Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበአዲስ አበባ ከአሳሳቢም በላይ ለሆነው ከተወሰነው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር መፍትሔው ምንድን ነው?

በአዲስ አበባ ከአሳሳቢም በላይ ለሆነው ከተወሰነው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር መፍትሔው ምንድን ነው?

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ በዋና መንገዶች 60 በመቶ ያህል፣ በውስጥ ለውስጥና መጋቢ መንገዶች 70 በመቶ ተሽከርካሪዎች ከፍጥነት ወሰን በላይ የሚጓዙ በመሆኑ፣ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ በፍጥነት የማሽከርከር ወሰን ላይ ጠንካራ ቁጥጥር ማድረግ፣ የፊትና የኋላ ወንበሮች ተሳፋሪዎች የደኅንነት ቀበቶ አለማሰራቸው በቅጣት ውስጥ እንዲካተት እንዲደረግ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ከጆንስሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳት ምርምር ተቋም ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ ከ2007 ዓ.ም. እስከ 2014 ዓ.ም. ያደረገውን የአሽከርካሪዎችና የተሽከርካሪ ተጠቃሚዎችን የመንገድ አጠቃቀም የመንገድ ዳር ዳሰሳ የጥናት ውጤቱን መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል።

በአዲስ አበባ በናሙና በተመረጡ 12 አካባቢዎች ላይ ባደረገው ጥናቱ እንደገለጸው፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመጋቢ መንገዶች የተቀመጠው የፍጥነት ወሰን በሰዓት 30 ኪ.ሜ.  ቢሆንም፣ በከተማዋ ግን በተቃራኒው በሰዓት ከ30 እስከ 50 ኪሎ ሜትር ይሽከረከራሉ፡፡

- Advertisement -

 ከፍተኛ ፍጥነት ከፍተኛ የአደጋ ሥጋት የሚያስከትልና ለከባድ ጉዳት የማጋለጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነው ያለው ጥናቱ፣ በአዲስ አበባ መንገዶች 59 በመቶ ተሽከርካሪዎች የወሰን ገደቡን የሚተላለፉና አደጋ የማድረስ ድርሻቸውም ከፍተኛ እንደሆነ አመልክቷል፡፡

በሰዓት አንድ ኪሎ ሜትር ፍጥነት መጨመር የአካል ጉዳት የመከሰት ዕድልን ሦስት በመቶ፣ እንዲሁም በአደጋው ሞት የመከሰት ዕድልን ከአራት እስከ አምስት በመቶ ይጨምራል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና አስተባባሪ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት ዋና ተመራማሪና መምህር ዋቅጋሪ ደሬሳ (ፕሮፌሰር) የሰባት ዓመቱን የዳሰሳ ጥናት ቁልፍ ግኝቶችን ሲገልጹ፣ ለትራፊክ አደጋ መንስዔ የሆኑ በርካታ ነገሮች ቢኖሩም በፍጥነት ማሽከርከር ከሁሉም በበለጠ አደጋን እያስከተለ መሆኑን ጠቁመው፣ ለመፍትሔውም የመንገድ ደኅንነት የተለያዩ ተቋማትን ያሳተፈ ፈርጀ ብዙ ሥራዎችን መተግበር ይጠይቃል ብለዋል፡፡

በፍጥነት ማሽከርከር ባለፉት ሰባት ዓመታት በተከታታይ መጨመሩን ያመለከቱት ተመራማሪው፣ አሽከርካሪዎች ከአዘቦት ቀናት ይልቅ በዕረፍት ቀናት ፍጥነታቸውን በእጥፍ የመጨመር ዝንባሌ ይታይባቸዋል ብለዋል። በመሆኑም ባለ ድርሻ አካላት የተጠናከረ የወሰን ቁጥጥር በማድረግ በትራፊክ አደጋ እየጠፋ ያለውን የሰው ሕይወት መታደግ እንዳለባቸውም አስረግጠው ተናግረዋል።

ጥናቱ በመፍትሔ ሐሳብነት የሚመለከታቸው አካላት፣ በከተማዋ የትኛውም አካባቢ በተለይ በውስጥ ለውስጥና በመጋቢ መንገዶች ሳምንቱን ሙሉ በፍጥነት ማሽከርከር ላይ ቁጥጥር እንዲያካሂድ፣ ሁሉም ሞተረኞች የጭንቅላት መከላከያ ቆብን እንዲያደርጉና በትክክል እንዲያስሩ ቁጥጥር እንዲያደርጉ፣ ከኋላ ወንበር የሚቀመጡ ተሳፋሪዎች የደኅንነት ቀበቶ የመጠቀም ልምድን ለማሳደግ ቁጥጥር እንዲያደርጉ፣ አሁን ያለውን የጭንቅላት መከላከያ ቆብ አጠቃቀም ሕግ ‹‹በትክክል በማሰርና ባለማሰር›› በሚል ለይቶ በማስቀመጥ ሕጉ እንዲሻሻል አመላክቷል።

የጥናቱ ግኝት እንደሚያመለክተው፣ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር በአዲስ አበባ ውስጥ አሁንም ችግር እንደሆነ ቀጥሏል። የጭንቅላት መከላከያ ቆብን በትክክል የመጠቀም ልምድ በሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች 31 በመቶ ሲሆን፣ በተሳፋሪዎች ደግሞ በጣም ዝቅተኛ ማለትም 12 በመቶ ብቻ ነው።

በዕረፍት ቀናት የራስ ቅል መጠበቂያ ቆብን የመጠቀም ልምድ 40 በመቶ መቀነሱን፣ እንዲሁም ከውስጥ ለውስጥና ከመጋቢ መንገዶች አንፃር በዋና መንገዶች ላይ ደኅንነት ቆብ በትክክል የመጠቀም ልምድ በአምስት እጥፍ መጨመሩን፣ የሕግ ቁጥጥር ከሌለበት ይልቅ የትራፊክ ተቆጣጣሪ ፖሊስ ባለበት የራስ ቅል መጠቀሚያ ቆብን በትክክል የመጠቀም ልምድ እንደሚጨምርም ተገልጿል፡፡

በመዲናዋ 99 በመቶ የሚሆኑ አሽከርካሪዎች የደኅንነት ቀበቶን ሲጠቀሙ፣ 84 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከአሽከርካሪዎች አጠገብ የሚቀመጡ ተሳፋሪዎች ቀበቶን ያስራሉ፡፡ ከኋለኛው ወንበር ከሚሳፈሩት ውስጥ ደግሞ ስድስት በመቶ ብቻ የደኅንነት ቀበቶን ያስራሉ፡፡

ከፆታ አንፃር የሴቶች የደኅንነት ቀበቶ የማሰር ልምድ 40 በመቶ ሲደርስ፣ ከአምስት ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት ስድስት በመቶ ብቻ የሕፃናት የደኅንነት መቀመጫ እንደሚጠቀሙ ተጠቅሷል።

ለችግሩ ሁነኛ መፍትሔዎች ተብለው ከተጠቀሱት መካከል የፍጥነት ገደቦችን የመንገዶችን ዓይነትና አካባቢውን በተለይም ትምህርት ቤቶችንና የመኖሪያ አካባቢዎችን፣ የገበያ ማዕከላትንና የንግድ አካባቢዎችን መሠረት በማድረግ ማሻሻል ይገኙበታል። ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የመንገድ ተጠቃሚዎችን ከአደጋ ለመጠበቅ የአነስተኛ ፍጥነት መንገዶችን ለይቶ ማውጣትና የፍጥነት መቀነሻ ዘዴዎችን መሥራት አስፈላጊነቱ ተሰምሮበታል፡፡

‹‹የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የአጭርና የረዥም ጊዜ የመንገድ ደኅንነት ስትራቴጂ ዕቅድ አውጥቶ ውጤታማ የማሻሻያ ሥራዎችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፤›› ያሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር ኃላፊ አቶ ቢኒያም ጌታቸው ናቸው፡፡

እንደ ኃላፊው አነጋገር ዋና ዋናዎቹም ደኅንነቱ የተጠበቀ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ በተለይም አደጋ የሚበዛባቸው ቦታዎች ላይ የመንገድ ደኅንነት የምሕንድስና ማሻሻያዎችን ማድረግ፣ የባህርይ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫና የመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር ሥራዎች ማከናወንና የመረጃ አያያዝ ሥርዓትና የድኅረ አደጋ ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ተጠቃሾች ናቸው፡፡

እንደ ዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ምቹ ባልሆነ የአየር ፀባይና የመንገድ ሁኔታ ላይ በፍጥነት ማሽከርከር ለሞትና ከፍተኛ የአካል ጉዳት ይዳርጋል፡፡ የፍጥነት ወሰን በትንሹም ቢሆን አለማክበር የሞትና የሽረት ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡

በሰዓት አንድ ኪሎ ሜትር ፍጥነት መጨመር የአካል ጉዳት የመከሰት ዕድልን ሦስት በመቶ፣ እንዲሁም የሞት አደጋን ከአራት እስከ አምስት በመቶ እንደሚጨምር፣ በዓለም ላይ በየዓመቱ በአማካይ 1.3 ሚሊዮን ሰዎች በትራፊክ አደጋ እንደሚሞቱ፣ ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ለአካል ጉዳት እንደሚዳረጉ ነው የተገለጸው፡፡

የትራፊክ አደጋ ከአገሮች አጠቃላይ ምርት በአማካይ ከሦስት እስከ ምስት በመቶ የሚሆነውን እንደሚያሳጣ፣ ዕድሜያቸው ከአምስት እስከ 29 ለሆኑት ቁጥር አንድ ገዳይ እንደሆነ፣ አደጋው ለከባድ አካላዊና አዕምሮአዊ ዘላቂ ጉዳት እንደሚዳርግ፣ በተጎጂዎችና ቤተሰቦቻቸው ላይም ከፍተኛ የሆነ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር እንደሚያስከትል ከዓለም አቀፉ መረጃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...