Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየኢትዮጵያን የቡና ሥርዓት በዩኔስኮ የማስመዝገብ ውጥን

የኢትዮጵያን የቡና ሥርዓት በዩኔስኮ የማስመዝገብ ውጥን

ቀን:

የኢትዮጵያን ባህልና እሴት ከሚያንፀባርቁት መካከል የቡና ማፍላት ሥነ ሥርዓት አንዱ መሆኑ ይታመናል፡፡ አገራዊው የቡና ባህል የራሱን ቀለም ጠብቆ እስካሁን የቆየበት ምክንያት የቡና ምርቱ ብቻ ሳይሆን፣ የተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍ በማለቱ የተነሳ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ማኅበራዊ እሴቱ የጎላ የ‹‹ኑና ጠጡ!›› ጥሪም የኢትዮጵያዊነት መገለጫ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

በተለይ በኢትዮጵያ ቡና የሚያነቃቃ ትኩስ መጠጥ ብቻ ሳይሆን፣ ጎረቤት ከጎረቤት የሚቀራረብበት፣ ቤተሰብ የሚሰበሰብበት፣ የዕለት ከዕለት ባህል እንደሆነ ይነገራል፡፡ የቡና ባህሉ ወጥ ሆኖ እንዲቀጥል ዋርካ ኮፊ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ከአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ሰዎች የተሳተፉበት የቡና ማፍላት ፌስቲቫል ቅዳሜ መጋቢት 9 ቀን 2015 ዓ.ም.  በስካይ ላይት ሆቴል አካሂዷል፡፡ በፌስቲቫሉ ላይም የቡና አፈላል ሥርዓትን ካቀረቡት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡  

ሲዳማ

ሲዳማ ቡናን ከሚያመርቱ ክልሎች አንዱ ነው፡፡ በተለይም በሲዳማ የሚኖር አርሶ አደር ቡናና እንሰት ከጓሮ ከሌለው የአብራክ ክፋዩን የማግኘት አጋጣሚው ጠባብ ነው ይባላል፡፡

በዚህም የተነሳ የሲዳማ ደጅን የረገጠ ሰው ቡና ሳይጠጣ መሄድ አይችልም፡፡ በሲዳማ በተለምዶ ቁርስህን ወይም ምሳህን ብላ ሳይሆን ቡና ጠጣ ነው የሚባለው፡፡ ሲዳማ ውስጥ ቡና ሲፈላ እርስ በርስ የተጣሉ ሰዎች የሚታረቁበት፣ የደቦ ሥራ የሚሠራበት፣ ሴቶች የራሳቸውን ሥራ የሚሠሩበት ጭምር ነው፡፡

ቡና ሲፈላ እንደ ቡና ቁርስ የሚቀርበው ከእንሰትና ከቆጮ የሚሠራ ‹ኦሞልቾ› የተባለ ምግብ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ቆጮ፣ ቦሎቄ፣ ቂጣና ሌሎች ምግቦችም ይቀርባሉ፡፡ በተለይ በጎሳ መካከል ግጭት ካለ ‹‹አፊኒ›› በተባለ የሽምግልና ሥርዓት የሚፈታው ቡና በማፍላት ነው፡፡ ጎመን፣ ቦሎቄ መልቀምና ሌሎች የድግስ ሥራዎች ሲኖሩ ጎረቤቶች እርስ በርስ ተጠራርተው ቡና በማፍላት ሥራውን ያከናውናሉ፡፡ የቡና አፈላሉ ከጥንት ጀምሮ የነበረውን ባህላዊ ሥርዓቱን ጠብቆ የሚደረግ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ነዋሪዎችም ቡና የሚጠጡት በቅቤና በወተት ነው፡፡

ኦሮሚያ

በኦሮሚያ ክልል አብዛኛውን ጊዜ ቡና የሚጠጣው በቅቤ መሆኑ ነው፡፡ በትልቅ ጀበና የሚፈላውን ቡና ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ ጎረቤቶች ተጠራርተው ይቋደሳሉ፡፡ በተለይ የተቀቀለ ድንች፣ ቂጣ፣ በቅቤ የታሸ ቆሎና ሌሎች ምግቦች እንደ ቡና ቁርስ ይቀርባሉ፡፡

በኦሮሚያ ቡና ሲፈላ እናቶች የቡና ሥርዓቱን የሚያደምቁት ወተት በመናጥ ቅቤ የሚያወጡ ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ ዳንቴልና ሌሎች ነገሮችን በመሥራት ነው፡፡

በሌላ በኩል የተጋጩ ሰዎች ዕርቅ የሚያወርዱበት ጭምር ነው፡፡ በተለይም የአንዱን ቤት ገመና ሌላው ሰው የሚሸፍንበትና ቁም ነገር አዘል ጨዋታዎች የሚተገበሩበት ቦታ ነው፡፡

አፋር

በአፋር ክልል ቡና ሲፈላ ወንዶችና ሴቶች በተለያየ ጎራ ተቀምጠው ነው የሚጠጡት፡፡ ቴምር፣ የበቆሎ ቆሎና ሌሎች ምግቦች እንደ ቡና ቁርስ ይቀርባሉ፡፡ ጎረቤት ከጎረቤት ተጠራርተው ቡና ሲጠጡም የእጅ ጥበብ ውጤቶችንም እየሠሩ ነው፡፡ የቡና አፈላል ሥርዓቱም በተለይም ከሁሉም ቦታ የተውጣጡ ሽማግሌዎች አንድ ቦታ ላይ ይሰባሰቡና የተጣሉ ሰዎችን ያስታርቁበታል፡፡

የዕርቅ ሥርዓቱም በሚፈጸምበት ወቅት ቡና ይፈላል፡፡ በሌላ በኩልም አንድ አራስ ወልዳ ሰባት ቀናት ሲሆናት ‹‹መልህ›› ይባላል፡፡ በዚህ ወቅትም ሴቶች ተሰባስበው ቡና አፍልተው ይጠጣሉ፡፡

ጉራጌ

በጉራጌ ቡና ሲፈላ የድሮ ባህላዊ ሥርዓቱን ጠብቆ ነው፡፡ ለአገልግሎት የሚጠቀሙት ቡና ጀንፈል ይባላል፡፡ በተለይ ከጥንት ጀምሮ የሚጠቀሟቸው ሲኒና ጀበና፣ ረከቦትና ዘነዘና የጉራጌ ባህልን የሚያንፀባርቁ ሲሆን፣ አተርና ቆጮም በጉራጌኛም (ጌታረህ) በሚባል ምግብ ለቡና ቁርስነት ይቀርባል፡፡

ሰዎች ተሰባስበው ቡናን ሲጠጡ ጅባ፣ ቃጫ ሌሎች ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ በአጋጣሚው ለወንዶች የተለየ ክብር የሚሰጥ ሲሆን፣ በርጩማ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ሴቶች ደግሞ በጅባነት የተሠራ ‹‹መስመሌ›› ላይ ቁጭ ይላሉ፡፡  

በጉራጌ ባህል ቡና ትልቅ ቦታ አለው፡፡ ሽማግሌዎች የተጣሉ ሰዎችን በማስታረቅ ዕርቅ የሚያወርዱበት፣ ሐሳባቸውን በነፃነት የሚገልጹበት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡

ሶማሌ

በሶማሌ ክልል ቡና የሚፈላው የቡና ገለባውን በመጠቀም ነው፡፡ የቡና ገለባውን በአግባቡ በመቁላት ቡና ይፈላል፡፡ ቡናው ከተፈላ በኋላ በወተት ወይም በባዶ ለሚፈልጉ ሰዎች እንደ ፍላጎታቸው ይቀርባል፡፡ ቴምር፣ ፈንዲሻና በእርጎ የሚበላ አንባብር፣ ባጊያና ሌሎች ምግቦች ለቡና ቁርስነት ይቀርባሉ፡፡

አብዛኛውን ጊዜ ቡና የሚፈላው ባህሉን በጠበቀ መልኩ ሲሆን፣ ሴቶችም የተለያዩ የእጅ ሥራ በመሥራት ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ የቡና ማዕድ ሲዘጋጅ ወንዶችም ሴቶችም በጋራ ቀርበው ሐሳባቸውን ይጋራሉ፡፡

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ

በቤኒሻንጉልና ጉሙዝ ቡና ሲፈላ ረከቦትን አይጠቀሙም፡፡ ቡና ከተፈላ በኋላ በርከት ያሉ ሲኒዎችን በመያዝ፣ ሽማግሌዎች ያሉበት ቦታ ድረስ ተሄዶ ይቀዳላቸዋል፡፡ የቡና ድግሱም ሲከናወን የከሰል ማንደጃ እንኳን አይጠቀሙም፡፡   

ከበፊት ጀምሮ ጉልቻዎችን በማዘጋጀት ቡናን የሚያፈሉ ሲሆን፣ የጀበና ማስቀመጫ ቁስ ሆኖ የሚያገለግለው ዕቃም ለሁለት ዓይነት አገልግሎት ይውላል፡፡ የጀበና ማስቀማጫው ቡናውን ለማዋሃድ ይጠቅማል፡፡ ቡና ሲያፈሉ ለየት ያለ ጭስ የሚጠቀሙ ሲሆን እሱም ‹ከበሬት› ይባላል፡፡ ይህም ጭሳጭስ ከእንጨትና ከሽቶ ይሠራል፡፡  

በአካባቢው ቡና ሲፈላ እናቶችና ሽማግሌዎች ይመርቃሉ፡፡ እናቶች ቡናው እየተፈላ ዳንቴል፣ ሰሌን (አርብሪሽ) እና ሌሎች ነገሮች ይሠራሉ፡፡ በቆሎ፣ ከማሽላ የተሠራ ቂጣና ሌሎች ምግቦችም ለቡና ቁርስነት ይቀርባሉ፡፡

አማራ

በአማራ ክልል ቡና ሲፈላ ጎረቤት ከጎረቤት ተጠራርተው ችግሮቻቸውን ይወያያሉ፡፡ በተለይም የተጣሉ ሰዎች ካሉ ሽማግሌዎች ያስታርቃሉ፡፡ ከበፊትም ጀምሮ ቡና ሲፈላ ከቀይ ጤፍ የሚሠራ አነባበሮ፣ ቆሎ፣ ኑግና አሹቅ የተሰኙ ምግቦች ለቡና ቁርስ ይቀርባሉ፡፡ ቡና ሲፈላ የተለያዩ ጭሳጭሶችን የሚደረግ ሲሆን፣ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ድረስ ቁጭ ብለው ይጠጣሉ፡፡ ቡናውን አፍልተው ጠጥተው እስኪጨርሱ ድረስ እንደየፊናቸው ዳንቴል መሥራት፣ ጥጥ መፍተልና ስፌት መስፋትን ይሠራሉ፡፡

ትግራይ

በትግራይ ክልል የቡና ማፍላት ሥርዓት ሲተገበር ቡና ለመጠጣት የሚመጡ ሰዎች የየራሳቸውን ሥራ ይሠራሉ፡፡ በተለይም እርስ በርስ በመወያየት ችግሮቻቸውን ይፈታሉ፡፡ በክልሉም ቡና ሲፈላ የተጣላ ሰው የሚታረቅበት ጭምር ሲሆን፣ ቆሎ፣ አምባሻና ሌሎች መሰል ምግቦች ለቡና ቁርስነት ይቀርባሉ፡፡

የቡና ፌስቲቫሉን አስመልክቶ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሒሩት ካሳው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ የብዙ ቡና ምርት ባለቤት ብትሆንም፣ እስካሁን ግን ምርቶቿን አስተዋውቃ ዩኔስኮ ላይ አለማስመዝገቧ ዘርፉ ላይ ችግር መኖሩን ያሳያል፡፡

በዓለም ላይ አብዛኛውን የቡና ምርት የሚያመርቱ አገሮች ቡናቸውን በማስተዋወቅ በዩኔስኮ ማስመዝገባቸውን ጠቅሰው፣ ይህንንም ተሞክሮ በመውሰድ ‹‹ቡናችንን ማስተዋወቅ ይኖርብናል፤›› ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቡና አፈላል ሥርዓት ከቦታ ቦታ የሚለያይ መሆኑን፣ ቡናም ሲፈላ  ማኅበራዊ ግንኙነታችን የምናጠናክርበት መንገድ ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡

ቡናን በቀን ሚሊዮኖች ፉት ሳይሉ አይውሉም፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በየቀኑ 2.25 ቢሊዮን ሲኒ ቡና በዓለም ላይ ይጠጣል፡፡ በዓለም አንደኛ ቡና አቅራቢ አገር ብራዚል ስትሆን፣ ለጥቃ ያለችው ቡናን ከሦስት አሠርታት በፊት ማምረት የጀመረችው አገር ቬትናም ነች፡፡ በቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ግን ቀዳሚዎቹን አራት አገሮች ትከተላለች፡፡

ቡና እያመረቱ ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ የመጀመርያዎቹ አሥር አገሮች ብራዚል፣ ቬትናም፣ ኮሎምቢያ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሆንዱራስ፣ ህንድ፣ ዑጋንዳ፣ ሜክሲኮና ጓቲማላ ናቸው፡፡ ቡና በከፍተኛ መጠን ከሚጠጣባቸው አገሮች ተርታ ደግሞ ፊንላንድ፣ ኖርዌይ፣ አይስላንድ፣ ዴንማርክ፣ ኔዘርላንድ፣ ስዊድን፣ ስዊዘርላንድ፣ ቤልጂየም፣ ሉክሰምበርግና ካናዳ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ ቡናን ለዓለም ያስተዋወቀችው ኢትዮጵያ በቡና ፍጆታ ከቀዳሚዎቹ ባትሆንም የቡና ሥርዓቷ ግን ልዩ ያደርጋታል፡፡

በቀጣይም ፌስቲቫሉን በየዓመቱ በማዘጋጀት ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ሰዎች ቡናቸውን እንዲያስተዋውቁ የሚደረግ መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...