የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና ለዳይሬክተሮች ቦርድ ተጠሪ የሆኑ ንዑሳን ኮሚቴዎች ሚና
በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የግል ባንኮች እስካሁን መዋለ ንዋይ በማቅረብ፣ የሀገር ገቢን በማሳደግ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ለባለአክሲዮኖች ትርፍ በማከፋፈል፣ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣትና የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ያደረጉት አበርክቶ የጎላ ነው።
አሁን ላይ “ባንኮቻችን ወዴት እየተጓዙ ይሆን? ባንኮች በችግር ውስጥም ሆነው የማትረፋቸው ምስጢር ምንድን ነው? የባንኮች የትርፍ መጠን ዕድገት ከምን የመነጨ ነው?” የሚሉ ጥያቄዎች እየተጠየቁ ናቸው። ታማሚ የብድር መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት የፍትሕ ሚኒስቴር ባደረገው ጥናት በአንዳንድ ባንኮች ውስጥ ማጭበርበርና ስርቆት መፈጸማቸው ተረጋግጧል። ጥያቄዎቹና ጥናቱ ባንኮቹ መስቀለኛ መንገድ ላይ እንደሆኑ ማሳያ ናቸው።
“ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት” መጽሐፍ ኩባንያ አሰተዳደር ላይ ትኩረት አድርጎ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ባንኮች ስላሉበት ሁኔታና ስለሚጠብቃቸው ፈተና የማንቂያ ጥሪ ደወልን ማስተላለፍ ዓላማው ነው። አንድ ባንክ በማንኛውም ጊዜ ችግር ላይ ሊወድቅ ይችላል። በ2008 እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በዳይሬክተሮች ቦርድ ደካማ ቁጥጥርና ክትትል የነLehman Brothers ባንክ ዓይነት ኪሳራ ዛሬም ቀጥሎ Silicon Valley ፣ Signature ፣ Credit Suisse ፣ እና First Republic የተባሉ ባንኮች በምድረ አሜሪካና አውሮፓ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው።
ነገን በማሰብ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ባለአክሲዮኖች (ግለሰቦችና ተቋማት) ገንዘባቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የግል ባንኮች ኢንቨስት ያደረጉ ሁሉ ስለባንኮቻቸው ጤናማነት በየጊዜው መከታተል አለባቸው። ምንም እንኳን በኢትዮጵያ የከሰረ ባንክ እስካሁን ባይኖርም ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት አስፈላጊ የሆኑ ጥንቃቄዎች ሊወሰዱ ይገባል። ችግሮች ከተከሰቱ ደግሞ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል አቅም ሊኖር ይገባል። የየባንኩ የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና ለዳይሬክተሮች ቦርድ ተጠሪ የሆኑ ንዑሳን ኮሚቴዎች በባንኮቻቸው ውስጥ ቆይቶ የሚፈነዳ ቦምብ አለመኖሩን ማረጋገጥ አለባቸው። ባንክ በዕውቀት መመራት አለበት። ለባንኮች ውጤታማነት የሚያግዙ የማሻሻያ ጽንሰ ሀሳቦችና አዳዲስ አሠራሮች ለውይይትና ለቀጣይ ሥራ በመጽሐፉ ውስጥ ቀርበዋል።
ጸሐፊው ዶ/ር ዓይናለም አባይነህ ማሞ የባንክ ባለአክሲዮን፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባልና ለዳይሬክተሮች ቦርድ ተጠሪ የሆነ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው። ይህ ተግባራዊ ተሞክሮአችው የትንታኔያቸውና የድምዳሜዎቻቸው መነሻ ነው። በሥራ አመራረ የዶክትሬት ዲግሪ እና በአካዎንቲንግና ሥራ አመራር ሳይንስ የማስትሬት ዲግሪ እንግሊዝ ሀገር ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተቀብለዋል። ጎልዲ የሥራ አመራር የማማከር አገልግሎት ኩባንያን አቋቁመው በስልታዊ ዕቅድ፣ በሥራ አመራር፣ በአስተዳደር እና በተቋምና ዐቅም ግ ንባታ ዙሪያ ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ።
ባለአክሲዮኖች ስለውጤታማ ኩባንያ አስተዳደር ለመረዳትና ባንካቸውን በቅርበት በመከታተል ለሀገር ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጾ በማበርከት የነገ ተስፋቸውን እንዲያለመልም መጽሐፉን በብር 500 (አምስት መቶ) ገዝተው እንዲያነቡ ተጋብዘዋል።0911 25 64 88 ላይ በመደወል ወይም [email protected] ላይ መልዕክት በመተው ስለመጽሐፉ አጠቃላይ መረጃማግኘት እንዲሁም መጽሐፉን መግዛትና ስልጠናዎችን መውሰድ ይቻላል።