- አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር ሚኒስትር?
- እርሶዎማ ቀጠሮ መያዝ አያስፈልግዎትም። ምን ገጠመዎት?
- እኔማ ምን ይገጥመኛል፣ አንተኑ ልጠይቅህ እንጂ?
- ምን?
- እውነት ለመናገር የማየው ነገር አሳስቦኛል።
- ይንገሩኝ ምንድነው ያሳሰበዎት?
- ሌት ተቀን የሚሠራው ነጋዴ እየከሠረ ነው።
- መቼም የውጭ ኃይሎች የፈጠሩብንን ችግር ያውቁታል።
- ከእሱ አይገናኝም ክቡር ሚኒስትር!
- እንዴት?
- ሌት ተቀን የሚሠራ ታታሪ ነጋዴ ችግር እሱ አይደለም።
- ምንድነው?
- ታታሪ ነጋዴ እየመነመነ ሳለ በተቃራኒው ግን ሌላ…
- በተቃራኒው ምን?
- መሽቶ ሲነጋ ሀብት አፍርተው የሚታዩ ሰዎች እንደ አሸን እየፈሉ ነው።
- ምን ማለትዎ ነው?
- ጠንክሮ መሥራት ሀብት የሚፈጠርበት መንገድ መሆኑ ቀርቶ ሌላ ዓውድ ተፈጥሯል እያልኩ ነው።
- የምን ዓውድ?
- ሲነጋ ሀብታም መሆን የሚቻልበት ዓውድ።
- አልገባኘም?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- ሁሉን ነገር አስረዳ እያሉኝ እኮ ነው።
- እውነት አልገባኝም? እንዴት ያለ ዓውድ ነው በብርሃን ፍጥነት ሀብት የሚያስገኘው?
- አልገባኝም ካሉማ እንግርዎታለሁ።
- ይንገሩኝ!
- ሲነጋ ሀብት የሚፈጠርበት ስልት አንድና አንድ ነው።
- ምንድነው?
- ከከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ግንኙነት የመፍጠር ስልት ነው። ወንድም ወይም ዘመድ አዝማድ የመሆን ስልት!
- እሱን ነው እንዴ?! ይህንንማ እኛም ገምግመናል።
- ምን ብላችሁ ገመገማችሁት?
- በዝተዋል ብለን ገምግመናል።
- እነማን ናቸው የበዙት?
- በብርሃን ፍጥነት ሀብታም እንሁን የሚሉ።
[የመደመር ትውልድ መጽሐፍን በመሸጥ ገቢውን ለታለመለት ፕሮጀክት ግንባታ እንዲያውሉ ለክልል ርዕሰ መስተዳድሮች ኃላፊነት እየተሰጠ ሳለ፣ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሲጠሩ የተሳቀበትን ምክንያት ለማወቅ የፈለጉት የሚኒስትሩ ባለቤት ሚኒስትሩን ለምን እንደተሳቀ እየጠየቁ ነው]
- የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድርን ሲጠሩ ለምንድነው የተሳቀው?
- አልሰማሽም እንዴ?
- ምን?
- ርዕሰ መስተዳድሩ መድረኩ ላይ ሲደርሱ የተናገሩት ያሉትን?
- ምን አሉ?
- ወደ ሚኒስትሩ ጠጋ ብለው ፕሮጀክቱን ጢያ ትክል ድንጋይ እናድርገው ሲሉ በድምጽ ማጉያው ውስጥ አልፎ ለታዳሚውም ተሰማ።
- ታዲያ ይኼ ምን ያስቃል?
- ያስቃል እንጂ።
- ለምን?
- የቀረው እሱ ነዋ!
- ከምን?
- ከደቡብ ክልል
- እንዴት?
- ሲዳማም ከደቡብ ክልል ወጥቶ ራሱን የቻለ ክልል ሆነ፡፡
- እህ …
- እነ ዳውሮም ራሳቸውን ችለው የደቡብ ምዕራብ ክልል ሆኑ።
- እህ …ሰሞኑን ደግሞ …
- ሰሞኑን ደግሞ ምን?
- እነ ወላይታም የራሳቸውን ክልል ለመመሥረት ሕዝበ ውሳኔ ላይ ናቸው።
- እህ… ልክ ነው ከደቡብ ክልል የቀሩት እነ ሶዶ ናቸው?
- አዎ። ርዕሰ መስተዳድሩም ፕሮጀክቱን የጢያ ትክል ድንጋይ እናደርገው ያሉት ለዚያ ነው።
- እህ… ሚኒስትሩ የተናገሩትም ምን ማለት እንደሆነ ገባኝ?
- ምን ተናገሩ?
- አልሰማህም እንዴ?
- አልሰማሁም፣ ምን አሉ?
- የመደመር ትውልድ ለደቡብ በጣም ያስፈልገዋል አሉ እኮ!
- ምን ማለተቻው ነው? ምንድነው የገባሽ?
- እኔን የገባኝ?
- እ…?
- ያው ሚኒስትሩ የገባቸው ነገር ነዋ።
- ምንድነው እሱ?
- ሚኒስትሩ የገባቸው?
- እ…?
- መደመር እያሉ ደቡብ ክልል መለያየቱ ነዋ።
- አትሳሳቺ!
- እንዴት?
- በእርሳቸው መደመር ውስጥ መደመር ብቻ አይደለም ያለው።
- ሌላ ምን አለ?
- መቀነስ!