የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ሪፎርም በሦስት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ የመጀመሪያው የመቆጣጠር ሥልጣኑን ለማጠናከርና የተሻለ ተቋማዊ ነፃነት ያለው ሆኖ እንዲንቀሳቀስ የሚያደርገው የሕግ ማሻሻያ ሥራ ነው ተብሏል፡፡
ባንኩ እንደ ሌሎቹ የፋይናንስ ዘርፍ ተዋንያን የሰው ሀብቱን የበለጠ ለማሻሻል ‹‹የዲጂታላይዜሽንና ሒዩማን ካፒታል ዴቨሎፕመንት›› ሥራ ሁለተኛው ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ሦስተኛውና መሠረታዊ የተባለው ደግሞ የፖሊሲ ማሻሻያዎች መሆናቸውን፣ የገንዘብ ፖሊሲውንና የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚደረጉ ተጨማሪ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ተጠናቀው በቅርቡ ይፋ እንደሚደረጉ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ መጋቢት 14 ቀን 2015 ዓ.ም የካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል ምሥረታ በይፋ ዕውን በተደረገበት ሥነ ሥርዓት ላይ ተናግረዋል፡፡
አቶ ማሞ እንዳስታወቁት፣ ባንኩ በቅርብ ጊዜ አዲስ የሪፎርም አጀንዳ ለመጀመር ጥረት እያደረገ ነው፡፡ በአጠቃላይ ዝግጅቱ የተጠናቀቀው ሥራ ይፋ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
‹‹የፋይናንስ ዘርፉን በተመለከተ ቁልፍ ግባችን ዘርፉ ጤናማ፣ ተደራሽ፣ ዘመናዊ እንዲሆንና እነዚህን እንደ ቁልፍ ዓላማ ይዘን በተቻለ መጠን የክፍያ ሥርዓቱ ደግሞ ዘመናዊና ዲጂታል እንዲሆን እየሠራን ነው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ከጥሬ ገንዘብ የተላቀቀ ኅብረተሰብ (Cashless Society) የሚለውን ብሔራዊ ባንክ ቁልፍ ግብ አድርጎ ወደፊት አጠናክሮ ከሚሠራባቸው ጉዳዮች ውስጥ እንደሚገኝበት የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የፋይናንስ ዘርፉ በቴክኖሎጂ፣ በአሠራር ሥርዓትና በሰው ኃይል መጠናከር ይኖርበታል ብለዋል፡፡
አብዛኛው ሕዝብ አሁንም ገንዘብ ከባንክ ለማውጣት ወይም ለማስገባት በአካል ወደ ባንክ ቅርንጫፎች እንደሚሄድ፣ ሕዝቡ የባንክ ብድር የማግኘት ዕድሉ አናሳ መሆኑ፣ የሕይወትና የሌሎች ረዥም ጊዜ መድን ሽፋኖች ውስን መሆናቸው፣ የፋይናንስ ገበያው በደንብ የተደራጀና እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሙሉ አቅሙ መደገፍ የሚችል አለመሆኑ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲውን በገበያ ሥርዓት በአግባቡ እንዳይመራ መሰናክል ሆኖበታል ሲሉ አቶ ማሞ አስታውቀዋል፡፡
ይህንን ሁኔታ በመገንዘብ መንግሥት የፋይናንስ ሥርዓቱን ለማዘመንና ለማጠናከር የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፣ በቅርቡ ይፋ የሚደረጉ ተጨማሪ ዕርምጃዎች እንደሚኖሩም ተሰምቷል፡፡
የፋይናንስ ተቋማትን የካፒታል አቅም ለማጠናከር የተከፈለ ካፒታላቸው ከፍ እንዲል መደረጉ፣ የሰው ኃይል አቅማቸው ቀጣይነት እንደሚኖረው፣ እያንዳንዱ የፋይናንስ ተቋም ከዓመታዊ መደበኛ ወጪው ሁለት በመቶ የሚሆነውን ለሥልጠናና ለአቅም ግንባታ እንዲያውል መደረጉ፣ መንግሥት የፋይናንስ ሥርዓቱን ለማዘመንና ለማጠናከር እየወሰዳቸው ካሉ ዕርምጃዎች ተጠቃሾቹ ናቸው ተብሏል፡፡
‹‹የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሻሻል እ.ኤ.አ. በ2025 ላይ 70 በመቶ ኢትዮጵያውያን አገልግሎቱን እንዲያገኙ ለማድረግ ግብ ተይዞና ስትራቴጂ ተቀርፆ እየተተገበረ ይገኛል፤›› ያሉት አቶ ማሞ፣ የክፍያ ሥርዓቱን ዲጂታልና ተደራሽ ለማድረግ ከዚህ በፊት በሥራ ላይ የነበረው አዋጅ እንዲሻሻል መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
ከባንክ ውጪ የሆኑ የቴሌኮሙዩኒኬሽን ኩባንያዎች፣ ፊንቴክ፣ የክፍያ ኤጀንቶችና የመሳሰሉት ተቋማት በክፍያ አገልግሎቶች ዘርፉ እንዲሳተፉ መደረጉ ተጠቅሷል፡፡ የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢ ሆኖ በቅርቡ ሥራ ለጀመረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ ብሔራዊ ባንክ የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ፈቃድ እንደሚሰጥ የባንኩ ገዥ አስታውቀዋል፡፡
በተጨማሪም የካፒታል ገበያ ለማቋቋምና ለመቆጣጠር አስቻይ ሁኔታ መፈጠሩን፣ የካፒታል ገበያ አስተዳደር ባለሥልጣን ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩን፣ ገበያውን ለማስጀመር የሚያስፈልጉ ደንቦችና መመርያዎች እየተዘጋጁ እንደሆነ፣ በተጨማሪ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ የፖሊሲ አቅጣጫ ተቀምጦ የሕግ ሥርዓቱ በአሁኑ ጊዜ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
የፋይናንስ ዘርፉ በቴክኖሎጂ፣ በአሠራርና በሰው ኃይል መጠናከር ቢኖርበትም ከዘመኑ ጋር የዋጀና የላቀ ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት በአገሪቱ አሁንም ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የተጠናከረ፣ የተደራጀ፣ በዘርፉ ዕድገት ላይ የሚያተኩር የምርምር፣ የማማከርና የሥልጠና ተቋም መኖር ወሳኝ መሆኑ የካፒታል የፋይናንስ ልህቀት ማዕከል የተሰኘ በፋይናንስ ተቋማት ባለቤትነት የተቋቋመው አዲስ ድርጀት ይፋ በተደረበት ወቅት ተጠቁሟል፡፡