Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የደመወዝ መጠን የሚወስን ቦርድ እንዲቋቋም ትኩረት አልተሰጠም ተባለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን የሚወስን ቦርድ እንዲቋቋም ትኩረት እንዳልተሰጠ፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አስታወቀ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤትና ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ቦርዱን የማቋቋም ሒደት ምን ደረጃ እንደደረሰ በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ምንም ዓይነት ምላሽ እንዳላገኙ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ዝቅተኛ የደመወዝ መጠን የሚወስነውን ቦርድ ለማቋቋም የተደረሰበትን ሒደት ለማወቅ ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ደብዳቤ መጠየቃቸውን አቶ ካሳሁን ገልጸው፣ በተለያዩ መንገዶች ምላሽ ቢጠብቁም ምንም ዓይነት ምላሽ አልተገኘም ብለዋል፡፡

ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ትኩረት እንዲሰጠው ኮንፌዴሬሽኑ ደብዳቤ ቢጽፍም፣ ትኩረት ሰጥቶ ምላሽ የሚሰጥ አካል እንዳልተኘ ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፣ በኢትዮጵያ የኑሮ ሁኔታ ከ800 እስከ 1000 ብር በወር የሚያገኙ ሠራተኞች ለአንድ ወር ሕይወታቸውን ለማዝለቅ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ ጎዳና መውጣትና መለመን እንደቀራቸውም ፕሬዚዳንቱ አክለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የአሠሪና ሠራተኛ አማካሪ ቦርድ እንደነበረ ጠቁመው፣ በየጊዜው የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ አፈጻጸም እንደሚገመግም አስታውሰዋል፡፡

ከ2013 ዓ.ም. አጋማሽ በኋላ ቦርዱ ሥራ ማቆሙን ገልጸው፣ ሥራ ያቆመው ለምን እንደሆነ ምክንያቱም ግልጽ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡ በዚህም በመንግሥት፣ በአሠሪና በሠራተኛ መካከል በሦስትዮሽ የተፈጠሩ ክፍተቶች ላይ የመወያየትና ችግሮችን የመፍታት ሒደት ግንኙነት መቋረጡን አስረድተዋል፡፡

ቦርዱ ለምን ሥራ እንዳቆመ ለማወቅም በደብዳቤ ቢጠይቁም፣ ምላሽ የሚሰጥ አንድም አካል እንዳላገኙ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በአሠሪና ሠራተኛ የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ቦርዱ ያግዝ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፣ የሠራተኞችን የመኖር ያለመኖር ጥያቄ በተለያዩ መንገድ ለሚመለከታቸው አካላት ቢያቀርቡም፣ በውይይትና በደብዳቤ ምላሽ የሰጠ አካል የለም፡፡

ችግሩ ከአቅም በላይ በመሆኑ ለኮንፌዴሬሽን ምክር ቤት ለማቅረብ በሒደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ምንጮች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የአነስተኛ የደመወዝ ምጣኔ የሚወስነውን ቦርድ ለማቋቋም በድጋሚ ጥናት እየተደረገ ነው፡፡ ቦርዱን ለማቋቋምና በእያንዳንዱ ዜጋ ኪስ ውስጥ የሚገባውን ገንዘብ ለመወሰን፣ ሁሉንም ወገኖች ያሳተፈ ጥናት የሚያስፈልገው ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የቀረበው ሪፖርት ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ተልዕኮ አኳያ በሚገባ መቃኘት እንዳለበት መታመኑን የገለጹት ምንጮች፣ በድጋሚ እንዲታይ መወሰኑ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ውጪ ቀጣሪ ድርጅቶች ሠራተኞቻቸውን በተለያዩ መንገዶች ሊጠቅሙ በሚችሉበትና በተለይም በቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የገቡ ድርጅቶችንም ያማከለ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ጉዳዩ በድጋሚ መታየት አለበት ብለዋል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ጉዳዩ የደመወዝ ቦርድ መቋቋም ብቻ አለመሆኑን፣ በኢንዱስትሪና በሌሎች ቀጣሪ ድርጅቶች ሠራተኞችን ከደመወዝ በተጨማሪ ሊጠቅሙበት የሚችሉባቸው አሠራሮችን ለማበጀት በድጋሚ ማየቱ ጠቃሚ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ ቦርድ ከመቋቋሙ በፊት አካባቢያዊ ተኮር እንዲሆን፣ ሴክተሮችን ማለትም (ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት) ያማከለ ውሳኔ ለመወሰን በድጋሚ መታየት እንዳለበት በመታመኑ ሊዘገይ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ሁሉንም አካታች በሆነ መንገድ በድጋሚ መታየት ስላለበት፣ ሚኒስቴሩ በዘለቄታ ችግሮችን ሊቀርፍ በሚችል አግባብ በድጋሚ ጥናት ለማድረግ በሒደት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች