ሱዳን ከኢትዮጵያ ለምትጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ መክፈል ያለባትን ባለማጠናቀቋ፣ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ ተገለጸ።
ሱዳን ከኢትዮጵያ ለሚላከው የኤሌክትሪክ ኃይል በየወሩ ሙሉ ለሙሉ መክፈል ቢኖርባትም ካለፈው ዓመት ጀምሮ ክፍያዋን በማቆረጧ፣ ተከፍሎ ያላለቀና መጠኑ ያልተገለጸ በርካታ ሒሳብ እንዳለባት ሪፖርተር ለመረዳት ችሏል።
የቀረውን ክፍያ ለማስከፈል በኢትዮጵያ በኩል ጥረቶች ሲደረጉ እንደቆዩና በአሁን ጊዜም፣ ‹‹ከሁለቱ አገሮች የኤሌክትሪክ ተቋማት በዘለለ መንግሥትም እንዲገባበት›› ጥረቶች መጀመራቸውን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ለሦስት የጎረቤት አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ትልካለች፣ አገሮቹም አንደኛው ወር ሲጠናቀቅ የሚቀጥለው ወር ላይ ሆነው ባለፈው ወር ለተላከው የኤሌክትሪክ ኃይል ክፍያ የፍጆታ ይፈጽማሉ ብለዋል።
ሱዳንም በእንዲህ ዓይነት አሠራር መክፈል የነበረባትን ነገር ግን ያልፈጸመችው ክፍያ እንዳለ ገልጸዋል። ‹‹ሱዳኖች የተወሰነ ክፍያ እየፈጸሙ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ክፍያቸውን ጨርሰው እየከፈሉና እያጠናቀቁ አይደለም፤›› ሲሉ ተናግረዋል።
የክፍያ መቆራረጡ የተጀመረው ካለፈው ዓመት ጀምሮ መሆኑን፣ ከሱዳን ውጪ ከሌሎች አገሮች ጋር ከክፍያ ጋር በተያያዘ የሚገጥም ችግር እንደሌለ የገለጹት አቶ ሞገስ፣ ‹‹የሱዳንም ቢሆን በነበረባት የውስጥ ችግር የተነሳ ነው፤›› ብለዋል።
ወደ ሱዳን እየተላከ ላለው የኤሌክትሪክ ኃይል ሊከፈል የሚገባው ነገር ግን ያልተጠናቀቀው የክፍያ መጠንን በሚመለከት አቶ ሞገስ ሲገልጹ፣ ‹‹ካለፈው ዓመት ጀምሮ የተወሰነ ክፍያ እየከፈሉ የተወሰነውን እያሻገሩ ስለሆነ፣ ምን ያህል ወር ክፍያ እንዳለባቸው ለማወቅ ያስቸግራል፤›› ሲሉ ተናግረዋል። በአንዳንድ ወር ከሚተላለፈው ኃይል የሚመጣውን ክፍያ ሳይፈጽሙ ቀርተው፣ በሌላኛው ወር ደግሞ የተወሰነውን ብቻ እንደሚከፍሉም አክለው ገልጸዋል።
‹‹የአንድ ወር ሙሉ የሚከፈልበት፣ ሌላው ሙሉውን የማይከፈልበት፣ አልያም ደግሞ በከፊል ከሌሎች ክፍያዎች ጋር እያደረጉ እያቆራረጡ እየከፈሉ ነው የተጠራቀመው፤›› ብለዋል። መንግሥትም ክፍያው እንዲፈጸም ለማስደረግ ነው በዲፕሎማሲ መንገድ ጣልቃ እንዲገባ እየተደረገ ያለው ሲሉም አክለዋል።
ባለፉት ሰባት ወራት ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን፣ ጂቡቲና ኬንያ ከተላከው የኤሌክትሪክ ኃይል መንግሥት ለመሰብሰብ ካቀደው 59 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ መሰብሰብ የቻለው 48.23 ሚሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ ታውቋል። አፈጻጸሙ በ82 በመቶ ሆኖ ሙሉ ለሙሉ ያልሆነበትን ምክንያት አቶ ሞገስ ሲገልጹ፣ በዚህ ዓመት የተጀመረው ወደ ኬንያ የመላክ ዕቅድ ዘግይቶ ተግባራዊ በመሆኑ ከኅዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ ከሁለት ወራት በላይ ለሆነ ጊዜ በሙከራ ላይ ስለሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል።
ወደ ኬንያ የሚላከው የኤሌክትሪክ ኃይል የሙከራ ጊዜ ላይ ከመሆኑና በአነስተኛ መጠን ከመላኩም ባሻገር፣ መንግሥት እንደሚልክ አቅዶ የነበረው ባለፈው ዓመት ነበር። በባለፉት ሰባት ወራት ወደ ኬንያ ለመላክ በዕቅድ ደረጃ ተይዞ የነበረው ወደ ስምንት ሚልዮን ዶላር ገቢ ለማስገባት ሲሆን፣ የተገኘው ግን 3.9 ሚሊዮን ዶላር ነው ተብሏል።
‹‹በኬንያ በኩል እስካሁን ምንም ችግር የለም፣ የዓመት ዕቅዳችንም አነስተኛ ነው። የተጠየቀው ክፍያም ለሙከራ ጊዜ ለሄደው የኤሌክትሪክ ኃይል ስለሆነ ብዙም አይደለም፤›› ሲሉ የተናገሩት አቶ ሞገስ፣ ከአከፋፈል ጋር በተያያዘ ችግር እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪ ከጂቡቲ በኩል እስካሁን የክፍያ ችግር እንደሌለ አስረድተዋል።
ከሦስቱ አገሮች በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለበርካታ የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ለመላክ ዕቅድ ይዛ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን፣ ከደቡብ ሱዳን ጋርም የመግባቢያ ሰነድ መፈራረሟ ይታወሳል።