Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

ቀን:

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል››

ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የፌዴራል መንግሥትና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)፣ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ያደረጉት ስምምነት አፈጻጸም ላይ ግልጽ መረጃ እንደሌላቸው ተናገሩ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የምክር ቤቱ አባላት ይህንን የተገናሩት መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው የስድስተኛው ዙር ሁለተኛ ዓመት አንደኛ ልዩ ስብሰባ፣ ከሁለት ዓመት በፊት በምክር ቤቱ በአሸባሪነት ተሰይሞ የነበረውን ሕወሓት ከአሸባሪነት መዝገብ ለመሰረዝ የቀረበ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡  

በዚሁ ልዩ ስብሰባ በፕሪቶሪያ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረት ሕወሓት በሽብርተኝነት እንዲሰየም ካደረጉት ተግባራትና እንቅስቃሴዎች ሁሉ ለመታቀብና በአጠቃላይ ወደ ሕጋዊ አግባብ ሥርዓት ለመመለስ የተስማማ በመሆኑና በአጠቃላይ የሽብር ተግባራትን ስላቆመ፣ የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በወጣው አዋጅ ቁጥር 1176/12 አንቀጽ 24 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት የሽብርተኝነት ስያሜውን ለማሰረዝ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ ቤልጂጌ ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

በፕሪቶሪያ በተደረገው የሰላም ስምምነት የሕወሓት ኢሕገ መንግሥታዊ አካሄዶች መቀልበሳቸውን፣ በፖለቲካ ባህሉም ቢሆን በኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የቆየው የፖለቲካ ባህል የአሸናፊና የተሸናፊ፣ የመጠፋፋት፣ እንዲሁም አብሮ የመሥራት ልምምድ የሌለበት እጅግ ኋላቀር በመሆኑ፣ ይህንን ለመቀየር በሚያግዝ መንገድ ለአንድ አገር የትኛውም ዓይነት የፖለቲካ ልዩነት ቢኖር በውይይትና በንግግር ለመፍታት የሚያስችል ተጨማሪ ልምድ የተገኘበት የሰላም ስምምነት ስለመሆኑ አቶ ተስፋዬ አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ የአቶ ተስፋዬን ማብራሪያ ተከትሎ ከፓርላማ አባላቱ በርካታ ዓይነት ጥያቄዎች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ ለሦስት ሰዓት ያህል በቆየው ዝግ ስብሰባ በርካታ የተቃውሞና የድጋፍ ሐሳቦች ተነስተውበታል፡፡

ወ/ሮ ቅድስት አርዓያ የተባሉ የብልፅግና ፓርቲ የፓርላማ አባል በሰጡት አስተያየት፣ ከአጠቃላይ የስምምነቱ አፈጻጸም መካከል አንዱ መሣሪያ ማስረከብ መሆኑን አስታውሰው ‹‹አፈጻጸሙ እንደ አንድ የምክር ቤት አባልና እንደ አንድ ሕግ አውጪ አካል፣ እጄን አውጥቼ እንደምወስን አካል፣ ማንኛውም ሕዝብ ቢጠይቀኝ መልስ የለኝም፣ በቂ መረጃ አልተሰጠኝም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ቅድስት አክለውም በሕወሓት ወራራ የተያዙ አካባቢዎች አለመለቀቃቸውን፣ የሽብርተኝነት ስያሜውን ለማንሳት ጊዜው አለመሆኑንና ቆም ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

የትግራይ ክልል ሕዝብ የሕወሓት አመራሮች በድጋሚ እንዳይመጡብን እያለ ስለመሆኑ አብራርተው፣ በተጀመረው የጊዜያዊ አስተዳደር አደረጃጀት የሕወሓት የበላይ አመራሮች ለሥልጣን ሽሚያ እርስ በርሳቸው ግጭት ውስጥ መግባታቸውንም አክለዋል፡፡

‹‹እነሱ የሞተውን እንኳ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ እኔ ለምን የታሪክ ተጠያቂ እሆናለሁ? ለምን የህሊና ተጠያቂ እሆናለሁ? እዚህ የምክር ቤት አባልነት ደረጃ እስክደርስ ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና ትምህርት ቤቶች የቀረፁብኝ ሰብዕና አለ፡፡ ስለሆነም እኛ ሕፃን አይደለንም ትልቅ ሰው ነን፡፡ መወሰንና መነጋገር እንጂ እዚህ ለድጋፍ፣ ለተዓቅቦ ወይም ለተቃውሞ ሳይሆን ከዚያ አለፍ ብለን ሕዝብና አገርን ማሰብ አለብን፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

አክለውም፣ ‹‹ሕወሓት ይቅርታ ሳይጠይቅና ስምምነቱን በሚገባ ሳያከብር ከዚህ የሽብር ስያሜ ተነሳ ማለት፣ ለሌሎች ጥጋበኛ ኃይሎች የልብ ልብ የሚሰጥ መሆኑን ያወሱት ወ/ሮ ቅድስት፣ ‹‹ስለዚህ አሁን ይህን ስያሜ የምናነሳበት ጊዜ አይደለም፤›› ሲሉ አጠንክረው ገልጸዋል፡፡

ይቅርታ ማድረግ ትልቅ ነገር መሆኑን የተናገሩት ወ/ሮ ቅድስት፣ ‹‹ሥርዓትና ሕግ መከበር አለበት፣ ዕድርና ዕቁብ ሳይቀሩ ሥርዓትና ሕግ አላቸው፤›› ብለው፣ በእያንዳንዱ ስምምነት ላይ የተወሰደውን ዕርምጃ በኃላፊነት መግለጽ ሳይቻል፣ ሕወሓትን ከአሸባሪነት መዝገብ ለመሰረዝ የቀረበው ውሳኔ ሐሳብ መፅደቅ የለበትም ሲሉ አክለዋል፡፡

የጌዴኦ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ጌሕዴድ) ተወካይ አቶ አለሳ መንገሻ በበኩላቸው፣ ምክር ቤቱ የጠራውን ስብሰባ ለመሳተፍ እንደ ተጠሩ እንጂ አጀንዳው ምን እንደሆነ እንዳልተገነራቸው አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የምክር ቤት አባሉ አብርሃም በርታ (ዶ/ር)፣ ‹‹በመንግሥት በኩል የቀረበው ሕወሓት ከሽብርተኝነት ድርጊቱ ተቆጥቧል ተብሎ የቀረበው ምን ማስረጃ ተገኝቶ ነው? በይፋ ያገኛችሁት ማስረጃ ምንድነው፤›› በማለት ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡

አብርሃም (ዶ/ር) አክለውም፣ ሕወሓት ባለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለፈጸመው በደል ይቅርታ ሊጠይቅ እንደሚገባ፣ አሁንም የሰላም ስምምነት ከተደረገ ወዲህ የታጠቀውን መሣሪያ እንዲፈታ፣ እንዲሁም አዲስ ታጣቂዎችን እያሠለጠነ መሆኑንና ሕወሓት ከሽብርተኝነት ስያሜ መሠረዝ ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ ከሕወሓት ጋር ያለውን ‹‹ጉንጭ መሳሳም›› በማቆምና ባለፉት 27 ዓመታት ሕወሓት የሄደበትን መንግሥታዊ ሥርዓት በመተው አዲስ አሠራር በመዘርጋት፣ የአገርን ሰላም እንዲረጋገጥ የዜጎች መፈናቀልና መሞት የሚቆምበት ሁኔታ መፈጠር አለበት ብለዋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አባልና የምክር ቤት አባል ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) የሰላም ስምምነቱን የፌዴራል መንግሥቱ ከሞላ ጎደል በሆደ ሰፊነት እየፈጸመ ቢሆንም፣ በሕወሓት በኩል የሰላም ስምምነቱን አየፈጸመ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

 በመሆኑም በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሕወሓት ትጥቁን እንደሚፈታ፣ ተዋጊዎቹን ወደ ማኅበረሰቡ ለመቀላቀል በተዘጋጀው የተሃድሶ ፕሮግራም ያልፋሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ነገሩ ‹‹ስላቅ›› ካልሆነ በስተቀር አንድም ነገር ተፈጽሟል በሚያስብል ደረጃ አይደለም ያለው ብለዋል፡፡

ደሳለኝ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) በምክር ቤቱ በተካሄደ ዝግ ስብሰባ የሕወሓትን የትጥቅ ማስፈታት አስመልክተው፣ ‹‹ሕወሓት ያን ያህል ሊፈታው የሚችለው መሣሪያ እንደሌለውና ለሞራል ያህል ትጥቅ እንዲፈታ እንጂ፤›› በሚል ያደረጉትን ንግግር፣ ‹‹ለእኔ ከዚህ የበለጠ ስላቅ የለም፤›› ብለውታል፡፡

ሕወሓት አሁንም የወታደር ምልመላና ሥልጠና እያካሄድ እንደሆነ ገልጸው፣ ድንበር አካባቢ ያለው ሕዝብ ሥጋቱ እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡ በዚህ ሒደት ላይ ሆኖ ሕወሓትን ከሽብርተኝነት ማንሳት ዘላቂ ሰላም እንደማያመጣና መንግሥት ሕወሓት አራተኛ ዙር ወረራ እንደማያካሂድ ማስተማመኛ ይሰጣል ወይ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ የሽብርተኝነት ስያሜው መነሳት ስምምነቱ ላይ ያሉ ነገሮች ሁሉ እንዳሉ ተተግብረው አብቅተው ማብቂያው ወይም ማሳረጊያው ላይ ሳይሆን፣ ሌሎች ግዴታዎች እየተተገበሩ አብሮ በሒደት መፈጸም ያለበት ነገር ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የተነሳ የሰላም ስምምነቱ ዘላቂና ውጤታማ እንዲሆን ፍረጃውን ማንሳት አስፈላጊ መሆኑን፣ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲመለስ በአካባቢው ያሉ ዜጎች ሰላም እንዲያገኙ፣ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት መመለስ እንዲችሉ፣ ሕሙማን ሕክምና ማግኘት እንዲችሉና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለክልሉ ያፀደቀው የድጎማ በጀት መተላለፍ እንዲችል የሸብርተኝነት ስያሜውን ማንሳት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ምጣዱ እንዲተርፍ አይጧ ማለፍ አለባት፡፡ ምጣዱ የትግራይ ሕዝባችንን ጨምሮ ነው፡፡ በአዕምሯችን የኢትዮጵያ ሕዝብ ስንል የትግራይን ሕዝብ ትተን ከሆነ፣ ካርታው ውስጥ ያሉ ሰዎችን ረስተን ከሆነ የምንናገረው፣ አይጡን ለመምታት ምጣዱን በደንብ መስበር ይኖርብናል፤›› ያሉት ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) ናቸው፡፡

የትግራይ ሕዝብ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መወከል አለበት ብሎ ፓርላማው የሚያምን ከሆነ፣ የትግራይ ሕዝብ ሰላም ያስፈልገዋል ያሉት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ሕዝቡ በወቅቱ በነበረው ትርክት፣ ልትበላ ነው፣ ልትፈርስ ነው፣ አደጋ ሊመጣብህ ነው፣ ተብሎ እንደተነገረው አስረድተዋል፡፡ ‹‹በነገራችን ላይ ከትንሽነት አባዜ የሚመነጭ ከፋፍሎ የመግዛት ፍላጎትም ሆነ፣ መለኪያው እኔ ነኝ ከሚል ትልቅነት አባዜ የሚመነጭ ጨፍልቆ የመግዛት ፍላጎት ሁሉም ከተለያዩ መነሻዎች የሚነሱ ድምዳሜዎች እኩል ጥፋት ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አንዳንዴ የሚሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ የሚባለው እውነታ ነው የሚሆነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹የሕወሓትን ከፋፍሎ መግዛት የሚፈራውን ያህል፣ ብዙ ሰው አንተ እኔን ካልመሰልክ እኔን አታክልም የሚለውን የጭፍለቃ ሐሳብ እኩል እንደሚያሠጋው መወሰድ ጠቃሚ ነው፤›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡

መሣሪያ ማስፈታትን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ ‹‹ይህ ለትግራይ ብቻ የሚሠራ አይመስለኝም፡፡ እንደ እኔ እምነት ከሆነ ከመከላከያ ሠራዊት ውጪ ከባድ መሣሪያ፣ እንዲሁም በየክልሉ ካለው የተፈቀደለት ፖሊስ ውጪ ሌላ ሰው አንካሴ እንኳ ይዞ ባይንቀሳቀስ ኢትዮጵያ ሰላም ትሆናለች፤›› ብለዋል፡፡

 መሣሪያ በገፍ የፈሰሰው ትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ እንዳልሆነ ገልጸው፣ በሕግ መሣሪያ እንዲይዝ የተፈቀደለትም ያልተፈቀደለትም ያለው ክልል ትግራይ ብቻ አይደለም በማለት አብራርተዋል፡፡

 ስለዚህ በእያንዳንዱ ክልል ያልተገባ መሣሪያ ተሰብስቦ ወደ የሚመለከተው ተቋም ገብቶ ዜጎች መዶሻና ማረሻ ይዘው እንዲሄዱ ማድረግ ቢቻል፣ በየሠፈሩ ያለውን ቁርቋሶ መልክ ለማስያዝዝ እንደሚቻል አስታውቀዋል፡፡

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዞኛው መልክ ይዘዋል፤›› ያሉት ሬድዋን (አምባሳደር)፣ ‹‹ሕወሓት ላይ ያለን ጥላቻ ግን እንደ ራሳችን እምነትና ፍላጎት የሚለያይ ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

ሕወሓቶች ለጊዜያዊ አስተዳደር ለሹሙት ያቀረቡትን ሰው አይቻልም ተብለው እንዲቀየሩ መደረጉን፣ ነገር ግን አማራጭ አምጥተው ይኼኛውስ ይሆናል ወይ በማለት ለማቅረብ ስለመገደዳቸው ገልጸዋል፡፡

ምክር ቤቱ ሕወሓትን ከሽብርተኝነት ስያሜ ለመሰረዝ በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ ተወያይቶ በመጨረሻም በ61 ተቃውሞ፣ በአምስት ድምፀ ተዓቅቦና በአብለጫ ድምፅ አፅድቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...