Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአሜሪካ መንግሥት ያወጣውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መግለጫ ‹‹ግጭት ቀስቃሽ›› ሲል መንግሥት አጣጣለው

የአሜሪካ መንግሥት ያወጣውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መግለጫ ‹‹ግጭት ቀስቃሽ›› ሲል መንግሥት አጣጣለው

ቀን:

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለሁለት ዓመታት ዘልቆ በተጠናቀቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ ‹‹የጦር ወንጀል ተፈጽሟል›› በሚል የሰጠውን መግለጫ ‹‹ጊዜውን ያልጠበቀ፣ ግጭት ቀስቃሽና የጅምላ ፍረጃ ነው›› ሲል መንግሥት አጣጣለው፡፡

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የነበራቸውን የሁለት ቀን ጉብኝት አጠናቀው የተመለሱት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፣ ሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተከትሎ የሰጡት መግለጫ፣ ‹‹የአንድ አካል ብቸኛ አቋም፣ ዋጋ የሌለውና የጥላቻ አቋም የያዘ ነው›› ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማክሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ብሊንከን በመግለጫቸው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አውዳሚ፣ ሕፃናት፣ ሴቶችና ወንዶች የተገደሉበት፣ እንዲሁም ሴቶችና ሕፃናት ለአሰቃቂ የፆታዊ ጥቃት የተጋለጡበት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቀዬአቸው በኃይል የተፈናቀሉበት፣ የተወሰኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በማንነታቸው ብቻ ለጥቃት ዒላማ የተዳረጉበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ሁሉ ሊከናወን የቻለው ታስቦበትና ተጠንቶበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም መሥሪያ ቤታቸው ሕግና እውነታዎችን በጥንቃቄ ከመረመረ በኋላ የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ወታደሮች፣ የትግራይ ክልል ታጣቂዎችና የአማራ ክልል ታጣቂዎች የጦር ወንጀል መፈጸማቸውን ማረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ታጣቂዎች ከሰብዓዊነት ያፈነገጡ የመብት ጥሰቶች ግድያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ፆታዊ ጥቃትና የመሳሰሉት ፈጽመዋል ብለዋል፡፡

የአማራ ልዩ ኃይል በሰብዓዊነት ላይ ያነጣጠረ የመብት ጥሰቶች መፈጸሙን የገለጹት ብሊንከን፣ በኃይል ማፈናቀልና ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋወር፣ እንዲሁም ብሔርን መሠረት ያደረገ ግድያ መፈጸሙን አስረድተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም የኢትዮጵያ መንግሥት ለውይይት ይፋ ያደረገውን የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ረቂቅ የውይይት ሰነድ አድንቀው፣ በውይይቱ የችግሩ ሰለባ የሆኑ አካላት ድምፃቸው የሚሰማበትና ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት፣ እንዲሁም ሕወሓት በጭፍጨፋ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ ይህ ተጠያቂነትን የማምጣትና ዕርቅ የመፍጠር ሒደት፣ በብሔርና በፖለቲካ ግጭት እየታወከች ያለችውን ኢትዮጵያን ካሰበችበት እንድትደርስ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው መግለጫው ወገንተኝነት የታየበት፣ ጊዜውን ያልጠበቀ፣ እንዲሁም ቁጣ ቀስቃሽ ነው ሲል ገልጾታል፡፡ በመግለጫው የቀረበው በጦርነቱ የተሳተፉ አካላትን ሚና በትክክለኛ ድርሻ ያልገለጸና አንድ አካልን ነፃ ለማውጣት የጣረ መሆኑን አብራርቶ፣ በጦርነቱ ተፈጸሙ የተባሉ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ አካላት ወንጀል ስለመፈጸማቸው የሚያሳይ ግልጽ መረጃ ቢኖርም፣ መግለጫው ግን ወገንተኝነት የታየበት ነው ብሎታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በመግለጫው እንዳስታወቀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ተዘጋጅቶ ለውይይት መቅረቡንና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ሥራ መጀመሩን፣ በዚህም ቀጣይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራዎችን እንደሚያካሂድ በተገለጸ፣ ማግሥት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ወቅቱን ያልጠበቀ መግለጫ አውጥቷል ብሏል፡፡

መግለጫው ቁጣ ቀስቃሽ መሆኑን ያብራራው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የአሜሪካ መንግሥት ያወጣው መግለጫ ምንም ዓይነት ዓላማ ባይኖረውም ፅንፍ የያዘና አንድን ማኅበረሰብ ከሌላው ጋር ሊያጋጭ የሚችል መሆኑን አብራርቷል፡፡

በመሆኑም መግለጫው ወገንተኛ፣ ከፋፋይና በሚገባ ያልተጠና መሆኑን አመላክቷል፡፡ የውጭ ጉዳይ በመግለጫው ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት እያከናወነች ባለችበት በዚህ ሰዓት ያልተመጣጠነ ወቀሳና ማረጋገጫ የሌለው መግለጫ የአሜሪካ መንግሥት ማውጣቱ፣ ኢትዮጵያ ለምታደርገው ሁሉን አቀፍ ሽግግር ሊያደርግ የሚችለውን ድጋፍ አደጋ ላይ ይጥለዋል ብሏል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሊንከን በቅርቡ ያደረጉት ጉብኝት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ያሻሽላል የሚል ተስፋ እንደነበር የሚያብራራው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረው ግልጽ ውይይት ምክንያት ከዚህ በፊት የነበረውን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ነበረበት ይመልሰዋል የሚል ተስፋ እንዳለ አብራርቷል፡፡

ኢትዮጵያ ገንቢ ለሆነ ዓላማ ድጋፍ የሚያደርጉ ወዳጆቿን እንደምትቀበል በመግለጽ፣ ሁሉንም ዓይነቶች ዕርምጃዎች በመውሰድ ተጠያቂነት ለማምጣት በሽግግር ፍትሕ ረቂቅ ፖሊሲው አገር አቀፍ ውይይት በማካሄድ፣ እንዲሁም ለተጎጂዎች የሚደረገው ፍትሐዊነት በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማካይነት ይረጋገጣል ብሏል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ በነበራቸው ጉብኝት ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚ  ሽን (ኢሰመኮ) ዋና ኮሚሸነር ዳንኤል (ዶ/ር) ጋር ያደረጉትን ውይይት አስመልክቶ ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር የነበረው ውይይት ‹‹አዎንታዊና ፍሬያማ›› መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ መግለጻቸውን አስታውሷል፡፡ በዚህም ውይይቱ በአገር አቀፍ ደረጃ ተጎጂዎችን ያማከለና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚታይበት የሽግግር ፍትሕ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊነትን ለመነጋገር ዕድል የፈጠረ መሆኑንም አስታውቋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...