ዶ/ር ተስፋዬ መኮንን የተወለዱት በጅማ ከተማ ቢሆንም፣ ዕድገታቸውንና የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት ሐረር ነው፡፡ ‹‹ወታደር አንድ ቦታ ስለማይቀመጥና የወታደር ልጅ በመሆኔ ዕትብቴ በተቀበረበት ጅማ ከተማ ብወለድም፣ አባቴ ወደ ሐረርጌ በመቀየሩ ሐረር አድጌያለሁ፡፡ እስከ ዘጠነኛ ክፍል ከተማርኩ በኋላ ወደ ኩባ ሄድኩኝ፤›› የሚሉት ዶ/ር ተስፋዬ፣ ወደ ኩባ ሐቫና የሄዱት አባታቸው በካራማራ ጦርነት በመሰዋታቸው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት (ደርግ) ከኩባ መንግሥት ጋር በነበረው መልካም ግንኙነት የጀግኖች ልጆች የትምህርት ዕድል ሲሰጣቸው እሳቸውም አንዱ በመሆናቸው ነው፡፡ አብረዋቸው ለትምህርት ከሄዱት ኢትዮጵያዊት ጋር በማግባት ሦስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡ በኢትዮጵያ በተለይ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል በሕክምና ሲያገለግሉ ቆይተው ለትምህርት ወደ አሜሪካ ከሄዱ በኋላ ኑሯቸውን እዚያው አሜሪካ አድርገዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ ሦስተኛ ወገን የመድን ኢንሹራንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ በሕግ ተደንግጎ ተግባራዊ እንዲሆን ተነሳሽነቱንና ጥያቄውን ያቀረቡ ናቸው፡፡ እንዲሁም ‹‹የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል (አፍሪካ ሲዲሲ) ኢትዮጵያ ውስጥ መገንባት አለበት›› ብለው ንድፈ ሐሳቡን ለጤና ሚኒስቴር በማቅረብና ዕውን እንዲሆን በማድረግ ከፍተኛ ሥራ የሠሩም ናቸው፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ የሕክምና ባለሙያ ብቻ ሳይሆኑ ደራሲም ናቸው፡፡ በ1928 ዓ.ም. ስለተደረገው የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት እውነተኛ ገጽታን የሚተርክ ‹‹ቀይ አንበሳ›› የሚል መጽሐፍና የሌሎች መጻሕፍትም ደራሲ ናቸው፡፡ በጤናው ዘርፍ ከመቶ በላይ የምርምር ሥራዎችን ሠርተው፣ 60 የምርምር ውጤቶች በዓለም አቀፍ የሳይንስ ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ ዶ/ር ተስፋዬ ከውልደት እስከ ዕድገት፣ ስለሕክምና ሙያቸው፣ ለአገራቸው ኢትዮጵያ ስላበረከቱት ተግባራትና እየሠሯቸው ስላሉት የምርምር ሥራዎችን በሚመለከት ከታምሩ ጽጌ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡- ሶማሊያ ኢትዮጵያን በ1969 ዓ.ም. በመውረሯ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ሲዘምቱ የእርስዎም አባት አንዱ ነበሩ፡፡ ወራሪው የሶማሊያ ጦር ካራማራ ላይ ግብዓተ መሬቱ ሲፈጸም የሕይወት ዋጋ ከከፈሉ (ከተሰው) ጀግኖች ኢትዮያውያን መካከልም አንዱ ነበሩ፡፡ በዚያን ወቅት እርስዎ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ነበሩ፡፡ እንዴትና በምን ሁኔታ ወደ ኩባ ሊሄዱ ቻሉ?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- እንደነገርኩህ የተወለድኩት ጅማ ክፍለ አገር ቢሆንም፣ ያደግኩት ግን ሐረር ነው፡፡ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቴን ከአንደኛ እስከ ዘጠነኛ ክፍል የተማርኩትም ሐረር ነው፣ የወታደር ልጅ ነኘ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ (ሀይስኩል) እያለሁ ከዘጠነኛ ወደ አሥረኛ ክፍል ሳላልፍ አባቴ በሶማሊያ ጦርነት ተሰዋ፡፡ በወቅቱ በሶማሊያ ጦርነት የተሰው የጀግኖች ልጆች ወደ ኩባ ሄደው እንዲማሩ በተሰጠው ዕድል (ሁለተኛ ዙር ላይ) እኔና እህቴ ዕድሉን አግኝተን ለመሄድ ቻልን፡፡ ኩባ ከሄድን በኋላ ‹‹ደሴት›› በሚባል የሕፃናት ማሳደጊያ ቦታ ገብተን አደግን፡፡ ቋንቋውን ከለመድን በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ጨርሼ ወደ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ፡፡ በኩባ ታዋቂ በሆነው የሕክምና ዩኒቨርሲቲ ‹‹ሳንቲያጎ ዩኒቨርሲቲ›› ገብቼ የመጀመርያ ዲግሪዬን በሕክምና ያዝኩኝ፡፡
ሪፖርተር፡- የመጀመርያ ዲግሪዎን በሕክምና ከያዙ በኋላ ሥራ የጀመሩት እዚያው ኩባ ነበር?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- አይደለም፡፡ የመጀመርያ ዲግሪዬን እንደጨረስኩ በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቅ ሁለተኛ ዲግሪ (ማስተርስ ኦፍ ሜዲሰን) እንድማር ዕድል ተሰጥቶኝ ነበር፡፡ ነገር ግን እኔ ወደ አገሬ ተመልሼ በአገሬ መሥራት እንደምፈልግ ተናግሬ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩኝ፡፡ ምንም እንኳን አባቴ ወታደር የነበረ ቢሆንም፣ እኔ ግን በሲቪል ሆኜ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል የመጀመርያ ሕክምና ሥራዬን ጀመርኩኝ፡፡ ለስምንት ዓመታትም አገልግያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ከእህትዎ ጋር ወደ ኩባ ከሄዱ በኋላ ‹‹ደሴት›› በሚባል ሕፃናት ማሳደጊያ እንደገባችሁ ነግረውኛል፡፡ ነገር ግን በኩባ ‹መንግሥቱ ኃይለ ማርያም› እና ሌሎችም በኢትዮጵያ ስሞች የተሰየሙ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ ሰምቻለሁ፡፡ እንዴት ወደ እነዚያ ትምህርት ቤቶች እንድትገቡ አልተደረገም? ምክንያቱም ሕፃናት ስለነበራችሁ ኢትዮጵያዊነታችሁን እያሰባችሁና እያወቃችሁ እንድታድጉ ከማድረግ አንፃር?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- እውነት ነው አሉ፡፡ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ካራማራ፣ ሰኔ ሃያ አንድ (ደርግ በይፋ የተቋቋመበት ቀን ነው) እና ቆሬ (ከሶማሊያ ጋር ትልቅ ጦርነት የተካሄደባት ትንሽ ከተማ ነች) ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ትምህርት ቤት 600 ተማሪዎች በድምሩ 2,400 ተማሪዎች ይማሩባቸዋል፡፡ ሁሉም ተማሪዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ሁሉም ትምህርት ቤቶች በደሴቷ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ እኔ ሁለተኛ ደረጃን (ሃይስኩል) የተማርኩት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትምህርት ቤት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያውያን መምህራን በኩባ ትምህርት ቤቶች (ዩኒቨርሲቲዎች) እንደሚያስተምሩ ሰምቻለሁ፡፡ እርስዎ በተማሩበት መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና በሌሎቹም በኢትዮጵያ ስሞች የተሰየሙ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ ኢትዮጵያውያን መምህራን ነበሩ?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- መጀመርያ ወደ ኩባ ከገባንበት ጊዜ ጀምሮ ለስድስት ወራት የተማርነው ስፓኒሽ ቋንቋ ነው፡፡ ቋንቋውን እንደቻልን ወደ ትምህርት ቤት ገባን፡፡ የሚገርመውና መናገር የምፈልገው ትምህርቱ የቀለም ትምህርት ብቻ አይደለም፡፡ ግማሽ ቀን ቀለምና ግማሽ ቀን እርሻ (የተግባር ትምህርት) ነው የተማርነው፡፡ እርሻ ማረስ፣ ብርቱካን መኮትኮት፣ ማዳበሪያ መርጨት፣ ውኃ ማጠጣትና የተለያዩ ሥራዎችን ለሦስት ሰዓታት እየሠራን ነው የተማርነው፡፡ ይህ ለእኛ በተለየ የተሰጠ ሳይሆን፣ የአገሪቱ ዜጎች ጭምር የሚተገብሩትና የአገሪቱ የትምህርት ካሪኩለም የተቀረፀበት የአሠራር ሒደት ነው፡፡ የተግባር ሥራው የሚጀምረው ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአገሪቱ ሥነ ምኅዳር አቀማመጥ ምን ይመስላል?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- የኩባ አቀማመጥ ሜዳ ነው፡፡ እኛ የነበርንበት ደሴትም ሜዳ ነው፡፡ ከፍተኛ የብርቱካን ምርት የሚመረትበት የእርሻ መሬት ያለበት ነው፡፡ በእርግጥ ኩባ ከፍተኛ የሸንኮራ አገዳ ምርት የሚመረትባት መሆኗ ይታወቃል፡፡ ከፍተኛ የስኳር ምርትም አምራች አገር ነች፡፡ እኛ የነበርንባት ደሴትም በስፓኒሽ ‹‹የወጣቶች ደሴት›› (Youth Island) ትባላለች፡፡ ከዋና ከተማዋ ሐቫና በፈጣን መርከብ የሁለት ሰዓታት ጉዞ ትርቃለች፡፡
ሪፖርተር፡- ደሴቷ በተለያዩ ምክንያቶች የሌሎች አገሮች ዜጎች የሚማሩባት (የሚኖሩበት) ደሴት ነች? ወይስ የኩባ ተወላጆች (ዜጎች)ም ይማሩባታል?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- የአገሪቱ ተወላጆችም አሉ፡፡ ግን በብዛት ከሌሎች አገሮች የሚመጡ ይበዛሉ፡፡ ከአንጎላ፣ ከሞዛምቢክ፣ ከኒካራጓ፣ ከናሚቢያና ከሌሎችም የአፍሪካ አገሮች የሄዱ ወጣቶች አሉ፡፡ ሁሉም በአገራቸው የተሰየሙ ትምህርት ቤቶች አሏቸው፡፡ ለምሳሌ ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትምህርት ቤት ጎረቤት ‹ሳሞራ ማሼል› የሚባል የሞዛምቢክ ትምህርት ቤት አለ፣ የሌሎችም እንዲሁ፡፡ እረፍት ስንሆን እግር ኳስና የተለያዩ ጨዋታዎችን እናደርጋለን፡፡ ሁሉም ነገር የኢንተርናሽናል ኮሙዩኒቲ ፖሊሲን የተከተለ በመሆኑ ሁሉም አገር ደረጃውን የጠበቀ ነው፡፡ አስተዳደጋችንም ይህንኑ ፖሊሲ የተከተለ ነበር፡፡ የኩባን መንግሥት የማመሠግነው በዚያን ወቅት ቋንቋችንን እንዳንረሳ፣ ባህላችንን እንዳንረሳ፣ አገራችንን እንዳንረሳ፣ የታሪክ መምህር፣ የጆኦግራፊ መምህርና የአማርኛ መምህር ከኢትዮጵያ እየመጡና በየሁለት ዓመቱ እየተቀያየሩ አስተምረውናል፡፡ በዚህ ምክንያት አገራችንን፣ ባህላችንንና ቋንቋችንን እንዳንረሳ ላደረጉን ኢትዮጵያውያን ምሥጋናችን ላቅ ያለ ነው፡፡ በአጠቃላይ የኩባ መንግሥት በሶማሊያ ጦርነት ለኢትዮጵያ ካደረገው ውለታ በተጨማሪ፣ በጦርነቱ የተሰውትን ጀግኖች ኢትዮጵያውያንን ልጆች ወስደው በማስተማራቸው ሊመሠገኑ ይገባዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በሶማሊያ ጦርነት የተሰው ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ልጆች ኩባ ሄደው እንዲማሩ የተደረገው በኢትዮጵያ መንግሥት ጥያቄ ነው? ወይስ የኩባ መንግሥት በራሱ ተነሳሽነት የሰጠው ዕድል?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- እንደሚመለስኝ መንግሥት ለመንግሥት ተነጋግረው የወሰኑ ይመስለኛል፡፡ እኔ በወቅቱ የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ፡፡ አባቴ የሦስተኛ ክፍለ ጦር አባል ነበር፡፡ በጦርነት የተሰው የጀግኖች ልጆች በየክፍለ ጦሩ ተጠርተን የሕክምና ምርመራ አድርገው ወሰዱን፡፡ በእርግጥ በጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና በጓድ ፊደል ካስትሮ መካከል በተደረገ ስምምነት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ወደ ኩባ የሄዱት በጦርነቱ የተሰው ጀግኖች ልጆች ብቻ አልነበሩም፡፡ ለምሳሌ ከሐረር የሄድነው 485 ስንሆን፣ ሁላችንም ከሐረር ብቻ ሳይሆን ከቀብሪ ድሃር የጅግጅጋ ልጆች፣ ከአዲስ አበባም ከሕፃናት አምባና ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ ልጆች ተደባልቀን ነው የሄድነው፡፡ እንደ እህትና እንደ ወንድም አብረን ነው ያደግነው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ አፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ታዳጊ ልጆች ወደ ኩባ ተወስደው እንዲማሩ ተደርጓል፡፡ የምትማሩት ከየአገሩ የሄዳችሁት ለብቻችሁ ነው? ወይስ ተደበላልቃችሁ?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- እኔም ሆንኩ እህቴ እስከምንጨርስ ድረስ የተማርነው ለብቻችን (ኢትዮጵያውያን ብቻ) ነበር፡፡ ሌሎችም የአፍሪካ አገሮችም ለብቻቸው ነበሩ፡፡
ሪፖርተር፡- ሁሉም የአፍሪካ አገሮች ዜጎች ወደ ኩባ የሄዱ በአገሮቻቸው መሪዎች ወይም አገራዊ ስያሜ ትምህርት ቤቶች ተሰይመውላቸው ነበር?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- አዎ! በአገሮቻቸው ስያሜ በተሰጣቸው ትምህርት ቤቶች ነው የተማሩት፡፡ መጨረሻ ላይ ግን ተማሪዎቹ እያነሱ ሲመጡ በአንድ ትምህርት ቤት ተሰባስበው እንዲማሩ የተደረጉ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እኛ ግን ያ ዕድል አልገጠመንም፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ በሳንቲያጎ ዩኒቨርሲቲ ከተማሩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በጦር ኃይሎች ሆስፒታል አገልግለዋል፡፡ ይህ የሆነው እርስዎ ፈልገው ነው? ወይስ መንግሥት ለመንግሥት የተስማሙበት ሁኔታ ነበር?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- እኔ የመጣሁት በራሴ ፍላጎት ነው፡፡ ምንም እንኳን በውጭ አገር የተማሩ እንደ ትምህርት ዓይነቱ በሚመለከተው ተቋም የሚመደቡ ቢሆንም፣ እኔ ግን በጤና ጥበቃ በኩል አልተመደብኩም፡፡ ምክንያቱም የወታደር ልጅ በመሆኔና በጦርነቱ ወቅት (በሶማሊያ ጦርነት) የ12 እና 13 ዓመት ዕድሜ ላይ ብሆንም፣ በጦርነቱ የተሳተፍኩ በመሆኔና ያ ስሜት ስለነበረኝ፣ ‹‹እኔ ማገልገል ያለብኝ አባቴ ባገለገለበት ተቋም ነው›› በማለት በፍላጎቴ በሲቪልነት በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ተመድቤ ለ15 ዓመታት አገልግያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ያጠኑት ወይም ስፔሻላይዝ ያደረጉት የሕክምና ዘርፍ ምን ነበር?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- ያጠናሁት ጠቅላላ ሕክምና (General Practitioner) ነበር፡፡ በማዕከላዊ ሆስፒታል ለአራት ዓመታት ካገለገልኩ በኋላ፣ በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ገብቼ በሰመመን (Anesthesia) ትምህርት ስፔሻላይዜሽን ለሦስት ዓመታት ተምሬያለሁ፡፡ ለ12 ዓመታት በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ካገለገልኩ በኋላ ለሦስት ዓመታት ደግሞ በዓለም የጤና ድርጅት በኢትዮጵያ አገልግያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎትን በሚመለከት የመጀመርያ ምርመር ያደረጉት እርስዎ መሆንዎን ሰምቻለሁ፡፡ እስኪ ስላደረጉት ምርመርና ውጤቱ ይንገሩን?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- የሰመመን ሕክምናውን ስሠራ የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር የድንገተኛ ሕክምና መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ይህንንም ልረዳ የቻልኩት በሥራ ላይ እያለሁ ሰዎች በተለያየ ምክንያት ተጎድተው ወደ ሕክምና ቦታ ይመጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ለትንሹም ለትልቁም የምንጠራው እኛው ነን፡፡ እንደ እነዚህ ያሉ ድንገተኛ ችግሮችን መወጣት የምንችለው የድንገተኛ ሕክምና በማቋቋም መሆኑን በመረዳቴ፣ ‹‹በኢመርጀንሲ ሜዲሰን ኮንሰፕት›› ዙሪያ ምርምር ማድረግ ጀመርኩ፡፡ በ1995 ዓ.ም. ሐሳቡን ለኢትዮጵያ ሐኪሞች ማኅበር አቀረብኩ፡፡ ከዚያም ከብዙ ጓደኞቼ ጋር በመመካከርና በመነጋገር ‹‹ቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት በኢትዮጵያ›› የሚለውን አገልግሎት መስጠት እንዲጀመር አድርጌያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት የጀመሩት እርስዎ ባደረጉት ምርምር ብቻ ነው? ወይስ ተጨማሪ ሥልጠናዎችን አግኝተዋል?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- ተጨማሪ ሥልጠናዎችን በጀርመንና በእስራኤል ወስጃለሁ፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ስፔሻላይዝ ሳደርግ ያየሁትና የተረዳሁት ዲፓርትመንቶቹ የሰርጂካል፣ የፔዲያትሪክስ፣ የውስጥ ሕክምና በማለት የተከፋፈሉ ከመሆናቸው በስተቀር፣ ድንገተኛ ሲመጣ በተለየ ቦታ የሚታከምበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ራሱን በመቻል የኢመርጀንሲ ስፔሻሊስት ሐኪሞችና ነርሶች መኖር አለባቸው ብዬ መሥራት ስጀምር፣ አድቫይዘሬ ጀርመናዊ ስለነበረች በእሷ አማካይነት ወደ ጀርመን ሄጄ ስለኢመርጀንሲ የሕክምና ሥልጠና ወስጃለሁ፡፡ ከጀርመን ተመልሼ በመሥራት ላይ እያለሁ በድንገት ወደ እስራኤል ልሄድ ችያለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ እስራኤል በድንገት ለምንና እንዴት ሄዱ?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- በወቅቱ የመገናኛና ትራንስፖርት ሚኒስትር የነበሩት አቶ አብዱልሙጂድ ሁሴን ነበሩ፡፡ እሳቸው በመሣሪያ ተመትተው ለሕክምና ወደ እስራኤል እንዲሄዱ ሲደረግ እሳቸውን ይዤ ነው የሄድኩት ተመልሼ ለድንገተኛ ሕክምና ሥልጠና ሄድኩኝ፡፡ በቴሊአቪቭ ዩኒቨርሲቲ ለሦስት ወራት ሠልጥኛለሁ፡፡ እኔና ሌሎች ጓደኞቼ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን በድንገተኛ ሕክምና ዙሪያ ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ ለምሳሌ ያህል የጠብታ አንቡላንስ ባለቤት አንዱ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በ1996 ዓ.ም. የመጀመርያውን የድንገተኛ ሕክምና ከጓደኞችዎ ጋር ሆነው የጀመሩት ከዱባይ አምቡላንሶችን አስመጥታችሁ ‹‹መስኮት›› በሚል ስያሜ ነበር፡፡ እስኪ ስለአጀማመራችሁ ያስረዱኝ?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- ስለድንገተኛ ሕክምና እኛ ከሠለጠንን በኋላ ሌሎችንም ማሠልጠን ጀመርን፡፡ ነገር ግን ሥራውን በራሳችን ጀምረን አርዓያ መሆን አለብን በማለት፣ 18 ሐኪሞች ተሰባስበን የአንድ መስኮት የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎትን ጀመርን፡፡ ከእኛ በኋላ ሥራው ተስፋፍቶ አሁን የደረሰበት ላይ ደርሷል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ በብዛት እየደረሰ ያለውን የተሽከርካሪ አደጋ በመመልከት፣ በተለይ እርስዎ የሦስተኛ ወገን መድን መጀመር አለበት የሚል ሐሰብ በማንሳት እስከ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሄደው እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡ ያንን መሠረት በማድረግም አሁን የሦስተኛ ወገን መድን ተግባራዊ ሊሆን ችሏል፡፡ እስኪ ስለእሱ ይንገሩን?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- ሕክምና ስንሠራ አንዱና ትልቁ ችግር የመኪና አደጋ ነው፡፡ የመኪና አደጋን በሚመለከት የሌሎች አገሮችን አሠራር ስናጠና የሦስተኛ ወገን መድን (ኢንሹራንስ) አላቸው፣ በኢትዮጵያ ግን የለም፡፡ የሚገርመው ነገር እኛ ይህንን ጥናት ስናጠና ኤርትራ ነፃ አገር ከሆነች ስምንት ዓመቷ ቢሆንም፣ የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ግዴታ ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ተሽከርካሪዎች ወደ ኤርትራ ሲገቡ መድን ይቆርጣሉ፡፡ የኤርትራ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ግን የመድን ዋስትና አይገቡም፡፡ በዚህ ምክንያት ለምን በኢትዮጵያ የሦስተኛ ወገን መድን ኢንሹራንስ አይጀመርም ብዬ ሐሳብ አነሳሁ፡፡ በኢትዮጵያ ያሉ የመድን ድርጅቶችን ስናነጋገግር በጣም ደስተኛ ሆነው ሐሳቡን አበረታቱ፡፡ በዚያው ሰሞን የኢትዮጵያ አደጋና መከላከል ዝግጁነትን በሕግ ለማቋቋም ፓርላማው የምክክር መድረክ ማዘጋጀቱን ጠቁሞ ለምክክር ጥሪ አደረገ፡፡ እኔ በሕዝብ ምክክር መድረክ ላይ ለመገኘት ፓርላማ ሄድኩ፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የሦስተኛ ወገን መድን አስፈላጊነትን በዝርዝር አስረዳሁ፡፡ እኔ ሦስተኛ መድን ክፍያ ከአሥር እስከ 15 በመቶ እንዲሆን ጠይቄ ነበር፡፡ ይህ የሆነው እ.ኤ.አ. በ2001 ሲሆን፣ በ2008 ዓ.ም. አዋጁ ፀደቀ፡፡ እኛ በአደጋ ሰው ከሞተ በፐርሰንት እንዲከፈል የጠየቅነውን ከአሥር እስከ 15 በመቶ ክፍያ፣ ፓርላማው አዋጁን ሲያፀድቅ 30,000 ብር በሚል በቁርጥ አደረገው፡፡ ይኼ ደግሞ ‹‹ኢንፍሌሽን›› ይበላዋል፡፡ በፐርሰንት ቢሆን ግን ወቅቱን የተከተለ ይሆን ነበር፡፡ አዋጁ በ2008 ዓ.ም. ፀድቆ ለአራት ዓመታት ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል፡፡ እኔ ከውጭ ስመጣ አዋጁ ተግባራዊ ሳይደረግ መቆየቱን በማወቄ ወደ ትራንስፖርት ሚኒስቴር ሄጄ ለምን ተግባራዊ እንዳልተደረገ ጠየቅሁ፡፡ በወቅቱ የነበሩት ምክትል ሚኒስትር በ2013 ዓ.ም. እንደሚተገበር ቃል ገብተውልኝ በቃላቸው መሠረት ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ሦስተኛ ወገን መድን እንዲጀመር ተነሳሽነቱን ከመውሰድ እስከ አዋጅ ማስፈጸም የታገሉበት የተለየ ምክንያት ነበረዎት?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- እውነት ለመናገር ምንም ዓይነት ገፊ ምክንያት አልነበረኝም፡፡ ሁሉንም ነገር ያደረግኩት ለወገኔና ለሕዝቤ ስል ነው፡፡ እኔ ወደ ዓለም ጤና ድርጅትም የገባሁት በዚሁ በድንገተኛ ወይ የመኪና አደጋ መከላከል (Traffic Prevention) ሥራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዓለም የጤና ድርጅት ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ሠሩ?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ነው የሠራሁት፡፡ ከዚያ ወደ አሜሪካ ሄድኩኝ፡፡ አሜሪካ የሄድኩት በፌሎሺፕ ነው፡፡ ለሁለት ዓመታት ከተማርኩ በኋላ ‹‹Epidemic Intelligence (Epidemiology)›› በሠለጠንኩበት ሙያ የምርምር ሥራ ጀመርኩኝ፡፡ በዚያው የተለያዩ ሥልጠናዎችን (ስፔሻላይዜሽን) ለሁለት ዓመታት ወስጄ ራሴን አበቃሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ያልተመለሱት ለምንድነው?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- ምንም እንኳን እዚያው ሆኜ እየሠራሁ ቢሆንም፣ ለአገሬም እየሠራሁ ነው፡፡ የተማርኩትና የሠለጠንኩበት ሙያ ለአገሬም ይበልጥ የማገልግልበትን ዕውቀት ስላገኘሁ፣ እስካሁን ከአሥር ጊዜ በላይ ተመላልሻለሁ፡፡ የተለያዩ ሥራዎችንም ሠርቻለሁ፣ እየሠራሁም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የእርስዎ አባት የአገር ፍቅር ያላቸውና ለአገራቸው ነፃነት ተዋግተው ካራማራ ላይ የተሰው ጀግና ነበሩ፡፡ እርስዎም በአባትዎ የጀግንነት ሥራ የመማር ዕድል አግኝተው የሕክምና ሙያ በማጥናት አንቱ የተባሉ ሐኪም ሆነዋል፡፡ ታዲያ በጤናው ዘርፍ ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን ደረጃ እንድታገኝና ወገንዎትን በዘርፉ፣ በአመራርነትም ሆነ በቀጥታ አገልግሎት በመስጠት ማገልገል ሲገባዎ በውጭ አገር ሆነው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በቂ ነው ይላሉ?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- አገሬንና ያስተማረኝን ሕዝብ የበለጠ ልጠቅም የምችለው በውጭ ሆኜ ብሠራ ነው፡፡ በውጭ አገር ሆነህ አገርህን ማገልገል የምትችልበት የበለጠ ነገር አለ፡፡ በጤናው ዘርፍ የሚያስፈልጉ በርካታ ነገሮች በውጭ ዓለም አሉ፡፡ እዚህ በአንድ ዘርፍ ተሾሜ ወይም አማካሪ ሆኜ ከምቀመጥ ለሕዝቤ የሚያስፈልገውን ነገር ባበረክት የተሻለ ነው፡፡ እኔ ፖለቲከኛ ስላልሆንኩ ማገልገል የምችለው በሙያዬ በጤናው ዘርፍ ብቻ ነው፡፡ አብዛኞቹ በጤናው ዘርፍም ሆነ በሌላው የመንግሥት አመራርነት ላይ ያሉ ወገኖቼ በዕድሜ ከእኔ በጣም ያነሱ በመሆናቸው፣ የምመለከተውንና ስህተት ነው ብዬ የማምንበትን ሁሉ ስለሚስተካከልበት ሁኔታ ምክሬን እለግሳለሁ፡፡ እንደ ታላቅ ወንድምና እንደ አንድ ዜጋ ትክክል ያልሆነውን ትክክል አይደለም በማለት ሐሳቤን እሰነዝራለሁ፡፡ በጤናው ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኜ የማላገኘውን ነገር ከዚያ የመላክና በተቻለ መጠን ለመርዳት እየሞከርኩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሊገለጽ የሚችል አሜሪካ ሆነው ለኢትዮጵያ አበረከትኩ የሚሉት ነገር ካለ ቢነግሩን?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- ትልቁ ነገር አበረከትኩ የምለው በኅብረተሰብ ጤና ላይ ብዙ ምርምር በማድረግ፣ የተለያዩ ምርምሮችን በመቆጣጠርና በመምራት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ፡፡ የምርምር ውጤቶችም ታትመው ይገኛሉ፡፡ የአቃቂ ውኃ ተበክሏል ተብሎ ከሌሎች የምርምር ባለሙያዎች ጋር ያደረግኩት ምርምር ተጠቃሽ ነው፡፡ በትግራይ ክልልም በጉበት ላይ ችግር ተፈጥሮ ያደረግነው ምርምርም ውጤታማ ነበር፡፡ የምርምሩን ሒደትና ውጤት ከሙያ ሥነ ምግባር አንፃር መግለጽ ተገቢ ባይሆንም፣ ግን ብዙ ምርምሮችን አድርገናል፡፡ በማስተማርም ያለኝን ዕውቀት ለወገኖቼ አስተላልፌያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሌላው የአፍሪካ በሽታ መቆጣጠርና መከላከል ማዕከል (Africa CDC) የምርምር ተቋም በአገር ውስጥ መቋቋም እንዳለበት በማመን ንድፈ ሐሳቡን በማዘጋጀት ለጤና ጥበቃ አቅርቤያለሁ፡፡ ጤና ጥበቃ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ተቋሙ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ የተቋሙ መመሥረት ከውጭ የሚገኝ የዕርዳታ ገንዘብ በአግባቡ ለሚፈለገው ተግባር መዋሉን ለመቆጣጠርና ቀጣይ ተመሳሳይ ችግር ቢፈጠር ያለ ምንም መጠራጠር በግልጽ እንዲረዳ ለማድረግ መፍትሔ ሰጪ ይሆናል በሚል ነበር ሐሳቡን ያቀረብኩት፡፡
ሪፖርተር፡- በጤናው ዘርፍ ያለው የጤና ፖሊሲ አፈጻጸምን በብልፅግና አመራር የአገዛዝ ዘመን እንዴት ይገመግሙታል?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የፖሊሲ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቀደም ብለው የነበሩት የጤና ፖሊሲና አሁን እየተሠራበት ያለውን ፖሊሲን አነፃፅሮ ምላሽ ለመስጠት መመርመር ያስፈልጋል፡፡ የእኔ ጥናት ፖሊሲ ላይ አይደለም፡፡ ጥናቴ በድንገተኛ አደጋዎችና ተያያዥ ነገሮች ላይ ነው፡፡ እንደ አጠቃላይ ግን የተወሰኑ ለውጦች አሉ፡፡ ድንገተኛ የሕክምና ተቋማት በብዛት ተቋቁመዋል፡፡ ግን ለሁሉም ይደርሳል ባይባልም የተሻለ ነው፡፡ በእርግጥ የሚቀሩ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ መከላከልና ዝግጁነት ላይ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የተቀናጀና መልስ መስጠት የሚችል ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ለአንድ ድንገተኛ አደጋ፣ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ አምቡላንስ፣ የቀይ መስቀል አምቡላንስና የሆስፒታል አምቡላንስ በተለያየ አቅጣጫ ተሯሩጠው ይደርሳሉ፡፡ ይህ ሀብትና ጉልበት ማባከን ነው፡፡ በጀት ለስንቱ ይመደባል? ይህንን አቀናጅቶ አንድ ለድንገተኛ አደጋ መልስ የሚሰጥ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ አንድ የስልክ ጥሪ ብቻ ይበቃል፡፡ ይህ አሠራር ‹‹Intergrated Medical Response›› ይባላል፡፡ አሠራሩ እንደ እዚህ መሆን አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ላለፉት ሁለት ዓመታት በሕወሓትና በማዕከላዊ መንግሥት መካከል በነበረ ጦርነት፣ በተለይ እርስዎ በሚኖሩበት አሜሪካ ያሉ ሚዲያዎች በማዕከላዊ መንግሥት ላይ ከፍተኛ የሆነ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ከፍተው ነበር፡፡ እርስዎ የነበረዎት ምልከታ ምን ነበር? ወይም ሁኔታውን እንዴት ነበር የሚከታተሉት?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- ጦርነት ማንንም አይመርጥም፡፡ ሁሉንም ይቀጥፋል፣ ያጠፋልም፡፡ የአካል ጉዳት ብቻ ሳይሆን የማይድን የአዕምሮ ጉዳትም አለው፡፡ የጤና ባለሙያ ግን ምንም ሆነ ምንም አገልግሎቱን እከሌ ለእከሌ ሳይል ሁሉንም እኩል ማገልገል አለበት፡፡ በዚህ ጦርነት የተሳተፉ ሁለቱም ወንድሞቻችን ናቸው፡፡ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ በጦርነቱ ተቋማት ወድመዋል፡፡ ለምን? አሸናፊም ኖረ ተሸናፊ ንብረት ለሁሉም ያገለግላል፡፡ ያ መሆን የለበትም ነበር፡፡ የሆነውን ሁሉ እከታተል ነበር፡፡ ምንም ያመለጠኝ ነገር የለም፡፡ ይህ ነው ተብሎ ባይነገርም ማድረግ የሚገባንን አድርገናል፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን ሁለቱም ወገኖች የተኩስ አቁም ስምምነት አድርው በሰላማዊ መንገድ ውይይቶች እየተደሩጉ ነው፡፡ በዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- አሁን የተጀመረው የሰላም መንገድ ጥሩ ነው፡፡ እንዳይረበሽ ጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሌሎች ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ቀድሞ መከላከልና መሠራት ያለበት ነገር ሁሉ ቀድሞ መሠራት አለበት፡፡ ልክ እንደ ሕክምና በፖለቲካውም ቅድመ ጥናት ተደርጎ ግጭቶችን መከላከል ያስፈልጋል፡፡ የግጭት ምክንያት በሆኑ ነገሮች ላይ ጥናት አድርጎ መፍትሔ መፈለግና ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የባድመው ሲቆጨን የሰሜኑ መደገሙ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ አገራችንን ከማንም በላይ መጠበቅና በመካከላችን ያለውን ልዩነት በመፍታት ለራሳችን ራሳችን መፍትሔ መስጠት አለብን፣ ኃላፊነቱ የራሳችን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በ2005 ዓ.ም. በእርስዎ አነሳሽነት ወይም ሐሳብ አቅራቢነት የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (Africa CDC) እንዲቋቋም የጀመሩት እንቅስቃሴ ከአሥር ዓመታት በኋላ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡ እስኪ ስለዚህ ጉዳይ ይንገሩን?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ አፍሪካ ውስጥ ዕውቀቱ ቢኖርም ተቋማት የሉም፡፡ ትልቁ ችግር የተቋም አለመኖር ነው፡፡ ተቋሙ ቢኖር አገርም፣ ሕዝብም ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በመሆኑም ፕሮፖዛል ጻፍኩና በመንግሥት ደረጃ ጥያቄው መቅረብ ስላለበት የጻፍኩትን ፕሮፖዛል ለጤና ሚኒስቴር ሰጥቼ ለአፍሪካ ኅብረት እንዲቀርብ ተደረገ፡፡ ሐሳቡን በኅብረቱ ጉበዔ ላይ ኢትዮጵያ አቀረበች፡፡ ሐሳቡ ተቀባይነት አግኝቶ ኢትዮጵያ ጥናት አድርጋ እንድታቀርብ ኃላፊነት ተሰጣት፡፡ በእነ አክሊሉ ሀብተ ወልድና በእነ ከተማ ይፍሩ የሰማነውን ታሪክ እኛ ደግሞ ዕድል ገጥሞን ለአፍሪካ እንዲህ ያለ ነገር ማስደረግ መቻላችን ያስደስታል፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ዕቅድና ሐሳቡን አቅርበው በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በኩል ተቀባይነት አግኝቶ በአገር ደረጃ ለአኅጉሩ ኅብረት ቀርቦ ከፀደቀ በኋላ፣ ተቋሙ (አፍሪካ ሲዲሲ) ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይሆን ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሞ ነበር፡፡ ስለነበረው ተግዳሮት ቢያስረዱን?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- የአፍሪካ አገሮች ናይጀሪያ፣ ሞሮኮና ግብፅ ተቋሙ መቋቋም (መገንባት) ያለበት እነሱ ጋ መሆኑን ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ሲዲሲ አፍሪካ አምስት ሪጅናል ቢሮዎች አሉት፡፡ ዋናው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ ሌሎቹ ዛምቢያ፣ ግብፅ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ምዕራብ አፍሪካ፣ ምሥራቅ አፍሪካና ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ አሉ፡፡ ሁሉም ግን ዓይናቸው ያለው እዚህ ነው፡፡ ዋና መሥሪያ ቤቱ እኛ ጋ ይሁን የሚል ተግዳሮት ነበር፡፡ ዋናው ነገር ተግዳሮቱን ተቋቁሞ እዚህ እንዲሆን መደረጉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ተቋሙ ብዙ ጥቅም አለው፡፡ የአፍሪካ ኅብረትን የፀነሰችው፣ የወለደችውና ያሳደገችው ኢትዮጵያ በመሆኗ አፍሪካ ሲዲሲንም በማቋቋም ቀዳሚ ሆናለች፡፡
ሪፖርተር፡- ዶ/ር ተስፋዬ የሕክምና ባለሙያ ብቻ አይደሉም፣ ደራሲም ናቸው፡፡ እስኪ ስለድርሰት ሥራዎችም ይንገሩን?
ዶ/ር ተስፋዬ፡- እንደነገርኩህ እኔ ያደግኩት ኩባ ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ይመሥገን ኢትዮጵያውያን መምህራን ኩባ እየተላኩ ስላስተማሩን ቋንቋችንን እንዳንረሳ ረድቶናል፡፡ የብርሃኑ ዘሪሁን መጻሕፍትንም አነብ ነበር፡፡ 11ኛ ክፍል ሆኜ ስለኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነት በሚመለከት አንድ ጽሑፍ በጋዜጣ ላይ ወጥቶ አነበብኩ፡፡ የጣሊያንና የኢትዮጵያ ጦርነት የተደረገው በ1928 ዓ.ም. ነው፡፡ እኔ ወደ ኩባ የሄድኩት በ1969 ዓ.ም. ነው፡፡ እንዴት ይህ ታሪክ በኩባ ጋዜጣ ላይ ሊወጣ ቻለ? የሚል ጥያቄ ፈጠረብኝ፡፡ ጋዜጣውን ይዤ ለታሪክ መምህሬ ስነግረው፣ ‹‹እንደ እዚህ የሚባል ታሪክ የለም›› አለኝ፡፡ ጋዜጣው የጻፈው ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ላይ ስለፈጸሙበት በደልና የውጊያ ሒደት ነው፡፡ ታሪኩ በመጽሐፍ ተጽፎ በ1936 ዓ.ም. አንድ መቶ ኮፒ ብቻ ታትሟል፡፡ አንድ መጽሐፍ ገዝቼ አስቀመጥኩኝ፡፡ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ መጥቼ ደራሲና ጋዜጠኛ ኤፍሬም እንዳለን አገኘሁት፡፡ ስለመጽሐፉ ስንነጋገር እንድተረጉመው ስለገፋፋኝ ተረጎምኩት፡፡ ‹‹ቀይ አንበሳ›› የሚል መጽሐፍ በ2000 ዓ.ም. 3,000 ኮፒ ታተመ፡፡ እጅግ በጣም የተወደደ መጽሐፍ ሆነ፡፡ አሁን ገበያ ውስጥ የለም፡፡ ምናልባት ወደፊት በድጋሚ ይታተማል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡ ሁለተኛው መጽሐፌ ‹‹ጣምራ ቁስል›› የሚል ሲሆን፣ እኛ ያለፍንበትን የሚገልጽ እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ሦስተኛውና አራተኛው መጽሐፍቶቼ የግጥም ደምብል ሲሆኑ በኅትመት ላይ ናቸው፡፡