Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሞባት ሕይወቷ ያለፈ ታዳጊን ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

አስገድዶ መድፈር ወንጀል ተፈጽሞባት ሕይወቷ ያለፈ ታዳጊን ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

ቀን:

ከሳባት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ. በ2016 በ17 ዓመቷ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሲፈጸምባት ሕይወቷ ባለፈው ‹‹ውብአንቺ›› የተባለች ታዳጊን ታሳቢ ያደረገ ፕሮጀክት በ206 ሚሊዮን ብር ይፋ ተደረገ፡፡

ወላጆችና ተንከባካቢ የሌላቸውን ታዳጊዎች አስፈላጊውን ሁሉ በሟሟላት የማኖር፣ የማሳደግና የማስተዳደር ድጋፍ በማቅረብ የሚታወቀውና በሁለት የፈረንሣይ ዜጎች የተቋቋመው ‹‹ብሉ ብላንስ ሮዥ›› የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት፣ ፕሮጀክቱን አስመልክቶ መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

እንደ ድርጅቱ ገለጻ፣ ውብ አንቺ የተባለችው ታዳጊ ባሳዛኝ ሁኔታ ተደፍራም በግፍ ተገድላለች፡፡ እሷን ለማሰብም ‹‹ውብአንቺ›› የተሰኘ ፕሮጀክት የተዘጋጀው እንደ ውብአንቺ በችግር ላይ የወደቁ ታዳጊዎችን በመሰብሰብ ለማገዝ ነው፡፡

ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ የሕፃናት ማሳደጊያዎች በተለያዩ ምክንያቶች ለሚወጡ ታዳጊዎች የቤተሰብ ይዘት ያላቸው ቤቶችን በማዘጋጀት፣ ሁሉ አቀፍ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ወላጅ አልባ ሕፃናትን በማሰባሰብ፣ የቤተሰብ ይዘት ያላቸው ቤቶችን በመገንባት ለመንከባከብ ዓላማ ያደረገ ነው ተብሏል፡፡

“ብለ ብላንስ ሮዥ ፋውንዴሽን” በተባለ የቤተሰብ ይዘት ያላቸው ቤቶችን (ፋሚሊ ሆምስ) ከፍቶ፣ ወላጅና ተንከባካቢ የሌላቸውን ታዳጊዎችን፣ ተፈላጊውን ነገር በሟሟላት የማኖር፣ የማሳደግና የማስተዳደር ድጋፍ በሚያቀርበው የበጎ አድራጎት ድርጅት ይፋ የሆነው የ“ውባንቺ” ፕሮጀክት፣ እ.ኤ.አ. ከ2023 እስከ 2025 ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑ ታውቋል፡፡

የፋውንዴሽኑ የፕሮግራም ኃላፊና የሕግ አማካሪ ለምለም ፀጋዬ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ‹‹ውባንቺ›› የተባለች በአስገድዶ ደፋሪ ምክንያት በግፍ የተገደለች ታዳጊ ሕልፈትን ለማሰብ የተነደፈው ፕሮጀክት፣ በተለይም ከሕፃናት ማሳደጊያ ወጥተው በችግር ላይ የወደቁ ታዳጊዎችን በመሰብሰብ በቤተሰብ መልክ ለማገዝ የተቋቋመ ነው፡፡

በ206 ሚሊዮን ብር ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በቀጥታና ቀጥታ ባልሆነ መንገድ ዕድሜያቸው የደረሰ ታዳጊና ወጣቶች ራሳቸውን ችለው እንዲወጡ ያደርጋል የተባለው ፕሮጀክት፣ በአጠቃላይ 750 ዜጎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል፡፡

ተጠቃሚ ይሆናሉ ከተባሉት ውስጥ 400 ያህሉ ቀጥታ የቤተሰብ ይዘት ያላቸውን ቤቶች በማቋቋም የሚደገፉ መሆናቸውን፣ የተቀሩት ደግሞ ቀጥታ ባልሆነ መንገድ በመንግሥት ተቋማት ሥር የሚገኙ የማሳደጊያ ማዕከላት ታዳጊ ወጣቶች እንደሆኑ ለምለም አስታውቀዋል፡፡

የ“ብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን” የአገር ውስጥ ተወካይ ወ/ሮ ፀደይ ተፈራ የውባንቺ ፕሮጀክት መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል ይፋ ሲደረግ እንዳስታወቁት፣ ፋውንዴሽኑ በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች ከሚዘጉ የሕፃናት ማሳደጊያዎች የሚወጡ ታዳጊ ወጣቶችን ከአደጋ መጠበቅ ዋነኛ ተግባሩ አድርጎ እየሠራ ነው፡፡

በሕፃናት ማሳደጊያ ተቋማት የሚያድጉ ሕፃናት ከማኅበረሰቡ የተነጠሉ ስለሚመስላቸው ወደ ሥራ ሲገቡ በሕይወታቸው ላይ ፈተናዎች እንደሚያጋጥማቸው ያስረዱት ወ/ሮ ፀደይ፣ “ብለ ብሎ ሩዥ ፋውንዴሽን” ታዳጊ ወጣቶችን የቤተሰብ ይዘት ያላቸው ቤቶችን (ፋሚሊ ሆምስ) በማዘጋጀት ትምህርት እንዲማሩና ከማኅበረሰቡ ጋር ሳይነጠሉ እንዲኖሩ የሚያደርግ ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡

ፋውንዴሽኑ በተጨማሪም በመንግሥት ሥር የሚተዳደሩ ማሳደጊያ ተቋማት ውስጥ ለሚኖሩ ታዳጊዎች የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ውጪ ሙሉ የሕክምና፣ የአልባሳትና ሌሎች መሠረታዊ የትምህርትና የሥነ ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ እንደሚያግዝ ተገልጿል፡፡

የሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚነስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት ድጋፍ የሚሹ በርካታ ሕፃናት መኖራቸውን ጠቁመው የዚህ ፕሮጀክት ወደ ሥራ መግባትም ሚናው በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀና የሺጥላ በበኩላቸው፣ ፋውንዴሽኑ በተለያዩ ሁኔታዎች ከቢሯቸው ጋር ሲሠራ መቆየቱን ገልጸው፣ አሁን ደግሞ ወላጅ አልባ የሆኑ ሕፃናትን በመሰብሰብ ለማሳደግ የጀመረው ሥራ ለከተማውም ሆነ ለአገሪቱ ትልቅ ትውልድን የመታደግ ተግባር ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...