Wednesday, October 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

ይኼ ጊዜ እንዴት ይነጉዳል እባካችሁ? አምስት ዓመታት አምስት ቀናት ይመስሉ እንደ ዋዛ አልፈው እዚህ ብንደርስም፣ ያለፉት አምስት ዓመታት ግን ከሚገባን በላይ አሳራችንን ያሳዩን እንደነበሩ ነጋሪ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄ የቋጠራት ስንኝ አትረሳኝም፡፡ እሱ በዚያ የአፍላ ጉርምስና ጊዜው ምን ልቡን እንዳበራለት ባላውቅም፣ ያቺ ታሪካዊ ግጥም ግን ዛሬም በህሊናዬ ውስጥ ትመላለሳለች፡፡

“የየዘመን ረመጥ በነደደ ቁጥር፣

ለጣደን ስንጣድ ጉልቻ ስንቆጥር፣

ጉደኛ ነፍሳችን አትበስል አትከስል፣

ትገላበጣለች ጢቢኛ ይመስል፤”

ይህችን ግጥም የህሊናዬ ማኅደር ውስጥ አስቀምጬ ያለፍንባቸውን የመከራ ዓመታት ሳስብ፣ አንዳንዴ ሳላውቀው ባክኖ የቀረው ልጅነቴና ወጣትነቴ ትዝ እያለኝ ያስቆዝመኛል፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣናቸው በወታደራዊ ኃይል ሲገለበጡ ገና አሥር ዓመቴ ነበር፡፡ ነገር ግን ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ታላላቅ ባለሥልጣናት ጀምሮ የቀይና የነጭ ሽብር ዕልቂትና የ17 ዓመታት ጦርነት በእኔ ሕይወት ውስጥ መራራ ትዝታ አላቸው፡፡ ከቅርብ ቤተሰብ አባል እስከ ዘመዶች፣ በቅርበት ከምናውቃቸው ጎረቤቶቻችን እስከ ሠፈራችንና ራቅ ያሉ አካባቢዎች በወገኖቻችን ሞት፣ እስራት፣ ስደትና ሥቃይ ድረስ ከልጅነቴ እስከ ወጣትነቴ ያየሁዋቸው ሰቆቃዎች ናቸው፡፡

“እንዳያልፉት የለም ያ ሁሉ ታለፈ…” እያለ ደርግን እየተራገመ የራሱን ብፁዕነት እየሰበከ መላ አገሪቱን የተቆጣጠረው ሕወሓት መራሹ ኢሕአዴግ፣ አዲስ አበባ ከተማ ከረገጠ ጀምሮ ለ27 ዓመታት ያላሳየን ዓይነት ሰቆቃ የለም፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ጊዜ ቦምብ እየፈነዳ የሚበታትናት ቋንቋን መሠረት ያደረገውን የብሔር ፌዴራሊዝም ከመጫን አንስቶ፣ ሁሉንም የፖለቲካና የኢኮኖሚ አውታሮች በመቆጣጠር ምን ዓይነት አግላይ ሥርዓት እንደፈጠረ ማንም አይዘነጋውም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ሁሉን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ተቀብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ግለሰባዊ መብቶችን በመደፍጠጥ በብሔር ብሔረሰቦች ስም ያደረሰው ጥፋት አሁንም መከራችንን እያበላን ነው፡፡ በዚህ ላይ ግድያው፣ እስራቱ፣ ማሰቃየቱ፣ አፈናውና ቅጥ ያጣው ዘረፋ ኢትዮጵያን አንገት ያስደፋ ነበረ፡፡

ይህ ሁሉ ግፍ ያንገሸገሻቸው ኢትዮጵያውያን በቃን ብለው በየአቅጣጫው በሥርዓቱ ላይ በተቃውሞ ሲነሱ፣ በሠራዊቱና በአፋኝ የደኅንነት መዋቅሩ ይመካ የነበረው ሕወሓት መብረክረክ ጀመረ፡፡ ለ27 ዓመታት ያህል በአገር ወዳድ ዜጎች በርካታ ምክሮችና ተማፅኖዎች ቢቀርቡለትም ለመስማት ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ከራሱ ከኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችና አጋሮች ውስጥ ያደፈጡ ኃይሎች ሕዝባዊውን እንቢተኝነት በመቀላቀል ሕወሓት ሳይወድ በግድ እውነታውን ለመቀበል ተገደደ፡፡ ከዚያ በፊት ግን ዓይኑ ተጋርዶ፣ ጆሮው ደንቁሮ፣ ልቡና አዕምሮው ተዳፍኖ የነበረው ሕወሓት ሕዝባዊውን ማዕበል መቋቋም ተስኖት የበላይነቱን ያፀናበት መንበሩን ማስረከብ ግድ ሆነበት፡፡

ትዝ ይላችሁ እንደሆነ የብአዴን መሪ አቶ ደመቀ መኮንን፣ የሕወሓት መሪ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ የኦሕዴድ መሪ አቶ ለማ መገርሳ፣ እንዲሁም የደኢሕዴን መሪ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለበርካታ ቀናት በር ዘግተው “ከሰማይ በታች ያልተወያየንበት ነገር የለም” በማለት ድርጅታቸው ኢሕአዴግ ለቁርጠኛ ተሃድሶ መዘጋጀቱን ቢያስታውቁም ረፍዶ ስለነበር ሰሚ አላገኙም፡፡ ይልቁንም ሕዝባዊ እንቢተኝነቱ በየአቅጣጫው በመጋጋሉ የወቅቱ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ድንገት በቴሌቪዥን ብቅ ብለው “ጫማዬን ሰቅያለሁ” አሉ፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ያልተለመደ ውሳኔ ቢሆንም፣ ብዙዎች በእሳቸው “በቃኝ” ማለት አልደነገጡም፣ አልተገረሙምም፡፡ ይልቁንም እየመጣ ላለው ለውጥ እንደ “መንገድ ጠራጊ” ነበር የታዩት፡፡

ሕወሓት 35 ቀናት ያህል መቀሌ በር ዘግታ ህልውናዋን ለማስቀጠል የቻለችውን ሁሉ ለማድረግ ብትፍጨረጨርም፣ ነገሮች እየፈጠኑና ከቁጥጥሯ ውጪ በመሆናቸው ሳትወድ በግድ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ተጠርቶ አዲስ ሊቀመንበር ለመምረጥ ተወሰነ፡፡ ሕወሓት ይህንን አጋጣሚ ለራሷ ለመጠቀም ብሔራዊ ምክር ቤቱ ስብሰባ በተቀመጠባቸው 11 ቀናት፣ በውጭም በአገር ውስጥም በተሰማሩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አጫፋሪዎቿ ግራ የሚያጋቡ መግለጫዎች በመልቀቅ ማወናበዷን በስፋት ተያያዘችው፡፡

በወቅቱ በፌስቡክ ላይ የነበረው የሐሰተኛ መረጃ ብዛት ብዙዎችን ተስፋ ሲያስቆርጥ፣ ከብሔራዊ ምክር ቤቱ ስብሰባ በምንጮቻቸው አማካይነት የተጣራ መረጃ ያላቸው ደግሞ ተስፋ መቁረጡን ለማስወገድ ሲፋለጡ ኢትዮጵያውያን አናት ላይ ያንዣበበው የጥፋት ደመና ሥጋት አይረሳም፡፡ እነዚያ 11 ቀናት የ11 ዓመታት ያህል ጊዜ የረዘሙ ይመስል ፍራቻው እንዲህ በቀላሉ የሚገልጹት አልነበረም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሕወሓት ሥልጣኗን ካጣች አገር ከማፍረስ አትመለስም የሚለው የብዙዎች እምነት ነበር፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ሕወሓትና አጫፋሪዎቿ ኢትዮጵያን ያለ ምንም ተቀናቃኝ ቢያንስ ለ50 ዓመታት ቀጥቅጠው ለመግዛት እንደሚችሉ ስለሚፎክሩ ነበር፡፡ ያ ካልሆነ ግን ከማፍረስ እንደማይመለሱ በግልጽ የሚዝቱ ነበሩ፡፡

ያም ሆኖ ግን የኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ፍፃሜውን መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሚጠናቀቅ ይፋ ሲደረግ፣ በለውጥ ፈላጊውና በሕወሓት ተቸንካሪዎች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ተፈጠረ፡፡ መጋቢት 18 ቀን ከማለዳ ጀምሮ እስከ አመሻሽ ድረስ የነበረው ስሜት ከሚገልጹት በላይ አስፈሪ ነበር፡፡ ምሽቱ እየገፋ የሁለት ሰዓት ዜና ቢጠበቅ ምንም ፍንጭ አልነበረም፡፡ ፍራቻው በአደገኛ ሥጋቶች ተከቦ ሦስት፣ አራት፣ አምስት ሰዓት ቢደረስም ከጠብቁ ውጪ መልስ አልነበረም፡፡ አምስት ሰዓት ተኩል እያለፈ እያለ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ (ኢቢሲ) ”ሰበር ዜና” ጠብቁ አለ፡፡ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት እየሆነ ሳለ እውነትም “ሰበር ዜና”ው የጭንቁን ሰዓት ፍፃሜ አበሰረ፡፡ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተባሉ የወቅቱ የኦሕዴድ ሰው ሊቀመንበር ሆነው ኢሕአዴግን ለመምራት ማሸነፋቸው ይፋ ሆነ፡፡

መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ላይ በከፍተኛ ድምፅ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር መሆናቸው የተነገረላቸው ዓብይ (ዶ/ር)፣ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓርላማ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሲሰየሙ ባደረጉት ንግግር መላው ሕዝብ ሊባል በሚችል ሁኔታ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የሚመስል ድጋፍ አግኝተው መንበረ ሥልጣኑን ተቆናጠጡ፡፡ እጅግ አስደሳች የነበረ የነፃነት ስሜት በታየበት በዚያ ወቅት ወጣቱ መሪ ከውዳሴ እስከ የዓለም ሰላም ኖቤል ሽልማት ድረስ ተንበሸበሹ፡፡ ይሁንና እያደር ግጭቱ፣ ጦርነቱ፣ ጥላቻው፣ ሞቱ፣ መፈናቀሉና አገር ሊያፈርስ የሚችሉ በርካታ መከራዎች በዚህች አገር ላይ እንደ መዓት ወረዱ፡፡ ብዙ ችግሮችን ብዙዎቻችሁ ታውቃላችሁና ብዙ አልልም፡፡ ነገር ግን ለውጡ ሐዲዱን ስቶ ብዙዎችን እያራቀ ለሌላ ዙር ጥፋት እየተዘጋጀን ስለሆንን፣ ቢያንስ ካለፉት የታሪክ ስህተቶች በመማር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ አቅጣጫውን የሳተው ብልፅግና ፓርቲ ከጥፋታቸው ይማሩ፡፡ “ከታሪክ የማይማር የታሪክ ማስተማሪያ” ይሆናል እንዲሉ፣ ኢትዮጵያን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት የሁሉም ዜጎች ትብብር ይጠየቅ፡፡ የጽንፈኛ ብሔርተኝነት ፖለቲካ ከልማቱ ይልቅ ጥፋቱ የከፋ ነውና፡፡

(ታመነ ስሜ፣ ከወይራ ሠፈር)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...