በቶፊቅ ተማም
የዘንድሮው ረመዷን የፆም ወቅት ከመጋቢት 13 አሊያም 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ወር ምዕመኑ በፆምና በፀሎት የሚያሰልፈው ሲሆን፣ ምዕመኑም በርከት ያሉ በረከት የሚያስገኙ መልካም ነገሮች ይከውናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ፆም ማለት በእምነቱ አስተምህሮ መሠረት ሙዕሚኖች ፀባያቸውን የሚያንፁበትና የሚያስተካክሉበት ትልቅ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ይኸውም ከነፍስ ጋር የሚታገሉበት፣ ስሜትን ከሸይጣን ጉትጎታ የሚከላከሉበት፣ ሰው የሚጎዳበትን ኃይለኛነቱን ዋጥ አድርጎ ትዕግሥት ወደ ተላበሰ ሕይወት የሚመለሱበት፣ ሥርዓትና ደንብ የሚማሩበት፣ በልብ ውስጥ እዝነትና ሩህሩህነት የሚፀድቅበት፣ ሙስሊሞች እርስ በእርስ በመተዛዘን የሚተሳሰሩበትና የሚረዳዱበት ትልቅ ማዕከል ነው፡፡
ፆም ወደ አላህ ከሚቃረቡበት ከታላላቅ የኢባዳ ዓይነቶች አንዱ ነው፡፡ ሙዕሚኖች በፆም ከአላህ የሚያገኙት ምንዳ ወደርና ልክ የለውም፡፡ በመፆም ያለፉት ወንጀሎች ይማራሉ፡፡ በመፆም ፊት ከእሳት ይርቃል፡፡ ፆመኛች ልዩ ሆነው በጀነት በር ይገባሉ፡፡ ፆመኛ ፈጣሪውን ሲገናኝ ይደሰታል፡፡ አቡ ሁረይራ (ረ ዐ) ባወሩት ሀዲስ ረሱል (ሰ.አ.ወ.)፣ ‹‹አላህ የአደም ልጆች ሥራቸው ሁሉ ለራሳቸው ነው፣ ፆም ብቻ ሲቀር ፆም የኔ ነው፣ ምንዳውንም የምከፍለው እኔው ነኝ አለ፡፡ ፆም ጋሻ ነው፣ ከአንዳችሁ መሀል በሚያምንበት ቀን እንዳይረክስ እንዳይጮህ እንደ ማንኛውም አንዱ ቢሰድበው ወይም ቢጣሉ እኔ ፆመኛ ነኝ ይበል፡፡ የፆመኛ ሰው የአፉ ጠረን የቂያማ ቀን ከምስክ የተሻለ ይሆናል፡፡ ለፆመኛ ሰው ሁለት ደስታዎች አሉ፡፡ ደስታቸውም ፆመኛ ማታ ሲያፈጥርና በአሄራ ጌታውን ሲገናኝ ነው፡፡›› ቡሃሪ ሙስሊም እንደዘገቡት አቡ ሁረይራ ረዲያላሁ አንሁ ባወሩት ሀዲስ ረሱል (ሰ.አ.ወ.)፣ ‹‹የረመዳን ፆም ግዴታ መሆኑን አውቆ (በኢማን) ምንዳውን አገኝበታለሁ ብሎ የፆመ ሰው ያለፈውን ወንጀል ይማርለታል፡፡››
ሙስሊሞች በወርኃ ረመዳን ራሳቸውን ለሥነ ሥርዓት በማስገዛት ያሳልፋሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ በሰዎች ውስጥ የሚገኝን ስግብግብነት፣ የራስ ወዳድነት፣ የምቀኝነት፣ የተንኮል፣ የጠብ አጫሪነት፣ የሌሎችን መዝረፍና ሌሎች ፀያፍ ተግባራትን ራሱን በማንፃት ለፈጣሪ ራሱን ያስገዛል፡፡ ረመዳን በዋነኛነት ከማንኘውም ወር ሁሉ በተሻለ ራስን ለሥነ ሥርዓት በማስገዛት በሰላምና በመቻቻል ማለፍ ያለበት ወር መሆኑን የሃይማኖቱ አባቶች አበክረው ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ባለፈም በቅዱስ ቁርዓን አስተምህሮ መሠረት ምዕመኑ የዘር፣ የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የዜግነትና የቀለም ልዩነት ሳያደርግ ከሁሉም ኅብተተሰብ ጋር ታቻችሎ እንዲኖር ከፍ ባለ የእምነት ስሜት፣ በፍቅርና በመደጋገፍ የሰውን ታላቅነት ተቀብሎ አስፈላጊውን ክብር በመስጠት በዋነኛነት የተቸገሩትን በመርዳት እንዲያሳልፈውና ከፈጣሪ ጋር ያለው ግንኘነት እንዲያድስ ማድረግ ነው፡፡
ረመዷን አሏህን የመፍራት ወር
ረመዷን 11 ወር ሙሉ ስሜቱንና መጥፎ ምኞቱን ተከትሎ ለኖረ ሰው ሁሉ ልጓም፣ ለመልካም ሠሪዎች በረካ ሲሆን አዲስ የለውጥ ቤዛ ነው። ታዲያ ፆምን ፆም የሚያደርገው የምግብና የመጠጥ ተአቅቦ ብቻ ሳይሆን፣ አሏህ የከለከላቸውን ነገሮች ሁሉ በመከልከል ያዘዛቸውን ነገሮች በመታዘዝ መልካም ነገሮችን መሥራት ነው። ይህን ላደረገ ሰው ሲሳዩ በዱንያም በአሂራም ይሰፋል፡፡ እንከኖቹን አስወግዶ ራሱን በኢስላም ዲሲፕሊን በማነፅ የለውጥ ምሳሌ መሆን ይችላል። በረመዷን ወቅት ነብዩ( ሰ.ዐ.ወ.) ከሌላው ጊዜ በበለጠ በኢባዳ ይተጉ ነበር። ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! አሏህን ትፈሩ ዘንድ ፆም ከእናንተ በፊት በነበሩ ህዝቦች ላይ እንተደነገገው ሁሉ በእናንተም ላይ ተደነገገ።›› {አል-ቁርዓን 2፡183}፡፡
ረመዷን ለአሏህ ብለን የምንሠራቸውን ሥራዎች የምናድስበትና የበለጠ መልካም ሥራዎችን ለመሥራት ራሳችንን የምናነቃቃበት አመታዊ የሥልጠና ፕሮግራም ነው። ፆም ራስን መቆጣጠር ያዳብራል። እንዲሁም ራስ ወዳድነትን፣ ስግብግብነትን፣ ስስታምነትን፣ ስንፍናንና ሌሎች ስህተቶቻችንን ሁሉ እንድንቀርፍ ይረዳናል። ይህ የትዕግስት ወር ረሃብ ወይም ችግር ምን ማለት እንደሆነ የምናውቅበት ዕድል ሲሆን፣ ለድሆች ወይም ለምስኪኖች ያለንን አመለካከት በደግነት የተሞላ እንዲሆን ያደርጋል። እንዲሁም ፆም ለምቾትና ለድሎት ያለንን ውዴታ እንድንቆጣጠር ያስተምረናል።
ፆም ወደ አሏህ ፍራቻ የሚያደርስ መንገድ ነው። በቁርዓን ውስጥ መፆም በእኛ ላይ የተደነገገው ተቅዋ (የአሏህ ፍራቻ) ይኖረን ዘንድ እንደሆነ ተገልጿል። በእርግጥ ይህ ተቅዋ በረመዷን ወቅት በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ ይጎለብታል። ዋናው ነገር ግን በዚህ ወር ያገኘነውን መንፈስና ትምህርት ዓመቱን ሙሉ እኛ ጋ እንዲቆይ ለማድረግ መጣር ነው። ሁላችንም ይህ ስሜት ወይም መንፈስ ከረመዷን ውጪ ባለው ሕይወታችንም እኛ ጋ እንዲኖር መጣርና መታገል ይኖርብናል። በእርግጥም ትልቁ የረመዷን ግብና ፈተና ይህ ነው።
በሙስሊም በተዘገበው ሐዲስ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) በአሏህ መንገድ ለሚፆም ማንኛውም የአሏህ ባሪያ በዚህ ቀን ምክንያት አሏህ ፊቱን ሰባ ዓመት የሚያህል ርቀት ያህል ከጀሃነም እሳት ያርቅለታል ብለዋል። ፆም የምግብና የደም ባንቧን ያጠባል። እነሱም የሸይጧን ቦዮች እንደሆኑ ይታወቃል። ይሁንና ፆም በጥጋበኝነት የሚፈጸም ወንጀልን፣ ሥጋዊ ስሜትንና ሐሳብን፣ የእንቢተኝነትንና የትዕቢተኝነት ስሜትን ያደክማል። ፆም አካላዊ ጤናን ይጨምራል። ቆሻሻን ወይም የተመረዙ ነገሮችን ከአካላችን በማስወገድ ሆድ ያቀላል፣ ደም ያጠራል፣ የልብ አሠራርን የተስተካከለ ያደርጋል፣ መንፈስን ያድሳል፣ ሰብዕናን ይቀርፃል። በፆምን ጊዜ ነፍሳችን የተነሳሳች ትሁት ትሆናለች፡፡ ሥጋዊ ስሜታችነም ይወገዳል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ፆም ለአሏህ ትዕዛዝ ያለንን ታዛዥነትና ባርነት የምናሳይበት እንደ መሆኑ መጠን ትልቅ ምንዳ አለው፡፡
በረመዷን ምን ይጠበቅብናል
ለበጎ ተግባር መሮጥና ለሰዎች መልካም ውለታ ለመዋል መጣር ለቀልብ የሚያተርፈው ትልቅ የኢማን ፀጋ አለ። ኢማን ይጨምራል። ሰውየውንም በአላህ ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን ያደርገዋል። ይህ የበጎ አድራጎት በር ትልቅ ነው። በተለይም በረመዳን ሁላችን እንድንገባበት ያሻል። ‹‹የአላህ መልዕክተኛ ቸር ነበሩ። በተለይም በረመዳን ጂብሪል ስለሚያገኛቸው ይበልጥ ቸር ይሆናሉ። በረመዳን በየሌሊቱ ጂብሪል ያገኛቸዋል። ቁርዓን ያጣናቸዋል። የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ከተለቀቀ ጎርፍ የበለጠ ቸር ነበሩ።›› በዚህ ወር ውስጥ መልካም ተግባርን በመፈጸም ራሳችንን ለአላህ ዕይታ የበለጠ መርረብ የሚገባን ሲሆን፣ በረመዳን ከሚጠበቅብን ዓበይት ተግባራት መካከል ጥቂቱን እንመልከት፡፡
ልግስና
በቡኻሪ እንደተዘገበው ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) በተፈጥሮ በጣም ለጋስ (ቸር) ሰው ነበሩ። በረመዷን ወር ከሌላው ጊዜ ይበልጥ በጣም ለጋስ ይሆኑ ነበር። አሏህ (ሱ.ወ.ተ) ከሰጠን ነገር በረመዷን ውስጥ ሶደቃም ይሁን ዘካ ለመስጠት መሞከር ይኖርብናል። ማጣት አያሳስበን፡፡ በማንኛውም ጊዜ የሆነ ነገር ስንሰጥ አሏሁ አዘወጀል አካላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ህሊናዊ ሁኔታችነን ያቀልልናል፡፡ ሲሳያችነንም ያሰፋልናል። ሶደቃ ግዴታ ገንዘብ ብቻ አይደለም፣ መልካም ሥራም ይሆናል። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) መልካም ንግግር ሶደቃ ነው። መጥፎ ነገር ከመንገድ ማስወገድ ሶደቃ ነው አይደል ያሉት። ይሁን እንጂ ገንዘብ ካለን የተወሰነ ለሚገባቸው ሰዎች መስጠት ይኖርብናል። ብዙ ሙስሊሞችም ዘካቸውን በረመዷን ውስጥ ይከፍላሉ። ምክንያቱም ምንዳው በረመዷን ውስጥ በላጭ ነውና። በትርሚዘ በተዘገበው ሐዲስ ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ይህ የአማኞች ሲሳይ የሚጨምርበት የልግስና ወር ነው። ፆመኛን የመገበ ወይም (የሚያፈጥርበትን) አንዲት ተምር ወይም አንድ ጉንጭ ውኃ የሰጠ ሰው ለወንጀሎቹ መሃርታ ያገኛል፡፡ ከጀሃነም እሳት ይድናል። እሱም ተመሳሳይ ምንዳ ያገኛል ብለዋል። ፆመኛን ማስፈጠር ትልቅ ምንዳ ያለው በመሆኑ ምክንያት በብዙ ቦታዎች ማፍጠሪያ መስጊድ ውስጥ ይቀርባል፡፡ አሊያም ሰዎችን ከቤታቸው ጠርተው ያስፈጥራሉ።
ረመዳንን ችሮታና ልግስናን የምንለምድበት አጋጣሚ እናድርገው። ከገንዘባችን፣ ከጊዜያችንና ከጉልበታችን አላህ ላይ አንሰስት። ያለ ሒሳብ ለአላህ እንለግስ። በኢማም በይሀቂይ ‹‹ሹዐቡል ኢማን›› በተሰኘው መጽሐፍ ላይ እንዲህ የሚል ተዘግቧል። ‹‹የዚድ ኢብኑ መርዋን ብዙ ገንዘብ መጣለት። ከዚያም እየዘገነ ለወንድሞቹ ይልክ ገባ።›› እንዲህም ይል ነበር፣ ‹‹እኔ ለወንድሞቼ ጀነት እንዲሰጣቸው እየተማፀንኩት ከገንዘቤ ብሰስትባቸው አላህን አፍረዋለሁ!!››፡፡ ሌላው በረመዳን የተወደደው የልግስና ተግባር ሰዎችን ምግብ ማብላት ሲሆን፣ ይህ ትልቅ የበጎ ተግባር ደጃፍ ነው። ነገር ግን ብዙዎች ችላ ብለውታል ጀነት ውስጥ ሰገነቶች አሉ። የውጭው ክፍል ከውስጥ ይታያል። የውስጡን ደግሞ ከውጭ በኩል ማየት ይቻላል።” አሉ፤ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.)። የአላህ መልእክተኛ ሆይ! ለማን የተዘጋጁ ናቸው? ብለው ጠየቁ ሶሐቦቹ። ‹‹ምግብ ላበላ፣ ንግግርን ላሳመረ፣ ሰዎች ተኝተው ሳሉ በለሊት ለሰገደ›› ሱሀይብ (ረ.ዐ.) ብዙ ምግብ ያበላ ነበር። ከዚያም ዑመር (ረ.ዐ.) ‹‹ሱሀይብ ሆይ! አንተ ብዙ ምግብ ታበላለህ። ይህ ደግሞ ገንዘብን ማባከን ነው›› አሉት። እርሱም ‹‹የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ከእናንተ መሀል ምርጣችሁ ምግብ ያበላና ሰላምታን የመለሰ ነው ብለውኛል። እኔንም ብዙ እንዳበላ ያደረገኝ ይህ ነው›› አለ። ዐሊይ ኢብኑ አቢጣሊብ (ረ.ዐ.) እንዲህ ይሉ ነበር። ‹‹ወደ ሱቅ ወጥቼ አንዲት ባርያ ገዝቼ ነፃ ከማደርግ ጓደኞቼን ሰብስቤ አንዲት ቁና ምግብ ባበላ እመርጣለሁ››።
በመሀላችን ያለውን ትስስርና ፍቅር ለማጠንከር ጓደኞቻችንን፣ወዳጆቻችንን፣ ወንድሞቻችንን እና ጎረቤቶቻችንን ሰብስበን ብንጋብዝ መልካም አየር እንፈጥራለን። ከዚሁ ጋር ምስኪኖችን ማብላት ደግሞ ልዩ ጥቅም አለው። ልቡ በመድረቁ እየተጎዳ መሆኑን የገመተ አንድ ሰው የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ሲሉ መክረውታል፡፡ ‹‹ልብህ እንዲለሰልስ ከፈለግክ ምስኪኖችን መግብ። የየቲምን ራስ አብስ››። ለድሆችና ለሚስኪኖች የማፍጠሪያ ግብዣዎችን እናዘጋጅ። ከእነርሱም ጋር አብረን በመቀመጥ ምግባቸውን ብንቋደስና የወንድምነትና የእህትነት ስሜታቸውን ለማሳደግ ብንሞክር ልብ ላይ የሚፈጥረው የኢማን ስሜት ልዩ ነው። ከዚህም ጋር ችግር ያለባቸውን፣ በበደል ሥር የሚኖሩ፣ በእስር የሚማቅቁት፣ በመሳደድ ላይ የሚገኙና በረሃብ አረንቋ እየተንገላቱ የሚገኙ ሕዝቦችን እናስብ። ‹‹ፆመኛን ያስፈጠረ ሰው የፆመኛው ምንዳ ሳይቀንስ ለእርሱም የፆመኛው አምሳያ ምንዳ›› የሚለውን የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) ብስራት እንዳንረሳ።
የሰዎችን ጉዳይ መፈጸም
ከታላላቅ በጎ ተግባሮች ውስጥ ለሰዎች ጉዳይ መሮጥና ስለሰዎች መጨነቅ አንዱ ነው። ምክንያቱም በጎ አድራጊ ለአላህ ብሎ ለፍጡሮች አዝኗል። ስለዚህ ምንዳውም የተግባሩ አምሳያ ነው። የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ከሰዎች መሀል አላህ ዘንድ ተወዳጁ ለሰዎች ጠቃሚ የሆነው ነው። አላህ ዘንድ ተወዳጅ ሥራ ሙስሊም ልብ ውስጥ የምታስገባው ደስታ፣ የምትገላግለው ጭንቅ፣ ከዱንያ የምትፈጽምለት ጉዳይ ወይም የምትገፈትርለት ረሃብ ነው። በአላህ እምላለሁ መስጂድ ውስጥ ወር በሙሉ ኢዕቲካፍ አድርጌ ከምቀመጥ ለሙስሊም ወንድሜ ጉዳይ ብሮጥ እመርጣለሁ። ቁጣውን የሚደብቅ አላህ ነውሩን ይሸፍንለታል። ቁጭቱን የዋጠ ሰው የቂያም ቀን አላህ ልቡን በውዴታው ይሞላለታል። የሙስሊም ወንድሙ ጉዳይ እስኪፈጸም ድረስ የተንቀሳቀሰ የሰዎች እግር በሚስትበት ቀን አላህ እግሩን (በሲራጥ ላይ) ያረጋለታል። መጥፉ ሰብዕና ልክ ኮምጣጤ ማርን እንደሚያበላሽ መልካም ሥራን ያበላሻል››፡፡
በሌላ በኩል ባለቤታቸው የሞተባቸው ሴቶችንና ሚስኪኖችን መንከባከብ የተለየ ምንዳ እንደሚያስገኝ ነብያዊ ሀዲሶች አበክረው ይጠቁማሉ። የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) እንዲህ ይላሉ፣ ‹‹ባላቸው ለሞተባቸው ሴቶችና ለሚስኪን ጉዳይ የሚሮጥ በአላህ መንገድ ላይ እንደሚታገል (ሙጃሂድ) ወይም ለሊት እንደሚቆምና ቀን እንደሚፆም ሰው ነው፡፡›› እነዚህ ሐዲሶች ብዙ ትንታኔ የሚያሻቸው አይደሉም። ተግባር ዋናው ነገር ነውና የሐኪም ኢብኑ ሒዛምን ተግባራዊ ምሳሌ እናንሳ። ሐኪም ሊረዳው የሚችለው ባለጉዳይ ወይም ችግርተኛ ያጣ ቀን በጣም ይተክዛል። እንዲህ ይላል፣ ‹‹ባለጉዳይ ያጣሁበት እያንዳንዱ ቀንን ትልቅ አደጋ እንደ ደረሰብኝ ቆጥሬው (ለትዕግሥቴ) ከአላህ ምንዳ እከጅልበታለሁ›› በማለት ይገልጻሉ፡፡
የአላህን ምህረት መለመን
የአሏህን መሃርታ ከምንሻባቸው ነገሮች አንዱ አሏህ ያዘዘንን ነገር መታዘዝና ከከለከለን ነገር ሁሉ መራቅ ነው። ለምሳሌ ፆማችንን በትክክል በመፆም፣ ሶላታችነን በወቅቱ በመስገድ፣ የተራዊህ ሶላት በመስገድና ላለፉት ወንጀሎቻችን ተውባ በማድረግ ነው። ቅን የሆኑ ሰዎች ከትልልቅ ወንጀሎች ከራቁ ዓመቱን ሙሉ የሠሯቸው ትንንሽ ወንጀሎች በረመዷን እንደሚማርላቸው ያውቃሉ። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ.) የረመዷን የመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት አሏህ በሙዕሚኖች ላይ እዝነቱን የሚያዘንብበት የእዝነት ጊዜ ነው። ቀጣዮቹ አሥር የረመዷን ቀናት ደግሞ ሙዕሚኖች በመጀመሪያዎቹ አሥር ቀናት በመፆማቸው ምሕረት የሚያገኙበት ነው። የመጨረሻዎቹ አሥር ቀናት ደግሞ ከጀሃነም እሳት የሚጠበቁበት (አሏህ ሰዎችን ከጀሃነም እሳት የሚያወጣበት) ነው ብለዋል። ታዲያ ይህን ወር በኢባዳ፣ በዱአ፣ በዚክር፣ በስቲግፋር ማሳለፍ ይኖርብናል። ብዙ እስቲግፋር የምናደርግ ከሆነ አሏህ ከችግሮቻችን ሁሉ የምንወጣበትን በር ይከፍትልናል። እንዲሁም ከጭንቀታችን ያላቅቀናል።
በመጨረሻም ይህን ረመዳን አንዳች አዎንታዊ ተግባር ለመከወን የምንችልበት፣ ለዕድገታችን የሚበጅና አሁን ላለንበት አገራዊ እጥረቶች ማሟያ አድርገን ልናየውና ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ በሀገራችን የሚታዩ በተለይ በአገራዊ አንድነት፣ በዘላቂ ሰላምና በሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሳቢያ የሚታዩ መንገራገጮችን ለማረቅ የጋራ ፍቅርን ማደርጀት፣ በወጉ መረዳዳት፣ መቻቻል፣ መተሳሰብና መከባበርን በዚህ ወር ይበልጥ በማጎልበት አገራችን በሁሉም መስክ የበለፀገች ያደርግልን ዘንድ ፈጣሪ እንማፀናለን፡፡
መልካም ረመዳን!! አላሁመ ባሪክ ለና ፊ ረመዳን!!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡