ኢትዮጵያ የቲቢ፣ ሥጋ ደዌና ሌሎች የሳንባ በሽታዎች ጫና ካለባቸው 30 አገሮች አንዷ ናት፡፡ በዚህም በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ታስተናግዳለች፡፡
ችግሩን ለመከላከል የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ የቆዩ ሲሆን፣ ሰሞኑን ደግሞ ይህንን ችግር ለማቃለል ያስችላል ተብሎ የታመነበት ስትራቴጂክ ዕቅድ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሕይወት ሰለሞን እንደገለጹት፣ የቲቢና ሥጋ ደዌ በሽታን ለመላከልና ለመቆጣጠር የሚሠሩ ሥራዎች በመንግሥትና በለጋሽ ድርጅቶች ዕርዳታ ይንቀሳቀሱ የነበረ ሲሆን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀደም ሲል የነበረውን ፕሮግራም የመደገፍ ሁኔታ እየቀነሰ መጥቷል፡፡
በቀደመው ሰነድና ፕሮግራም በበሽታው ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከመቀነስ አኳያ ስኬታማ የሚባሉ ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም፣ በሽታዎቹ አሁንም በኅብረተሰቡ ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ 143,000 የቲቢ ታማሚዎች እንደሚኖሩ፣ ከእነዚህም መካከል በዓመት 19,000፣ በቀን 53 ሰዎች በዚሁ በሽታ ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ የገለጹት ደግሞ በሚኒስቴሩ የቲቢ ሥጋ ደዌና ሌሎች የሳንባ በሽታዎች ዴስክ ኃላፊ አቶ ታዬ ለታ ናቸው፡፡
እንደ ኃላፊው፣ በበሽታው መያዙ የተረጋገጠ ማንኛውም ሰው ወደ መንግሥት ጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን ሕክምና በነፃ ማግኘት ይችላል፡፡ ሁለት ሳምንትና ከዚያ በላይ ካሳለው፣ የክብደትና የምግብ ፍላጎት መቀነስ እንዲሁም ማታ ማታ የላብ ስሜት ካለ የቲቢ በሽታ ምልክት ሊሆን ስለሚችል ወደ ጤና ተቋም በመሄድና መመርመር ያስፈልጋል፡፡
በቆዳው ላይ ነጣ፣ ነጣ ወይም ቀላ፣ ቀላ ያሉ ምልክቶች ከታዩ የሥጋ ደዌ ምልክት ሊሆን ስለሚችል ወደ ጤና ተቋም ሄዶ መመርመር ያለበት መሆኑንም ገለጸዋል፡፡
በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፣ ቲቢ በባክቴሪያ (ማይኮባክቴሪያም ቲዩበርክሎዝ) የሚከሰት ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜ በሳንባ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡
የሳንባ ከረጢት ቲቢ፣ ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓት ቲቢ፣ የሽንት አወጋገድ ሥርዓት፣ አጥንትና መገጣጠሚያዎች ላይ በተለይም (የአከርካሪ አጥንት ቲቢ) እንዲሁም ሌሎችም የዚሁ በሽታ ዓይነቶች ናቸው፡፡
ለበሽታው አጋላጭ ሁኔታዎች የሚባሉት፣ በሽታው ካለበት ሰው ጋር የቅርብ ግንኙነት ሲኖር፣ በሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳክሙ በሽታዎች (ለምሳሌ ኤችአይቪ፣ ካንሰርና የስኳር በሽታ ሲኖሩ፣ የጤና እንክብካቤ ሠራተኞች ደግሞ በሙያቸው ምክንያት ተጋላጭ ናቸው፡፡
ለሦስት ሳምንት እና ከዚያ በላይ፣ የሚቆይ ሳል፣ የደረት ሕመም፣ ከፍተኛ የድካም ስሜት፣ ክብደት መቀነስ፣ ትኩሳት፣ ማታ ማታ ማላብ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት ምልክቶቹ ሲሆኑ፣ ሊታከም የሚችልና የሚድን በሽታ በመሆኑ በሕክምና መዳን ይቻላል፡፡
የመድኃኒት መላመድ የሚከሰተው ፀረ ቲቢ መድኃኒቶች አግባብ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውሉ፣ በጤና እንክብካቤ አቅራቢዎች የተሳሳተ መድኃኒት ሲታዘዝና ታካሚዎች ሕክምናውን ያለጊዜው ሲያቆሙ በመሆኑም የጤና ባለሙያዎችም ሆነ ታማሚዎች ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡
መድኃኒትን የተላመደ ቲቢ ሁለተኛ መስመር ላይ ያሉ መድኃኒቶችን በመጠቀም ሊታከምና ሊድን እንደሚችል፣ ነገር ግን የሁለተኛው መስመር ሕክምና አማራጮች ውስን፣ ውድና መርዛማ ከመሆናቸው ባሻገር እስከ ሁለት ዓመት ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡