Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት በሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራት በኩል ለከተማዋ ነዋሪ ጤፍ እያቀረበ ይገኛል፡፡ 

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አስረስ ጌታቸው፣ ሰሞኑን በሸማቾች የሚቀርበውን ጤፍ ለመሸመት እጅ እንዳጠራቸው ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከዘመድ አዝማድ በብድርም ቢሆን ያገኙትን ገንዘብ የጤፍ ግዥ ላይ ለማዋል ወደ ሸማቾች ቢዘልቁም፣ ዋጋው መንግሥት እንደተናገረው እንዳልሆነ በንዴት ይገልጻሉ፡፡ 

ከሰሞኑ መንግሥት በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ሸማቾች ሱቅ በኪሎ ከ52 ብር እስከ 59 ብር ለማኅበረሰቡ ቢያቀርብም እንደነ ወ/ሮ አስረስ እጅ ያጠራቸው ግን ይህን ለማግኘት አልታደሉም፡፡ 

የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ከአራት ቀናት በፊት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ በቆሎና ሌሎች ምርቶችን ለማኅበረሰቡ በቅናሽ ዋጋ መቅረቡን ገልጿል፡፡ 

በዚህም ነጭ ጤፍ በኩንታል በ5,600 ብር፣ ሠርገኛ ጤፍ 5,400፣ ስንዴ 5,400 እና በቆሎ ደግሞ 3,300 ብር እየተከፋፈለ መሆኑን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስፍሯል፡፡ 

በሁሉም ባልቴቶች ጓዳ ተፈላጊ የሆነው ጤፍ ለማግኘት ወደ ሸማች ሱቅ ያመሩት ወ/ሮ አስረስ፣ አንድ ኪሎ ጤፍ 80 ብር መሆኑን ሲያውቁ ሳይገዙ መመለሳቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ብሥራት ጉለሌ ኅብረት ሥራ ዩኒየን ሰብሳቢ አቶ በእርሱ ፈቃድ ኃይሌ እንደሚሉት፣ በክፍለ ከተማው በሚገኙ በሁሉም ሸማቾች ሱቅ ሰሞኑን ጤፍ ለኅብረተሰቡ በቅናሽ ዋጋ ሲቀርብ ነበር፡፡ 

ይሁን እንጂ ዩኒየኑ ዋጋ ለማረጋጋት ያቀረበውን ጤፍ በሙሉ እስከ ከመጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ለኅብረተሰቡ ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡ 

ያለውን የጤፍ አቅርቦት ችግር ለመፍታት የዩኒየኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወደ ባህር ዳር መሄዳቸውን የገለጹት አቶ በእርሱ ፈቃድ፣ በቅርቡም የጤፍ አቅርቦት ችግር ይቀርፋል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

በቅርቡ ጨፌ ኦሮሚያ ማኅበር ጤፍ ለመግዛት የሁለት ሚሊዮን ክፍያ ፈጽመው ከአርሶ አደሮች የመሰብሰብ ሒደት ላይ መሆናቸውንም አቶ በእርሱ ፈቃድ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪ ከክፍለ ከተማው ኅብረት ሥራ ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን ሰበታ ከተማ ላይ ጤፍ ለመሸመት በሒደት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡ 

በተለይም በክፍለ ከተማው ወረዳ ዘጠኝ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ በተመለከተ ሪፖርተር ጥያቄ አቅርቦላቸው በሰጡት ምላሽ በአካባቢው የሚገኙ የሸማት ማኅበራት ጤፍ የሚገዙት ከዩኒየኑ ከሆነ ዋጋው በኪሉ ከ55 ብር እንደማይበልጥ ተናግረዋል፡፡ 

ነገር ግን ዩኒየኑ የጤፍ ግዥ ሒደት ላይ በመሆኑ፣ ኅብረት ሥራ ማኅበራቱ የኅብረሰቡን ፍላጎት ለመሙላት ከዩኒየን ወጪ ከሌሎች ደንበኞቻቸው ገዝተው ሊያቀርቡ እንደሚችሉና በዚህም ምክንያት ዋጋው ጭማሪ ሊያሳይ እንደሚችል ጠቁመዋል።

የኅብረት ሥራ ማኅበራት ከሌሎች ደንበኞቻቸው ጤፍ ገዝተው ለሸማቾች የሚያቀርቡ በሚሆንበት ጊዜ የዋጋ ጭማሪ እንደሚኖረው የገለጹት አቶ በእርሱ ፈቃድ፣ ማኅበራት ከሌሎች አቅራቢዎች የሚገዙት ጤፍ በኪሎ ከ60 እና 70 ብር አንደሚሆን፣ በዚህም ምክንያት ተጠቃሚው ማኅበረሰብ ጋር ሲደርስ የሚሸጥበት ዋጋ ከፍ እንደሚል ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የሸማች ማኅበራት ጤፍ የሚረከቡት ከዩኒየኖች ከሆነ በአንዱ ኪሎ ከ50 ሳንቲም እስከ አንድ ብር በላይ ማትረፍ ስለማይቻል፣ ለኅብረተሰቡ በዝቅተኛና ተመጣጣኝ ዋጋ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡ 

በክፍለ ከተማው የሚገኘው ብሥራት ለጉለሌ ዩኒየን ሥር አሥር የሸማች ማኅበራት መኖራቸውን፣ በዚህም 16,700 አባል ተጠቃሚ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡ ዩኒየኑ የሚያቀርበውን ጤፍ የሚገዛው በኩንታል 5,900 ብር እንደሆነ፣ ለወዝ አደር፣ ለትራንስፖርትና መሰል ወጪዎች ተደምረው በገማች ኮሚቴ አማካይነት ለኅብረተሰቡ የሚቀርብበት ዋጋ እንደሚተመን አብራርተዋል፡፡ 

ሌላኛው በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ተስፋ ብርሃን ሸማቾች ማኅበር ከመጋቢት 4 እስከ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ጤፍ በኪሎ በ55 ብር ዋጋ ሲያቀርብ እንደነበርና ለአንድ አባወራ የተፈቀደውም 25 ኪሎ ግራም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ይሁን እንጂ በዚህ ወረዳ በመጋቢት 11 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የጤፍ ዋጋ በኪሎ ከ76 ብር እየቀረበ ሲሆን ለአንድ አባወራ ከ25 ኪሎ ግራም እየተሸጠ መሆኑን ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡ 

የወረዳው ነዋሪዎችም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ መንግሥት ገበያውን አረጋጋለሁ ብሎ የዋጋ ተመን ቢያወጣም፣ በአንዳንድ ሸማች ሱቅ የሚቀርበው ጤፍ ከተተመነው ዋጋ በላይ መሆኑን በቅሬታ አንስተዋል።

በሸማች ማኅበራት እየቀረበ ያለው የጤፍ ምርት ነጋዴዎች በወፍጮ ቤት ከሚሸጡበት ዋጋ ያለው ልዩነት የአሥር ብር ብቻ እንደሆነ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

መንግሥት ወጥ የሆነ የጤፍ ዋጋ ተመን እንዳወጣ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ሲገልጽ የነበረ ቢሆንም፣ በአንዳንድ ሸማች ማኅበር የአቅርቦትና ዋጋ ተመን ልዩነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ 

ይህም መንግሥት ሰሞነኛ የዋጋ ማረጋጋት እንጂ ዘለቄታዊ የዋጋ ማስተካከያ አልተደረገም በማለት በቀጣይ የጤፍ ዋጋ ከዚህም በላይ ጭማሪ ሊኖረው እንደሚችል ነዋሪዎች ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

አቶ በላይ ቶሌራ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ የምዕራብ ኅብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ዩኒየኑ ለ23 የሸማች ማኅበራት በሥራቸው እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ በእነዚህም ማኅበራትም ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችና የፋብሪካ ውጤቶችን ለኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ 

በአዲስ አበባና ከተማዋ ጣሪያ የነካው የጤፍ ዋጋ ለማረጋጋት ዩኒየኑ በዝቅተኛ ዋጋ ጤፍ እያቀረበ እንደሚገኝ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ 

ለሸማቾች የቀረበው በ100 ኪሎ ግራም ጤፍ ከ6000 እስከ 7000 ብር ድረስ ማቅረባቸውን አስረድተው፣ ለመጋቢ እናቶችና ለመንግሥት ሠራተኞች አንድ ኩንታል ጤፍ በ5,500 ብር መሸጣቸውን ገልጸዋል፡፡ 

እስከ ቅርብ ቀናት ዩኒየኑ 6,800 ኩንታል ጤፍ ለማኅበረሰቡ ማቅረቡን የሚገልጹት አቶ በላይ፣ ለአንድ አባወራ ከ25 እስከ 50 ኪሎ ግራም ድረስ በሸማች ማኅበራት አማካይነት መሸጣቸውን አስረድተዋል፡፡ 

የሸማቾች ቅሬታን በተመለከተ ተጠይቀው እርሳቸው ለማመሩት የምዕራብ ኅብረት ሥራ ዩኒየን የቀረበ ቅሬታ አለመኖሩን ገልጸዋል፣ ይሁን እንጂ የአቅርቦት ችግር በስፋት መኖሩን ሸማቾች በቅሬታ እንደሚያነሱ አልሸሸጉም፡፡ 

እንደ አቶ በላይ፣ በዩኒየኑ በቂ ጤፍ ለማቅረብ አማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ደብረ ማርቆስ ከተማ ጤፍ ለመሸመት መሄዳቸውን ገልጸዋል፡፡ 

በአካባቢው የጤፍ ምርት በበቂ ሁኔታ መኖሩን የገለጹት አቶ በላይ፣ የመንገዶች ዝግ መሆንና ምርቱን የማሳለፍ ችግር እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ በሚቀጥሉት ቀናትም ለከተማው በቂ የጤፍ ምርት ለማቅረብ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬና ባህር ዳር ዙሪያ ግዥ ለመፈጸም እንደሚያቀኑ ገልጸዋል፡፡ 

ሥራ አስኪያጁ በሄዱባቸው የጤፍ አምራች ቦታዎች ምርቱ በበቂ ሁኔታ መኖሩን፣ አርሶ አደሩም የመሸጥ ፍላጎት እንዳለው አስረድተዋል፡፡ 

በአካባቢው የጤፍ ዋጋ አንድ ኩንታል ጤፍ 5,500 እስከ 5,800 ብር ድረስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ትልቁ ችግር ባለፉት ሳምንታት ጤፍ ገዝተው ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ከደጀን ከተማ ማለፍ እንዳልተቻለ ጠቁመዋል፡፡ ችግሩንም ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች