Monday, April 15, 2024

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ ነው፡፡ የሽግግር ጊዜ አስተዳደሩን ደግሞ አቶ ጌታቸው ረዳ እንዲመሩ በሕወሓት በኩል ቀርበዋል፡፡ የሕወሓት የበላይነት ለግማሽ ክፍለ ዘመን ገናና በሆነበት የትግራይ ፖለቲካ ነባር ከሆኑ ታጋዮች ውጪ የሆነ ሰው ወደ ከፍተኛ አመራርነት መምጣቱ ያልተለመደ አጋጣሚ እየተባለ ነው፡፡ በትግራይ ፖለቲካ ታሪክ ከረዥም ጊዜ በኋላ የደደቢት በረሃን የማያውቅ ፖለቲከኛ ወደፊት መምጣቱ ያልተጠበቀ አጋጣሚ እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡

አቶ ጌታቸው የሽግግር አስተዳደሩን እንዲመሩ ሕወሓት ቢያቀርባቸውም፣ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት የፌዴራል መንግሥት ይሁንታ ይጠበቃል፡፡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ አመለካከቶች እንዲስተጋባ እያደረገ ይገኛል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ወቅት የሕወሓት ዋና አፈ ቀላጤ የነበሩት፣ በኋላም ከመንግሥት ጋር የተደረገውን የሰላም ድርድር የመሩት አቶ ጌታቸው የሽግግር መንግሥቱ መሪ ለመሆን ከፊት መሆናቸው፣ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣ የሚገምቱ አሉ፡፡

በሌላ በኩል በሽግግር መንግሥቱ የሚደረግ የአዲስ አመራሮች መምጣት የሕወሓትንም ሆነ የትግራይን ፖለቲካ ባህል የማይቀይር ክስተት ሆኖ የታያቸው ወገኖችም አሉ፡፡

የሰላም ስምምነቱን ትግበራ ሒደት መስመር ለማስያዝ አቶ ጌታቸው ከሌሎች የሕወሓት ሰዎች የተሻሉ መሆናቸውን የሚናገሩ በርካታ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በተቃራኒው ማንም ወደ ሽግግር አስተዳደሩ ቢመጣ፣ የሰላም ስምምነቱን አተገባበር ከሕወሓት ተፅዕኖና ፍላጎት የሚያላቅቅ እንዳልሆነ የገመቱም በርካታ ናቸው፡፡

ከመጀመሪያው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በኋላ በፌደራል መንግሥቱ ተዋቅሮ በነበረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ የመቀሌ ከተማ ከንቲባ ሆነው የሠሩት አቶ አታክልቲ ኃይለ ሥላሴ፣ የሽግግር አስተዳደር መቋቋሙን እንደሚደግፉ ይናገራሉ፡፡

‹‹እኔ ትልቅ ቦታ የምሰጠው በቶሎ ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር ቢቋቋም፣ ሕዝቡ ለረዥም ጊዜ የተቸገረበትን አገልግሎት መልሶ እንዲያገኝ የሚያግዘው መሆኑን ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ሕወሓትን እንደ አንድ ፓርቲ ነው የማያት፡፡ ግለሰቦች ደግሞ በአቅም አንዱ ከሌላው የተለያዩ መሆናቸው ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ስለዚህ አዳዲስ አመራር ወደ ሽግግር አስተዳደሩ መምጣቱ የራሱ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብሎ መገመት ጤናማ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ከሕወሓት የፖለቲካ ባህል አንፃር በዚህ ላይ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ አቶ ጌታቸው ደደቢት ባይገቡም ከሕወሓት አቋም ውጪ አይሆኑም፡፡ የሕወሓትን ማንነት ለመውረስ ከ50 ዓመታት በፊት ለምን አልተፈጠሩም ልል አልችልም፡፡ የሕወሓት አመራርና የሕወሓት ዓላማ አስፈጻሚ ናቸው፤›› በማለት የአቶ ጌታቸው ወደ ሥልጣን መምጣት የተለየ ለውጥ ይዞ የሚመጣ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ፖለቲከኛው አቶ ጊዴና መድህን በበኩላቸው፣ በሽግግር አስተዳደሩ የአቶ ጌታቸው ወደ መሪነት መምጣት የተለየ ለውጥ እንደማያመጣ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሕወሓትን በመፍጠርና እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ከሌሎች አንፃር እንደ መሐንዲስ የሚታዩ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ሕወሓት ለዘመናት በፈጸማቸው ወንጀሎች የበዛ ተሳትፎ ያላቸው አይደሉም ሊባሉ ይችላሉ፡፡ የሰዎች በአንድ ኃላፊነት ላይ መፈራረቅ ለውጥ ማምጣቱ የሚጠበቅ ተፈጥሮአዊ ዑደት ሊሆንም ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህም ሁሉ ሆኖ የሕወሓት መዋቅር ከላይ እስከ ታች ተነቅሎ ካልተተካ በስተቀር የጌታቸው መምጣትና መሄድ ብቻውን የሚቀይረው አንዳችም ልዩነት የለም፤›› በማለት ነው ስለሒደቱ ያላቸውን ምልከታ ያጋሩት፡፡

የባይቶና ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ክብሮም በረኸ አሳታፊና አካታች የሽግግር አስተዳደር መመሥረት እንደሚበጅ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ችግሩን ያመጣው አካል ችግሩን ለመፍታት አይችልም፡፡ ይብዛም ይነስም ሁሉም ወገን የትግራይ ቀውስ እንዲቆምና ሰላም እንዲሰፍን የራሱ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ስለዚህ መሆን የነበረበት ሁሉንም የትግራይ ፖለቲካ ኃይሎች ያወያየና ያማከለ ውይይት በማድረግ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሊዋቀር ይገባ ነበር፡፡ የሕወሓት የፖለቲካ መንገድ በዜሮ ወይም በመቶ ብቻ ነው፡፡ አሁን የተከተሉትም የዜሮ መንገድ ሲሆን፣ ይህ ለሽግግሩ የማይበጅና እኛንም የሚያጠፋ ነው፤›› በማለት የጊዜያዊ አስተዳደ አወቃቀር ሊፈጥር የሚችለውን ቀቢፀ ተስፋ አስረድተዋል፡፡

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የፖለቲካ ተንታኝ ግን በሽግግር ሒደትና በሰላም ትግበራ ስም፣ በትግራይ ወደ ፖለቲካ ሥልጣን የመምጣት ፍላጎት ከብዙ አቅጣጫዎች መኖሩን ይናገራሉ፡፡ ገዥው የብልፅግና መንግሥት የሚፈልጋቸው ሰዎች ብቻ በትግራይ ፖለቲካ ሚና እንዲኖራቸው ይፈልጋል፡፡ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ከራሳቸው የመነጨ የፖለቲካ ፍላጎት አላቸው የሚሉት ተንታኙ፣ ‹‹አንዳንዶቹ በፌዴራል መንግሥቱ ትከሻ ተንጠላጥለው በትግራይ የፖለቲካ ሚናቸውን ለማጉላት የሚፈልጉ ናቸው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ወንዝ መሀል ሆነህ ፈረስ አትቀይርም›› የሚል የፈረንጆች አባባል የተዋሱት የፖለቲካ ተንታኙ፣ አሁንም ቢሆን በትግራይ ፖለቲካ ውስጥ የሕወሓትን ያህል ‹ሕዝባዊ መሠረት› (Constituency) ያለው የለም ይላሉ፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር መመሥረት በርካታ የሐሳብ ክርክሮች እየቀረቡበት ነው፡፡ አንዳንዶች አቶ ጌታቸው በምዕራባዊያኑ በተለይም በአሜሪካ ፍላጎት የመጡ አመራር ስለመሆናቸው ይናገራሉ፡፡

አዲሱን ሹመት ተከትሎ፣ ‹‹አማራው ጌታቸው፣ እንዲሁም የአሜሪካ ወኪል ጌታቸው ተሾመ፤›› የሚሉ በተጨባጭ ማስረጃ ሊረጋገጡ የማይችሉ ትችቶች ሰውዬውን ሲከተሏቸው ይስተዋላል፡፡

የአቶ ጌታቸው ወደ ሥልጣን መምጣት በትግራይ ክልል እየተተገበረ ያለውን ሰላም የበለጠ ያፀናል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ የእሳቸው መምጣት የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎችን (የሕወሓት አመራሮችን ጨምሮ) ለፖለቲካ መከፋፈልና ትግራይን ለበለጠ አለመረጋጋት የሚዳርግ ነው ይሉታል፡፡

አቶ ጌታቸው የፌደራል መንግሥቱ በጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደሩ ውስጥ ሌሎች ሰዎች ወደ አመራርነት እንዲመጡ ባለመፈለጉ የተሾሙ ሰው ስለመሆናቸው በሰፊው እየተነገረ ነው፡፡ የጌታቸው መምጣትም ሆነ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመሠራረት የትግራይ ክልልን ፖለቲካ በመቀየር አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል የሚል ግምት ቢያሳድርም፣ የሽግግር ሒደቱ ከባድ እንቅፋት ሊገጥመው እንደሚችልም በተቃራኒው እየተገመተ ነው፡፡

አቶ ጌታቸውም መጡ ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ወይም ሌላ የትግራይን የፖለቲካ አቅጣጫ የሚወሰኑ መሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ገና አለመነካታቸውን የሚናገሩ በርካታ ናቸው፡፡ የሕወሓት ክንፍን ጨምሮ በተለያዩ የትግራይ ፖለቲካ ኃይሎች ጦርነቱን ተከትሎ በሰፊው መቀንቀን የጀመረው ትግራይን ነፃ አገር የማድረግ ፍላጎት፣ ወደ ፊት መግፋት ወይም መቆም የሚወሰንበት ስለመሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ የሽግግር አስተዳደሩ በአቶ ጌታቸው ከተመራ የትግራይ ፖለቲካ ኢሊትን ወደ አንድነት ያሰባስባል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፣ በተቃራኒው የፖለቲካ ክፍፍልን ይፈጥራል የሚል ሥጋት የሚያነሱም አሉ፡፡

ይሁን እንጂ የሽግግር አስተዳደሩ ምሥረታም ሆነ የአዳዲስ ሰዎች መመረጥ መታየት ያለበት፣ ለትግራይ ሕዝብ ከሚያመጣው ጥቅም አኳያ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ፡፡  

ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆኑት ፖለቲከኛው ጊዴና መድኅን የግለሰቦች በሕወሓት የፖለቲካ ሜዳ መለዋወጥ እምብዛም ለውጥ የሚያመጣ አለመሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የትግራይ ፖለቲካ እኮ የሕወሓት ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ሕወሓቶች ግን የሽግግር ሒደቱንም ቢሆን የራሳቸው ፍላጎት ብቻ ማራመጃ ለማድረግ እየሠሩ ነው፡፡ አንጋፋ የሚባሉት ደብረ ጽዮን (ዶ/ር)፣ ዓለም ገብረ ዋህድ፣ ታደሰ ወረደ፣ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረ እግዚአብሔር (ሞንጀሪኖ) እና የመሳሰሉት መጀመሪያ የራሳቸውን ፍላጎት ያማከለ አመራር ነበር መርጠው የላኩት፡፡ ተቀባይነት ሲያጡ ግን መልሰው እነ ጌታቸውን፣ አትንኩት (ዶ/ር)፣ አቶ ብርሃን የመሳሰሉትን ወጣት የሚባሉ ሰዎችን ወደፊት በመላክ ከጀርባ ተሠልፈዋል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

‹‹የቆዩ የሕወሓት አመራሮች (ኦልድ ጋርድ) የሚባሉት ትግራይ ሁሌም ከእነሱ ጥላ እንዳትወጣ ይፈልጋሉ፡፡ ለምሳሌ የአቶ ጌታቸው ምክትል ሆኖ የተመረጠው ፍሰሐ ሀፍተ ጽዮን (ዶ/ር) ከነባር የሕወሓት ታጋዮች አንዱ ወደፊት ያመጡት የቅርብ ሰው ነው፡፡ ሕወሓቶች የሽግግር ጊዜ አስተዳደሩንም ሆነ የትግራይ ፖለቲካ መድረክን ልክ እንደ ሰሜን ኮሪያ እየተወራረሱ ሥርወ መንግሥት አድርገው ሊይዙት እንደሚፈልጉ በግልጽ እያየን ነው፤›› በማለትም አቶ ጊዴና ያክላሉ፡፡ ፖለቲከኛው እንደሚናገሩት፣ ሕወሓቶች የሽግግር አስተዳደሩንም ለመመሥረት የተገደዱት በወታደራዊ መስክ ስለተሸነፉና ከውጭም ከውስጥም ጫና ስለበረታባቸው ብቻ ነው፡፡

አቶ አታክልቲ በበኩላቸው፣ ‹‹ሕወሓት ራሷ ማን ናት? ሕወሓት በአመራርም ሆነ በፖለቲካ የበላይነት የማን እንደሆነች፣ እንዲሁም የየት አካባቢ ተፅዕኖ እንደሚጎላባት በደንብ ይታወቃል፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ የሕወሓት ነባር ሰዎች በፖለቲካ አመለካከት ከሚጠሉት አካባቢና ማኅበረሰብ የወጣ ሰውን ወደፊት ማምጣታቸው እንደማይዋጥላቸው ነው አቶ አታክልቲ የሚያብራሩት፡፡

‹‹የጌታቸው መምጣት ከፍተኛ አጀንዳ ሲሆን አየዋለሁ፡፡ ነገር ግን የተለየ ነገር እኮ በሕወሓትም ሆነ በትግራይ ፖለቲካ አልተፈጠረም፡፡ አሁንም ቢሆን እኮ የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ነው፡፡ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ደግሞ ዓለም ገብረ ዋህድ ነው፡፡ ያውም እጅግ ውስን የሆነ ሥልጣን ባለው የሽግግር መንግሥት ውስጥ የአቶ ጌታቸው መመረጥ ምንም የሚለውጠው ነገር የለም፤›› በማለት ነው አታክልቲ ያስረዱት፡፡

አቶ አታክልቲ እንደሚሉት፣ አቶ ጌታቸው ሆኑ ሌላ ግለሰብ መጣ የሰላም ትግበራ ሒደቱ መርህን ያልተከተለና ‹‹ጨዋታ›› ዓይነት ነው፡፡ ሒደቱ ምንም ቢሆን ግን የትግራይ ክልል ሕዝብ በጦርነቱ ከገጠመው ችግር አንፃር መጠነኛ ዕፎይታን የሚሰጥና እንዲያገግም ካደረገ፣ በራሱ በአዎንታዊነት እንደሚመለከቱት ተናግረዋል፡፡

የባይቶናው አመራር አቶ ክብሮም በበኩላቸው፣ የሽግግር ጊዜ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ምሥረታ በትግራይ ሕዝብ ላይ የተደረገ ሌላ ዙር በደል መሆኑን ያወሳሉ፡፡ ‹‹ብንወያይበት፣ ሁሉም ቢሳተፍበትና በጎ ሐሳቦችን ቢያዋጣ መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን እነሱ ሁሉንም በር ዝግ አድርገው ያካሄዱት የሽግግር ጊዜ አስተዳደር ምሥረታ ነው፤››ይላሉ፡፡

ሆን ብለው ሒደቱን ሲጎትቱት እንደነበር የጠቀሱት አቶ ክብሮም፣ ‹‹ለስድስት ወራት የሚቆይ አስተዳደር ለመመሥረት ስድስት ወራት ሊወስድባቸው ነበር፤›› ሲሉ መንቀርፈፉን ተችተዋል፡፡ ሆኖም አሁን፣ ‹‹ሥልጣን ከራሳቸውና ከቤተሰባቸው እንዳይወጣ የሚፈልጉ የሕወሓት ሰዎች ሒደቱን ዝግ አድርገውና አካልበው ለራሳቸው መጠቀሚያ የሆነ አስተዳደር ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል፡፡ አቶ ጌታቸው ወጣት ናቸው፣ ይሁን እንጂ በሕወሓት ቤት ማደጋቸው የዴሞክራሲ ጠላት ያደርጋቸዋል፤›› በማለት ነው ሒደቱን ዴሞክራሲያዊ አሳታፊነት የጎደለው መሆኑን የተቹት፡፡

ስሜ አይጠቀስ ያሉት የፖለቲካ ተንታኝ ግን፣ ሕወሓትን ይዞ መቀጠሉ ለሽግግር ጊዜ ሒደቱ መስመር የተሻለው አማራጭ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ብዙ ጊዜ የትግራይን የፖለቲካ ባህል ያለ መረዳት ችግር አለ፡፡ ዛሬም ድረስ በትግራይ ሰፊ ማኅበራዊ መሠረት ያለው ሕወሓት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ አሁን የተፈጠረውን ሰላም ሕወሓት ነው ያመጣልን የሚል ሰፊ አመለካከት ሕዝቡ ውስጥ ሲንፀባረቅ እታዘባለሁ፡፡ የትግራይ ሕዝብ የገጠመውን የፖለቲካ ስብራት ለመጠገንም ሆነ ከሌላው ጋር ተቋርጦ የቆየውን ማኅበረሰብ ደግሞ ከዓለም ጋር ለመቀላቀል፣ ሕወሓትን ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደሩን እንዲመራ ማድረጉ የተሻለ መፍትሔ ነው፤›› ይላሉ፡፡

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር አስተዳደር ምሥረታ በክልሉ እየተተገበረ ላለው የሰላም ስምምነት፣ እንዲሁም ለመላው ኢትዮጵያ ሰላም የሚበጅ ጠቃሚ ዕርምጃ መሆን አለመሆኑ ወደፊት የሚታይ መሆኑ ብዙዎችን ያስማማል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -