(ክፍል ሁለት)
በሞገስ ዘውዱ
በክፍል አንድ መጣጥፍ የንዑስ ብሔርተኝነት ብያኔ፣ ውልደቱና መገለጫው፣ በአጠቃላይ የብሔርተኝነት ምንነትን በወፍ በረር ለመዳሰስ ሞክሬያለሁ። በዚህ ክፍል ደግሞ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ ምን እንደሚመስልና አደጋውን ለማመላከት እሞክራለሁ። የመፍትሔ አቅጣጫዎች ወይም መውጫ መንገዶች ክፍል ሦስት ላይ የሚቀርብ ይሆናል።
ኢትዮጵያም የዓለም አካል እንደ መሆኗ፣ በተለይ ደግሞ ውስብስብና ያልተጠናቀቀ የአገረ መንግሥትና ብሔረ መንግሥት ግንባታ ሒደት የሚታይባት አገር በመሆኗ፣ የብሔርተኝነት ፖለቲካ ሰለባና የአዙሪቱ ተጠቂ ሆናለች፣ እየተናጠችም ትገኛለች። የንፅፅር ታሪክና ፖለቲካ አጥኚዎች እንደ ሚያሳስቡን ከሆነ የሁለት አገሮች ተሞክሮ እንኳን በሁሉም ረገድ ተመሳሳይ ሊሆን አይችልም። ኢትዮጵያም በበርካታ ምክንያቶች ሳቢያ የራሷ ልዩ የሆነ ማንነት (State Identity)፣ ታሪክና የፖለቲካ መገለጫ አላት። “የብሔርተኛ ወረርሽኝ” ያስተናገደችውም ቆይታ በ1960ዎቹ መባቻ ነው። የፖለቲካ ታሪክና ሁነቶችን መዳሰስ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ባለመሆኑ፣ የብሔርተኝነት ውልደት ዕድገትና እንደ አሸን መፍላት (Proliferation of Ethno-Nationalism) እንደ ሚከተለው ይቀርባል።
፩. ብሔርተኝነት እንዴት ተወለደ?
የኢትዮጵያ ማኅበረ ፖለቲካ በብዙ መልኩ ከሌላው አገር ቢለይም የብሔርተኝነት ውልደት ገፊ ምክንያቶች የብሔረ መንግሥቱ ግንባታ ሒደትና የትርክት ውጤት ናቸው። በብሔረ መንግሥት ግንባታ ሒደት በዋናነት የሚገለጸው፣ የጋራ ታሪክና ማንነት በማዳበር፣ ቢሮክራሲውን በማዘመንና የዴሞክራሲ ባህልን በማንበር ነው። ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን በቅጡ መስመር ያልያዘ የብሔረ መንግሥት ባለቤት ነች። ሁሉም ጉዳዮች (ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ማኅበራዊ ፍትሕ ወዘተ.) እንደ ሚያነታርክ መግለጽ ለቀባሪው ማግሣት ነው።
በመሆኑም፣ ብሔርተኝነት ያለ እርሾ አይሠራምና በብሔረ መንግሥት ግንባታ ችግሮች (ሽንቁሮችን) እንደ ነዳጅ በመጠቀምና በማርክሲስት ሌኒኒስት ርዕዮተ ዓለም በመታገዝ የግራ ዘመም የፖለቲካ ቡድኖች ብሔርተኛነትን ለኢትዮጵያ አገረ መንግሥት አስተዋወቁ። አስቻይ የፖለቲካ ሁኔታ ስላገኙ ኮትኩተው አሳደጉት፣ ለወግ ለማዕረግ አበቁት። ይኼው ዛሬ ላይ በእየ መንገዱ እያጓራ ዜጎችን እያስፈራራ ይገኛል።
በክፍል አንድ እንደ ተመለከተው፣ ይኼ ዓይነት ብሔርተኝነት “ለአገሩ እንግዳ ነኝ” በሚል ዕሳቤና ጥቂት እርሾ የተወለደ ነው። ከእርሾዎቹ መካከል፣ በሰሜንና ደቡብ መካከል ያለው የመሬት ፖሊሲ፣ የቋንቋና የባህል ውክልና፣ ፍትሐዊ የሀብት አጠቃቀምና የልሂቃን ሥልጣን ፍላጎት (የገዥ መደብ ሽኩቻ) ሊጠቀሱ ይችላሉ። ብሔርተኝነት የበለጠ እንዲያብብ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ውስጥ ዋንኛው ሥልጣን ላይ ያለው ቡድን ለብሔርተኝነት ጥያቄው የሚሰጠው መልስ ነው። መልሶቹ ችግር እንደ ሌለ ችላ ማለት፣ ችግሮች ቢኖሩም ለሌላ ጊዜ ማሳደር፣ በኃይል ማፈንና በከፊል መልስ መስጠት ይካተታል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ደግሞ ጥያቄው የብሔርም ሆነ ሌላ የሚሰጠው መልስ በአመዛኙ ማፈን ነው። ይኼ ደግሞ ብሔርተኝነት በሕይወት እንዲቆይ ምክንያት እንደ መስጠት ነው። በከፊል መልስ መስጠት (የ1966ቱ አብዮት) ራሱን የቻለ መዘዝ አለው። ዕውቁ የፖለቲካ ፈላስፋ የሆነው ቶክቪል እንደሚያስረዳን ‹‹አብዮትና ብሔርተኝነት ጠራርጎ የሚወስደው ሳይዘጋጅ በሩን በርግዶ የሚከፍት መንግሥትና በአንፃሩ የተሻለ ሥርዓትን ነው።›› በሌላ አነጋገር፣ ከፊል መፍትሔ (ደርግ እንዳደረገው) ብሔርተኝነት እንዲቀጭጭ ሳይሆን እንዲፋፋም ያደርጋል፣ በተለይ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ባልተገነባበት ሥርዓት ውስጥ።
ከጥቂት እርሾዎች ውጪ ግን ዛሬ ላይ የምናያቸው ያልተገራ የብሔርተኝነት ግስጋሴ የትርክትና ንግርት ፍብረካና የልሂቃን የሥልጣን ሽኩቻ ውጤት ነው። በዳይ ቡድን ይፈጠራል፣ ተበዳይ ነኝ ባይ እየበደለ እንኳን ቢሆን በየአደባባዩ ለቅሶና ዋይታ ያሰማል፣ ታሪክ ይንጋደዳል (Distortion)፣ ምንም የማያውቀው ደሃው ሕዝብ ይሳደዳል፣ ዋጋ ይከፍላል፣ የአገር ምሰሶ በሒደት ይናዳል።
ከሁለቱ የብሔርተኝነት ውልደት አንፃር ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሁሉም በሚባል ደረጃ በመጀመርያው መንገድ ‹ማንነቴ በኢትዮጵያ ውስጥ በበቂ ሁኔታ አልተንፀባረቀም› የሚል ነው። የኦሮሞ፣ የሲዳማ፣ የወላይታ፣ የኤርትራ (እስክትገነጠል ድረስ)፣ ትግራይ፣ ወዘተ. ብሔርተኝነት የዚህ ፍልስፍና ውጤት ናቸው። የሁለተኛውን የብሔርተኝነት ውልደት ማሳያ የሚሆነው የአማራ ብሔርተኝነትን ሲሆን፣ የጉራጌ የክልልነት ጥያቄና የብሔርተኝነት እንቅስቃሴም በዚህ መልኩ እየተቃኘ ነው። የአማራ ብሔርተኝነት የማደራጃ ፍልስፍና ‹‹የእኛ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር አይጣላም፣ ትግላችን መንታ ሲሆን፣ መዳረሻችን ኢትዮጵያን ማዳን ነው፤›› የሚል ነው። የአማራ ብሔርተኝነት ልዩ ባህሪያትና አሁናዊ መገለጫዎች ከታች ንዑስ ክፍል አራት ይዳሰሳል።
የትግራይ ብሔርተኝነት (በሕወሓት የሚቀነቀነው) ውልደትና ዕድገት በብዙ መልኩ በወለፈንዲ የተሞላ ነው። ሲጀመር የገዥ መደብ አካል ሆኖ ሳለ እኔ ለአገሩ ባዳ ነኝ የሚል ትርክት ይዞ ተወለደ። አገር እየመራም ቢሆን የተበዳይ ትርክት ይዞ ቀጥሏል። በመደበኛው የብሔርተኝነት ውልደት ብያኔ መሠረት ከሄድን የትግራይ ብሔርተኝነት እኛ የአገር ልዩ ተቆርቋሪ ነን የሚል ይሆን ነበር። በእርግጥ፣ ሕወሓት ሥልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ሥልጣኑን በዋናነት የተቆጣጠረበትን ምክንያት ቅቡልነት ለማስረዳት ‹‹እኛ ዘመናዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ብዙ ዋጋ ከፍለናል›› የሚል ትርክት ያሠራጭ ነበር። አልፎ አልፎም “የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት ሕዝብ” የሚል አቋም ሲያንፀባርቅም ታይቷል። በአንፃራዊነት ሲታይ፣ የትግራይ ብሔርተኝነት በአመዛኙ የትርክትና የፖለቲካ ውሳኔ ውጤት ነው ማለት ይቻላል።
፪. ሁሉም ነገር ወደ ብሔር ፖለቲካ…!
ለመሆኑ ፖለቲካችን፣ ማኅበራዊ ግንኙነትና የታሪክ ክርክር ሁሉ በብሔር እንዲቃኝ የተደረገው በምን ምክንያት ነው? በእውነት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ማደራጃ ከብሔር ውጪ የለም? ታሪካችንስ በብሔሮች ግንኙነት ዙርያ ብቻ እንዲያጠነጥን እንዴት ተደረገ? የተቀረው ዓለም ከብሔር ፖለቲካ በሒደት እየሸሸ እኛ ጭራሽ ‹‹ሁሉም መንገዶች ወደ ብሔር ያመራሉ›› የሚል አሠራር እንዴት ፈጠርን? እነዚህና መሰል ጥያቄዎች መሠረታዊና በአንድ መጣጥፍ ብቻ የሚመለሱ አይደሉም። ይልቁንስ ቆም ብለን ያሳለፍነውን መንገድ፣ አሁን የቆምንበት ቦታና የወደፊት ዕጣ ፈንታችን ምን ሊሆን እንደሚገባ እንድናጤን ውይይት ለመክፈት የታሰበ ነው።
በእኔ አረዳድ ሁሉም መንገድ ወደ ብሔር ፖለቲካ እንዲያመራ የተደረገበት ዋና ዋና ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡፡ (፩) የብሔር ፖለቲካ ተቋማዊ ድጋፍ ስላገኘና የዜግነት ፖለቲካ እንቅስቃሴ በሒደት እየደበዘዘ በመሄዱ፣ (፪) የኩረጃ ፋሽን ስለተንሰራፋና (፫) የቀውስ ፖለቲካ አየሩን ስለተቆጣጠረ።
ብሔርተኝነት ብቸኛው የፖለቲካ ማደራጃ የሆነው በርዕዮተ ዓለም፣ በሕገ መንግሥትና በሌሎች ተቋማትና አሠራር ስለተደገፈ ነው። ሌላ ተቀናቃኝ እንዳይኖር ቢኖርም እንዲጠፋ ተደርጓል። ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የነበረው የአማራጭ የፖለቲካ ፍልስፍና የበለጠ እንዲቀጭጭ ሆኗል። ይኼም የሆነው በውጫዊ ጫናና በውስጣዊ የአደረጃጀት ድክመት ምክንያት ነው። አንድ የፖለቲካ ትርክት ተቋማዊ መልክ ከያዘ በኋላ በቀላሉ መንቀል አይቻልም። የቤት ሥራውንም የሚያከብደው ይኼ ነው (ዝርዝር ጉዳዮችን በመፍትሔ ክፍል እንመለስበታለን)።
በሁለተኛ ደረጃ ብሔርተኝነት እንደ አሸን እየፈላ መጥቶ ማቆሚያ ያጣው አንዱ የሌላውን አሠራር እየኮረጀ በመሄዱ ነው። ይኼ ደግሞ የብሔር ማንነትን ከአገራዊ እሴት፣ አንድነትና ታሪካዊ ቁርጠኝነት አግዝፎ ማየት፣ ከዚያም አልፎ ለሌላው ብሔር ክልል ስለተሰጠ ለእኔም አሁኑኑ ይሰጠኝ ወደሚል ደረጃ ደርሷል። ይኼን የፈጠረው የፍትሕ፣ እኩልነትና ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ያደረጉት ለምን ይቀርብኛል የሚል የፖለቲካ አካሄድ ነው። እስከ ዛሬ ደረስ በአንፃራዊ ሰላም አብሮ የኖረ ሕዝብ (ብሔሮች) እንደ ጎርፍ የክልል ጥያቄ ያቀረበበት ምክንያት ምንድነው? እውነት ሁሉንም ብሔሮች በአንድ ጊዜ “የህልውና አደጋ” ስለገጠማቸው? በዴሞክራሲ ስለዳበረና በፖለቲካ ምኅዳሩ ስለሰፋ? ይኼንን የክልል ይሰጠኝ ውድድር የበለጠ የሚገልጸው የደኅንነት ሥጋት ጡዘት ያስከተለው እኔስ ከማን አንሼ እሳቤ ነው። ለመሆኑ የህልውና አደጋ ምንድነው? ምንጩስ?
፫. የህልውና አደጋ?
በአሁናዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዲስኩር ውስጥ “የህልውና አደጋ” የሚለው ጉዳይ ቀዳሚ ሥፍራ ይይዛል። የዚህ ፅንሰ ሐሳብ ዋናው ማጠንጠኛ፣ በተለይ ደግሞ ከብሔር ግጭት አንፃር ሲታይ፣ አንድ ማኅበረሰብ በሕይወት የመኖር ወይም እንደ ፖለቲካ ማኅበረሰብ የመቀጠል ሥጋት ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲፈጠር ነው። የመጥፋት ሥጋት እንዲኖር ደግሞ የሥጋቱ ምንጭ የሆነው ሌላ ብሔር ወይም አካል መኖር አለበት። በዚህ ረገድ ሲታይ፣ ሁሉም ብሔር በተመሳሳይ መልኩ፣ በአንድ ጊዜ እንዴት የህልውና አደጋ ሊደርስበት ቻለ? አንድ ማኅበረሰብ ሊያጠፋ የሚችል አደጋስ ተደቅኗል ወይ?
በመሠረቱ፣ በሌላው ዓለም የተለመደውን የህልውና አደጋ ተደቅኖብኛል የሚለው ኅዳጣን የሆነ ቡድን ነው። በተቃራኒው ለኢትዮጵያ ፖለቲካ ብቻ የሚሠራ ፍልስፍና ይመስል የህልውና አደጋ ደርሶብኛል የሚሉት በሕዝብ ቁጥርም ሆነ ፖለቲካ ተሳትፎ ግልጽ ሚና ያላቸው ቡድን ናቸው። ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግራይ፣ ወላይታና ጉራጌ በአንድ ድምፅ የህልውና አደጋ ተጋርጦብናል እያሉ ነው። ምናልባት ይኼ ስሜት በተጋነነ የደኅንነት ሥጋት ምክንያት የተፈጠረ ሊሆን ይችላል። ማንነት ተኮር ጥቃቶች በየቦታው አሉ፣ የደኅንነት ሥጋትም እንደዚያው። ሆኖም ግን፣ ጥቃት ሁሉ የህልውና አደጋ አይደለም። በአሁን ጊዜ እንደ ሕዝብ የመጥፋት አደጋ የተጋረጠበት ቡድን የለም። ቢሆን እንኳን፣ ሁሉም ቡድን በሚባል ደረጃ የህልውና አደጋ ከገጠማቸው ችግሩ ብሔራዊ ቀውስ እንጂ የአንድ ወይም ሁለት ቡድን ሊሆን አይችልም። በዚያው ልክ መፍትሔውም የጋራ ይሆናል።
፬. የአማራ ብሔርተኝነት ውልደቱና ዕድገቱ
የአማራ ብሔርተኝነት ውልደቱ፣ አስቻይ ትርክቱና የፖለቲካ ግቡ ከሌሎች የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ጋር ሲታይ ልዩ ባህሪያት አሉት። ሲጀመር የአማራ ብሔርተኝነት አለ ወይስ የለም የሚለው ራሱ ገና እልባት አላገኘም። ነገር ግን የብሔርተኝነት አቀንቃኞች አለ ስለሚሉ፣ ሌሎች ብሔርተኛ ቡድኖች ስለፈረጁት (Ascriptive) እና እንቅስቃሴው እየጎለበተ የመጣውም ከማንነት ተኮር ጥቃቶች ጋር ተያይዞ ስለሆነ ልዩ ትኩረት ይሻል።
የአማራ ብሔርተኝነት መሠረቱ (በግርድፉ ሲታይ) ጥቃት እየደረሰብኝ ስለሆነ፣ ያለው ሥርዓት ደግሞ ይኼንን ጥቃት ማቆም ስላልቻለ ወይም ራሱ ጥቃት አድራሽ ስለሆነ፣ ይኼንን ጥቃት በተደራጀ መልኩ መመከት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል የሚል ነው። እውነት ነው ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ደርሰዋል፣ እየደረሱም ነው። ከትርክት ጀምሮ መዋቅራዊና አካላዊ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ቆይተዋል። ይኼ በገሀዱ ዓለም ያለ እውነታ ነው። ጥቃቱ እንዳይደርስም የአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ሁሉም በአንድነት ማስቆም ሞራላዊ ግዴታ ነው።
ጥያቄው ያለው ውልደቱ፣ መገለጫውና መዳረሻው ላይ ነው። የአማራ ብሔርተኝነት ፊት አውራሪዎች እንደሚገልጹት የአማራ ብሔር መገለጫው መንታ ነው። መንታ የሆነበት ምክንያት ከኢትዮጵያዊ ማንነት (State Identity) ጋር በእጅጉ የተቆራኘ መሆኑ ይነገራል። ይኼ እውነት አለው። በአንድ በኩል የብሔርተኝነት አቀንቃኞች ይኼንን ብያኔ ተቀብለውታል። በሌላ መልኩ፣ የተቀሩት ብሔርተኞች ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን ለአማራ አሸክመው ትግላቸውንም የቀረፁት በዚህ ላይ በመመሥረት ነው። የአማራ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያ እሴት፣ ታሪክና የፖለቲካ ግብ ጋር መቆራኘቱ ችግር የለውም። ሲጀመር አማራ የኢትዮጵያ አንድ አካል በመሆኑ፣ አማራ ላይ የሚደርሰው ጥቃትም ኢትዮጵያን በቀጥታ ይጎዳል።
የአማራ ብሔርተኝነት ውልደቱ ጥቃት ለመመከትና ተበድያለሁ ከሚለው የመነጨ በመሆኑ፣ መገለጫውም ከኢትዮጵያ ማንነትና ዕጣ ፈንታ ጋር የተያያዘ ስለሆነ፣ በከፍተኛ ጥንቃቄና ጥበብ መያዝ ይጠይቃል። የሌላው ዓለም ተሞክሮ እንደሚያሳየን ጥቃት መመከት ላይ የተመሠረተ (Reactionary Nationalism) አንዴ ከልጓም ካፈተለከ መመለሻ የለውም፣ ጉዳቱም በዚያው ልክ ነው። ለምሳሌ፣ የዩጎዝላቪያን መፍረስ ያፋጠነው የግራ ዘመም ብሔርተኞች ትጋት ብቻ ሳይሆን የሰርቢያ “እኔ የአገረ መንግሥቱ ጠባቂና ልዩ ተበዳይ ነኝ” እንቅስቃሴ ነበር።
ሌላው ከአማራ ብሔርተኝነት ጋር ተያይዞ የሚቀርበው የአማራ ትግል “ኢትዮጵያን የማዳን” ዓላማ ያነገበና ለሌሎች ሥጋት ያልሆነ ነው የሚል ትርክት ነው። ከላይ እንደተገለጸው፣ የህልውና አደጋ ሁሉም ቡድን ከገጠመው የአማራ ብሔርተኝነት አዳኝ እንጂ ችግር አይደለም ማለት አይችልም። ምክንያቱም የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ፣ ለዚያውም በትጥቅ የታጀበ (ሁሉም ክልል የራሱ ልዩ ኃይል እንዳለው ልብ ይሏል) ሲሆን የሥጋት ጡዘት ማባባሱ ተፈጥሯዊ ነው። ይኼንን ደግሞ በተግባር እያየን ነው። የሰሜን ጦርነት ባህሪ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች መካከል የሚታየው መፋጠጥ ህያው ማሳያ ናቸው።
ሌላው ቢቀር፣ በአማራ ስም ተደራጅቶ፣ መፈክሩን ‹‹አንድ አማራ ለሁሉም አማራ፣ ሁሉም አማራ ለአንድ አማራ፤›› አድርጎ፣ በታጠቀ ኢ መደበኛ ኃይል ታጅቦ፣ ከተቻለ ሥልጣን ለመቆናጠጥ እየተንቀሳቀሰ ያለ ቡድን “የእኔ ብሔርተኝነት ልዩ ነው” የሚያስብል አንዳች ምክንያት አይኖርም። አንዴ የሥጋት ጡዘት ከተፈጠረ አንዱ የሚወስደው እያንዳንዱ ዕርምጃ በሌላው ዘንድ እንደ ሥጋት ይታያል፣ የአንዱ ደኅንነት ማስጠበቂያ የሌላው ደኅንነት ሥጋት ስለሚሆን። በሌላ አነጋገር፣ ሁሉም ነገር ሲጦዝ “እንዴት አደርክ?” ራሱ የፀብ ምንጭ ይሆናል።
በአማራጭ፣ የመብት ትግል ሁሉ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ባለመሆኑና ግዴታም ስላልሆነ፣ የአማራ ሕዝብ ትግል ‹‹የእኩልነትና የሕይወት ዋስትና ማረጋገጥ ንቅናቄ፤›› ነው ተብሎ ሊገለጽ ይገባል። ይኼ ከሆነ ደግሞ፣ የትግል ሥልቱና ፖለቲካዊ አካሄድ በዚያው ልክ መልሶ መገምገም ይኖርበታል።
፭. ማጠቃለያ
በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ በዘርፈ ብዙ ብሔራዊ አደጋዎች ተከባለች፣ የሰላም ዕጦት፣ የአገር አንድነት መላላት፣ የሉዓላዊነት መሸርሸር፣ የኢኮኖሚ መላሸቅና የኑሮ ውድነት፣ የተጠያቂነት ባህል መጥፋት፣ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ መሸርሸር፣ ወዘተ.፡፡ ነገር ግን ከሁሉም በላይ የአገርን ህልውና እየተፈታተነ ያለው ያልተሸበበ ብሔርተኝነት ነው። የብሔርተኝነት ነዳጅ ሆነው እያገለገሉ የነበሩና አሁንም እያባባሱ ያሉ መዋቅራዊ ችግር ካልተፈቱ እንደ አገር የመቀጠል ዕድላችን ራሱ በጣም ጠባብ ነው።
በተጨማሪም፣ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የንዑስ ብሔርተኝነት አቃፊና አዳኝ እንደሌለ ታውቆ አዲስ የፖለቲካ ፍልስፍናና አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል። ብሔርተኝነት ከባድ ሱስ ነው፣ አንድ ዕርምጃ በሰጡት ቁጥር የብሔርተኝነት አቀንቃኞችን ጥልቅ ባህር ውስጥ እያሰመጠ፣ የአገርን ዋልታና ማገሮች እያነቃቀለ በሒደት ያፈርሳል። በቅርቡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ህልውና የተፈታተነው ሌላ ተዓምር ሳይሆን ያልተገራው ብሔርተኝነት ፍሬ አፍርቶ ነው። የብሔርተኝነት መጨረሻው ራስን ማጥፋት ሲሆን፣ በሒደት ግን ሕዝብን ያጫርሳል፣ አገርን ያወድማል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ይኼንን ሊገነዘበው ይገባል።
ሲጠቃለል፣ በኢትዮጵያ ያለው ብሔርተኝነት ከሌላው ዓለም የተለየ ሳይሆን፣ አንዱ የመነጠል መንገድ የሚከተል ሲሆን፣ ሌላኛው የፋሺዝም ታናሽ ወንድም ነው። ሁለቱም ለአገር ሰላምና ደኅንነት ትልቅ አደጋ ናቸው። ይኼ አደጋ የቁልቁለት ጉዞ፣ ጊዜ ሳይሰጠው መፍትሔ ካላገኘ፣ ውጤቱ የማያባራ ግጭት፣ የሕዝብ ዕልቂትና የአገር መፍረስ ነው።
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡