በአዲስ አበባ ከተማና በክልል ከተሞች ባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች (በተለምዶ ባጃጅ በሚል የምንጠራቸው) እየሰጡ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት በቀላሉ የምናየው አይደለም፡፡
በተለይ ውስብሰብ የትራንስፖርት ችግር ባለበት በአዲስ አበባ በከተማዋ ዳር አካባቢዎች ያለውን ሰፊ የመጓጓዣ ክፍተት በመቅረፍ ሁነኛ ሚና ነበራቸው ማለት ይቻላል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ220 ሺሕ በላይ ባለ ሦስት እግር ተሽከርካሪዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የከተማ አስተዳደሩ የትራንስፖርት አገልግሎት መስመር ባልዘረጋባቸው የኮንዶሚኒየም መንደሮች ባጃጆች ሊተካ የማይችል የትራንስፖርት አገልግሎት እየሰጡ መቆየታቸውንም በግልጽ የሚታይ ነው፡፡
በአጠቃላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ኢትዮጵያ አሉ የተባሉት ተሽከርካሪዎች ቁጥር የሚነግረን እነዚህ ተሽከርካሪዎች ለኅብረተሰቡ እየሰጡ ያለው አገልግሎት ቀላል አለመሆኑን ብቻ አይደለም፡፡ በቀጥታ ከ220 ሺሕ በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ባጃጆችን በማሽከርከር የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው 220 ሺሕ ዜጎች ደግሞ ይብዛም ይነስም የሚያስተዳድሩት ቤተሰብ ይኖራቸዋል። ባጃጅ ተሽከርካሪዎችን የሚጠግኑ፣ የመለዋወጫ ዕቃ የሚያቅርቡና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን የሚሠሩ ዜጎች ሲደመሩ ደግሞ፣ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ለብዙዎች የመኖር መሠረት መሆናቸውን እንረዳለን።
ደግነቱ እነዚህ ተሽከርካሪዎች የሚሰጡት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቋረጥ የተወሰነው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ በአዲስ አበባ ከተማ የባጃጅ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች በድንገት ሥራ አቁሙ መባላቸው የብዙዎችን ጉሮሮ እንደመዝጋት ይቆጠራል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ላልተወሰነ ጊዜ አገልግሎት እንዲያቋርጡ የወሰነበትና በኋላም ዳግም እንዲጀምሩ የፈቀደበት ምክንያት የቱንም ያህል አሳማኝ ቢሆን እንኳን፣ ችግሩ ቀድሞ ሥራውን በአግባቡ ባለመሥራቱ የተፈጠረ መሆኑን መካድ የለበትም፡፡
ምክንያቱም እነዚህ ተሽከርካሪዎች በአብዛኛው በከተማው ዳርቻ መንደሮችና በዋና መንገድ ላይ ጭምር እንዲሠሩ የፈቀደው ይኼው የትራንስፖርት ቢሮ ነው። ወደ መሀል የከተማው ክፍል ገብተው እንዳይሠሩ የተደረገው ክልከላ በከተማዋ ዳርቻ ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ ሊፈቀድ ሲገባ ወደ መሀል ከተማ እንዲሠሩ መፈቀዱ ቁጥራቸው እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ስለዚህ ቀድሞም ቢሆን እንዲህ ያሉ ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ ትልልቅ ጎዳናዎች ላይ አገልግሎት እንዲሰጡ መፈቀዱ አግባብ እንዳልነበረ መታወቅ ነበረበት፡፡ ሆኖም ግን በከተማዋ ካለው የትራንስፖርት ችግር አንፃር እንኳንም ወደ መሀል ከተማ ገብተው አገልግሎት ሰጡ በሚያስብል ደረጃ ኅብረተሰቡን ሲታደጉ መቆየታቸው ግን የማይታበል ሀቅ ነው፡፡
በዚህ መተማመን ከቻልን እነዚህን ተሽከርካሪዎች በአግባቡ ሊሠሩ የሚችሉበት አሠራር መዘርጋትና መቆጣጠር የነበረበት የከተማ አስተዳደሩ ነው፡፡ ፈቃድ የሌላቸው ከነበሩም የሚሠሩት በአደባባይ ነውና ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድ ይገባም ነበር፡፡ ዛሬ ክልከላው ቢነሳም አገልግሎቱ በተቋረጠበት ወቅት የተሠራጨው ምክንያት ፖለቲካ ነክ መሆኑ፣ አስተዳደሩ ቀድሞውንም ቢሆን በእነዚህ ተሽከርካሪዎች ዙሪያ ብዙ መሥራት የነበረበትን የቤት ሥራ አለመሥራቱን ከማሳየቱ በላይ ቀጣይ አገልግሎቱ በየትኛውም ጊዜ ሊቋረጥ የሚችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይኖራል የሚል ሥጋት ጭሯል። በዚህም ሳቢያ ከዚህ ሥራ የመውጣት መነሳሳትን ብቻ ሳይሆን፣ በተግባር ሥራ ለመቀየር የተገደዱ መኖራቸው እየተሰማ ነው። ሌሎች ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጪ ወዳሉ ከተሞች የመውጣት አማራጭን እንዲያማትሩ ገፍቷል።
እነዚህ ተሽከርካሪዎች የከተማውን የትራንስፖርት ችግር ከማቃለል አንፃር ያላቸው አበርክቶ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ተሽከርካሪዎቹን ተጠቅመው ወንጀል የሚፈጽሙበት ጥቂቶች መኖራቸውም የሚካድ አይደለም፡፡ ነገር ግን ጥቂቶችን ለይቶ ዕርምጃ መውሰድ ሲገባ የጅምላ ፍረጃው ፈጽሞ አግባብ ሊሆን አይችልም፡፡
ስለዚህ ከሰሞኑ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች ላይ ተወስዶ የነበረው ዕርምጃ ምክንያት አለው ቢባል እንኳ ችግሩ አሽከርከሪዎች ወይም የባለንብረቶቹ ብቻ አይደለም፡፡ አስተዳደሩ ራሱ የራሱን ሥራ በአግባቡ ባለመሥራቱ ጭምር የተፈጠረ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን እነዚህ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዲሰጡ ሲፈቀድ የተቀመጠው አሠራር አድልኦ የሚታይበትና አገልግሎት ሰጪዎችን በፖለቲካ ደጋፊነት የማደራጀት አዝማሚያ የሚስተዋልበት መሆኑ እየተነገረ ነው። ይህንን በጥንቃቄ ተመልክቶ ውሳኔ ያለመስጠትና በሕጋዊ መንገድ የሚሠሩበትን መንገድ በቶሎ አለማመቻቸት አደገኛ መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
አስተዳደሩ እነዚህ ተሽከርካሪዎች እንዲሠሩ ሲፈቅድ እንደ አንድ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አሠራራቸው ሕግና ሥርዓት እንዲኖረው ብቻ ነው ማድረግ የሚጠበቅበት፡፡ ይህ ካልሆነ በትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን፣ ያልተገባ ታሪፍ የማስከፈል ተግባሮችንና የተገልጋዮች መጉላላትንም ማስቀረት አይቻልም።
በነገራችን ላይ የታሪፍ ጉዳይ ቁጥጥር የማይደረግበት ሆኖ ከዘለቀ ቆይቷል፡፡ የአሁን ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ዛሬ ከታሪፍ በላይ እየጠየቁ ያሉ ታክሲዎች የነዳጅ ድጎማ የሚደረግላቸው ሆኖ ሳለ፣ በድጎማውም እየተጠቀሙ ከታሪፍ በላይ ሲያስከፍሉ ሃይ ባይ ማጣታቸው የሚነግረን የትራንስፖርት ቢሮውም ሆነ ትራፊኮቻችን ሥራቸውን በወጉ አለመከወናቸውን ነው፡፡ ቢሮው ወደ አንዱ መስመር ወጣ ብሎ ቢመለከት አንድም በትክክለኛው ታሪፍ የሚሠራ ታክሲ የለም፡፡ ስለዚህ አስተዳደሩ አጠቃላይ የከተማዋ የትራንስፖርት ሥምሪትና የታሪፍ ጉዳይን ማስተካከል የማይችል ከሆነ ዘላቂ መፍትሔ አይኖርም፡፡
ከአስተዳደሩ የሚጠበቀው ዕርምጃ እንደተባለው ባጃጆቹን በሕጋዊ መንገድ እንዲሠሩ ማስቻል ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የትራንስፖርት ሥምሪቱን ማስተካከል ከታሪፍ በላይ ዋጋ የሚከፈልበትን አገልግሎት ሁሉ ማስተካከልና ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ኅብረተሰቡን መታደግ የሚያስችል ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም የከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት አጠቃላይ አሠራር ተገልጋዩን እየፈተነ ሕገወጥ አሠራሮች ሥር እየሰደዱ በመሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ አስተዳደሩ ማኅበረሰቡ የኖረበትን ችግር አስተዳደሩ ዛሬ ስለሰማ መፍትሔው የትራንስፖርት አገልግሎቱ ይታገድ፣ ነገ ደግሞ ይጀመር ሊሆን አይገባም። አስተዳደሩ የከተማውን ውስብሰብ የትራንስፖርት ችግር እንዴት በዘላቂነት ለመፍታት ማሰላሰልና ፍቱን መፍትሔ ማመንጨት ነው የሚጠበቅበት።