Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየበይነ መረብ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች መቋረጥ የጎዳቸው ተማሪዎች

የበይነ መረብ ማኅበራዊ ትስስር ገጾች መቋረጥ የጎዳቸው ተማሪዎች

ቀን:

  • የታተሙ የመማሪያ መጻሕፍት ለሁሉም ተማሪዎች አልተዳረሰም

በዓለም ላይ እንደ ፌስቡክ፣ ቴሌግራም፣ ቲክቶክ፣ ዩቲዩብና ሌሎች ማኅበራዊ ትስስር ገጾች ውስጥ ገብቶ መረጃ መፈለግ ከወጣቱ የዕለት ከዕለት ሕይወት የማይለይ ሆኗል፡፡ በተለይም የበይነ መረብ (ኢንተርኔት) አቅርቦቱ ይበልጥ በተስፋፋባቸው አገሮች አብዛኛው አገልግሎት የሚሰጠው በይነ መረብ ባማከለ መልኩ ነው፡፡ ሆኖም በዚሁ መስመር የሚደረግ ማናቸውም ግንኙነት በርካታ በጎ ጎኖች እንዳሉት ሁሉ መጥፎ ጎኖችም አሉት፡፡

አሁኑ ዘመኑ የደረሰበትን የበይነ መረብ ግንኙነት በመጠቀም ማንኛውም ሰው የፈለገውን መረጃ በፈለገው ሰዓት ካለበት ሆኖ ያገኛል፡፡ በዚህም የተነሳ ከመደበኛ መገናኛ ብዙኃን ይልቅ የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታዮች ቁጥር ከፍተኛ ሆኗል፡፡ በተለይ ስማርት ስልክ ከተሠራ ወዲህ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር እጅ ከፍ ማለቱንና ለዲጂታል ቴክኖሎጂው ዕድገት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

ይህንንም ተከትሎ በቅርቡ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንተርኔት በመቋረጡ የተነሳ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳደረ ሲሆን፣ ነጋዴዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶችና ሌሎች የበይነ መረብ ተጠቃሚዎች ችግር ገጥሟቸዋል፡፡ ነገር ግን ቪፒኤን (Virtual Private Net Work (VPN)) እና ሲፎን (PSIPhon) የተባሉ መተግበሪያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋሉ ነው፡፡ አገልግሎቱን ለመጠቀም ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ገንዘብ ቢያስወጣም አማራጭ ሆኗል፡፡

የበይነ መረብ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ግንኙነት መቋረጥን ተከትሎ ችግር ውስጥ ከገቡት መካከል ተማሪዎች ይገኙበታል፡፡ ወ/ሮ ፎዚያ መሐመድ ሁለት ልጆቻቸውን ሳውዝ ዌስት አካዴሚ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ እያስተማሩ ይገኛሉ፡፡   

በአሁኑ ወቅት የሚያስተምሯቸው ሁለቱ ልጆቻቸው የአምስተኛና የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች መሆናቸውን፣ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ልጃቸው ዘንድሮ ሚኒስትሪ ተፈታኝ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ልጆቻቸው የሚማሩበት ትምህርት ቤት ለመማሪያነት የሚሆን መጽሐፍ እጥረት ስላለበት አብዛኛው የትምህርት ዓይነት በቴሌግራም ላይ ተልኮላቸው እንደሚማሩ ያስረዳሉ፡፡

በቴሌግራም የሚላክላቸው መጽሐፎች ገጻቸው ረዥም በመሆኑ የተነሳ አንብበው ለመረዳት እንደሚከብዳቸው፣ በተለይም ከወር በፊት ጀምሮ ኢንተርኔት በመቋረጡ ምክንያት የፈለጉትን የትምህርት ዓይነት ከበይነ መረብ አውርደው ለልጆቻቸው ማቅረብ እንዳልቻሉ ሚኒስትሪ ተፈታኝ የሆነው ልጃቸው መቸገሩንም ያስረዳሉ፡፡

በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች ላይ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጀው የስምንተኛና የስድስተኛ ክፍል መማርያ መጻሕፍት ተደራሽ አለመሆኑን፣ አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ሶፍት ኮፒ በቴሌግራም ለወላጆች በመላክ የመማር ማስተማር ሒደቱን እንደሚጠቀሙ ገልጸዋል፡፡

በስድስተኛና በስምንተኛ የሚኒስትሪ ተፈታኝ ስለሆኑ ለማሳያነት ተነሳ እንጂ በሌሎችም ክፍሎች ቢሆን የታተሙ መጻሕፍት አልተዳረሱም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መጻሕፍት እየታተሙ ነው ብሎ ከገለጸ ሰባተኛ ወሩን ቢያስቆጥርም፣ በሶፍት ኮፒ ካደለው ውጪ መጽሐፉ አልተገኘም፡፡ ከዚህ ቀደም መንግሥት የሚያሳትመው የመማሪያ መጻሕፍት እጥረት ሲኖር፣ በተለይ በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ወላጆች መጻሕፍቱን ከገበያ የሚያገኙበት ዕድል የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ይህ የለም፡፡ አጋዥ ተብለው የሚዘጋጁ መጻሕፍትም ቢሆኑ በቀደመው ሥርዓተ ትምህርት የተዘጋጁ እንጂ በአዲሱ መሠረት የተቀናበሩ አይደሉም፡፡

በተለይ በክልል ትምህርት ቤቶች ችግሩ ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት እኚህ እናት፣ መንግሥት ቀደም ብሎ ምቹ ሁኔታዎችን ቢፈጥር ኖሮ በርካታ ተማሪዎች መጉላላት አይደርስባቸውም ነበር ይላሉ፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ የመጣው የተማሪ መማሪያ መጻሕፍትንና ትምህርቶችን በቴሌግራም መላክ፣ በወቅቱ ለነበረው ችግር መፍትሔ ሆኖ ቢያገለግልም ዛሬ ግን ችግር እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ኢንተርኔት ሲቋረጥ ከትምህርት በዘለለ ሌሎች ተቋማትም ችግር ውስጥ እንደሚወድቁ ከግምት በማስገባት፣ መንግሥት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የግል ትምህርት ቤቶች ኢንተርኔት ተኮር ያደረገ አሠራር እንደዘረጉ፣ ሁለቱም ልጆቻቸው የግል ትምህርት ቤት በመማራቸው የቴክኖሎጂ ዕውቀት ማዳበራቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይም በመጋቢት 28 የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንድ ልጃቸውን የሚያስተምሩት ወ/ሮ እጅጋየሁ ሲሳይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተቋረጠው ኢንተርኔት ምክንያት ስምንተኛ ክፍል የሚማረው ልጃቸው ችግር ውስጥ ወድቋል፡፡

መንግሥት የትምህርት ሥርዓቱን ከቀየረበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ የትምህርት ዓይነቶችን በሶፍት ኮፒ ቴሌግራም ላይ እንደሚላክለት ገልጸዋል፡፡

በቴሌግራም የተላከለትንም መጽሐፍ አውርደው ለማንበብ ኢንተርኔት እንደሚያስፈልግ፣ ይህንን ተፈጻሚ ለማድረግ ብዙ ውጣ ወረዶችን እያዩ መሆኑን ወ/ሮ እጅጋየሁ ተናግረዋል፡፡ መጻሕፍቱ በምዕራፍ ተከፋፍለው የሚላኩ መሆኑና ተጠቃሎ አለመገኘቱ ሌላው ችግር እንደሆነም አክለዋል፡፡

የኢንተርኔት አገልግሎቱን ለመጠቀም ሌሎች መንገዶች መጠቀሙ ችግሩን ይበልጥ እንዳባባሰው፣ ልጃቸውም ስምንተኛ ክፍል ተፈታኝ በመሆኑ የግድ በየወሩ ለኢንተርኔት የሚሆን ካርድ በመግዛት ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጡ አስረድተዋል፡፡

በአብዛኛዎቹ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች መጻሕፍት ተደራሽ አለመሆናቸው፣ ከዚህ ቀደምም ልጃቸውን ሲያስተምሩ እንዲህ ዓይነት ችግር ገጥሟቸው እንደማያውቅ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ከሁሉም በላይ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ወገኖች ከኑሮ ውድነት ጋር ተደማምሮ ልጆቻቸውን ለማሳደግ እንደከበዳቸው፣ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ደግሞ ከዚህ በፊት ለቅንጦት እንጂ ለሌላ ነገር ሲውል አይተው እንደማያውቁ አብራርተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አበበ ቸርነት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት የተቋረጠው ከፊል የኢንተርኔት አገልግሎት የትምህርት ዘርፍ ላይ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ አይፈጥርም፡፡

በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማርያ መጻሕፍት ተደራሽ መሆኑን፣ በቅርቡም የሚሰጠውን የሚኒስትሪና የማትሪክ ፈተና ወሳጅ ተማሪዎች ለፈተና በተገቢው መንገድ መዘጋጀት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

ከመማርያ መጻሕፍት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ቅሬታ ብዙም እንደሌለ፣ በአብዛኛው በትምህርት ቤቶች ያልተደረሱ መጻሕፍትን ትምህርት ቤቶች በሶፍት ኮፒ በማዘጋጀት ተማሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እያደረጉ መሆኑን አክለዋል፡፡

የስምንተኛና የስድስተኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ ተፈታኞች የተማሩት ትምህርት ብቻ በፈተና እንደሚቀርብላቸው፣ ምናልባትም አጋዥ የሆኑ መጻሕፍትን ለማግኘት ኢንተርኔት ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር አንዳንድ የንግድ ተቋማትንና ግለሰቦችን ባነጋገረበት ወቅት፣ በኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፊል በተቋረጠው የኢንተርኔት አገልግሎት ምክንያት የንግድ ተቋማትና ግለሰቦች በሥራቸው ላይ ጫና መፍጠሩን ተገንዝቧል፡፡

በኢንተርኔት ግንኙነት ላይ የተጣለው ገደብ የመገናኛ ብዙኃን ሥራቸውን በአግባቡ ለሕዝብ ተደራሽ እንዳያደርጉ እንቅፋት በመሆኑም፣ ገደቡ ሊነሳ ይገባል ሲል፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...