Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትዛሬም የአፍሪካ ኩራት እየሆንን ነው?

ዛሬም የአፍሪካ ኩራት እየሆንን ነው?

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ሀ) ከባንዲራዎችና ከመዝሙሮች ጋር የተያያዙ ውዝግቦች በአዲስ አበባ ተከስተው በነበሩበት ሰሞን በ‹‹ዩቲዩብ›› መድረክ የሚቀርብ አንድ የኢትዮጵያ ነክ ዝግጅት የአንድ አፍሪካዊ ወንድማችንን ትችት አጋርቶን ነበር፡፡ አፍሪካዊ ወንድማችን ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኩራትነትና የነፃነት ችቦነት ያዋጣችውን የታሪክ ድርሻ ተመርኩዞ የዛሬዋን ኢትዮጵያን ሲያስተውል፣ የሚሆነው ነገር ከታሪካዊ ሞገሷ ጋር አልግባባ ብሎት ሁለት እንደ ምላጭ የሚቀረድዱ ትችቶችን ይወረውራል፡፡ አንደኛው፣ ኢትዮጵያውያን በዓመት አንዴ የብሔር ብሔረሰቦችን ቀን ያከብሩና ሌላውን የዓመት ጊዜ በመራኮት ያሳልፋሉ የሚል መሳይ ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ የሚያፍርበት ሳይሆን የሚኮራበት መሆኑን ለእኛው መልሶ የሚያስታውስ ነበር፡፡ እነዚህ ሁለት ትችቶች አዕምሮዬ ውስጥ ከገቡ አንስቶ ለአንዴም ተዘንግተውኝ አያውቁም፡፡

የውስጥ እንቆቅልሾቻችንን ፈትተን ድፍን አፍሪካ ካሞገሰው ታሪካችን ጋር በአግባቡ የምንግባበትን ቀን እየናፈቅሁ ስብሰለሰል ሳለሁ፣ ጥር 10 ቀን 2015 ዓ.ም. መሰለኝ በአርትስ ቴሌቪዥን ‹‹ሀበጋር›› የክርክር መድረክ ዝግጅት ላይ፣ ‹‹ያለው መንግሥት አምባገነን የመሆን ዕድል አለው? ወይስ የለውም?›› የሚል ክርክር አጋጠመኝ፡፡ ተከራካሪዎቹ ‹‹የተማሩ›› ወጣቶች (አንደኛው ጋዜጠኛ፣ ሌላው የፖለቲካ ሳይንስ ምሩቅ፣ ወደ ዶክትርና ትምህርት እያመራ ያለ) ነበሩ፡፡ የሁለቱም ክርክር በአያሌው ገለባ ለገለባ ነበር ብል ነገር አጋንኜ አይደለም፡፡ አንደኛው ጨለምተኛ ኮናኝ ከመሆን ያልራቀ ሲሆን፣ ሌላው ደግሞ የመንግሥት የፕሮፓጋንዳ አፍ ከመሆን ያልተሻለ ነበር፡፡ የሁለቱም ሰዎች ክርክር ጠንካራ እቅጮችና መከራከሪያዎች በማቅረብ ረገድ የደኸየ ነበር፡፡ እቅጭ መረጃዎችንና ምክንያታዊነትን ተመርኩዞ መከራከር ምን ማለት እንደሆነ ለወጣቱ ትውልድ መማሪያ ምሳሌ ለመሆንም ክርክራቸው አልበቃም፡፡ አምባገነንነትን በመጥራት/በማዋለድም ሆነ ሥልጣን ላይ ያለ የመንግሥትን ቁንጮ ወደ አምባገነንነት በመቀየር ሒደት ውስጥ የታጠቀው የመንግሥት አውታር ሥሪት፣ ኅብረተሰብና ያሉበት የፖለቲካ አዙሪት ትልቅ ሚና እንዳላቸው ያጤነ ዕይታ ከአንዳቸውም ዘንድ አልፈነጠቀም፡፡

- Advertisement -

የግብፁን አልሲሲ ጎትጉቶ እያበረታታና እየመረቀ ወንበር ላይ ያስቀመጠው፣ ከመገተር አልፎ እየተዝረከረከ የነበረው የግብፅ የፖለቲካ ኢኮኖሚ አዙሪት እንደነበር ወጣቶቹ ስለማውቃቸው እጠራጠራለሁ፡፡ ቢያውቁ ኖሮ እኛ ዘንድ ያለው መንግሥት ወደ አምባገነንነት የመለወጥ ያለመለወጡ ነገር ከጋዜጠኛውም፣ ከምሁራኑም፣ ከፖለቲከኛውም፣ ከብሶተኛውም ሚና ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ ቅንጣት እንኳ ሲናገሩ በሰማን ነበር፡፡ በግብፅ ዓይኑን ገልጦ እውነታን ማጤን የተሳነው መሐመድ ሙርሲ ለዴሞክራሲ ግንባታ ተስፋ መሆን አልቻለም፡፡ የግብፅ እንቅስቃሴ ባለበት ከመገተርም ወደኋላ መንሸራተት ውስጥ ገባ፡፡ በዚህ ምክንያት የሕዝብ ድጋፍ የሸሸው ሙርሲ ሌሎች ጣጣዎችም መጡበት፡፡ የሽብር እንቅስቃሴ መስፋፋት ለአገሪቱ ሰላም ሥጋት ሆነ፡፡ በሰላም ሥጋት የታገዘው የግብፅ ኢኮኖሚያዊ ኑሮ በተለይ ከቱሪዝም ጋር የተያያዘ ትርታው ክፉኛ ተጎሳቆለ፡፡ ኑሮ ውድነትና ሥራ ማጣት ግብፅን አርመጠመጣት፡፡ መሐመድ ሙርሲ ለዚህ ሁሉ ችግር የመፍትሔ ተስፋ አልሆነም፡፡ ሕዝብ በሙርሲ ተስፋ ቆርጦ ሌላ የመፍትሔ ተስፋ ለማግኘት ቃበዘ፡፡ ይህንን ቃባዥ የፖለቲካ ንፋስ ያነበበውና የገዥነት ታሪክ ያለው ወታደራዊ ኃይል ተላወሰ፡፡ የፖለቲካ አየር ማንበብ የተሳነው ሙርሲ ከሕዝብም ጋር መሆን አልቻለም፡፡ ከወታደሩም ጋር ተሻርኮ ሥልጣን ላይ መቆየትን አልቻለበትም፡፡ እናም እሱ በጀብደኛ ነገረ ሥራው፣ ሕዝቡ ደግሞ ከአዙሪት የሚያወጣ ሌላ አማራጭ በማግኘት ተማፅኖው አንድ ላይ ተጋግዘው ጄኔራል አልሲሲን ተሸከሙና የግብፅ መንበረ ሥልጣን ላይ አወጡት፡፡

የኢትዮጵያ እውነታ ግብፅ ውስጥ ከሆነው ነገር በጣም የተለየ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ፣ ጣጣዎች እየተጎለጎሉበት የተቸገረ መንግሥት ወደ አምባገነንነት ለመሄድ መሣሪያ የሚያደርገው ወይም ከራሱ ከወታደሩ የአምባገነን መሪ ለማውጣት የሚስማማ የወታደራዊ ኃይል ባህርይ የለም፡፡ ለዚህ ዓይነት እንቅስቃሴ ምቹ የነበረው ወታደራዊ መዋቅር በሰሜን ዕዝና በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ተካሂዶ በነበር ደም ያፋሰለ ሸፍጥ ተንኮታኩቷል፡፡ አሁን ያለው ሠራዊት አገርን በማትረፍ ትግል ሒደት፣ በኢትዮጵያ ፍቅርና ለሙያ በመታመን የታነፀና እየታነፀ ያለ ሠራዊት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ያለው ዋና ቅራኔ በኢትዮጵያ የህልውና ትግልና የጥፋት ኃይሎች መካከል ነው፡፡ ጨለምተኞቹ ኃይሎች እርስ በርስ ዓይንህ ለአፈር የተባባሉት ጭምር፣ የአንድ ውጤት (የብተና፣ የሥርዓተ አልባነትና የመተላለቅ) ግብረ አበሮች ናቸው፡፡ ትንቅንቁ ተስፋ አስቆርጦ የጥፋት ኃይሎች እያየሉ ቢሄዱ ኖሮ፣ ተበታትኖ ከመባላት ይልቅ በአምባገነንነት ሥር መውደቅ አሥር እጅ ይሻላልና ብዙዎቻችን አምባገነን ገዥን መናፈቃችን አይቀርም ነበር፡፡

አሁን ባለንበት ሁኔታ፣ የብተናና የሥርዓተ አልባነት ግብረ አበሮች ከውጭ አጋዦቻቸው ጭምር የሽንፈት ሒደት ውስጥ ናቸው፡፡ አገራዊ ህልውናን የማትረፍና የማጠናከር ትግሉም፣ ከቤት ውስጥ እስከ ባህር ማዶ ድረስ የኢትዮጵያ ልጆችን ትግግዝ የማሰባሰብ አቅሙ ከጊዜ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ ጦርነቶችና ሽብሮች የመገባደድ ሒደት ውስጥ ናቸው፡፡ የኑሮ ውድነቱን ጨለምተኞች መነገጃ ለማድረግ እንዳይመቻቸው ከአገር ህልውና ተጋድሎ ጋር ሲካሄድ የቆየውና አገርን የማዳን አካል የሆነው የልማት መፍጨርጨር የጉሮሮ አጥንት ሆኖባቸዋል፡፡ በአጭሩ በኑሮ መወደድ መንገሽገሻችን ከመልካም ተስፋ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በአገር ህልውና ዙሪያ ከአገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ የተሰባሰብነው የኢትዮጵያ ልጆች በግንባታውና የከበደውን ኑሮ በማቅለል ርብርባችን እየጠነከረ ከሄደ፣ ብዙ ችግሮች መቃለላቸውና የአምባገነንነት ዕድል ከአጠገባችን እያራቀ መሄዱ አይቀርም፡፡ እየተወላገደም ቢሆን ጉዟችን በዚህ አቅጣጫ ውስጥ ነው፡፡ ያለው ፌዴራላዊ መንግሥት ኢተገማች በሆኑ ጥፋቶች ትብብርና ድጋፍን የማዝረክረክ እንከን ቢደጋግመውም፣ የኢትዮጵያ ልጆች በውስጥም በውጭም አገራዊ ህልውናንና ለውጥን በማጎልማስ ተልዕኮ ላይ ፊታቸውን አላዞሩም፡፡

የ‹ሀበጋር› ክርክር መነሻ ሆኖኝ በጻፍኩት የመጀመርያ ረቂቅ ጽሑፍ ላይ እነዚህን ነጥቦች አስፍሬ፣ ዋና የሐተታ ትኩረቴን በጥር መጀመርያዎች ለታየው ዓይነት የ‹‹ሀበጋር›› ወሸከሬ ክርክር ወጣቶቻችንን ምን አጋለጣቸው በሚል ጥያቄ ላይ አድርጌ ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያው በጥር ወር ውስጥ ዋል አደር ብሎ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተከሰተውን ክፍፍል የተመረኮዘ ቀውስ ትኩረቴን እንድቀይር አስገደደኝ፡፡

ከክፉው ጦርነት ያገኘነው በረከት (የመከላከያችን ለኢትዮጵያና ለሙያው በመታመን ከመላ የአገሪቱ ማኅበረሰቦች ተጠናቅሮ የተገነባ ትኩስ ኃይል መሆኑ) ከእግዲህ ያለ ሐሳብ እንተኛ የሚያሰኝ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና መትረፍ ላይ የተቀዳጀነው የአሸናፊነት (የኃይል ሚዛን) የበላይነትም ሆነ የኑሮ መክበድ ያላጨለመው የለውጥና የተሻለ ሕይወት ተስፋ ተገትረው የሚቆዩ ነገሮች አይደሉም፡፡ አዎንታዊ ብልጫን እያጎለመሱ የመሄድን ሥራ ካላወቅንበት፣ አዎንታዊ ብልጫ ሊንሸራተት (የአምባገንነትን ዕድል የሚቀናቀን ነባራዊና ህሊናዊ ስንቅ በሆነ ሽንቁር ሊፋሰስ) ይችላል፡፡ በጥር ወር ውስጥ የተከሰተውና እስከ አሥራ አካባቢ ወለም ዘለም ያለው፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተፈጠረ መከፋፈልና ፖለቲካዊ/ መንግሥታዊ እጅ የገባበት ቀውስ ‹ምርጥ› ሽንቁር ነው፡፡

ሃይማኖቴ ተነካ/ተጠቃ የሚያሰኝ ክስተት ‹‹ትንሽ ሥጋ እንደ መርፌ ትወጋ›› የሚለው ምሳሌ ከሚገልጸው በላይ፣ በየትኛውም አገራዊ ሙያዊ ሲቪልና ወታደራዊ ተቋም ውስጥ የተሰማሩ ሰዎችን ሊነዝርና ወደ ‹‹ተጋድሎ›› ሊስብ የሚችል ስስ ጉዳይ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ቀውስ በፍጥነትና በጥንቃቄ እንዲረግብና እንዳያዳግም ሆኖ ካልታረመ፣ የኮራንባቸውንና እያጠናከርናቸው ያሉ ተቋማትን ሁሉ ስንጥቅጥቃቸውን ሊያወጣ የሚችል ነው፡፡

በኦሮሚያ ውስጥ አፈንጋጮቹ ጳጳሳትና ተሿሚዎቻቸው ቤተ ክርስቲያናትን ሰብሮ በመያዝና ሕዝብ ገብ ድጋፍ ‹‹ብጤ›› በመላበስ ጥረታቸው፣ መንግሥታዊ አካላት አናዳጅና ጮርቃዊ ድጋፍ መስጠታቸውና የሶሻል ሚዲያ እሳት አራጋቢነት፣ የአገሪቱን ኅብረ ብሔራዊ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮችን በደም ፍላት አስነስቶ ቢሆን ኖሮ፣ ይፈጠር የነበረው የደም መፋስስ ለግምትም የሚከብድ በሆነ ነበር፡፡ ከዚያ ዓይነት ቀውስ በኋላም አገር አለኝ ማለት ባልተቻለ ነበር፡፡ በጊዜው የነበረው አደገኛ ሁኔታ ይጠይቅ የነበረው ወሬ ፍትፈታን ሳይሆን የጋዜጠኛውንም፣ የፖለቲከኞችንም፣ የምሁራንና የሃይማኖት መሪዎችን ነገር እንዲበርድ መካሪ የመሆን ሚናን ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ የአንዳንድ አገር ወዳድ ጋዜጠኛ ነን ባዮች ወሬ የመነገድ ጥማት አስተዛዛቢ ነበር፡፡ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከብዙ ምዕመኗ ጋር በፀሎትና በምህላ መሬት እየተኙ ወደ ፈጣሪ በመቅረብ ቅዋሜን መጀመሯ በጀ እንጂ የተዋከበ ሠልፍ ጠርታ ቢሆን፣ እዚያ ላይ በሚፈጠር ግብግብ ትንሿ ሽንቁር ወደ ስንጥቅጥቃማ ቀውስ በወሰደችን ነበር፡፡ ዋል አደር ብሎ የታቀደው ሰላማዊ ሠልፍ ተካሂዶ ቢሆን ኖሮም ከግራ ከቀኝ ያሉ የ‹ይለይልን› ፖለቲከኞች (ብተናንና መፋጀትን የሚናፍቁ ጨለምተኞች ጭምር) ሠልፉን ሰላም አልባና ደም አፋሳሽ ከማድረግ ባልፆሙ ነበር፡፡ ከሠልፉ ዕውን መሆን በፊት ዕርቅ ላይ መሠራቱና የተወሰኑ የኢንተርኔት ሶሻል ሚዲያዎች መዘጋታቸው ተንጠርብቦ የነበረውን አደጋ ከባድነት የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

የዓለማችን ግንኙነቶች በፍጥነት ተለዋዋጭ መሆን የመጣው ከሶቪዬት ኅብረት ጎራ መፈራረስ አንስቶ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ መንግሥት አካባቢ ስለዓለማችን ግንኙነቶች ተለዋዋጭ እየሆኑ መምጣት አሁን አሁን ሲወራ እንሰማለን፡፡ እኛ ደግሞ ከዚህ ባሻገር የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝብ የሚሰጠውን ውድ ድጋፍና አመኔታ ሳይታሰብ የመበተንና አንደገና መልሶ ለመሰብሰብ የመትረክረክ ኢተገማችነት ውስጥ እንደ ወደቀ ልብ እንዲል እንነግረዋልን ፡፡ ድጋፍ እየበተኑ መሰብሰብ የተቻለው የመንግሥት ብልጠት በሕዝብ ላይ ልቆ ሳይሆን፣ የአገር ህልውናና የሕዝቦች ሰላም አያኮርፉበት ሆኖ ነው፡፡ እንደዚያም ቢሆን ድጋፍ እየተቆመረበት ሊቀጥል አይችልም፡፡ ሥራ አጥነት፣ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት፣ የመንግሥት ቢሮክራሲ መንቀዝና የሸኔ ዓይነት አሸባሪነትና አፈናቃይነት የጉያ ብጉንጅ በሆነበት እውነታ ላይ፣ የጥር ወሩን መሰል ሰፊ የሕዝብ ቁጣ የሚወልዱ/የመንግሥትን ሕዝባዊ ድጋፍ እምቦጭ የሚያደርጉ ያልተገመቱ ጥፋቶች መደጋገማቸው ከቀጠለ፣ በሕዝብ ዘንድ ነገ ተነገ ወዲያ አለመተማመን እየጨመረ መሄዱ አይቀርም፡፡ ሥጋት ኑሮ መሆኑ ደግሞ፣ ‹‹አንድ ላይ አብሮ መኖር አይቻልም›› የሚል ጨለምተኛ ዋንጫን ለመሙላት የሚጥሩ በታኞች ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ነገር እየሠሩ እንዲቁለጨለጩ የሚጠቅም ነው፡፡

ያልተገመቱ ቁጣዎች መመላለስ ‹‹ያበጠው ይፈንዳ/ይለይልን›› በማለት አገር ህልውናዋ ባልፀናበት ለጋ ሁኔታ ውስጥ መንግሥትን በነውጥ ወደ መጣል ደንቆሮ ውሳኔ ሊወስድ ይችላል፡፡ መንግሥትም ነውጡን በጭፍጨፋ ቀጥቼ ወደ አምባገነንነት ልፍጠን ቢል ወይም ከወታደራዊ ተቋሙ ውስጥ መንግሥትን ልገልብጥ ባይ አምባገነን ብቅ ቢል ገዥዎችን በማገልገል የተገራ ልምምድ የሌለው የታጠቀ ሠራዊት ሙሉ ለሙሉ ከመታዘዝ ይልቅ መሰነጣጠቅ ይቀለዋል፡፡ የመሰነጣጠቅ ዕድልን ለማዳፈን ቢጠቅመኝ ብሎ ገዥው ቡድን በይፋዊው ወታደራዊ መዋቅር ውስጥ ሥውር መዋቅር ፈጥሮ ለክፉ ቀኑ ሊዘጋጅ ቢሞክር እንኳ፣ ክፉው ቀውስ ሲመጣ የሚሳካለት አይመስልም፡፡ የቅምሻ ታህል ያየነው የፌዴራላዊነት ልምድ፣ ከፓርቲው ጀምሮ በአራቱም ማዕዘን ወደ መቦዳደስ የሚወስድ አሻፈረን ባይነት ማምጣቱ አይቀርም፡፡ ይህንን ለማገዝ ደግሞ የጎረቤት መሬት ፈላጊዎች እንደማይዘገዩ ይታወቃል፡፡ በአጭሩ በዚህም በኩል ተወፈፈ በሌላ በኩል ራስን በራስ ማጥፋት የሁላችንም ድርሻ ይሆናል፡፡

ሰፊ ቁጣዎችን የሚወልዱ ድርጊት ነክ፣ ውሳኔ ነክና ንግግር ነክ ጥፋቶች ዱብ ዕዳ ሆነው ነገም ተነገ ወዲያም ይገጥሙን ይሆን? በበኩሌ ዕይታዬ ጉም ያፈነው ነው፡፡ ሥጋቱ አለኝ፡፡ ምክንያቱም ለኢተገማች ጣጣዎች የሚያጋልጡና ለአገር ሰላምና አንድነት ጠንቅ የሆኑ ርዝራዥ ነባራዊና ህሊናዊ ችግሮች ዛሬም አሉ፡፡ እነዚህ ችግሮች ምን ያህል መዘዘኛ እንደሆኑ አጢኖ መፍትሔያዊ ሚና በመጫወት ረገድ በፖለቲከኞቻችንም በምሁራንም ዘንድ ጉድለት አለ፡፡ የአማካሪ ዕገዛንና የግል ጠንቃቃነትን ከፍ በማድረግ ሊታረሙ የሚችሉና ቢነገሩ በሕዝብ ዘንድ ምን ውጤት ያስከትላሉ በሚል ሚዛን ላይ እየወጡ በደንብ ያልተፈተጉ ንግግሮችን በተደጋጋሚ ሰምተናል፡፡

ጉዳዩ የሕዝብ ጉርምርምታና ቁጣን ድንገት የሚወልዱ ኢተገማች ጥፋቶች ወደፊት ያዳግሙን ይሆን ወይስ አያዳግሙንም እያሉ የመራቀቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሆነ የኃይል ዕርምጃ እዚህ ወይም እዚያ ሲወሰድ፣ ‹‹መንግሥት እያሳየ ያለው ባህርይ ወደ አምባገነንነት የማዘንበል ነው›› እያሉ መግለጫ የማውጣት ‹‹አስተዋይነት›› ጉዳይም አይደለም፡፡ ‹‹የአምባገነንነት አደጋ ወይም የአገር መፈራርስ አደጋ ገና እንዳልተወገደ አስቀድሞ ታይቶኝ ነበር›› የሚል ወሬ ለራስም ለአገርም አንዳች ጥቅም አይሰጥም፡፡ ጉዳዩ አምባገነንነትም ሆነ ሌላ የባሰ አደጋ እንዳይመጣና አገር እንዳናጣ፣ አገር ከማጣትም በላይ ወደ አውሬያዊ የኑሮ አዘቅት እንዳንወርድ ከወዲሁ እንደ ምን አገራዊ እኛነታችንን እንርዳ ብሎ የማሰብና በሚቻለን ሁሉ አዎንታዊ ውጤት ያለው ዕገዛ የማዋጣት ኃላፊነት ጉዳይ ነው፡፡

2013 ዓ.ም. ይዞ በዚያ ክፉ ቀን የተገነባውና እየተገነባ ያለው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተራ ግንባታ ውጤት አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከገበሬ እስከ ተማረ ሰው ድረስ በአገር ፍቅርና በአርበኝነት ሆ ብለው ተነስተው ለመስዋዕትነት እየተጋፉ ውኔያቸውን እያራጩ እየተዋደቁና እየተሰው፣ በተሰውት እየተተኩ፣ በደምና በአጥነት የተገነባ የመላ ሕዝቦቿ ሠራዊት ነው፡፡ ይህ የመላ ሕዝቦቻችን ዓድዋዊ የርብርብ ውጤት የሆነ ሠራዊት የገዥ ቡድን/ግለሰብ አምባገነናዊ ፍላጎት መጫወቻ እንዳይሆን፣ በታኞች በብሔርና በሃይማኖት ገመድ እየጎተቱ እንዳይመነቃቅሩት ነቅቶ መጠበቅ/መንከባከብ ግዴታችን ነው፡፡ መከላከያ ሠራዊታችን በዓድዋዊ ግንባታው ያገኘው የሕዝብ ፍቅር፣ ‹‹የሁላችን ሠራዊት›› የሚል ሞገሱና ሕዝባዊ እትብቱ እንዳይበጠስ መንከባከብ የፖለቲከኞች፣ የምሁራንና የመላ ዜጎች ግዴታችን ነው፡፡ በተለይ አቅሙ ያለን ምሁራንና ፖለቲከኞች ሁሉ የምናገኘውን ቀዳዳ እየተጠቀምንና መንገድ እየፈጠርን የአምባገነንነት ዝንባሌ ልምላሜ እንዳያገኝ፣ ኢተገማች ጥፋቶች እንዲቃለሉ፣ ብሔርንና ሃይማኖትን ተገን ያደረጉ ወጥመዶች ዱብ ዕዳ ወልደው አገር እንዳያቃጥሉ ነቅቶ መሥራት ግዳችን ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ምሁራን!!!

ምሁራን ከፖለቲከኛ ወገንተኛነት በላይ ሆነን አዎንታዊ ሚና የምናበረክትባቸው ዘርፎች ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚያ ውስጥ የፖለቲካና ማኅበራዊ ሰላም ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ መንግሥት ንቁ ተሳተፎ አድርጉ ብሎ እስኪጠራን መጠበቅ የለብንም፡፡ ቢጠራንም ባይጠራንም ሐሳብና ምክር ማድረሻ ቴክኖሎጂ ቀላል በሆነበት ዘመን መንገድ መፍጠር ግዳችን ነው፡፡ አዎንታዊ አስተዋፅኦ ከደመወዝ ጉዳይ ጋር አይገናኝም፡፡ አስተዋፅኦችን ‹‹መንግሥት ምሁራንን ለመስማት ዝግጁ ነው ወይ›› በሚል ጥያቄና መልስ አይለካም፡፡ መንግሥት ለመስማት ዝግጁ ባይሆን እንኳ እንዲሰማን መጣር ግዳችን ነው፡፡ ይህ ኃላፊነታችን ‹‹ብትሰማ ስማ!›› ብሎ የሆኑ ሐሳቦችን ከመወርወር በላይም ነው፡፡ በቅድሚያ እንካ የምንላቸው ነገሮች የእውነታዊነትና የመርታት ጉልበታቸው ወሳኝ ነው፡፡ ሁለተኛ ምክሮቻችን የሚተናነቅ መራራ ቢኖራቸው እንኳ፣ መድኃኒት የሚኖረውን የጎን ጉዳት ለመቀነስ ሲባል ልባስ እንደሚደረግለት ሁሉ፣ ምክሮቻችን ጀርባ እንዳይሰጣቸው/መራራቸው ለስልሶ እንዲገባ እንደምን ብናቀርባቸው ይሻላል ብሎ መዘየድም ኃላፊታችን ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ሰላምና የፖለቲካ ጉዳዮች፣ ሁለት ሲደመር ሁለት ውጤቱ አራት ነው እንደ ማለት ሥሌታቸው ቀላል አይደለም፡፡ በፖለቲካና በሰላም ውስብስቦሽ ውስጥ ሁለትና ሁለት ድምራቸው ሦስት ሊሆን እንደሚችል ሁሉ አምስትም ሊሆን ይችላል፡፡ የዚህን እውነትነት ለምሁራን ማስታወስ ድፍረት ይሆንብኛል፡፡

ለ) በዚህ መንፈስ በአሁኑ ጊዜ የሚብሱ የሰላምና የአገር ጉዳይ ሆነው ወደሚታዩኝ ጉዳዮች ልሻገር፡፡

  • የወጣት ሥራ አጥነት ክምችትና ዓመታዊ ጭማሪ በሥራዎች ፈጠራና በሥራዎች መስፋፋት ታፍ ታፍ መቃለል መቻሉ የሰላም ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አሁን የተጀማመረው የመንግሥትና የምሁራን/የዩኒቨርሲቲዎች ትግግዝ ይስፋ ይጠናከር የሚያሰኝ ነው፣
  • የኢትዮጵያ ሠራዊት ወደ ሰባ ከመቶ የትግራይ አካባቢዎችን ተቆጣጥሮ ከነበረበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ጊዜ ድረስ ከነፍስ አድን ዕርዳታና ከኑሮ ማንሰራራት ሒደት ጋር በኢትዮጵያ ግቢ ውስጥ የትግራይን ሰላምና ልማት መፍካት የሚናፍቅ የብዙኃን እንቅስቃሴና የፓርቲ ፖለቲካ ሲላወስ ቆይቶ ከሆነ፣ መጋቢት ሲገባ (2015) በዋልታ ቴሌቪዥን ያየነው ውስን የትግራይ ታዳጊዎች በደነበዘች ሕይወታቸው ላይ ነፍስ ለመዝራት በኪነት/ውዝዋዜ አማካይነት የሚያደርጉት መፍጨርጨር የዚያ ነፀብራቅ ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ተጋሩዎች የተባበረ እንቅስቃሴ ስለመፈጠሩ እየሰማን ያለው ነገር ትግራይ ሕዝብ ውስጥ ሥር ያበጀና እስካሁንም ውስጥ ውስጡን ሲሠራ የቆየ ከሆነ፣ ሕወሓታዊ ተዋጊዎችም በአያሌው ካምፕ ገብተው ትርጉም ያለው ተሃድሶ እያካሄዱ ከሆነ፣ ሰላም መሬት እየተቆናጠጠ መጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ በትግራይ ሕዝብ ውስጥ ያለው የሰላምና የአገር ወዳድነት ትርታ በጦረኝነት ካልዛቆኑትና አገር ወዳድ ፖለቲከኞች ጋር ገና ያልተሸራረበ ከሆነ፣ ወደፊት የሚቋቋመውን የሽግግር መንግሥት ባለ ብዙ ነፍስ ሆነው (በፓርቲ ነፍስ፣ በተዋጊ ነፍስ፣ በ‹ምሁር› ነፍስ፣ በ‹ሲቪል ማኅበረሰብ› ነፍስ ምናምን) ለመሰብሰብ ሽርጉድ የሚሉት ሕወሓታዊያን የአደባባዩንም የሥር ሥሩንም ሜዳ ለብቻቸው እየፈነጩበት ከሆነ የትግራይ ሕዝብ ሰላም አስተማማኝነት ገና ጥሬ ነው ማለት ነው፡፡
  • የብልፅግና ፓርቲ ‹‹የአማራ ክልል›› ቅርንጫፍና ‹‹የክልሉ›› መንግሥት ዛሬም ድረስ ከሕወሓታውያን፣ ከሸኔና ከኦሮሞ ፅንፈኞች፣ ከአዲስ መጦቹ ጨለምተኛ የአማራ ብሔርተኞች ጋር ፍትጊያ አለባቸው፡፡ የዓብይን መንግሥት በተገኘው መንገድ ሁሉ ለመከንበል የሚሻው ዕውር ‹‹ፖለቲካ››ም አማራነት ላይ የተላከከ ነው፡፡ የሆነ የፀጥታ ሥጋት ወደ አዲስ አበባ ግድም ደመቅ ሲል ደጋግሞ ሲከሰት የታየው ከአማራ አካባቢዎች የሚመጡ ማጓጓዣዎችን አግዶ የማጉላላት ድርጊት፣ ለነገ መጥፎ ምልክት ከመስጠቱ ባሻገር በአማራና በኦሮሚያ አካባቢዎች የተማመነ ዝምድና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከጨለምተኞቹና ፅንፈኞቹ ግዝገዛ የላቀ ነው፡፡ ሁለቱም አካባቢዎች የውስጥና የእርስ በርስ ሰላማቸውን የሚጎደፍሩ ተተናኳዮች ያሉባቸው እንደ መሆናቸው የሁለቱ አካባቢዎች መናቆር ለሁለቱም ህልውናና ለኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ነው፡፡ እናም አንዱ ወገን መንገድ ዘጊ፣ ሌላው ወገን ተርኮምኳሚ የሚሆንበት ድርጊት ወለም ዘለም የሚባልበት አይደለም፡፡ ይዞት የሚመጣው መዘዝ ለሁሉም የሚተርፍ እንደ መሆኑ፣ የፀጥታ ሥራው የፌዴራል መንግሥቱና ሁለቱ ‹‹ክልሎች›› ሊቀናጁበት የሚገባና የሕዝብ ጉስቁልናን የሚያቀል መላ ያለው መሆን ይገባዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ከአዙሪት በሚገላግሉ አዛላቂ መፍትሔዎች ላይ መረባረብ ወሳኝ ነው፡፡
  • ከጎረቤት አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚሠርጉና ከቦታ ቦታ የሚዘዋወሩ የነፍስ ወከፍ መሣሪያችንና ተተኳሾችን ማመናመን፣ እንዲሁም ፖለቲካዊ ምክንያት አለን የሚል ማመከኛ ይዘው በተለያዩ ሥፍራዎች እየተሹለከለኩ በሰላም አደፍራሽነትና በዘርፎች በሌነት የሚኖሩ ቡድና ቡድኖችን በሚያዋጡ ዘዴዎች ሁሉ ተጣጥሮ ማድረቅ ብዙ ነገሮችን የማሻሻልና የማቃናት ጉዳይ ነው፡፡ የሰዎችን በሕይወት የመኖር ደኅንነት የማስከበር ጉዳይ ነው፡፡ ከቦታ ቦታ የመዘዋወርና በፈለጉት ሥፍራ ሠርቶ የመኖር መብትን የማስከበር ጉዳይ ነው፡፡ ኪሳራና ውድመትን፣ ከአቅም በታች ማምረትን፣ የምርት እጥረትን፣ የፍጆታ ዕቃዎች ዝውውር መረበሽን፣ የኑሮ መወደድን ተሳሳቢ ችግሮች የማቃለልና የሥራ መስፋፋትን የማገዝ ጉዳይ ነው፡፡ የ‹አማራ ክልል› እና የ‹ኦሮሚያ ክልል› ሕዝብን መልካም ግንኙነት የመጥቀም፣ የመንግሥትንና የሕዝብ ትምምንን የማሻሻል ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም በኩል መንግሥት ችግሮችን ለማቃለል እየሠራ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም፣ ይበጃሉ የሚባሉ ብልኃቶችንና አቅሞችን አስተባብሮ ከዘላቂ መፍትሔ ጋር እንዲያገናኘን አበክረን እንጠብቃለን፡፡
  • አገር ወዳድ ፖለቲከኞችና ተንታኞች ነን እያሉ በትንሽ ትልቁ የብልፅግና ፓርቲን የኦሮሚያ ቅርንጫፍና የኦሮሚያን መንግሥት በብሔርተኞችም ሆነ በብሔርተኛ ፅንፈኞች ቁጥጥር ውስጥ የወደቀ እያሉ ከጊዜ ጊዜ በማጣጣላቸው፣ የአካባቢውን የፓርቲ ቅርንጫፍም ሆነ መንግሥቱን ወደ ብሔርተኞቹና ፅንፈኞቹ ሠፈር እየገፉ ነው፡፡ ባዋደቅነው ቁጥር አፍሮ ይመለሳል ብለው የሚያስቡ ከሆነ፣ ወይም በብልፅግና ፓርቲ መሰነጣጠቅ ኢትዮጵያ ታተርፋለች የሚል ሥሌት ካላቸው ስላልገባቸው ነገር እያወሩ ነው፣ ወይም ማሰብ አቁመዋል፡፡ የኦሮሚያ ብልፅግናዎች ብዙ ዓይነት መርዘኛ አሉባልታ ከሚረጩ፣ ከሸኔ ጋር እየተሞዳሞዱም ሆነ አስተዳደራዊና ኢኮኖሚያዊ አሻጥር እየሠሩ የኦሮሞ ሕዝብ በብልፅግና ፓርቲ እንዲመረር በ‹‹ኦኤም›› እና በመሰሎቻቸው የውንጀላ ፕሮፓጋንዳ ኦሮሞ ከብልፅግና ፓርቲ እንዲቆራረጥ ነጋ ጠባ ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር ግጥሚያ አለባቸው፡፡ አገር ወዳድ ነን ባዮቹ ‹‹ኢብሔርተኞች›› ብልፅግናዎችን በብሔርተኛነትና በፅንፈኛነት ሲነቅፉ ለብልፅግናዎች ተጨማሪ ሕመም እንጂ አቅም አይሆኗቸውም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ የብልፅግናን ፓርቲ ቢተፋ ኢብሔርተኛ ነን እያሉ የብልፅግና ፓርቲን ሲያብጠለጥሉ ወደ ቆዩት ፖለቲከኞች የኦሮሞ ሕዝብ አይመጣም፡፡ የባሰባቸው ብሔርተኞች ሲሳይ ነው የሚሆነው፡፡ የብልፅግና ፓርቲ ተንሳፍፎም ሆነ ተሰነጣጥቆ የኦሮሞ ሕዝብ አስተሳሰብና ድምፅ ወደ አድፋጮቹ ብሔርተኞች ሄደ ማለት ደግሞ፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሰላምና ህልውና የሚፈታተን ሌላ አደጋ መጣ ማለት ነው፡፡ ‹‹ኢብሔርተኛ ፖለቲከኛና ተንታኝ›› ነን ባዮች አስተዋይ ዓይን ካላቸው የኢትዮጵያ ህልውናን የሚያግዙት፣ ብሔርተኞችና ፅንፈኞች ተቆጣጠሩህ እያሉ ብልፅግና ላይ እሩምታ በማውረድ ሳይሆን፣ የኦሮሚያን እውነታ በደንብ መርምረው (በተለያዩ የፈተና ሁኔታዎች ውስጥ ምን መባል እንዳለበትና እንደሌለበት አውቀው) የብሔርተኛ አፍራሾችን ፕሮፓጋንዳ፣ ውንጀላና ሻጥር በመታገል ማገዝ ከቻሉ ነው፡፡ በኦሮሚያ የሚገኝ ኦሮሞ ያልሆነ ኢትዮጵያዊም ከአፍንጫቸው ያልራቁ ተቺዎች አዳናቂ ከመሆን ትርፍ አያገኝም፡፡ ትርፍ የሚያገኘው የአካባቢ ሕዝብ አካል አድርጎ ራሱን በማሰብ በክፉም በደጉ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳታፊ በመሆን ነው፡፡ ለምሳሌ በደቡብ ኢትዮጵያ ከምሥራቅ እስከ መሀል ምዕራብ አካባቢዎች የደረሰውን ረሃብ በማቃለል እንቅስቃሴ ያለ ጎትጓች ንቁ ተሳታፊ መሆን፣ የብልፅግና አካባቢያዊ ቅርንጫፎችን አስተሳሰብና አስተውሎት ይበልጥ ሁሉን አካታች እንዲሆን ያግዛል፡፡ በዚህም የአስተሳሰብ ስፋት አካባቢዎችም ኢትዮጵያም ተጠቃሚ ናቸው፡፡ ይህ የማይታየን ጠባቦች ‹‹ኢብሔርተኛ›› ነን እንላለን?
  • 1984 ዓ.ም. ይዞ በመጣ አንጓላይ አተያይ፣ አሸናሸንና አጠራር የኢትዮጵያ ብዙ አካባቢዎች ወድቀው አሁን ድረስ የዘለቀ ብሔረሰባዊ ማንነትን ሒሳብ ውስጥ ያስገባ አካባቢያዊ የአስተዳደር ጥያቄ ያንገላታቸዋል፡፡ ትግራይ ግን በነባር ስሟ ውስጥ ያላት የውስጥ ሽንሻኖና አጠራር ከአንጓላይነት የራቀ ነው፡፡ የምናገኘው አጠራር ‹‹ሰሜን ትግራይ፣ ምሥራቅ ትግራይ፣ ማዕከላዊ፣…›› የሚሉ ዓይነት ነው፡፡ ይህ ኢአንጓላይ አጠራር ግን ከፍትሐዊነት ይዘት ጋር አልተገናኘም፡፡ በአማረ አጠራር ውስጥ በደፍጣጭነትና በአሀዳዊ ማዋዋጥ ዓይነተኛነትን አዳክሞ አንድ ብሔር የማነፅ ፕሮጀክት የራሱን ብልሽት ፈጠረና በሌላው የኢትዮጵያ ክፍል ያለው እኔ የተለየሁ ነኝ ባይ እንቅስቃሴ ትግራይንም ሊያምስ ቻለ፡፡ ሕወሓት ኢሕአዴጎች በትግራይና በቀሪዎቹ የኢትዮጵያ ልምዶች በጊዜ ትምህርት ወስደው አጠቃላይ ዕርማት ለማድረግ አልቻሉም፡፡ ቅራኔዎች በተለይ የወልቃይትና የራያ አደባባይ ከወጡ ወዲያ ቅራኔዎቹን እንደሚቃለሉ አድርጎ ከመፍታት ይልቅ፣ በጉልበት መዳመጥ ተመረጠ፣ ያ ደግሞ አገር እስከ መበርቀቅ ወሰደ፡፡ ያ ሁሉ ካለፈ ወዲያ የኢትዮጵያ ልሂቃን አሁን ድረስ በትግራይና ከትግራይ ውጪ ሁለት ዓይነት አሠራር ለምን እንደ ነበረና በሁለቱም ልምድ የታየውን ጎጂና ጠቃሚ ልምድ መርምረው ሊባንኑና የመሰነጣጠር ፍላጎቶችን የጣለ አጠቃላይ ግንዛቤ ሊፈጥሩ አልቻሉም፡፡ ዛሬም የአንድ ብሔረሰብ የብቻ ክልል እፈልጋለሁ ባይ እንቅስቃሴ እንደ አዲስ አለ፡፡ እንዲህ ያሉ የመሰነጣጠር ፍላጎቶችን ይዞ ኅብረ ብሔራዊነት ዕይታዬ ነው፣ አገራዊ ህልውናን የሚንከባከብ አካሄድ አለኝ እያሉ ማለት ቧልት ነው፡፡
  • የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት፣ ፈፅሞ ወለም ዘለም የማይባልበትና እንዳይጣስም ንቁ ጥበቃና እንክብካቤ የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ እንክብካቤው ከፓርላማም፣ ከሃይማኖት ተቋማትና ከኅብረተሰቡም በኩል የምር መምጣቱ ወሳኝ ነው፡፡ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ብዙ የዋለች የመሆኗን ያህል ብዙ ፈተናም አለባት፡፡ በረዥም ዘመን ታሪኳ ውስጥ የገዥዎች ርዕዮተ ዓለም፣ አንጋሽ፣ የገዥነት ሲሳይ ተካፋይ፣ የዘመቻዎች ባራኪም ዘማችም ሆና ሠርታለች፡፡ በዚህ የኋላ ታሪኳ ውስጥ አሉታዊም አዎንታዊም ገጾች ቢኖሩም፣ አሉታዊውን ብቻ አንጠልጥለው ዛሬም ቤተ ክርስቲያኒቱን እንደ ጠላት እያዩ ቂም የያዙ፣ ተበጫጭቆ መጥፋትን ሳይቀር የሚመኙላት ፖለቲከኞች አሉ፡፡ የዚህ ዓይነቱ መራራ ስሜት በአያሌው የዓለም የገዥነት ታሪክ ውስጥ ሃይማኖቶች የተጫወቱትን ሚና በአግባቡ ካለመረዳት የሚጀምር ነው፡፡ የዚህ ዓይነቱ የግንዛቤ ጉድለት፣ የኦርቶዶክስ ክርስትና ከገዥነት ጋር የተወራረሰ ታሪክ ከኦርቶዶክሳዊ እምነትነት የፈለቀ ባህርይ ሳይሆን፣ በገዥነት ታሪክ ውስጥ ያለፉ ሃይማኖቶች ሁሉ የተቋደሱት ሚና መሆኑን በተረዳ ግንዛቤ የሚቃና ነው፡፡ ችግሩ ግን ከግንዛቤ ማጠር ብቻ የመጣ አይደለምና በግንዛቤ የማይበገሩ አሉ፡፡

የቤተ ክርስቲያኗን የአንድ ሲኖዶስ ተዋረዳዊ መዋቅርና የሰዎችን ማኅበራዊና አካባቢያዊ አመጣጥን ዛሬ ድረስ የቀጠለ የሰሜኖች የበላይነት መገለጫ አድርገው የሚተረጉሙ ሰዎች አሉ፡፡ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የበቀሉ ጸሐፍት በጻፏቸው የነገሥታት ገድሎች ውስጥ ምድራዊ ዘመቻዎችና ሥራዎች ሰማያዊ ትርጓሜ ያገኙበት ሁኔታ ከመኖሩ በላይ፣ አፄዎችንና ቤተ ክርስቲያንን አጥቅተዋል የተባሉ አካባቢያዊ ገዥዎች የኩነኔ ታሪክ ተሰጥቷቸዋል የሚሉ ሰዎችም አሉ፡፡ አካባቢያዊ ሲኖዶሶች የማቋቋም ጥያቄዎች እነዚህን መሰል ፍላጎቶችና የጥቅም ሽኩቻዎችን ያዘሉ ናቸው፡፡

ይዘሉ እንጂ የባለፍላጎቶቹ ዒላማዎች በኢትዮጵያ ግቢ ውስጥ ብቻ የሚጠናቀቁ አይደሉም፡፡ በጦርነትና በማፋጀት ደባ ኢትዮጵያን መበተን ያልተቻላቸው ኃይሎች አስባብ ፈልጎ፣ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በክልላዊ ሲኖዶሶች መሸንሸን ወደ ብተና ግብ አንድ ዕርምጃ ያስጠጋል የሚል ሥሌት አላቸው፡፡ በቅርቡ የሰማነው ላፈነገጠ የሲኖዶስ ውጥን የተሰጠ ‹‹የኦሮሚያና የደቡብ ሕዝቦች…›› የሚል አጠራርም ከቆየና ኩሻዊ ዕይታ አለኝ ከሚል የፖለቲካ ሥሌት የተቀዳ ነው፡፡ ይህ ሥሌት በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ቤተ እምነቶችና በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ሥሌቱ ሲኖዶሳዊ ሽንሸና ከተደረገ በኋላ የብተና ፖለቲካ ሃይማኖታዊ ምላስና ይዘት ያገኛል (ፖለቲካ ሃይማኖት፣ ሃይማኖትም ፖለቲካ ይሆናል)፣ እናም ብተና ቀላል ይሆናል የሚል ሚስጥር አለው፡፡ ይህ የዋዛ ጣጣ አይደለም፡፡ ይህንን ጣጣ በድል ለመወጣት፣ ለኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና ለኢትዮጵያ መቀጠል እንዋደቃለን የሚሉ አንዳንዶች እንደሚመስላቸው፣ አደባባዮችን ለማጨናነቅ መቅበጥበጥና አርባ ክንድ ምላስ መዘርጋት ሳይሆን፣ ረጋ ብሎ አርባ ክንድ ብልኃት መፈለግ ነው፡፡

ቀደም ባሉ ጊዜያት ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ክብረ በዓሎቿን በኢትዮጵያ ባንዲራ የማሸብረቅ ልምድ ነበራት፡፡ እንደ ሠርግ ያሉ ድግሶችም ቢያንስ የበርና የዳስ መግቢያን በኢትዮጵያ ባንዲራ ያስጌጡ ነበር፡፡ የአገረ መንግሥት ባንዲራን ከእምነት ቅርበት ያራቀ መስሎት የሕወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት የክልከላ አዋጅ አውጥቶ ነበር፡፡ አዋጁ እንደ ፍላጎቱ ልማድን ማቋረጥ ባይቻለውም በተወሰነ ደረጃ ለማሸማቀቅ ችሎ ነበር፡፡ የዓብይ መንግሥት ከመጣ በኋላ በድጋፍና በተቃውሞ መግለጫነት አሉ የሚባሉ የባንዲራ ፖለቲካዎች አደባባይ አጣበቡ፡፡ ሕጋዊውን የኢትዮጵያ ባንዲራ ተጠቀሙ የሚልና የአገሪቱ ባንዲራ የአንድ እምነት መታወቂያም አይሁን የሚል ግፊት ተመልሶ ሲመጣ ደግሞ፣ የልሙጡ ባንዲራ ‹‹ፖለቲከኞች›› ስለኦርቶዶክስ የዓርማ መብት ተቆርቋሪ መስለው አርባ ክንድ ምላስ ዘረጉ፣ ዋል አደር ብሎ አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ሜዳ ላይ ዓርማ ያሳረፈ ሥራ ብቅ አለ፡፡ ይህም ፖለቲካና ሃይማኖት እንዲቀላቀል አድርጎ ትንቅንቁን አከፋው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ አግዳሚ ቀለማት ያላቸው ሁለት ባንዲራዎች (አንዱ ዓለማዊ ሌላው መንፈሳዊ) ያሉ የሚያስመስል መምታታት ሊፈጠርም ችሏል፡፡ በተለይ ረዥም የባንዲራ መቀነት ሲዘረጋ መምታታቱ ይደምቃል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ሃይማኖታዊ ካባ ለበሱም አልለበሱም ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ውስጥ ባላት ፖለቲካዊ ታሪክ ምክንያት የሚተናኮሏት ፖለቲከኞች እንደ መኖራቸው፣ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንንም በመደገፍና ተገን በማድረግ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን የሚያራምዱ አሉ፡፡ በእነሱ ፍትጊያ ውስጥ ቤተ ክርስቲያኗ ትንገላታለች፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ ሰንደቃዊ መታወቂያ ሦስት ቀለማትን ከእነ ሠልፋቸው ማበርከቷ የሚከበር አስተዋፅኦ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ዓርማን ከኢትዮጵያ ባንዲራ ጋር ማዳበል ለሰላሟ አይበጃትም፡፡ በድምቀት በተከበረው የ2015 ዓ.ም. የጥምቀት በዓል ላይ በረዣዥም የባንዲራ መቀነቶች ላይ የወረቀት ዓርማ መለጠፍን በዓርማ ስም የተካሄደ የፖለቲካ ጨዋታ አድርገው የተረጎሙም ነበሩ፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፣ በመነኮሳትና በባህታዊያን በመለበስ ከሚታወቀውና እንደ ‹ቡድሃዊያን› እና እንደ ‹ሂንዱ ብራሀሚኖች› የኦርቶዶክስ እምነትን ከሚወክለው ቢጫ ቅልመት ጋር ዓርማዋን ካላገናኘች በቀር፣ ቤተ ክርስቲያኗ ከሁለት በኩል ከሚመጣ የፖለቲካ ፍትጊያ መገላገል አይቻላትም እስከማለት የደመደሙም አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡

እልህ ያልተጋባ ብልህ አሳቢነት ለቤተ ክርስቲያኗም ለአገርም ካለ፣ ከላይ እንደተባለው፣ በማያሻማ የቅልመት መደብ ላይ ቃል ኪዳናዊውን ቀስተ ደመና ያዘለ ዓርማ በመጠቀም ከቤተ ክርስቲያኗ ኋላና በተቃራኒ የተፋጠጡ ፖለቲከኞችን መበተን ይቻላል፡፡ ከዚያ ወዲያ የቤተ ክርስቲያኗ መታወቂያ ቀለም ያለ መሀል ዓርማ በረዣዥም መቀነት ቢዘረጋ እንኳ ከሩቅም ከቅርብም የሚምታታበት አይኖርም፡፡ ይህንን በማድረግ ብቻ ትልቁ የፖለቲካ ልፊያ ይወገዳል፡፡ ከዚያ ባሻገር በሁሉም መንፈሳዊና ዓለማዊ ክብረ በዓላት ላይ የኢትዮጵያን ሕጋዊ ባንዲራ መስቀል/ማውለብለብ የተፈቀደና የተለመደ ቢሆን የኢትዮጵያን ባንዲራ ከሌላ ትርጉም ጋር ማያያዝ እየከሰመ ይሄዳል፡፡ ይህም የሚሳካው በሕግ ድንጋጌ ጉልበት ሳይሆን መከላከያ ሠራዊታችን ያገኘውን ዓይነት የሕዝብ ፍቅር ባለዓርማው ባንዲራችንም ካገኘ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ አገራዊው ምክክሩ ሰፊ መግባባት የተደረሰበት ነገር አበርክቶልን ተመስገን ለማለት እንደምንበቃ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በተረፈ በተቻለ መጠን የቤተ ክህነትን የሰዎች ጥንቅር እስከ ሲኖዶስ ድረስ ማስተካከል፣ በአንድ ሲኖዶሳዊ አመራር ሥር በአካባቢዎች ደረጃ የተወሰነ ነፃነትና ወሳኝነት ያላቸው አካላት ማደራጀት፣ ብዙ ሊቃውንት ያሏት እንደመሆኑ በቤተ ክርስቲያኗ በኩል የተሳሳቱ ናቸው የሚባሉ ታሪክ ነክ ስንክሳሮቿን ማጣራት፣ አጣራችም አላጣራችም በቅርስነት የያዘቻቸውን ለታሪክ ጥናት ሊውሉ የሚችሉ ቅርሶች ክፍት ከማድረግ በቀር የኢትዮጵያ ታሪክ አውሺ አብራሪ ከመሆን መቆጠብ፣ በኢትዮጵያ የዕውቀትና የጥበብ ቅርስ ያዋጣች፣ ብዙ ቅርስ ከጥፋት ሸሽጋም ያቆየች ታላቅ ባለውለታ የመሆኗን ክብር ዛሬ ከሚፈለግባት ከሁሉም ቤተ እምነቶች ጋር በእኩልነት ስሜት ከመኖር ጋር አጣጥሞ መያዝ፣ በውስጧ ዘረፉንና ሙስናን ከማስወገድ ጠንካራ ሥራ ጋር በየአካባቢዎች የበጎ አድራጎት ሥራ ውስጥ ጥሩ ስም ማበጀት፣ የኦርቶዶክስ ክርስትና ልዩ ልዩ ክብረ በዓላትን (አደባባይ የሚሹትን) በተቻለ መጠን የትራፊክ እንቅስቃሴ ለረዥም ጊዜ በማያውኩበት ሁኔታ በዋና ዋና የሕዝብ አደባባዮች ሰብሰብ ደመቅ ብለው የሚከበሩበትን ሁኔታ ከመንግሥታዊ አካላት ጋር ተግባብቶ ማቀድም ያዋጣ ይመስለኛል፡፡

ሐ) ይህንን ጽሑፍ ሳዘጋጅ በጽሑፌ ውስጥ የዓድዋ አካባበር ጉዳይ ይካተታል ብዬ ፈፅሞ አላሰብኩም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ማፈሪያ ፈንጋጣነት አያልቅብንምና በዚህ ዓመትም ወዲያ ማዶ የተለየ ዓይነት ዓድዋ፣ ወዲህ ማዶ ሌላ ዓይነት ዓድዋ ያለን መሰልን፡፡ አዲስ አበባ እንኳ ሁለት ዓድዋዎችን የምታውቅና የምታከብር ይመስል፣ ምኒልክ ሐውልት ዘንድ አበባ ጉንጉን ተደርጎ ወደ ዓድዋ ድልድይ ዝቅ ሲባል ከምኒልክ ጋር መቅረት የሚበልጥበት ታየ፡፡ እዚህም እዚያም ኢብሔርተኛ ነኝ/ጎሰኛ አይደለሁም ይባልልናል፡፡ ይህንን የሚሉ ሰዎች ግን በየብሔር በየክልል ጀግኖችን፣ የጦር መሪዎችንና ንጉሦችን እየተቃረጡ ሲያገዝፉ እናገኛቸዋለን፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ኢብሔርተኛ/ኢጎጠኛ ነኝ ባይ አፋቸው ‹‹ብሔርተኛ ፖለቲካን ካላስወገድን ሰላም አይዘልቅልንም” የሚሉ ቃላትን ነጋ ጠባ ይቆላል፡፡ በተግባር ግን በክልልተኛነትና በብሔርተኛነት የተቃረጧቸውን የታሪክ ሰዎች በውዳሴ ሲያጎኑና ሐውልት ሲገነቡላቸው ለጎጠኝነት/ለብሔርተኛነት መቀጠል ሐውልት እያቆሙ መሆናቸው አይታወቃቸውም፡፡

እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፣ የአሁኗ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ አገር ወዳድ እንጂ ፖለቲከኛ አይመስሉኝም፡፡ ከእኛ በላይ ፖለቲካ ላሳር የሚሉ የእኛ አገር ጉዶች ግን ፕሬዚዳንቷ ያላቸውን ያህል ሁሉን አካታች ግንዛቤ የላቸውም፡፡ የእሳቸውን ንግግር ያዳነቁት ሰዎች እንኳ እነማንን ይዘንና እያሰብን ዓድዋን ማክበር እንዳለብን ሳህለወርቅ የሰጡትን ትምህርት ከራሳቸው ጋር ማዋሃድ የቻሉ አይደሉም፡፡ አነሰም በዛ ያለ መሪዎች፣ ያለ አቃጆችና ያለ አደራጆች ታሪክ አይሠራም ብንል በአያሌው ልክ ነን፡፡ አመራርና ዕቅዱን ያገኘ የታሪክ ሥራ በዋናነት የሚከናወነው ደግሞ በብዙኃኑ ተሠላፊ ነው፡፡ የታሪክ አዘጋገባችን አትኩሮቱና የሐተታ ዓይኑ አድሎአዊ ስለሆነ፣ የብዙኃኑን ሥራ አጉልቶና አስፍቶ አይናገርም፡፡ ስለዓድዋም ሆነ ስለሌላ አኩሪ ጦርነት ስናወራ ከጥቂት አውራዎች፣ የጦር መሪዎችና ጀግኖች እልፍ ብለን ምን ያህል እናወራለን? አዲሱ ትውልዳችን የተሟላ ግንዛቤ እንዲያገኝ ምን ያህን እንጥራለን? እንደ ዓድዋ ባሉ ነባር ዘመቻዎች ቁሳዊና ‹‹መንፈሳዊ›› ስንቅና ትጥቁ አብሮ ነው የሚዘምተው ሲባል ምን ማለት ነው? የብዙ ሙያተኞችና የሥራ ዘርፎች የሥራ ቅንብር ከአዝማሪ ዝመራ፣ ከፉከራና ቀረርቶ እስከ ሃይማኖት ሰዎች ያለው መንፈስ የማጠንከር ሥራ፣ መሪዎች ሲያርፉ/ሲመክሩ፣ በቅሎና አጋሰስ ሲያርፍ፣ ብዙኃኑ (በተለይ ሴቶች) ስንት ሥራ አለባቸው? የሴቶች ሚና ከጉዞ እስከ እርፊት፣ ከዱር እስከ ማጀት፣ ከልዩ ልዩ የማዕድ ሥራ እስከ መኝታ፣ ከደጀን ሠፈር እስከ ጦር ሜዳ? …ጽሑፋዊ የታሪክ ትረካዎቻችን፣ የፊልም ትረካዎቻችን፣ በመታሰቢያነት የሚቆሙ የግድግዳ ላይ ምሥሎቻችን የሁሉም ባለታሪኮች ሚና የሚፈጥረውን ኅብራዊ ትርዒት ማሳየት ይገባቸዋል፡፡ በተወላገደ ትርክት ተወላግደን ያወላገድናቸው ወጣቶች በዓድዋ ድል አተራረክና አደናነቅ ቢሸነካከፉና ቢሰነጣጠሩ አይደንቅም፡፡

በተለያዩ የዕውቀትና የጥበብ ፈርጆች፣ የትውልድን አዕምሮ ሁሉን ያስተዋለ አድርጎ ማነፅ ከበድ ያለ ሥራ ነው፡፡ ቢከብድም ጊዜ ወስዶና በወጉ አቅዶ ማሟላት ግድ ነው፡፡ ሥልጠናና ትምህርት የማይጠይቅ ነገር ሲከብደን መታየታችን ግን ትልቅ ጉዳምነት ነው፡፡ በዓድዋ ዘመቻ፣ የጦርነት ተጋድሎና ድል ላይ ኢትዮጵያውያን ከንጉሥና ጦር መሪዎች እስከ ብዙኃን የገበሬ ዘማቾች ድረስ በአዛዥነት ታዛዥነትና በተዛማጅ የሥራ መረቦች ተሳልተው (እየወደቁ፣ አንዳቸው ሌላቸውን እያቀኑና እየተተካኩ) ያስገኙትን ድል እኛ በዓመት አንድ ቀን ለተወሰነ ሰዓት ሳንፈነጋገጥ ማክበር ገና አልተዋጣልንም፡፡ ለአፍሪካ፣ ለጥቁሮችና የቅኝ ቀንበርን ላዩ ሕዝቦች ሁሉ ኩራት የሆነው የ1888 ዓ.ም. የዓድዋ ገድል የኅብር ሥራቸው ፍሬ መሆኑን መቀበልና ከፍ አድርጎ መናገር ጓጎጠን!! እነሱና ለጣቂዎቻቸው በደምና በአጥንት ባቆዩት የነፃነት ኩራት ውስጥ እየኖርን፣ የኅብር ገድላቸውን ሳንሰነጣጥር ማመሥገን እንኳ አቃተን፡፡ በብሔረሰብ፣ በአካባቢ፣ በሃይማኖት፣ በቁርሾ፣ በሥልጣን ተዋረድ ሳይሸፋፈጡና ሳይሰነጣጠሩ ያስገኙትን ድል በተበጣጠሱ ዕይታዎች ከመቃረጥ ሳንወጣ (የዓድዋን ጦርነትና ድል የመላ ዘማቾችና ደጀኖች ተጋድሎ አድርገን ሳናይ፣ ተጋድሎውና ኢትዮጵያ ራሷ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝብ የኩራት ሀብት መሆናቸው ደማችን ውስጥ በቅጡ ሳይገባ) ‹‹የአፍሪካ ኩራት ነን!››፣ ‹‹ከአፍሪካውያን ጋር ወደፊት እናከብረዋለን!›› ስንል ትንሽም ኃፍረት ጠቅ አያደርገንም!? የየትኞቹንም ግለሰቦች ዝና ነጥለን አውጥተን በትርክት፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በሙዚቃ፣ በሥነ ጥበብ ስናጦዝ (‹‹ታቦት›› ስናደርግ) የቀሪዎቹን ተጋድሎ መጋረዳችን መሆኑ እስካልተገለጸልን ድረስ የአፍሪካ ኩራት መሆን አንችልም፡፡ አንዳንዶቻችን ጣይቱንና ምኒልክን እንኮኮ ስንል ሌሎቻችን ደግሞ እነሱን ከልለን ከየብሔርና ከየጎጣችን የተገኙ ናቸው ያልናቸውን ጀግኖችና የጦር መሪዎች እንኮኮ በማለት ውስጥ እስከባዘንን ድረስ (አባቶቻችንና እናቶቻችን ኢትዮጵያ አገሬን ብለው ያካሄዱትን ተጋድሎ በየብሔርና በጎጥ መከታተፍ እስከ ቀጠልን ድረስ)፣ ለአፍሪካና ለመላ ጥቁር ወገኖቻችን ኩራት ሳይሆን የትዝብት እንቆቅልሽ ነው የምንሆነው፡፡ ያለ አንዳች መወዛገብ አፍሪካውያን የዓድዋውንም ሆነ በፋሺስት ኢጣሊያ ላይ የተካሄደውን ተጋድሎ የአፍሪካ ተጋድሎና ድል ብለው ያከብሩታል፡፡ በእነዚያ ታሪካዊ ድሎች ላይ ኢትዮጵያውያን ስንርኮመኮም ደግሞ፣ ምን ነክቷቸዋል ሰዎቹ ለሚል ጥያቄ ምላሽ ያጡብናል፡፡

ምላሽ የሚያጡት ስላልገባቸው ነው የምትሉ ካላችሁ የባሰ የታሪክ መሳቂያ ነው የምትሆኑት፡፡ መርኮምኮማችን ለእኛም ለእነሱም መልስ የሌለው ያልገባቸው ነገር ስላለ ሳይሆን፣ እኛ የአሁኖቹና በቅርብ የቀረፁን አወቅን ባዮች ጥንግርግራችን የወጣ ስለሆነ ነው፡፡ ለማፈር ምናልባት ቢበጀን ከጥንግርግራችን ሰበዞች አንዳንዶቹን ልነካካ፡፡ ብሔረሰባዊ ማንነት የሚገኘው በመወለድ ነው በሚለው አስተሳሰብ ብንሄድ፣ የእነ ምኒልክና የጣይቱ ብጡል ትውልድ አማራ ካልሆነ ‹‹ዝርያ›› ጋር ያገናኘናል፡፡ ብሔረሰባዊ ማንነት በመወለድ ሳይሆን ከታነፅንበት ባህልና ሥነ ልቦና የሚገኝ ነው በሚለው አስተሳሰብ ከሄድንም፣ በአካባቢያቸው ቋንቋ አፍ እስከ መፍታት ድረስ የአካባቢያቸው ውጤት የሆኑ ሰዎችን በወላጆቻቸው/በአያቶቻቸው የጀርባ አመጣጥ እየፈረድን የምናደርሰው ጥቃት መሳቂያ ያደርገናል፡፡ እነ ምኒልክንና ጎበናን ከዓድዋ በፊት በሠሩት ሥራ ለመቀየም ስንፈልግ፣ በእነሱ ዘመን ውስጥ የእነሱን ቦታ ይዘን ብንፈጥር ኖሮ ከእነሱ አድራጎት ምን ያህል እንርቅ ነበር የሚል ጥያቄ ክፉኛ ይታዘበናል፡፡ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ጦረኞችን በግፍ ሥራ ተቀየምን ባዮቹ የዛሬ በቀለኞች፣ ስለብዙ የሰው መብቶች ከሚያወራ ዘመናቸው በ130 ዓመት ግድም ቁልቁል ተንከባለው የእነሱን ሥራ እየፈጸሙት በመሆናቸው ደግሞ፣ 21ኛው ክፍለ ዘመን ጭንቅላት የሚፈነክት ትዝብት ይወረውርብናል፡፡ ይህንን የታመመ ጊዜ በስክነትና በጥንቃቄ እንድናልፈው ብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ አንግባ፣ መነታረኪያ በሆኑ ነገሥታት አለባበስ እየተቀሸርን የተወሰነ ሕዝብን የእነ እከሌ አምላኪ ለሚል አደገኛ ፍረጃ ከማጋለጥ እንቆጠብ ለሚል ምክር ጆሮ የሌለን የአደባባይና የአዳራሽ ጀብደኞችም ጥንግርግራሞች ነን፡፡ እንዲህ ያሉ ጥቂት ግለሰቦችን ከማየት ተነስተን እነሱ ያደረጉትን የሙሉ ብሔረሰብ ባህርይ አድርገን የምናላክክም ግልቦች በጠንጋራነቱ ግቢ ውስጥ ነን፡፡ ይህንን የመሳሰለ ጥንግርግራችንን ሳናራገፍ፣ የታሪክ ሰዎች የየኖሩበት ዘመን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ውጤቶች መሆናቸውን ሳንቀበል፣ ከእንቆቅልሽነት መውጣት አንችልም፡፡ በአጠቃላይ ዓድዋን በኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ፣ ኢትዮጵያንም በአፍሪካና በጥቁር የታሪክ ቅርስ ውስጥ ከትተን ማየትና ቅርስነቱ እንዳይደበዝዝ፣ እንዳይቆሳስልና እንደይፈራርስ የመንከባከብ ኃላፊነታችንን እስካልተወጣን ድረስ የአፍሪካ ኩራት መሆን አንችልም፡፡ ከዚህ ታሪካዊ ኃላፊነት አኳያ የዓድዋ ችቦን ብሩህነት እያፈካን ለአፍሪካ ኩራት የምንሆነው ከብሔርተኛ/ጎጠኛ መጣበብ ወጥተን፣ ሰላማችን፣ የዕውቀትና የጥበብ ልምላሜያችን፣ ትስስራችንና ግስጋሴያችን ከአገር እስከ ቀጣናችንና አኅጉራችን ድረስ በዓድዋዊ ማጠንት የተሞላ ሲሆን ነው፡፡

ለዚህ ሁሉ ስኬት ሰፊ ልቦና፣ አርባ ክንድ ብልህነትና ዓድዋዊ አቅል አይለየን!!!!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...