Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ተጠየቀ

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ተጠየቀ

ቀን:

በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚደረጉ ድጋፎች ዘላቂነት እንዲኖራቸውና በተቀናጀ መልኩ እንዲከናወኑ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ጠየቀ፡፡

ማኅበሩ በቦረና በተከሰተው ድርቅና እያከናወነ ያለውን ድጋፍ አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በቦረና አካባቢ ዓመታትን ያስቆጠሩና በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ የድርቅ አደጋዎችን ለማቃለል ዘላቂ መፍትሔዎችን ማበጀት ያስፈልጋል፡፡

የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አበራ ቶላ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ በተለይም በዝቅተኛ አካባቢዎች ላይ የሚከሰቱ ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋዎች በዘላቂነት እንዲፈቱ የተቀናጀና አገር አቀፍ ርብርብ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ለዚህም መንግሥትና ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው መሥራት ይገባቸዋል፡፡

- Advertisement -

በቦረና ዞን በድርቅ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው አባባቢዎች በውኃ አቅርቦት፣ የተረፉትን ከብቶች ማከም እንዲሁም ኅብረተሰቡ ወደ ቀደመ የአኗኗር ዘይቤው እንዲመለስና ቀጣይ ሕይወቱን እንዲመራ፣ ማኅበራዊና ጤናን መሠረት ያደረጉ ድጋፎች ያስፈልጋሉም ብለዋል፡፡

ሰሞኑን የጣለውን ዝናብ ተከትሎ በከብት ዕርባታና በእርሻ ሥራ የሚተዳደሩ የተልተሌ አካባቢ ነዋሪዎች፣ ‹የዘር ድጋፍ አድርጉልን፣ ዘርተን እህላችን ደርሶ እስክናነሳም ዕርዳታ ይቀጥልልን› ብለው መጠየቃቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ተልተሌ ከከብት ዕርባታው በተጨማሪ የእርሻ ሥራው ጎን ለጎን የሚካሄድበት፣ እንደ ሌላው የቦረና አካባቢ በርካታ ከብት ባይኖርም፣ በእርሻው ጥሩ የሚሠራና ጤፍ አርሶ እስከ ሐዋሳና አርባ ምንጭ ድረስ የሚሸጥ አካባቢ እንደነበር በመጠቆም፣ በአካባቢው ከብቶች ሙሉ በሙሉ በማለቃቸውና ተልተሌ ውስጥ ሊያርስ የሚችል በሬ ባለመኖሩ የከብት ድጋፍ እንዲደረግም አሳስበዋል፡፡

በምግብ በኩል በተለይ ሕፃናትና ሴቶች መጎዳታቸውን፣ በአካባቢው በቦረና የገዳ ሥርዓት መሠረት ትልልቅ ሰዎች ራሳቸው ሳይበሉ ለሕፃናትና ለሴቶች የሚመግቡ በመሆኑ፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎች በጣም መጎዳታቸውን፣ ትንሽ አቅም የነበራቸው ደግሞ ወደ ኬንያ መሰደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ዲሎ በጣም ከተጎዱ የቦረና አካባቢዎች አንዱ መሆኑን፣ አብዛኛው አርብቶ አደር በሚገኝበት ዲሎ ከብቶች ማለቃቸውን፣ ለነዋሪው የምግብ ሥርጭት አሁን ቢደረግም ዝናብ መጣሉን ተከትሎ የተረፉትን ከብቶች ማከምና ከብቶችን ለአርብቶ አደሩ መግዛት እንደሚያስፈልግ አክለዋል፡፡ 

ማኅበሩ በድርቅ ለተጎዱ አካባቢዎች እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልና ለተጎጂ ወገኖች የሚፈልጉትን ከገበያ መርጠው እንዲገዙ ለማበረታታት ቀጥተኛ የገንዘብ ልገሳ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡

የማኅበሩ የወጣት በጎ ፈቃደኞች ተወካይ የቦርድ አባል  አዲስ ዓለም ሙላት (ዶ/ር)፣ በተልተሌና በዲሎ ተገኝተው ባደረጉት ጉብኝት ሕፃናት፣ አዛውንቶችና በዕድሜ የገፉ ሰዎች በድርቁ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ በተለይ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ልጆቻቸውንም ሆነ የልጅ ልጆቻቸውን የመንከባከብ ኃላፊነት ስላለባቸው፣ በድርቁ ይበልጥ የተጎዱ በመሆኑ ለአዛውንቶችም ትኩረት እንዲሰጥ አሳስበዋል፡፡

ኅብረተሰቡ በማኅበራዊ፣ በሥነ ልቦናም ሆነ በኢኮኖሚ በመጎዳቱ ከምግብና ከገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ፣ የሥነ ልቦናና የጤና ክትትል እንደሚያስፈልገው አዲስ ዓለም (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

‹‹በአካባቢዎቹ ውስጥ ሕዝቡ በሙሉ በሚባል ደረጃ ተጎድቷል፡፡ ሴቶች፣ ሕፃናትና አዛውንቶች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፤›› ያሉት አዲስ ዓለም (ዶ/ር)፣ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች ከአምስት ዓመታት በታች ላሉና ለሚያጠቡ እናቶች ድጋፍ የሚያደርጉ ቢሆንም፣ አዛውንቶች በከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጠቅተው ድጋፍ ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል፡፡

ኤፍ75 እና ኤፍ100 የተባሉና ከፍተኛ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸውን ሕፃናትን ለማከም የሚያገለግሉ ወተቶች በጉብኝታቸው ወቅት ቢያዩም፣ በበቂ ሁኔታ አለመኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ለሕፃናት፣ ለእናቶችና ለአዛውንቶች መድረስ ይገባል፤›› ያሉት አዲስ ዓለም (ዶ/ር)፣ ከፍተኛ የሆነ ድርቅና ረሃብ ሲመጣ በከፍተኛ ሁኔታ ለተላላፊ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድል ስላለ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ብለዋል፡፡

በሥነ ልቦና ረገድ የቦረና ሕዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው፣ ከ200 እስከ 400 ከብት የነበረው ቤተሰብ ባዶ መቅረቱን፣ በየቀኑ ወተት ይጠቀም የነበረ ማኅበረሰብ ዛሬ ቤቱ ባዶ መሆኑን፣ የከተማው ሕዝብ ከኬንያ የሚገባውን ማውንት ኬንያና ዳያማ የተባሉ ወተቶችን እንደሚጠቀም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ያበላና ያጠጣ የነበረ ሕዝብ ባዶ እጁን ሲቀር ከሚፈጠርበት የሥነ ልቦና ጫና ለማላቀቅ ሕክምና ያስፈልጋል፤›› የሚሉ የሕክምና ባለሙያዎች፣ በከፋ የምግብ እጥረት ምክንያት በሕፃናቱ ላይ የተከሰተው ችግር አሁን ስለታከመ የሚድን አለመሆኑን፣ በሕፃናት አዕምሮ ዕድገት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ የወደፊት ሕይወታቸውን ስለሚጎዳው ዘላቂ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡

የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌታቸው ታአ፣ ማኅበሩ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በቦረናና በሞያሌ አካባቢዎች 28 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር በድርቅ ክፉኛ ለተጎዱ የቦረናና የሞያሌ አካባቢዎች ወደ 27 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የምግብ ድጋፍ ለ6,130 ሰዎች እንዲሁም የ800 ሺሕ ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ለ1,000 ሰዎች ማድረጉን አክለዋል፡፡

ድርቁ በሰውም ሆነ በእንስሳት ላይ እያስከተለ ካለው ጉዳት አንፃር ተጨማሪ፣ ድጋፎችን ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ማኅበሩ ቀጣይነት ያለው የሀብት ማሰባሰብ ዘመቻ እያካሄደ ሲሆን፣ በዚህም ባለፈው ሁለት ሳምንት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

በማኅበሩ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ጀማል እንዳሉት፣ ማኅበሩ ባለፉት አራት ዓመታት በጣም የተጎዱ አካባቢዎችን በመለየት ሲደግፍ መቆየቱን፣ ሆኖም ችግሮች ከአቅም በላይ የሚሆኑበት ጊዜ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ማኅበሩ ከሚያደርጋቸው ድጋፎች ውስጥ በችግራቸው ምክንያት ለተለዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጥሬ ገንዘብ መለገስ እንደሚገኝበትና ይህም የፈለጉትን ገዝተው እንዲጠቀሙ ዕድል እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡

ማኅበሩ በድርቅ የተጎዱ ወገኖችን ለመታደግ 9400 ላይ Ok ብሎ በመላክ 1 ብር እንዲለግሱ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ በዓይነት ድጋፍ ለማድረግ ለሚፈልጉ ወገኖችም አዲስ አበባ ስታዲየም አካባቢ በሚገኘው የማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት ግቢ ድረስ በማምጣት መለገስ እንደሚቻል አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...