በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ የሆኑና ኢኮኖሚውን የሚገዳደሩ ጫናዎችን ለመፍታት፣ የማክሮ ፖሊሲ ሪፎርም እንደሚያስፈልግ የዓለም ባንክ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ተናገሩ፡፡
ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት ምክትል ፕሬዚዳንቷ ቪክቶሪያ ክዋክዋ፣ የፖሊስ ሪፎርም መደረጉ ኢኮኖሚው መልሶ እንዲያገግም በማድረግ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ያሳልጠዋል ብለዋል፡፡
የሚካሄዱ የሪፎርም ሥራዎች የመጨረሻ ትልማቸው ከወዲሁ ዕድገትን ማምጣት መሆን እንዳለበት የገለጹት ሚስ ቪክቶሪያ፣ የአፍሪካ አገሮች ሕዝብ ከሚያሳየው ዕድገት ጋር ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ኢኮኖሚውም እጥፍ ዕድገት ማምጣት እንደለበት ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በፊት የኢትዮጵያን የቴሌኮም ዘርፍ ለግሉ ዘርፍ መክፈትን ጨምሮ በርካታ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰው፣ ነገር ግን የተጀመረው ሥራ ባለማለቁ አሁንም ብዙ የቤት ሥራ እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን መዛነፍ ለማስተካከል እያንዳንዱን ዘርፍ በጥንቃቄ መገምገም ያስፈልጋል፤›› ያሉ ሲሆን፣ ይሁን እንጂ ምንም እንኳን ሪፎርሙ በትክክል መስመር ላይ ቢሆንም፣ ብዙ ለውጥ ለማምጣት በጣም ረዥም ርቀት መጓዝን ይጠይቃል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት የዓለም ባንክ በአጠቃላይ አፍሪካ ላይ የነበረውን የኢኮኖሚ ዕድገት ትንበያ፣ ዓለም አቀፍ ሁኔታውን በመገምገም ከነበረው ትንበያ ዝቅ አድርገናል ያሉ ሲሆን፣ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ያለውን ሀብት ምርታማ እንዳይሆን የሚያደርጉ መሰናክሎችን ማስወገድ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፡፡ የዓለም ባንክ የረዥም ጊዜ ፕሮጀክቶችን በመደገፍ፣ በተለይም ለግብርናው ዘርፍ ማነቆ የሆኑትን ችግሮች ለመፍታት የሚያግዙ ሥራዎች እንደሚሠራ አብራርተዋል፡፡
ግጭት ለቢዝነስና ለኢንቨስትመንት አመቺ አለመሆኑን፣ ነገር ግን በሰሜን ኢትዮጵያ የተጀመረው የሰላም ስምምነት አተገባበር በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ለውጥ ማሳየት እንዳለበትና የግሉ ዘርፍ ለተሻለ ፈጠራ እንዲንቀሳቀስ አሁንም በርካታ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ምክትል ፕሬዚዳንቷ፣ የዓለም ባንክ የሰሜን ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነትን ተከትሎ የሚታዩ ጥረቶች ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከእነዚህ በፊት የነበሩ የልማት ድጋፎች ለታሰበላቸው ዓላማዎች መዋላቸውን ከመንግሥት ጋር ቁጭ ብለው እንደሚገመግሙ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያን የብድር ጫና ላለማባባስ የዓለም ባንክ አሁን አገሪቱ የተሸከመችውን ዕዳ ሊያባብሱ የሚችሉ በትልልቅ ወለድ የሚታሰቡ ብድሮችን እንደማይሰጥ ምክትል ፕሬዚዳንቷ አስታውቀዋል፡፡