ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ር) አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ሹመቱን የሰጡት፣የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 (9) እና በአዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀፅ 14/2/ለ/ መሠረት፣ የትግራይ ከልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት፥ እንዲሁም በኢፌድሪ መንግሰትና በህወሃት መካከል ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና ግጭትን ለማቆም በፕሪቶርያ ደቡብ አፍሪካ በተደረገው የሰላም ስምምነት አንቀጽ( 1)መሰረት አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም በማስፈለጉ ነው። የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመጋቢት 9 ቀን 2015 ዓም ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የትግራይ ከልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር ደንብን አፅድቋል።
በዚሁ ደንብ አንቀጽ 3(2) መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸውን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳደር አድርገው ሾመዋል።
ርዕሰ መስተዳደሩ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችን ውክልና የሚያረጋገጥና አካታች የሆነ አስተዳደር በማዋቀር የክልሉን አስፈፃሚ አካል የመምራትና የማስተባበር ሃላፊነት ተጥሎባቸዋል።