‹‹ተኩዬ›› በተሰኘው የድምፃዊት ቤተልሔም ሸረፈዲን ነጠላ ዜማ መነሻ
በያሬድ ነጋሽ
አንዳንዱ፣ ሌት ተቀን ስለእሱ የሚማልዱለት፣ ጥብቅና የቆሙለትና ዘብ የሆኑት አያሌ ወዳጆቹ፣ የመብት ተከራካሪዎቹና ተቆርቋሪዎቹ በርክተው ቢገኙም፣ አጋሮቹን አመድ አፋሽ በሚያደርግ መልኩ፣ በንፍር ውኃ ሊገሉት ለሚያሰናዱት አካላት ውኃ ቀድቶ፣ ለእሳት የሚሆነውን እንጨት ፈልጦና እሳት አቀጣጥሎ ያሰናዳል። ወደ ገዳዮቹ ዘንድ የሞቱን ደብዳቤ ያደርሳል። ሊጎዱት የማይቦዝኑ ዙሪያው ሳሉ፣ ጠላቶቹ ባደፈጡበት ድንግዝግዝና በመሸጉበት ሰርጥ ራሱን አጋልጦ ይጓዛል። ይኼ ሐሳብ በአዕምሮዬ የተመላለሰው፣ በቅርብ ቀን በወጣት ድምፃዊት ቤተልሔም ሸረፈዲን የተሰናዳ ‹‹ተኩዬ›› የተሰኘ ተወዳጅ ነጠላ ዜማ በማድመጥ ላይ ሳለሁ ነበር።
የሴቶች መብትና እኩልነትን በማስከበር ረገድ መንግሥታዊም ይሁኑ አይሁኑ አያሌ ተቋማትና ግለሰቦች በርክተው ሳለ፣ ነገር ግን እንስቶቹ የተለያዩ ጋሬጣ በመንገዳቸው አሰናድተው ለሚጠብቋቸው አካላት የተመቸ፣ በማወቅም ይሆን ባለማወቅ ከተባባሪነት ባልተናነሰ መልኩ ሚና ኖሯቸው ሲገኙና ስለመብትና እኩልነት የሚሞግቱላቸውን አካላት እጀ ሰባራ ሲያደርጉ እንታዘባለን።
ሴት ልጅ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላትን ሚና አሉታዊ በሆነ መልኩ መመልከት በሃይማኖት፣ በባህልና በተለያዩ ጫና ውስጥ በሚገኘው የታችኛው የማኅበረሰብ ክፍል ይቅርና ‹ራሳቸውን ከተለያዩ ጫናዎች አላቀዋል› በሚባሉ ፈላስፎችና አሰላሳዮች ዘንድ ሳይቀር በጉልህ የሚታይ ነው። በዘመንም ቢሆን ከጥንታዊው የጋርዮሽ ሥርዓት አንስቶ ያለንበት ክፍለ ዘመን ብርሃን በበራላቸው ምሁራን ዘንድ ጭምር፣ በሴት ልጆች ዙሪያ ጥያቄ የሚያስነሱ አስተያየቶች ሲሰጡ ተመልክተናል። ከጥንታዊ የግሪክ ፈላስፎች አንስተን፣ አሁን እስካለንበት ክፍለ ዘመን የነበሩና ያሉ አሰላሳዩች፣ በእንስታዊነት ዙሪያ ያላቸውን አሉታዊ ምልከታ እናንሳ።
አፍላጦን ወይም ፕሌቶ ‹‹ሪፐብሊክ›› በተሰኘ ድርሰቱ ‹‹ወንዶችና ሴቶች በአንድ መሥራት ቢችሉም እንኳን ሁሌም ሴቶች ከወንዶች ያነሰ አፈጻጸም ወይም ብቃት ይኖራቸዋል›› ይላል (ትርጉም፣ ቤንጃሚን ጆዌት)፡፡
አርስጣጣሊስ ወይም አርስቶትል “ኦን ዘ ጄኔሬሽን ኦቭ አኒማልስ” (on the Generation of Animals) በሚል ድርሰቱ “በሁሉም እንስሳ ውስጥ ሴቶች ከወንዶች ሲነፃፀሩ ገና ያላለቁ ፍጡሮች ናቸው። …ሴቶች ያጡት መሠረታዊ ነገር ነፍስ ነው። …ባልና ሚስት ልጅ በመውለድ ሒደት ላይ ሴቶች አካል ብቻ ሲያዋጡ፣ ወንዶች ደግሞ ለጽንሱ ነፍስ ያዋጣሉ። …ብዙ ጊዜ ሴቶች የሚፀነሱት፣ አካሏ ካልዳበረ ወይም የማረጥ ጊዜዋ ከደረሰ እናት ወይም ሴታ ሴትና ኮስማና ከሆነ አባት ሲወለዱ ነው።” ይላል (ትርጉም፣ ኤ.ኤል.ፔክ)፡፡
ጀርመናዊው ኢሚኑኤል ካንት (እ.ኤ.አ. 1724 – 1804) ‹‹አንትሮፖሎጂ ፍሮም ኤ ፕራግማቲክ ፖይንት ኦቭ ቪው›› (Anthropology from a pragmatic point of view) በሚል ድርሰቱ “ሴቶች ከወንዶች ጋር ሲነፃፀሩ ከወንድ ይልቅ ስሜት ያጠቃቸዋል። አመክኖአዊነታቸው በስሜታቸው የበላይነት የተጨቆነ ነው። ስሜታዊነታቸውንም በመፍራትና በራስ ያለመተማመን ችግር ውስጥ ቁልጭ ብሎ ይታያል። በዚህ የተነሳ ግድ የወንድ ጥገኛ ይሆናሉ” ይላል።
ሌላው ጀርመናዊ ሾፐርሀወር (እ.ኤ.አ. 1778 – 1860) “ኦን ዉሜን” (on women) በሚል ሥራው “ሴቶች በየአጋጣሚው ለመታየት፣ በብዙኃን ዓይን ውስጥ ለመግባት ይመኛሉ። አቅመ ቢስነታቸውን ለመሸፈን ቅን፣ የዋህ፣ ጥሩ ሆነው ይታያሉ። መርህን፣ ደንብን፣ ዕውቀትንና ምክንያትን በመጠቀም ረገድ የሴቶች ደካማነት ቁልጭ ብሎ ይታያል። የሴቶች ደካማነት “ደካማነት” ተብሎ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ነገር ግን ራሳቸውን የሚከላከሉበት የህልውና መንገድ ነው። . . . ሴቶች ከመውለድ ያለፈ ዓላማ የላቸውም። ቢኖራቸው እንኳን ከራሳቸው አቅም ይልቅ የወንዶች ጥገኛ ሆነው ፍላጎቶቻቸው በተዘዋዋሪ መንገድ ያሟላሉ።” ይላል።
የ20ኛው ክፍለ ዘመን የሳይኮአናሊስስ አባት የሆነው ሲግመን ፍሮይድ “ሴቶች ከወንዶች ጋር ሲነፃፀሩ በበታችነት ስሜት የሚሰቃዩ ናቸው። ለዚህም ምክንያቱ የወንዶች ዓይነት ብልት (የወሲብ አካል) ስለሌላቸው ሲሆን፣ በዚህ ሳቢያ ትንሽነት ይሰማቸዋል፣ የቅናት መንፈስ ያቃጥላቸዋል፣ ራሳቸውን ይጠላሉ። …ሴቶች እንደ ወንድ ሁሉ ጠንካራ ባለመሆናቸው ወንዶች የሚችሉትን ሁሉ መቻል አይሆንላቸውም። በምድር ላይ ሁለተኛ ደረጃ ፍጡራን ሲሆኑ፣ ቀለል ያሉ የሕይወት ተልዕኮዎችን በወንዶች ሥር ሆነው መፈጸም ተፈጥሯቸው ነው።” ይላል (የፍልስፍና መግቢያ፣ በደሳለኝ ሥዩም)፡፡
ይህ አስተሳሰብ ከላይ ባየነው መልኩ በውጭው ዓለም ሰዎች ብቻ ሳይሆን በእኛ አገር አሰላሳዮች ጭምር የተስተዋለ ሲሆን፣ ድርሰት አዘጋጅተው በሴቶች ኑባሬን ለመበየን የተሞከረባቸው ጊዜያት እንደነበሩም ለማየት ችለናል።
ደራሲና ኃያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ በተለይ ያለንበትን ዘመን ላይ አተኩሮ፣ ስለሴት ልጅ ይህንን ይለናል፣ “ሴቶች የወንዶች አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ሆነዋል። ዓይኑን፣ ልቡን፣ ስሜቱን፣… ያገለግሉታል። የሴቶች የመጨረሻ አማራጭ የወንዶች ገበያ እንደሚፈልገው ሆኖ መገኘት ነው። ሕይወታቸው በወንዶች ህልም የተፈበረከ ነው። ከሰው የሚጠበቀው ከዘንድሮ ሴት አይገኝም። ወንድ የሚፈልገውን ግን አያጣም ። …ሴቷ የወንድ ቀልብ እንደ ንብ ሲጠመድላት ከማየት ውጪ ሌላ ህልም የላትም። የዘንድሮ ሴቶች፣ ሴት የመሆን መብት የላቸውም፣ ወንድ የሚፈልገውን ዓይነት ሴት እንጂ። ሴቶች የወንድን ህልም ለመተርጐም ሕይወታቸውን የሚሰዉ ጭዳዎች ናቸው። በመሠልጠን ስም ራሳቸውን ለፆታ ባርነት አጋልጠዋል። …የሴት ፍላጎት የት ነው? ምርጫ? ህልም? ሕይወት? ኑሮ? ከወንዶች አንፃር የሚቆመው እኩልነታቸው የታል? ሰውነታቸውስ? ክብራቸውስ? ነፃነታቸውስ? የራሳቸው የሆነ ፍርኃታቸውስ የት ነው? …የእኛ ሴት ጋ የሚጎድለው ይኼ ነው። ወደ ፋሽን ኢንዱስትሪ በተቀየረው የወንዶች ፍላጎት ውስጥ መዳከራቸውን አይጠይቁም። የወንዶች አቅርቦት መሆናቸውን አይመረምሩም። ዳሌያቸው እንዲኮራ፣ ጡታቸው እንዲቀለበስ፣ አንጀታቸው እንዲሞላ፣ አካሄዳቸው እንዲቀየር (ካትዎክ)፤ ሲጠየቁ ያለ ተጨማሪ ማብራሪያ ያደርጉታል። ያልተመረመረ ሕይወት ውስጥ የነፃነት ኑሮ እንደሌለ አያውቁም። …ዘመናችን የሴቶች ግርዛትን አውግዟል። ግርዛት አስፈላጊ የሚሆንበት ዘመን ቢመጣና የተፈላጊ ሴት መሥፈርት ቢደረግ ሴቶቻችን ይቃወሙት ይሆን? አሁን ባለው ሁኔታ አይመስለኝም!!! እራቁት አደባባይ እስከመውጣት የቀጠለው የወንዶች መሥፈርት አስተግብረው የለም? ለሚሸፋፈነው ለግርዛት ገመና መልሳቸው ዕንቢ ይሆናል ብሎ ማሰብ አዳጋች ነው።” (መለያየት ሞት ነው፣ ከገጽ 116-119)፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከላይ የተመለከትናቸውን አሉታዊ አስተሳሰቦች ለመሞገት፣ ተጣመመ የሚሉት ለማቃናትና ስለሴት ልጅ መብት የተቆረቆሩ፣ ከወንዶች ጋር እኩል መሆኗን ለማረጋገጥ የማሰኑ፣ አለኝ የሚሉትን አንግበው ለእንስቷ ጠበቃ ለመሆን የሞከሩ የተለያዩ ግለሰቦችን ምላሽ እንመልከት።
የሴትን መብት ጥያቄ አንግበው፣ ከወንዶች ጋር ያላትን እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ፣ በዓለም ደረጃ መቀንቀን ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ በ1950ዎቹ በኢትዮጵያዊ ምድር “ውርድወት” የተሰኘች እንስት የሴት ልጅ መብት ተሟጋች ሆና በቀዳሚነት እናገኛታለን። ነገር ግን ታሪኳና ገድሏ “የቃቄ ውርድወት” በሚል በቴአትር መልክ ተሰናድቶ በብሔራዊ ቴአትር የተመለከትነው በመሆኑ፣ አሊያም ይህ ዕድል ላልደረሰው፣ በእንዳለ ጌታ ከበደ (ዶ/ር) የተሰናዳውን “እምቢታ (የቃቄ ውርድወት)” የተሰኘ መጽሐፍ ማንበብ ሁሉን ያስገነዝባልና የእሷን ነገር በዚህ አልፈን ወደ ሌሎቹ እንሻገር።
ሜሪ ዊስቶን ክራፍትን “ቪንዲኬሽን ኦቭ ዘ ራይት ፎር ዉመን” (Vindication of the Right for Woman) በተሰኘ መጽሐፏ፣ ለዘብ ባለ አቋም “ሴቶች በተፈጥሯቸው ሆደ ቡቡ፣ ደካማ፣ አልቃሻ፣ ስሜታዊና አናሳ ሆነው አልተፈጠሩም። ይልቁን በማኅበረሰቡ እንዲህ እንዲሆኑ ይሠራሉ እንጂ፣ ሴቶች በተፈጥሮ ከተፈጠሩበት በላይ ማኅበረሰቡ እንዲሆኑ ወደሚመኝላቸው ደካማነት እንዲጓዙ የሚደረግባቸው ጫና ይበዛል። ሴቶች አይችሉም ብሎ ከመከልከል ይልቅ ወንዶች በሚሰማሩበት ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ተቋም ውስጥ ሴቶችም ተመሳሳይ ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ ችግሩን ይፈታዋል።” በሚል ሐሳቧን ብትገልጽም ይህ ብቻ አይበቃም በሚል ነገሩን በማጦዝ የራሳቸውን አቋም ያንፀባረቁም አልታጡም።
የፌሚኒዝም ቅዱስ መጽሐፍ ተደርጎ የሚቆጠረውን “ዘ ሰከንድ ሴክስ” (The second sex) የተሰኘ መጽሐፍ ያዘጋጀችው ፈረንሣዪቷ ሲሞን ዲቦቮር፣ “ለወንዱ ጎራዳነት፣ ድምቡጭነት፣ ውፍረት ወይም ክሳት መሥፈርት አይሆንም። የወንድ መልክ ለውድድር አይቀርብም። ወንድ አያለቅስም፣ ወንድ ደረቱን ነፋ ማድረግ አለበት። በአንፃሩ ሴት መኳኳል አለባት፣ አካሏን ካልጠበቀች የሚነካትና የሚመኛት እንደሌለ ይነገራል። ረዥም ሰዓቷን መስታወት ፊት እንድትቆም ታደርጋለች። …ወንድነት ፆታው እንጂ ገላው እንደማይጠየቀው ሁሉ፣ ሴትነት ገላ ሳይሆን ራሱን የቻለ ህልውና ነው። ፆታ ከተፈጥሮ ይልቅ ለሰው ሠራሽነት የቀረበ ነው። የፆታ ክፍፍል የሰዎች ስምምነት እንጂ፣ ተፈጥሯዊ አይደለም። የሴቶችን የበታችነት ለማስቀረት ከተፈለገ “እርሷ” ከሚለው ፆታ ጠቀስ አግላይነት መሻገር ይገባቸዋል። ይህንን ማድረግ ሲቻል ሴቶች ቁስ መሆናቸው ይቀርና ሰው መሆን ይችላሉ” ትላለች።
ከዚህም ሲያልፍ ከ1990ዎቹ በኋላ የመጡ የእንስታዊነት አስተሳሰብ መዳረሻውን አስፍቶ “ፆታና ሥርዓተ ፆታ ይለያያል። ሴት ልጅ በሃይማኖት፣ በባህል፣ በትዳር፣ በኢኮኖሚ ሥርዓቶች ሰበብ ‹ለትዳሯና ለማኅበረሰቧ እንዲህ ሆና ነው መኖር ያለባት› እየተባለ የሚወጣው የሕይወት ዘይቤ ፍፁም ተቀባይነት የለውም። ሴቷ ከፈለገች ወንድ አርግዛ ዞር በማለትና ልጇን ለብቻዋ ማሳደግ ወይም የጭቆና ሀሁ ከወንድ አካል ይጀምራልና የወንድንም አካል ሳትፈልግ ከሚመስሏት ሴቶች ጋር ወሲባዊ ተግባራትን መከወን ትችላለች።” ከሚል፣ “በወንድ ስም የሚጠራ አምላክ አናመልክም።” እስከ ማለት የደረሱ አካላትም በመፍትሔ አፈላላጊ ስም ሐሳባቸው ተደምጧል (የፍልስፍና መግቢያ፣ በደሳለኝ ሥዩም)፡፡
በተለይ ሴት ልጅ ክብሯን በማይመጥን መልኩ ወኪል ሆና መመልከት በተዘወተረበት የመዝናኛው ዓለም ያለውን ሒደት በፅኑ በመቃወም ለመብቷ ጥብቅና በመቆም ሐሳቡን የሰነዘረው፣ አቀናባሪ ኤልያስ መልካ (ነብሱን ይማር) ሲሆን፣ “የከተማው መናኝ” በሚል የሕይወት ታሪኩ በተዘከረበት የይናገር ጌታቸው (ማዕረግ) መጽሐፍ ውስጥ የሠፈረውን ሐሳብ እንመልከት።
“በአገራችን ሆነ በውጪው ዓለም በሚሠሩ ማስታወቂያዎች ላይ ሴቶች ራሳቸውን ገላልጠው ምርቱን ለማሻሻጥ ሲሞክሩ ማየት የተለመደ ነው። ይህ ተግባር ከእኩልነት መብት አራማጆች ዕይታ ሴትን ልጅ እንደ ወሲብ ዕቃ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ወንድን አምራች፣ ሴትን ሸማች የሚያደርግ ነው። …የሕዝባዊ ባህላችን ማደሪያችን በሆነው ዘፈናችንም ውስጥ ይኼው መንገድ ገዥ መስሏል። በስንኞች ሆነ በሙዚቃ ቪዲዮዎች ውስጥ ሴት ልጅ አዘውትራ የምትሳለው በወሲብ ዕቃ ጽንሰ ሐሳብ ነው። “ነይ ማታ ማታ” እና “ላግኝሽ ማታ ማታ” ከሚለው አንስቶ ውጫዊ ውበትን እየጠቀሰ በሐሳብ የሚናውዘው ሙዚቃዊ ገጸ ባህሪ ብዙ ነው።
‹አሆ ሳላወጣሽ ካልጋ፣
ንገሪኝ ዋጋ።
አሆ ሳልመዝነው ጥጡ፣
ንገሪኝ ቁርጡን።› ይሄ የታደሰ ዓለሙ ስንኞች የሠርግ ማድመቂያ ብቻ አይመስሉም። አባታዊ በሚባለው ማኅበረሰባችን ውስጥ ሴትን የተረዳንበት የልቦና ውቅር ገሃድ ያወጣሉ። …ኤልያስ መልካ ‹ፌሚኒሴትነቱን የካደ መንፈሳዊ ፌሚኒስት› መሆኑ ቁልጭ ብሎ የሚታየው እዚህ ሥፍራ ላይ ነው። ሴት ልጅ በወንድ አዕምሮ የተሣለች ፍጡር ሳትሆን የአምላክ መልካም ሥራ ያደርጋታል። የተለየች ናት የሚለው አመለካከቱም ከቀዳሚዎቹ ባህላዊ ፌሚኒሴቶች ጋር ያመሳስለዋል። ከወሲብ ዕቃነት መላቀቅ አለባት ብሎ መሻቱም ሕዝባዊ ባህልም ውስጥ ካሉት የመብት አቀንቃኞች ጋር ያቀራርበዋል። ለዚህ ጥሩ ማስረጃ የሚሆነው ኤልያስ መልካ “ደብዝዘሽ” የተሰኘውን የኢዮብ መኮንን የሙዚቃ ቪዲዮ ለተመልካች እንዳይቀርብ ያደረገበት ምክንያት ነው። የከተማው መናኝ የአምላክ ውብ ሥራ ናት የሚላትን ሴት ልጅ ሰውነቷን ገላልጣ ሙዚቃውን እንድታሻሽጥለት አልፈለገም። እናም ብዙ የተለፋበትን የሙዚቃ ቪዲዮ ለዕይታ እንዳይበቃ አደረገ። …በአንድ ወቅት ኢቲቪ ድረስ በመሄድ፣ በቴሌቪዥን ጣቢያው በሚተላለፉ ሙዚቃዎች ላይ የሚታዩትን ሴቶችን መነሻ አድርጎ ‹ለምን በዚያ መልኩ ለሕዝብ ትታያለች› የሚል ወቀሳውን በማቅረብና የሚስተካከልበትን መንገድ ካለ በሚል አቤቱታውን አቅርቧል።” (የከተማው መናኝ፣ ከገጽ 288-291)፡፡
ከመግቢያዬ እንደጠቀስኩት፣ የዚህ አንቀጽ ዝግጅት መነሻ፣ “ተኩዬ” የተሰኘ የወጣት ድምፃዊት ቤተልሔም ሸረፈዲን ነጠላ ዜማ ማድመጤ ነበር። ሙዚቃው በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል። እንዲህ ትላለች፡-
“እንድለይ ከወደዱህ፣
ልክ እንደኔ ከሚያፈቅሩህ፣
አለህና ብዙ ምርጫ፣
በምን ላሳይ የእኔን ብልጫ።
ተኩዬ ተኩዬ … ተኩዬ ልምጣ ወይ፣
ላንተ መሽቀርቀሬን ትወደዋለህ ወይ?!
ተኩዬ ተኩዬ … ደሞ ጉድ እንዳልሆን፣
እጅ ያወዛው መልኬን አትወደው እንደሆን?!”
. . . . (ቀሪውን ሙዚቃውን ያዳምጧል)
ድምፃዊቷ ትልቅ ተሰጥዖ ያላትና ከፊት ለፊት ብሩህ ተስፋ የሚጠብቃት የ24 ዓመት ወጣት ናት። መነሻዋ “የእኛ” በተሰኘው ተከታታይ ድራማ ውስጥ ሁለተኛ ትውልድ በመሆን ነው። ከዚህ ቀደም “ግን” የተሰኘ ነጠላ ዜማ ጥሩ አድርጋ አሰናድታ ለአድማጭ አቅርባለች። “ተኩዬ” የተሰኘው ይሄ ሁለተኛ ሥራዋ፣ ዜማውን በተዋበ ድምጿ ስትወጣው ከመመሰጥ በቀር ጥያቄ የማያነሳ ሊኖር ይችላል። ወጣቷም ሰይፉ በኢ.ቢ.ኤስ በተሰኘው የመዝናኛ ዝግጅት ላይ ቀርባ፣ የዘፈኑ ዓላማ ለፍቅር የሚከፈል መስዋዕትነት እንደሆነ ገልጻለች።
ሆኖም እኔ ግን በግጥሙ ይዘት ላይ ትልቅ ጥያቄ አነሳሁ። ግጥሙ ሴት ልጅ ከዚህ ሌላ ሚና የላትም በሚል በማኅበረሰቡ ዘንድ የተሰጣትን አናሳ ግምትና ውክልና የሚያጠናክር፣ ለሴት ልጅ መብት የሚሞግቱትን በተለይም በመዝናኛው መስክ እንደተነሱት የአቀናባሪ ኤልያስ መልካ ዓይነት ለሴት ልጅ ክብር የሞገቱትን እጀ ሰባራ የሚያደርግና ከላይ በዓለማየሁ ገላጋይ “መለያየት ሞት ነው” በተሰኘው መጽሐፍ፣ “የሴቶች የመጨረሻ አማራጭ የወንዶች ገበያ እንደሚፈልገው ሆኖ መገኘት ነው። ሴቷ የወንድ ቀልብ እንደ ንብ ሲጠመድላት ከማየት ውጪ ሌላ ህልም የላትም።” በሚል የተነሳውን ሐሳብ የሚያጠናክር ነበር።
ድምፃዊቷ ከፊቷ ለሚጠብቃት ረዥም የሙዚቃ ሕይወቷ ውስጥ የሚመጡላትን ሥራዎች አይታና መርምራ ወደ ሕዝብ ብታደርስ፣ ካላት ተሰጥዖ ጋር ተዳብሎ ልክ እንደ አንጋፋዎቹ፣ ወደ ሕዝብ ልብ የምትገባበት በር ወለል ብሎ ተከፍቶ እንደሚጠብቃት አልጠራጠርም። ሌሎች እንስት ድምፃውያትም ይህንን ጉዳይ በአንክሮ ቢገመግሙት መልካም ይሆናል።
የመጋቢት ወር የሴቶች ቀን ታስቦ የሚውልበት ወርኃ “ማርች” ነው። በዚህ አንቀጽ ዝግጅት ካነሳሁት ጉዳይ በተመሳሳይ ይሁን በተለየም፣ በተቋማት ይሁን በግለሰቦች ደረጃ፣ በኅትመት ይሁን በኤሌክትሮኒስ ሚዲያ ሴትን ልጅ አስመልክቶ ብዙ ብዙ ይነሳል፣ ተሳትፎዋ ይወሳል፣ አበርከቶዋ ይዘከራል፣ ስለመብትና እኩልነቷ ይሞገታል። በየትኛውም መስክ ያሉ ሴቶች፣ አሉታዊ አስተያየት ለሚሰነዝሩባቸው፣ አሳንሶ ለሚያዩዋቸው፣ በግዞት ሊያኖራቸው ለሚመኛቸው፣ ሚናቸውን ለሚያንኳስሱባቸው አካላት መግቢያ የሆኑ ክፍት በሮቻቸውን በመዝጋት፤ ስለሴቷ መብትና እኩል ተጠቃሚነት ከሚሞግቱና ትብትቡን ለመፍታት ከሚጣጣሩ አካላት ሥራ ጋር የተጣጣመ ኑባሬን ምርጫ ማድረግ ለነገ የማይባል የቤት ሥራቸው ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected]. አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡