Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሕገወጥ የሽያጭ መመዝገቢያዎች ሲያስገቡ እንደተያዙ ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሽያጭ መመዝገቢያዎችን ከውጭ እንዲያስገቡ ከተፈቀደላቸው 16 ተቋማት ውጪ፣ በኮንትሮባንድ ወደ አገር ውስጥ ሲያስገቡ የተያዙ ኤምባሲዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት መኖራቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ይህን ያስታወቀው ዓርብ መጋቢት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የሸማቾች መብት ቀንን በማስመልከት ባዘጋጀው የምክክር መርሐ ግብር ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ገለጻ ያደረጉት በገቢዎች ሚኒስቴር የታክስ መረጃና ሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ አስተዳደር ዳይሬክተር ወ/ሮ ራቢያ ይማም እንዳስረዱት፣ መሥፈርቱን አሟልተው የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ እንዲያስገቡ የተፈቀደላቸው 16 ተቋማት ብቻ ናቸው፡፡

ዕውቅና ከተሰጣቸው ውጪ በኮንትሮባንድ የሚያስገቡ ተቋማት መኖራቸውን ገልጸው፣ ከእነዚህም ውስጥ ኤምባሲዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ እንዲሁም የመንግሥት ጥላ ከለላ ይሆናሉ ተብለው የሚታመኑ ድርጅቶች እንደሚኙበት አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ጠፉ ተብለው የተመዘገቡ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎችም ጭምር ሕገወጥ መንገድ ታክስ ለማጭበርበር ሥራ ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል፡፡

በሐሰተኛ ደረሰኝ ለማጭበርበርና አንዳንዶቹ በገቢዎች ሚኒስቴር ዕውቅና ባልተሰጠው የሽያጭ መሣሪያና ሶፍትዌር ደረሰኞች አዘጋጅተው እንደሚቀርቡ ገልጸዋል፡፡

የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት መመዝበር በተለያዩ መንገዶች እንደሚከናወን ያስረዱት ዳይሬክተሯ፣ በተሰረቀ (በጠፋ) የሽያጭ መሣሪያ ጭምር ሲያጭበረብሩ መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፣ በደረሰኝና በተያያዥ ጉዳዮች የሚታዩ ማጭበርበሮች በርካታ ናቸው፡፡ ማኅበረሰቡ ለሚገዛው ዕቃ በትክክለኛው መንገድ ደረሰኝ በማስቆረጥ መንግሥትንና ራሱን ከጥፋት መከላከል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

‹‹ሸማቾች መብታቸውን በማወቅ ያለ ደረሰኝ የሚከናወን የትኛውንም ዓይነት ግዥ እንቢ በማለት በራሳቸውና በመንግሥት ላይ ከሚደርሰው ኢኮኖሚያዊ አሻጥርና ውድቀት መጠበቅ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የማስተዋሉ ዘርፍ ብዙ ችግሮችን ለመቅረፍ በንግድ ውድድርና በሸማቾች ጥበቃ ቁጥጥር 813/2006 አንቀጽ 14 መሠረት የተዘረዘሩ የሸማቾችን መብት በማወቅ መብቱን የሚያስከብር ዜጋ ለመፍጠር ሁሉም ባለድርሻ አካላት መሳተፍ አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል፡፡

ከሸማቾች መብቶች መካከል በደረሰኝ መግዛት ተጠያቂነትን የሚያሰፍንና የምርትን ጥራት ዓይነትና ትክክለኛት የሚያሳይ በመሆኑ፣ ዜጎች መብቶቻቸውን በማወቅ ሊደርስ ከሚችለው የታክስ ማጭበርበር አገርን እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች