Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት በግማሽ ዓመት 100 ቢሊዮን ብር ያህል ቀጥታ ብድር መውሰዱ ታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የአገር ውስጥ ብድር ከ1.6 ትሪሊዮን ብር በላይ ሆኗል
  • የብሔራዊ ባንክ ቦንድ ከ433 ቢሊዮን ብር በላይ ሆኗል

በዘንድሮ በጀት ዓመት የመጀመርያዎቹ ሁለት ሩብ ዓመታት ወይም ግማሽ ዓመት ውስጥ መንግሥት ወደ 100 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ፣ ከብሔራዊ ባንክ በቀጥታ ብድር (ገንዘብ በማተም) መውሰዱ ታወቀ፡፡

መንግሥት በ2015 በጀት ዓመት ሁለተኛው ሩብ ዓመት 40 ቢሊዮን ብር በቀጥታ ብድር የወሰደ ሲሆን፣ ይህም በመጀመርያው የሩብ ዓመት ከወሰደው 60 ቢሊዮን ብር ጋር በስድስት ወራት ውስጥ 100 ቢሊዮን ብር ቀጥታ ብድር (Direct Advance) መውሰዱን ያሳያል፡፡

በ2014 ዓ.ም. ሙሉ በጀት ዓመት መንግሥት የወሰደው የተጣራ ቀጥተኛ ብድር 76 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም በተያዘው ግማሽ ዓመት ብቻ የተሰጠው የቀጥታ ብድር መጠን ካለፈው ሙሉ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ32 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ያወጣው የሁለተኛው ሩብ ዓመት የብድር ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰው፣ የመጀመርያው ሩብ ዓመት ከተጠናቀቀ ከሰባት ቀናት በኋላ (ማለትም እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 7 ቀን 2022 ዓ.ም.) ለሦስት ዓመታት ሲንከባለል የመጣው አጠቃላይ 236.5 ቢሊዮን ብር መንግሥት በቀጥታ የወሰደው ብድር ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ መቀየሩ ተጠቅሷል፡፡

በዚህ ሒደት መንግሥት ያለበት አጠቃላይ የረዥም ጊዜ ቦንድ ዕዳ ወደ 433.9 ቢሊዮን ብር ማደጉን በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ መንግሥት እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ የወሰደው የ187.2 ቢሊዮን ብር የቀጥታ ብድር በ2012 በጀት ዓመት ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ ተቀይሮ ዕዳውን 199.2 ቢሊዮን ብር አድርሶት ነበር፡፡ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም. መንግሥት መጠነኛ ክፍያ ሲፈጽም ቆይቶ በ2014 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 197.9 ቢሊዮን ደርሶ ነበር፡፡

የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ቺፍ ኢኮኖሚስት አቶ ፈቃዱ ደግፌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቀጥታ ብድሩ ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ ተቀይሯል፡፡ ከሦስት ዓመታት በፊትም በተመሳሳይ ሁኔታ የተጠራቀመ የቀጥታ ብድር ወደ ረዥም ጊዜ ቦንድ መዞሩን አረጋግጠዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ ዘንድሮ ለመንግሥት የሰጠው ቀጥታ ብድር በፊት በዚህን ያህል ጊዜ ከሰጠው ትልቁ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደግፌ፣ ቀደም ብሎ የመንግሥት ወጪ ቀነስ ያለ እንደነበርና የወጪ መብዛት “በቅርብ ጊዜ በቀጥታ ብድር የሚውለውን ገንዘብ ከፍ እንዳደረገው” ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ወጪ ከፍ በማለቱ የቀጥታ ብድርን ጨምሮ በተለያዩ መንገዶች ገቢ እያገኘ እንደሆነ ምክትል ገዥው ጠቅሰዋል፡፡ “አሁን ወጪ ለመቀነስ እየሠሩ ነው፤” ያሉት አቶ ፈቃዱ የመንግሥትን የአገር ውስጥ ገቢ፣ ከውጭ የሚገኙ ብድሮችንና ዕርዳታዎችንም ለማሳደግ እየተደረገ ያለውን ጥረት ገልጸዋል፡፡ “ስለዚህ ከዚህ ዓመት በኋላ እየቀነሰ ይሄዳል ብለን እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት ለተያዘው በጀት ዓመት 786.6 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡ ይታወሳል፡፡ ከተመደበው በጀት ውስጥ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ የበጀት ጉድለት እንደሚከሰት ተይዞ የነበረ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የበጀት ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ፣ ይህንን የበጀት ጉድለት ለመሙላት የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭንና የቀጥታ ብድርን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮችን ሊጠቀሙ እንደሚችሉ ጠቁመው ነበር፡፡

ሆኖም የገንዘብ ሚኒስቴር ያለፈው ሳምንት ሪፖርት እንደሚጠቁመው፣ የባለፈው በጀት ዓመት ሲጠናቀቅ ተጠራቅሞ የነበረው የግምጃ ቤት ሰነድ ዕዳ 317.6 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ያለፉት ሁለት ሩብ ዓመታት ሲጠናቀቁ ግን ወደ 315.4 ቢሊዮን ብር ዝቅ ብሏል፡፡ ይህም የሆነው መንግሥት በግምጃ ቤት ሰነድ የተበደረውን ብድር እየከፈለ በመምጣቱ ነው፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢኮኖሚ አማካሪ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት ካሉት ሁሉ አማራጮች በዚህኛው ዓመት ሊጠቀም የሚችለው ይህንን የብሔራዊ ባንክ ቀጥታ ብድር ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ከውጭ ሊገኝ የሚችለውም ምንጭ ደርቋል፡፡ በአገር ውስጥ ያለውም ሌላው ምንጭ የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ በተቋማት ፍላጎት አለመኖር ሳይሳካ ቀርቷል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት የበጀት ጉድለቱን ለመምራት የሚችላቸውን አማራጮች እያጣ እንደሆነ ሲገባው፣ የመንግሥት ተቋማትን ወጪ እንዲቀንሱ እንደ ከፍተኛ መፍትሔ ዓይቶ ሲሠራ እንደነበር የተናገሩት ባለሙያው፣ ‹‹የገንዘብ ሚኒስቴር ለተቋማት የተፈቀደውን ወጪ ራሱ ሳይሰጥ ይይዝ እንደነበር ዓይተናል፤›› ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ ‹‹ቀጥተኛ ብድር በኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለው ጫና ከፍተኛ እንደሆ፣ የኑሮ ውድነትንም አሁን ካለው የባሰ ቢያደርገው እንኳን እንዳይቀንስ ያደርገዋል፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

በአጠቃላይ መንግሥት ያለበት የአገር ውስጥ ብድር ያለፈው በጀት ዓመት ሲጠናቀቅ ከነበረው 1.53 ትሪሊዮን ብር የአሥር በመቶ ዕድገት በማሳየት፣ በዚህኛው ግማሽ ዓመት 1.68 ትሪሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በዶላር መጠን ሲለካም 29.4 ቢሊዮን ዶላር የነበረው ነው ወደ 31.5 ቢሊዮን ዶላር አድጓል፡፡

በአሁኑ ጊዜ መንግሥት ካለበት 1.68 ትሪሊዮን ብር የአገር ውስጥ ዕዳ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች 41 በመቶን ሲሸፍን፣ ማዕከላዊ መንግሥት ደግሞ 59 በመቶውን ይይዛል፡፡

ሪፖርቱ እንደሚገልጸው በግማሽ ዓመቱ የውጭ ብድር  27.8 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ ባለፈው በጀት ዓመት መጨረሻ ላይም በተቀራራቢ 27.9 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ከአጠቃላይ የውጭ ብድር 69.3 በመቶው በማዕከላዊ መንግሥት የተወሰደ ሲሆን፣ ቀሪው ደግሞ በመንግሥት ዋስትናና ያለ መንግሥት ዋስትና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የወሰዱት ነው፡፡

ዓመቱ በተጀመረ በመጀመርያዎቹ ስድስት ወራት የ641.8 ሚሊዮን ዶላር አዳዲስ ብድሮች ውል የተፈጸመ ሲሆን፣ ወደ መንግሥት ካዝና በዚህ ጊዜ የመጣው ደግሞ 543 ሚሊዮን ዶላር ነው፡: በግማሽ ዓመቱ መንግሥት ለተበዳሪዎች ዋና ብድርንና ወለድን ጨምሮ 974 ሚሊዮን ዶላር መክፈሉ ታውቋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች