘኛው የራሱ የሆኑ ጠንካራ ጎኖችና ድክመቶች እንዳሉበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶስሴሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት አምዲሳ ተሾመ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡

ጥቅል አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) የማያካትታቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች እንዳሉ የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ለምሳሌ መደበኛ ያልሆነው ዘርፍን (Informal Sector) ለመለካት እንደማያስችል ይገልጻሉ፡፡

መደበኛ ያልሆነው ዘርፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በሥራ ላይ ያሳተፈ ቢሆንም፣ ነገር ግን በትክክል ተለክቶ በዚህ አመላካች ውስጥ ማስገባት ያልተቻለ አንዱ ክፍል ከመሆኑ ውጪ ሌሎችም አሥር የሚደርሱ ዓይነቶች (Items) በጂዲፒ ውስጥ እንደማይካተቱ አስረድተዋል፡፡

በጥቅል ምርት ዕድገት (ጂዲፒ) ላይ ሊካተቱ ያልቻሉ ጉዳዮች ለምንድነው ሊካተቱ ያልቻሉት? ምን ስለሆነ ነው የሚለውን ይህንን የጂዲፒ አመላካች ከሚያዘጋጁ ተቋማት ጋር ተነጋግሮ ምላሽ ማግኘትን ይጠይቃል፡፡ 

ላለፉት 30 ዓመታት በርካታ የምርምርና ጥናት ሥራዎችን ያደረገው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን እስካሁን ካደረጋቸው ጥናቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ያለውንና ዓለም አቀፋዊ ገፅታ ያለው፣ ፈርጀ ብዙ የሆነ አመላካች መመዘኛ (Multidimensional Indicator) ለማዘጋጀት በሚል ፕሮጀክት ነድፎ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡

አሶሴሽኑ የጠነሰሰው ፕሮጀክት ዋና መነሻ ሐሳብ በአገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ልማት የሚለካበት ክፍተት ወይም እጥረትና ውስንነት እንደሆነ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የሪሰርችና ፕሮግራም ዳይሬክተር ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡ 

የተለያዩ አገሮች ልማትን በመለካት ሒደት ላይ መሰል ችግር ስላለባቸው ከዚህ የተነሳ በተለይም ያደጉትን ሳይሆን ኢትዮጵያን ጨምሮ በሽግግርና በልማት ላይ ያሉ ወደ 138 የሚሆኑ የሽግግር (ትራንዚሽናል) ኢኮኖሚ አገሮችን ልማት መለካት የበለጠ ጠቃሚ ነው በሚል ፕሮጀክቱ መነደፉ ይገለጻል፡፡

ፕሮጀክቱ ሁለት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ አንደኛው የፈርጀ ብዙ ልማት መመዘኛ (Multidimensional Development Index – MDI) የሚባለው ሲሆን፣ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የልማት መመዘኛ (Ethiopian Multidimensional Index -EDI) የሚባል ነው፡፡ 

የፈርጀ ብዙ ልማት መመዘኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሠራና በዓለም ላይ የሚገኙ 138 የሽግግር (ትራንዚሽናል) ኢኮኖሚ አገሮች በሚዘጋጀው መለኪያ ደረጃ የሚሰጥ ነው፡፡ በየሁለት ዓመቱ ደረጃቸውን መወሰንም የሚያስችል ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የልማት መመዘኛው ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ፈርጀ ብዙ ዕድገት ምን ይመስላል? የሚለውን ከ11 ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች አንፃር ምን ይመስላል? የሚለውን የሚለካ፣ ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ ልማቷ ምን ያህል ነው? የሚለውን በመለኪያዎቹ ደረጃ የሚሰጥ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ 

ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚ ነፃነት፣ የፖለቲካ ነፃነት፣ የሲቪል ነፃነት፣ የፆታ እኩልነት አካባቢ የሚባሉ ጉዳዮች ሁሉ የልማት አካሎች ናቸው፡፡ እነዚህን ነገሮች እንዴት ተደርግው ተለክተው በአንድ ላይ በልማት መለኪያ ሊካተቱ ይችላል የሚለው ዋና የፕሮጀክቱ ጥያቄ በመሆኑ ይህንን የሚመልስ ይሆናል፡፡ 

የኢኮኖሚክስ አሶሴሽን የሚያዘጋጀው ይህ መለኪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት (ቪዚቢሊቲ) እንዲኖረው የራሱ የሆነ የፕሮጀክቱ ኢንተርአክቲቭ ዌብሳይት እንዲሁም ለፖሊሲ መነሻ ግበዓት የሚሆን የተሟላ መረጃ ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ለኢትዮጵያ ተብሎ የሚዘጋጀው የልማት መመዘኛ በዋናነት በአገሪቱ ውስጥ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆን የተሟላ ሳይንሳዊ ገለልተኛ የሆነ መረጃ ስለሌለ ይህንን ሊያስወግድ የሚችል የተሟላ ሳይንሳዊ፣ ወቅታዊና የሚታመን መረጃ ለማቅረብ በሚል የተነደፈ እንደሆነ ተነግሯል፡፡

የፈርጀ ብዙ ልማት መመዘኛ (Multidimensional Development Index -MDI) የሚባለው ክፍል ከሚዳስሳቸው ሦስት ዘርፎች የመጀመርያው የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገት የሚለው ይገኝበታል፡፡ 

ደግዬ (ዶ/ር) እንደሚያስረዱት፣ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የሚለካው ዕድገት የኢኮኖሚው እንጂ የማኅበራዊው ዕድገት አይደለም፡፡ በዚህ ውስጥ እስካሁን የምንጠቀምበትና ለማክሮ ኢኮኖሚው የሚለካው የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን (ስታተስ) የሚባለው ነው፡፡ የአንድ አገር የማምረት አቅም እዚህ ውስጥ ይገባል፣ የሰው ኃይል ልማት (Human Development) ይካተታል፣ የማኅበራዊ ደኅንነት (Social Wellbeing) የሚለው ይገባል፡፡ ልብ ሊባል የሚባለው ጉዳይ ኢኮኖሚክ ዌልቢንግና ማክሮ ኢኮኖሚ የተለያዩ መሆናቸው ነው፡፡ 

ሁለተኛው ፈርጅ (ዳይሜንሽን) መለኪያው መልካም አስተዳዳርና ዴሞክራሲ (Democratic Governance) የሚባለውን ነው፡፡ ዴሞክራታይዜሽን ከሌለ ልማትን ማፋጠን አይችልም፡፡ መልካም አስተዳደር (Good Governance) የሚባለውን ይለካል፡፡ 

ሌላው ሁሉን አቀፍ በተለያየ መንገድ ሊገቡ የሚችሉ ፈርጆች ሲሆኑ፣ ለምሳሌ ግሎባላይዜሽን አንዱ ነው፡፡ በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ግሎባላይዝድ እንደመሆናችን አንዱ ምሰሶ (ፒላር) ይህ መሆኑን ይገለጻል፡፡ በሌላ በኩል መንግሥታትና አገሮች የሚገጥማቸው ተጋላጭነት (ስቴቴ ፍሬጅሊቲ) ነው፡፡ ለምሳሌ በምሥራቅ አፍሪካ ይህ ተጋላጭነት ብዙ ነው፡፡ ይህ ተጋላጭነት በየጊዜው ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ነው ያለው የሚለው የሚለካ ሲሆን፣ ይህም የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የመልካም አስተዳደር ፈርጆች ያሉት ነው፡፡ 

ሦስተኛው ፈጠራ (ኢኖቬሽን) የሚለውና ልማት ውስጥ ያለው ጉዳይ ነው፡፡ በአጠቃላይ ጥናቱ 12 ምሰሶዎች፣ ሦስት ፈርጆች (Dimension) ወደ አንድ የተለየ አመላካች (ዩኒክ ኢንዱኬተር የሚያቀርብ ይሆናል)፡፡

 በአገር ደረጃ የሚዘጋጀው የኢትዮጵያን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በመክተት ስድስት ፈርጆች (Dimensions) ያሉት ሲሆን፣ የመጀመርያ እጅ መረጃ በመጠቀም የሚሠራ እንጂ ሁለተኛ ደረጃ መረጃ ተሰብስቦ የሚሠራ አይደለም፡፡ 

የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የልማት መመዘኛ (Ethiopian Multidimensional Index- EDI) በየሁለት ዓመቱ ከ426 በላይ የተለያየ ሙያ ያላቸው ባለሙያዎች የሚሳተፉበት መለኪያ ነው፡፡ የጤና ዘርፉን ተፅዕኖና ጉዳዮች ለመለካት የኅብረተሰብ ጤና ባለሙያ፣ ትምህርትን ለመለካት የትምህርት ባለሙያ የሚመዝነው፣ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚስማሙበትና እርስ በርሳቸው የሚወዳደሩበትና ለመልካም አስተዳደር፣ ለፖሊሲ ግብዓት ይጠቅማል የሚል እምነት ስላለ ለኢትዮጵያ የመጀመርያውና አጠቃላይ የሆነ የልማት መለኪያ በሚል የሚዘጋጅ መሆኑን ተገልጿል፡፡ 

ፕሮጀክቱን አስመልክቶ በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች፣ ከመንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም ከትምህርት ተቋማት ተጋብዘው የመጡ ባለሙያዎች ሊጤን ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች በዕለቱ ሰንዝረዋል፡፡

ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር እንደመጡ የገለጹት ተሳታፊ በመመዘኛው ላይ 122 የሚደርሱ አመላካቾች መቀመጡ በርካታ መሆኑን በመግለጽ በሌላ በኩል ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ሲገባ የፖለቲካ ሁኔታውን እንዴት መለካት ይችላል? ጣልቃ ገብነት አይኖረውም ወይ? በልኬቱ ላይ ጣልቃ ገብነት ቢኖር ትክክለኛውን ውጤት ያስገኛል ወይ? የሚል ሐሳብ ሰንዝረዋል፡፡ 

ከአፍሪካ ልማት ባንክ ተወክለው የመጡት አቶ አድምጥ በበኩላቸው፣ ሁለቱንም ጥናቶች በተመሳሳይ ጊዜ፣ አሁን ላይ ማድረግ ለምን አስፈለገ፣ አሶሴሽኑ ይህንን የመመዘኛ ፕሮጀክት ይፋ ለማድረግ ላይ ታች ሲል (ሲያስብ) ዓለም አቀፍ የሚባሉት ተቋማት ዩኤንዲፒ፣ የዓለም ባንክ ዝም ይላሉ ማለት አስቸጋሪ ነው የሚል ሥጋታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ 

ቴዎድሮስ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ እንደ ዩኤንዲፒ ባሉ ተቋማት እየተሠሩ የሚገኙ መሰል የመመዘኛ ጥናቶች እንደመኖራቸው በኢኮኖሚክስ አሶሴሽኑ የሚደረገው ፕሮጀክት የቱን ጉድለት መሸፈን እንደሚደረግ ማሳየት ይጠበቅበታል፡፡ በሌላ በኩል ለመረጃ አሰባሰቡ የሚሳተፉ ወይም የሚመረጡ ኤክስፐርቶች ምን ዓይነት ኤክስፐርቶች ናቸው? የሚለውን በግልጽ ማስቀመጥ ይሻል፡፡ 

ፕሮጀክቱን በገንዘብ የሚደግፉ ተቋማት ከሚጠይቋቸው ጉዳዮች አንዱ ፕሮጀክቱ የፖሊሲ አስፈጻሚውን ፍላጎትን ያገናዘበ ወይም ከዚያ ጋር የተጣጣመ ሊሆን ይገባል የሚለው እንደመሆኑ፣ ይኼም ፕሮጀክት ፕሮፖዛል ሲቀርብ የሚያደርገው አበርክቶዎች በደንብ ሊቀርብ እንደሚገባ የውይይቱ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡ 

ታደለ ፈረደ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዕድገት ኢኮኖሚን ብቻ የሚመለከት እንዳልሆነ፣ መልካም አስተዳዳር፣ ጤና፣ የሥነ ፆታ ሌሎች ጉዳዮችን በሚመዝን መልኩ ተዋቅሮ ሊቀርብ እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ 

ሁሉም በየፊናው የሚሰጠውን አስተያየት ወደ ጎን በመተው ሁሉም የሚስማማበትና የተመዘነ መሥፈርት ስለሚያስፈልግ፣ በአሶሴሽኑ በኩል የሚደረገው ጥናት አገራዊና ክልላዊ የልማት ግቦች ጋር በተጣጣመ መልኩ ሊፈትሽ የሚችል ከመሆኑ በተጨማሪ በምዘናው መሥፈርት የተመለከተው ጥሩም ሆነ ጥሩ ያልሆነ ደረጃ ተገኘ የሚለውን በማሳየትና ከዚያም በመነሳት ሊተኮርባቸው የሚገቡ አካባቢዎችን ትኩረት እንዲሰጥባቸው የሚያደርግ ይሆናል ብለዋል፡፡ 

በሦስት ዓመት ውስጥ ሙሉ ዝግጅቱ የሚጠናቀቀውና በድምሩ 2.2 ሚሊዮን ዶላር የሚጠይቀው ይህ ፕሮጀክት፣ ከመቶ በላይ የልማት መለኪያዎችን በመጠቀም በዓለም ያሉ አገሮች አድገዋል ወይስ አላደጉም? የሚለውን አንድና ወጥ በሆነ መመዘኛ የሚያስቀምጥ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች