Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የውጭ ሕክምና ጉዞ ሒደት ላይ የሚስተዋሉ ብዥታዎች

በኢትዮጵያ ከተሞች በተለይ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሕክምናቸውን በውጭ አገር እንዲያደርጉ በቦርድ ተወሰኖላቸው እጃቸውን ለዕርዳታ የሚዘረጉ በርካታ ዜጎችን መመልከት የተለመደ ነው፡፡ በሌላ በኩል የገንዘብ አቅም ኖሯቸው ሕክምናቸውን በውጭ አገር ለማድረግ የተሰናዱም አሉ፡፡ በአንፃሩ ሁለቱም ታካሚዎች ከገንዘብ ባሻገር ሕክምናቸውን እንዴትና የት አገር ማከናወን እንደሚገባቸው ለማወቅ የተለያዩ መንገዶችን ይከተላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ታካሚዎች ሕክምና የሚያገኙበትን መንገድ የማማከር ሥራ የሚሠሩ ሕጋዊ ፈቃድ ያላቸው ድርጅቶች ቢኖሩም፣ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ታካሚን ወደ ውጭ አገር እንወስዳለን በሚል የሚያጭበረብሩ እንዳሉም ይነገራል፡፡ ይህም ወደ ውጭ አገር አቅንቶ ለመታከም የተሰናዳን ታካሚ ላይ ብዥታ መፍጠሩን ተከትሎ ማኅበረሰቡ እንዲጠራጠር ማድረጉም ይወሳል፡፡ በዚህም ምክንያት ሕጋዊውን መንገድ ተከትለው በሚሠሩ ተቋማት ላይ እንቅፋት መፍጠሩም ይገለጻል፡፡ በውጭ የሕክምና ጉዞ የማማከር ሥራ ሕጋዊ ፈቃድ ኖሮት ከሰባት ዓመታት በላይ የተሻገረው ጌትዌል ሜዲካል የጉዞ ተቋም፣ በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ አራት ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር በአገር ውስጥ ሕክምና ማግኘት ላልቻሉ በርካታ ታካሚዎች የማማከር አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ የተቋሙን እንቅስቃሴዎችን በተመለከት ከጌት ዌል ሜዲካል የጉዞ ተቋም ሥራ አስኪያጅና የማርኬቲንግ ተወካይ ሱራፌል ዘውዴ (ዶ/ር) ጋር ዳዊት ቶሎሳ ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ጌት ዌል ሜዲካል የጉዞ ተቋም የሚሰጠው የሕክምናና የማማከር ሥራ ምን ይመስላል?

ሱራፌል (ዶ/ር)፡- ጌት ዌል ሜዲካል የጉዞ ተቋም ማንኛውም የውጭ ሕክምና ፈልጎ ለመጣ ታካሚ የተሻለ ሕክምና እንዲያገኝ፣ እንዲሁም ታካሚው ከጉዞ አስቀድሞ ስለሕክምናው ቀድሞ መረጃ እንዲኖረው ይሠራል፡፡ ተቋሙ በተለያዩ በውጭ አገር ከሚገኙ የተለያዩ ሆስፒታሎች ጋር የሕክምና ሪፖርት እየተለዋወጠ፣ ታካሚዎች የሚኖራቸውን የሕክምና አማራጭ ተመልክቶ ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያደርግ ተቋም ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ የጌት ዌል ሕክምና አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር ለኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ዕድል ያመቻቻል፡፡

ሪፖርተር፡– ጌትዌል ሜዲካል ምን ዓይነት የሕክምና ጉዳዮችን ያስፈጽማል?

ሱራፌል (ዶ/ር)፡- አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች የውጭ አገር ሕክምና ሲፈልጉ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን ሕክምናው በአገር ውስጥ የማይቻል ከሆነና በአገር ውስጥ በሌለ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያ የሚፈታ ሲሆን ታካሚዎች ወደ እኛ ይመጣሉ፡፡ በዚህም መሠረት ጌትዌል ታካሚዎች ያጋጠማቸውን የጤና እክል በመረዳት እንዴትና ወዴት አገር አቅንተው መታከም እንደሚገባቸው እንዲሁም የትኛውን አማራጭ መከተል እንደሚገባቸው ያማክራል፡፡ ታካሚዎች ወደ እኛ ተቋም ሲመጡ የሕመማቸውን ሪፖርት በመመልከት የት ክትትል ማድረግ እንደሚገባቸው ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ የአንዳንድ ታካሚዎች ጉዳይ ከአገር ውጭ ብቻ ላይፈታ ይችላል፡፡ በዚህም መሠረት የሕክምና ሪፖርቱን ከተመለከትን በኋላ፣ ሕክምናው በአገር ውስጥ ሊሰጥ የሚችል ከሆነ በአገር ውስጥ እንዲፈታ እናደርጋለን፡፡ በማማከር ሒደት በቀዳሚነት የምንከተለው ሕክምናው ከውጭ አገር ይልቅ በአገር ውስጥ የሚፈታ ከሆነ ከተጨማሪ ወጪ እንዲድን ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ሕክምናው የግድ በውጭ አገር ብቻ የሚፈታ መሆኑን ካረጋገጥን፣ የሕክምና ዶክመንታቸውን በመያዝ ስለበሽታው ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ የሕክምና አማራጮችን እናቀርባለን፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ታካሚ ሕክምናው የግድ በውጭ አገር ብቻ እንደሆነ የማረጋገጥ ሒደትና አገልግሎቶቹ ምንድን ናቸው?

ሱራፌል (ዶ/ር)፡- የአንድ ታካሚ ሕክምና የግድ በውጭ አገር ብቻ የሚሰጥ መሆኑን ለማረጋገጥ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ አጋር ሆስፒታሎች የሕክምና ሪፖርቶችን አቅርበን የምናገኘውን ምላሽ ከተመለከትን በኋላ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ እንሸጋገራለን፡፡ ይኼም ታካሚዎች ወደ ውጭ አምርተው ሕክምናውን ለማድረግ ፈቃደኞች በሚሆኑበት ጊዜ በሕክምና ጉዞ ላይ የሚያስፈልጉ ተጓዳኝ አገልግሎቶች እንዲያገኙ ይደርጋል፡፡ በዚህም መሠረት የቪዛ ሒደት እንዲሟላ ማድረግ፣ ለሕክምና በሚያቀኑበት አገር ማረፊያቸውን ማሰናዳት፣ ባረፉበት አገር ክትትል የሚያደርግላቸው የዚያው አገር ሰው ማሰናዳት፣ ሕክምናቸው በተሳለጠ መንገድ እንዲከናወን ክትትል ማድረግና እንዲሁም ታካሚው በሰላም ወደ አገሩ እንዲመለስ የማድረግ አገልግሎቶችን እንሰጣለን፡፡ ታካሚው ወደ አገር ከተመለሰ በኋላ የጤናውን የዕለት ተዕለት ሁኔታ ክትትል እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡ ታካሚዎች የሚፈልጉትን የሕክምና አገልግሎት በሙሉ እምነት ማግኘት እንዲችሉ ምን ዓይነት መንገድ ትከተላላችሁ?

ሱራፌል (ዶ/ር)፡- ጌትዌል በተለያዩ አገሮች በሕክምናው ዘርፍ የሚሠሩትን ተቋማትን ሲመርጥ ያስቀመጣቸው መሥፈርቶች አሉ፡፡ ይህም ከሕክምና ጥራት፣ ከዋጋ አንፃር እንዲሁም የታካሚዎችን ፍላጎት ያማከለ መሆኑን በማረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ዓለም አገሮች የሚገኙ የሕክምና ተቋሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰጣቸው ደረጃ አለ፡፡ ስለዚህ እኛ በትብብር አብረን የምንሠራቸው የብቃት (JCI Accreditation) ደረጃ የተሰጣቸውን የሕክምና ተቋሞች በመለየት ነው፡፡ ሆስፒታሎችን ከለየን በኋላ ወደሚገኙበት አገር አቅንተን የሚሰጡትን የሕክምና አገልግሎት በደንብ ከገመገምን በኋላ በጋራ እንሠራለን፡፡ በዚህም መሠረት በህንድ፣ በቱርክ፣ በዱባይና በታይላንድ ከሚገኙ ሆስፒታሎች ጋር ተባብረን እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- በብዛት በውጭ አገር ሕክምና እንዲያገኙ የቦርድ ውሳኔ የሚያገኙ ጉዳዮች የትኛዎቹ ናቸው?

ሱራፌል (ዶ/ር)፡- የተለያዩ ታካሚዎች የተለያዩ ሕክምና እክል ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ከእነዚህም መካከል በተለይ የተለያዩ የካንሰር ሕመሞች፣ የኩላሊት ንቅለ ተከላ፣ የልብ ቀዶ ሕክምና የጭንቅላት ቆዳ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ከሥነ ተዋልዶ ጋር የተያያዘ ልጅን በመፈለግ፣ የተለያዩ የአጥንት ሕመሞች እንዲሁም አጠቃላይ የሕክምና ሁኔታቸውን ለማወቅ ፍላጎት ያላቸው ታካሚዎች ይመጣሉ፡፡ የሁሉም ታካሚ የሕመም ደረጃ በተለያየ ደረጃ ላይ ስለሚገኝ ሙሉ በሙሉ አገግመው የሚመለሱ እንዲሁም ካሉበት የሕመም ደረጃ ተሻሽለው የሚመለሱም አሉ፡፡ ሙሉ በሙሉ ያገገሙ እንዳሉም ሕክምናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በአገር ውስጥ የሕክምና ባለሙያዎች ክትትል የሚደረግላቸው ታካሚዎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በውጭ አገር ሕክምና ከማድረግ ጋር ተያይዞ፣ በዋናነት የገንዘብና የታማኝነት ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይኼን ጉዳይ እንዴት ትመለከቱታላችሁ?

ሱራፌል (ዶ/ር)፡- ይህንን ጥያቄ በሁለት መንገድ መመልከት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው በአሁን ጊዜ የውጭ አገር ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ሕጋዊ ፈቃድ አውጥተው የሚሠሩ ተቋማት እየተበራከቱ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሕጋዊ ሆነው አገልግሎቱን የሚሰጡ ተቋሞች አልነበሩም፡፡ ታካሚዎችም በሰው በሰው መረጃ እየተቀበሉ ስለሚሄዱበት አገር በቂ መረጃ ሳይኖራቸው፣ ለከፍተኛ ወጪ የተዳረጉበት አጋጣሚ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ኅብረተሰቡ የተዛባ መረጃ እንዲኖረው አስችሏል፡፡ ሌላው ታካሚዎች የውጭ ሕክምና ለማግኘት ወደ እኛ ተቋም ሲመጡ ይዘው የሚመጡት የሕክምና ዶክመንት እውነተኛነትን የምናረጋግጥበት መንገድ አለ፡፡ ከዚህም ባሻገር የምንመርጣቸው የውጭ አገር ሆስፒታሎች ጠንካራ ግንኙነት በማድረግ በታካሚው ዘንድ ያለውን ችግር በተጨባጭ መረጃ እንፈታለን፡፡ ከገንዘብ ጋር ተያይዞ ትልቁ ችግር ታካሚው የሚፈልገውን የውጭ ምንዛሪ አለማግኘቱ ነው፡፡ አንድ ታካሚ ሕክምናውን በአገር ውስጥ እንደማያገኝ በቦርድ ከተወሰነለት በኋላ፣ ከብሔራዊ ባንክ ምንዛሪ እንዲያገኝ ፈቃድ ያገኛል፡፡ በአንፃሩ ከብሔራዊ ባንክ ምንዛሪ እንዲያገኙ የማይፈቀድላቸው ታካሚዎች ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ያለው የሕክምና ሒደት ምን ይመስላል?

ሱራፌል (ዶ/ር)፡- የዘመኑ የሕክምና ሒደት እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ የኢትዮጵያም የሕክምና ደረጃ በመጠኑም ቢሆን እያደገ ነው፡፡ በአንፃሩ በኢትዮጵያ ያለው የታካሚዎች ቁጥርና ሕክምና የሚሰጡ ሆስፒታሎች ቁጥር መጠን ተመጣጣኝ አይደለም፡፡ ለአብዛኛው ማኅበረሰብ መዳረስ የሚችል የሕክምና ሒደት ማግኘት አልተቻለም፡፡ ጥራትና ብቃት ያላቸው የሕክምና ባለሙያዎች ፈርተዋል፡፡ ዘመናዊ የሆኑ የሕክምና መሣሪያዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ከማኅበረሰቡ ፍላጎት ጋር ተመጣጣኝ መሆን አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሳ ሰዎች ወደ ውጭ አገር አምርተው የመታከም ልምድ እያዳበሩ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዘርፉ እያጋጠማችሁ ያለውን ችግር ቢያነሱልን?

ሱራፌል (ዶ/ር)፡- ትልቁ እንቅፋት የሆነብን ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ታካሚዎችን የሚያጭበረብሩ፣ ታካሚዎችን ወስደው የሚያጉላሉ ተቋማት መኖራቸው ነው፡፡ ይህም በኅብረተሰቡ ውስጥ ጥርጣሬን እንዲፈጥር አስችሎታል፡፡ ይኼ እንደ ችግር እየፈተነን ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ችግር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሲሆን ይኼም ታካሚው የሚያስፈልገውን ሕክምና በአግባቡ እንዳያገኝ ያደርገዋል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በተቃርኖዎች መሀል የሚዋልለው የብልፅግና መንግሥት

ርዕዮተ ዓለም እንኳ የሌለው ይሉታል የሚቃወሙት ወገኖች፡፡ እሱ ግን...

አማራ ኢንሹራንስ ኩባንያን በሁለት ቢሊዮን ብር ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

አማራ ኢንሹራንስ ኩባንያ በሁለት ቢሊዮን ብር ካፒታል ሊቋቋም መሆኑ...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...