የፋይናንስ ተቋማት የአየር ንብረትን መደገፍ ላይ አጠናከረው እንዲሠሩ ለማስቻል፣ በማዕከል ደረጃ ቁጥጥር ለማጠናከርና አቅጣጫ ለመስጠት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ፡፡
ባንኩ ከተለያዩ የልማት አጋሮቹ ጋር በመሆን፣ በተለይም ከዓለም ባንክ ጋር አብረው የአየር ንብረትን በሚመለከት ሥራዎችን እየሠሩ እንደሆነ ለሪፖርተር የገለጹት በብሔራዊ ባንክ፣ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍሬዘር አያሌው ናቸው፡፡
ባፈለው ሐሙስ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. ኤፍኤስዲ ኢትዮጵያ ባዘጋጀው የአየር ንብረትን በፋይናንስ ከመደገፍ ጋር በተያያዘ የምክክር መድረክ ላይ፣ የብሔራዊ ባንክን ዕቅዶችና እንቅስቃሴዎችን ለተሳታፊዎች የገለጹት አቶ ፍሬዘር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባንኮች የአየር ንብረት ላይ የሚሠሩ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ላይ ትልቅ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡
‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደሚታወቀው ከአየር ንብረት መለዋወጥ ጋር በተያያዘ እየመጡ ያሉ ተጋላጭነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ናቸው፡፡ በዚህ መሠረት አንደኛው ተጋላጭ የሚሆነውም የፋይናንስ ዘርፉ ነው፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ፍሬዘር፣ የፋይናንስ ተቋማት ለራሳቸውም ሥራ ሲሉ ሊደግፉ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
የፋይናንስ ተቋማቶች ሚና እንዲያድግ የአቅም ግንባታና ማዕከላዊ የሆነ አቅጣጫ የመስጠት ሥራዎችን ለማሳካት፣ ከአጋር ድርጅቶች ጋር ብሔራዊ ባንክ የሚሠራው ሥራ በቅርቡ ይፋ ይሆናል፡፡ እንደ አገር ከአየር ንብረት ጋር ለተገናኙ ጉዳዮች የሚመጡ ፈንዶች ያሉ ሲሆን፣ እነዚህ ፈንዶች በገንዘብ ሚኒስቴርና በልማት ባንክ በኩል ለፋይናንስ ኢንዱስትሪው እንዲደርስ እየተሠራ መሆኑን አቶ ፍሬዘር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ፈንዶቹን የፋይናንስን ተቋማት ዳግም ከአካባቢና ከልማት ጋር ተስማሚ እንዲሆኑ ማድረግ አለባቸው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተለያዩ ተሳታፊዎች ተገኝተው ሐሳባቸውን ገልጸው የነበረ ሲሆን፣ ከተሳታፊዎች መካከልም የገንዘብ ሚኒስቴርና ብሔራዊ ባንክ በመንግሥት በኩል፣ እንዲሁም በተጨማሪ የተለያዩ የግል ተቋማት ኃላፊዎች በመሆን የፓናል ውይይት አካሂደዋል፡፡
ኤፍኤስዲ መሠረቱ እንግሊዝ የሆነና ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ላይ በተለያዩ የፋይናንስ ዘርፎች የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡ በኢትዮጵያም እ.ኤ.አ. በ2021 ሥራ ከጀመረ ወዲህ የካፒታል ማርኬት ላይ ማማከርን ጨምሮ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ነው፡፡